የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ከኃላፊነታቸው ለቀቁ
የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን በተሾሙት አቶ ፍፁም አረጋ ምትክ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ተሹመው የነበሩት በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ከማክሰኞ መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡
ከሚሽነሩ በኃላፊነት የቆዩት ለአምስት ወራት ነው፡፡ ከኃፊነታቸው ለመልቀቃቸው ይኼ ነው የተባለ ምክንያት ባይሰጥም፣ በገዛ ፍላጎታቸው መልቀቃቸውን ግን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በላቸው (ዶ/ር) ኮሚሽነር ሆነው እንዲያገለግሉ ሾመዋቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የኮሚሽነርነት ኃላፊነቱን ይዘው እንዲሠሩ ከመሾማቸው ቀደም ብሎ በምክትል ኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ ነበር፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የካቢኔ ሹም ሽር ወደ ኃላፊነት ከመጡት ተሿሚዎች የፓርቲ አባላት ካልሆኑት አንዱ የነበሩትን በላቸው (ዶ/ር)፣ ከአራቱ ምክትል ኮሚሽነሮች መካከል በአንደኛው አቶ ተካ ገብረየሱስ በተጠባባቂነት መተካታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡