Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ አገር ውስጥ ከገባ ሪሰርቸር ጋር ሆቴል ውስጥ ተገናኝተው እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ አገር ውስጥ ከገባ ሪሰርቸር ጋር ሆቴል ውስጥ ተገናኝተው እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ሰውዬ ለመሆኑ ጤነኛ ነህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ያጋጠመኝን እኮ ስላላወቁ ነው፡፡
 • ሁለት ቀን ሙሉ ስልክህን አጥፍተህ?
 • በእነዚህ ሁለት ቀናት የደረሰብኝን መከራ ስለማያውቁ እኮ ነው?
 • የላኩህ ቦታ ብጥብጥ አለ እንዴ?
 • ብጥብጥ እንኳን አልነበረም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምን ሆነህ ነው ልትገኝ ያልቻልከው?
 • የላኩኝን መልዕክት ለማድረስ ስንት መስዋዕት ስከፍል ነበር፡፡
 • የምን መስዋዕትነት ነው የምታወራው?
 • ክቡር ሚኒስትር የሰጡኝ ሥራ ከፍተኛ መስዋዕት የሚያስከፍል ነበር፡፡
 • እህቴ የምትበላው ስለተቸገረች ለእሷ ጤፍ አድርስ አይደል እንዴ የተባልከው?
 • እሱማ ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ይኼን መሥራት ካልቻልክ ምኑን ሾፌር ሆንክ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሥራው እንዲህ ቀላል አይደለም እኮ?
 • ምን ታካብዳለህ ሴትዮዋ በረሃብ ትሙት?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ማንም ኢትዮጵያዊ በረሃብ መሞት የለበትም፡፡
 • ስማ ይቺ ሴትዮ ብትሞት ግን አንተ እንደገደልካት ማወቅ አለብህ፡፡
 • የተባለውን አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ተባለ?
 • መግደል መሸነፍ ነው ተብሏል፣ ስለዚህ እኔ መሸነፍ አልፈልግም፡፡
 • የፖለቲካ ዲስኩርህን እዚያው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔማ የሰጡኝ ሥራ በቴክኖሎጂ ሳይቀር ታግዤ ለመሥራት አስቤያለሁ፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ይኸው እህሉን እንዴት ለእህትዎ በድሮን ማድረስ እችላለሁ ብዬ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡
 • የምትበላው የላት የምትከናነበው አማራት አሉ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለሥራችን እኮ ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን፡፡
 • ሰውዬ ለመሆኑ ስለድሮን ታውቃለህ?
 • እንዴ ይኸው በአገራችን ድሮን በመጠቀም የተለያዩ ነገሮች ለሰዎች እየተላኩ እኮ ነው፡፡
 • እና አንተም በድሮን 100 ኪሎ ጤፍ ልታደርስ አስበህ ነው?
 • ምን ችግር አለበት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለመሆኑ አንተ ስለቴክኖሎጂ ታውቃለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ቀኑን ሙሉ ፌስቡክ ላይ ተቀምጬ አይደል እንዴ የምውለው?
 • ስለዚህ ቴክኖሎጂ በሚገባ ታውቃለህ ማለት ነው?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር ይኼንን የድሮን ቴክኖሎጂ ራሱ እሱ ላይ አይደል እንዴ ያየሁት?
 • እንደ አንተ ዓይነቱ እኮ ነው ሁሉን አውቃለህ እያለ አገር የሚያጠፋው፡፡
 • ቴክኖሎጂ ብዙ አይመችዎትም መሰለኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ ለማንኛውም እስካሁን እህሉን ባለማድረስህ ቅጣት ይጠብቅሃል፡፡
 • የምን ቅጣት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የደመወዝ ቅጣት፡፡
 • ምን አጥፍቼ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው ለእህቴ አድርስ የተባልከውን እህል ሳታደርስ ሁለት ቀን የት ቆይተህ እንደመጣህ አይታወቅም፡፡
 • ምክንያቴን ቢያውቁት እኮ እንደዚህ አይሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው ምክንያትህ?
 • የእህትዎት ቤት ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
 • አካባቢውን አውቀኸዋል አይደል እንዴ?
 • አካባቢውን ባውቀውም ቤታቸው ለመግባት ዘዴ ስዘይድ ነበር፡፡
 • ቤቷ ለመግባት ለምን አልቻልክም?
 • ቤታቸው ለመግባት የሠፈሩ አቀማመጥ አይመችም፡፡
 • ምን ሆነብህ?
 • አባጣ  ጎርባጣ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ምነው ተከፍተሃል?
 • እንዴት አልከፋ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኮ ምን ሆንክ?
 • ክቡር ሚኒስትር ብዙ የቢዝነስ አጋጣሚዎች እኮ እያለፉን ነው፡፡
 • አገሪቱ እንደዚህ እየታመሰች እንዴት ቢዝነስ መሥራት ይቻላል?
 • አዩ ክቡር ሚኒስትር ሁለታችንም አርጅተናል ማለት ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በፊት እኮ በብጥብጥ ውስጥ ሳይቀር ቢዝነስ እንሠራ ነበር፡፡
 • ያኔማ የእኛ ሰዎች ሁሉም ቦታ ተቀምጠው ስለነበር ነው፡፡
 • ግን ክቡር ሚኒስትር በዚህ ከቀጠለ ዋጋ የለንም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • እንደዚህ ማሰብ ካቃተን የያዝናቸውን ቢዝነሶች ራሱ እንዳናጣቸው እሠጋለሁ፡፡
 • ምን ሆነህ ነው ይኼን ያህል?
 • ክቡር ሚኒስትር ምን ምን የመሳሰሉ ዕድሎች እኮ እያለፉን ነው፡፡
 • ከቲሸርትና ከባነሩ ቢዝነስ ሌላ ምን አመለጠን?
 • ክቡር ሚኒስትር እንደዚህ የተደበርኩት እኮ ሌላ ቢዝነስ ስላመለጠን ነው፡፡
 • እኮ የምን ቢዝነስ ነው?
 • የቀለም ቢዝነስ ነዋ፡፡
 • ሰውዬ እኔ መቼም ቢሆን የቀለም ፖለቲካን ስታገል እንደኖርኩ ታውቃለህ፡፡
 • እኔም እሱን ብዬ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ መቼም ቢሆን የቀለም ፖለቲካን አልደግፍም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ዝም ብለው ከበሩ እኮ?
 • እነማን ናቸው የከበሩት?
 • ምነው ያን ዝም ብሎ የተቆለፈ መጋዘን የቀለም ፋብሪካ አድርገነው ቢሆን ኖሮ?
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ክቡር ሚኒስትር ከአዲስ አበባ ወጣ ሲሉ እኮ ሁሉ ነገር ቀይና አረንጓዴ ነው የተቀባው፡፡
 • በነገራችን ላይ በእሱ ነገር በጣም ነው የተቃጠልኩት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ብቻ ምን አለፋዎት በቀላሉ የምንከብርበት አጋጣሚ ነው ያለፈን፡፡
 • ይኸው አሁን መንግሥት ማንም እንዳይቀባ ከልክሏል አይደል እንዴ?
 • ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር፣ ስልክ እንጨቱ አይሉ አጥሩ ምን አለፋዎት ሰው ራሱ ረዘም ላለ ሰዓት ቆመው ካገኙ ይቀቡ ነበር አሉ፡፡
 • ነገርኩህ እኮ ከዚህ በኋላ ቢዝነሱ ያከትምለታል፡፡
 • እኔስ ያናደደኝ ምንም ሳንሠራ ቢዝነሱ በመሞቱ አይደል እንዴ?
 • አሁን ስናወራ ግን አንድ ሐሳብ መጣልኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን መንግሥት የፅዳቱን ፕሮጀክት እንዲሰጠኝ አላደርግም?
 • የምን የፅዳት ፕሮጀክት?
 • በቃ የተቀባውን ቀለም ለማጥፋት እኛ ሥራውን እንውሰደዋ፡፡
 • አባ መላ እኮ ነዎት፡፡
 • ስለዚህ እንዲያውም በአፋጣኝ ማምጣት ነው፡፡
 • ምንድነው የምናመጣው?
 • ኬሚካሉን ነዋ፡፡
 • የምን ኬሚካል?
 • የቀለም ማስለቀቂያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን ቢሯቸው አስጠሩት]

 • ሪፖርቱን ተመለከቱት ክቡር ሚኒስትር?
 • እስኪ ቁጭ በል፡፡
 • ችግር አለ እንዴ?
 • ሥርዓት አልበኝነት እኮ እዚህ እኛ ቢሮ እንደገባ አላወቅኩም ነበር?
 • የምን ሥርዓት አልበኝነት?
 • ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ሥርዓት አልበኝነት እንዲመጣ ነው የምንጠብቀው?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ያዘዝኩት ነገር ካልተከበረ ከዚህ በላይ ሥርዓት አልበኝነት የት አለ?
 • ኧረ ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ትዕዛዜ ሳይከበር እንዴት ልረጋጋ?
 • የትኛው ትዕዛዝ?
 • ከዚህ በፊት መመርያ አላወጣንም?
 • የምን መመርያ?
 • ማንም ሰው እኔን ሳያስፈቅድ ፊልድ እንዳይወጣ አላልኩም?
 • ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ይኼ መመርያ የወጣው ለጨዋታ ነው?
 • ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምንድነው ተፈጻሚ ያልሆነው?
 • እየተፈጸመ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አያውቅም ብለህ ልትጫወትብኝ ነው?
 • እኔ እንደዚህ ዓይነት ንቀት ለእርስዎ የለኝም፡፡
 • ታዲያ ይኼን ወጪ አይተኸዋል?
 • የቱን ወጪ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለፊልድ የወጣውን ወጪ ነዋ፡፡
 • ተመልክቼዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ካቀረብክልኝ ወጪ ከ30 በመቶ በላይ ነው እኮ?
 • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ መመርያውን ከማውጣታችን በፊት ከነበረው በላይ ሆኗል እኮ ወጪው?
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • መመርያውን ለመተግበር ምንድነው ያስቸገረህ?
 • መመርያውንማ ተግባራዊ አድርጌዋለሁ አልኩ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ይላይ ይኼ? ወጪውን ዓይተኸዋል?
 • ክቡር ሚኒስትር ሪፖርቱን በደንብ ያነበቡት አልመሰለኝም?
 • ይኸው ፊት ለፊት እያየሁት አይደል እንዴ?
 • በደንብ ቢያዩትማ እንደዚህ አይጮሁብኝም ነበር?
 • ይኼ ለፊልድ የወጣ ወጪ አይደለም እያልከኝ ነው?
 • እሱማ ነው፡፡
 • ታዲያ እኔ ሳላውቅ ይኼ ሁሉ ወጪ እንዴት ይወጣል?
 • ክቡር ሚኒስትር ወጪውንማ በሚገባ ያውቁታል፡፡
 • እኔ እኮ እስከ ዛሬ ማንም ፊልድ እንዲወጣ ፈቅጄ አላውቅም፡፡
 • እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ማን ፊልድ ወጥቶ ነው ይኼ ሁላ ወጪ?
 • እርስዎ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ አገር ውስጥ ከገባ ሪሰርቸር ጋር ሆቴል ውስጥ ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ኢትዮጵያን መቼም እንደጠበቅካት አይደለም ያገኘሃት አይደል?
 • አዎ እንደጠበቅኳት አይደለም ያገኘኋት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ብዙ ለውጥ አለ አይደል?
 • በጣም ብዙ ለውጥ አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የአገሪቱ ልማት፣ ዕድገትና ሥልጣኔ አላስደነቀህም?
 • የምን ዕድገት? የምን ልማት? የምን ሥልጣኔ?
 • አሁን በሚገባ ነው ያረጋገጥኩት፡፡
 • ምንድነው ያረጋገጡት?
 • እናንተ ዳያስፖራዎች ጨለምተኛ መሆናችሁን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለእኔ የታየኝ ዕድገት ሳይሆን አገሪቱ የኋሊት መሄዷን ነው፡፡
 • ድሮም ጨለምተኛ ናችሁ እኮ፡፡
 • ሰሞኑን አገሪቱ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር አላስተዋሉትም ማለት ነው?
 • ምን እያልክ ነው?
 • ለምን ሌላ ቋንቋ ተናገርክ ተብሎ ሰው የሚገደልባት አገር የምን ሥልጣኔ ነው ያለው?
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር ለምን ለየት ያለ ልብስ ለበስክና ለምን ለየት ያለ ምግብ በላ ተብሎ ሰው ሲገደል እያየን ስለልማት ያወራሉ?
 • ስማ ይህች አገር የሦስት ሺሕ ዓመት ታሪክ ያላት ናት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ፈረንጆቹ ከዛሬ 500 ዓመት በፊት በሚጣሉበት ነገር እየተጣላን ስለዕድገትና ስለልማት እንዲሁም ስለሥልጣኔ ማውራት አንችልም፡፡
 • እስኪ ቀና ለመሆን ሞክር፡፡
 • ነገርኩዎት ክቡር ሚኒስትር አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ፣ በሚለብሰው ልብስና በሚበላው ምግብ እየለያዩ የሚያጋድሉበት አገር ዜጋ ነኝ ለማለት አፍራለሁ፡፡
 • እ. . .
 • ስለዚህ ኢትዮጵያ የሦስተኛ ዓለም አገር መሆን አይገባትም፡፡
 • እሱማ ካደጉት አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ወጥረን እየሠራን ነው፡፡
 • ወዴት ወዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ኢትዮጵያ መመደብ ያለባት ሌላ ዓለም ውስጥ ነው፡፡
 • የትኛው ዓለም?
 • አራተኛው ዓለም!