Skip to main content
x
ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አድማ በማድረግ ታግደው ከነበሩ ሠራተኞች ከተመለሱት ውስጥ ተወካያቸው ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር እያወራ ነው

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አድማ በማድረግ ታግደው ከነበሩ ሠራተኞች ከተመለሱት ውስጥ ተወካያቸው ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር እያወራ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር አሁን አሁን በጣም እየከፋኝ ነው፡፡
 • እየከፋኝ ነው ስትል?
 • ከቅርብ ወዳጆቼ ጋር ሳወራ ከእግዚአብሔር ታገኘዋለህ ስላሉኝ ነው እንጂ እየከፋኝ ነው፡፡
 • ምኑን ነው ከእግዚአብሔር የምታገኘው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔማ ከእናተም እፈልገዋለሁ፡፡
 • ምኑን ነው ከእኛ የምትፈልገው?
 • ክፍያዬን ነዋ፡፡
 • የምን ክፍያ?
 • ክቡር ሚኒስትር ለኢሕአዴግ እዚህ መድረስ እኔ ነኝ እኮ ተጠያቂ፡፡
 • አልገባኝም ምን እያልክ ነው?
 • ለኢሕአዴግ እንደዚህ አይበገሬ መሆን ዋናውን ሚና የተጫወትኩት እኮ እኔ ነኝ፡፡
 • ምን በማድረግ?
 • ተቃዋሚዎች እየተዳከሙ ኢሕአዴግ እንዲጠናከር የነበረኝ ሚና የአንበሳው ነው፡፡
 • እንዴት? እንዴት?
 • ይኸው የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠበበ ሲባል የእኔን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች ዘመዶቼም የውሸት ፓርቲዎችን በመክፈት ኢሕአዴግ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሚመራ ለማሳመን ስሠራ ነበር፡፡
 • ከሌሎቹም ፓርቲዎች ጋር በፍራንቻይዝ ነበር የምትሠራው ማለት ነው?
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጣም ጥሩ፡፡
 • ሲቀጥል ደግሞ ዳያስፖራ ሆነ ዲፕሎማት ቢሉ ስለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ሲጠይቁኝ ሽንጤን ገትሬ ነበር የምከራከረው፡፡
 • ግን እሱን አምነህበት መስሎኝ የምታደርገው?
 • በእርግጥ ክቡር ሚኒስትር፣ ይኼን ሳደርግ የነበረው ለአገሬ ከነበረኝ ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡
 • የአገር ፍቅር ስትል?
 • ማለቴ ተቃዋሚዎቹ ጥሩ የፖለቲካ ፕሮግራም ስለሌላቸው እኔ ሁሌም ለአገር የሚጠቅም ፕሮግራም ያለው ኢሕአዴግ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡
 • ታዲያ ኢሕአዴግን ለምን አትቀላቀልም ነበር?
 • እንደዚያ ከማድረግ አገሪቱ ውስጥ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሉ በማስመሰል ኢሕአዴግን ማገዝ ይበልጣል ብዬ ነዋ፡፡
 • ታዲያ አሁን ምንድነው ያስከፋህ?
 • እኛ ስንት መስዋዕትነት በከፈልንበት ፖለቲካ ውጭ ቆይተው የመጡት ሲፈነጩበት ሳይ በጣም ተናደደኩ፡፡
 • ማን ነው የፈነጨው?
 • ይኸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መስቀል አደባባይ እየወጡ እየተቀበሏቸው አይደል እንዴ?
 • የእናንተ ፓርቲ ደጋፊዎችስ ሠልፍ መውጣት ሲፈልጉ ትወጣላችሁ አይደል እንዴ?
 • እሱማ ባለፈው 27 የምንሆን ሰዎች ቢሮአችን ቦታ ስለጠበበን ኬክ ቤት አስፈቅደን ስብሰባችንን በሰላም አካሂደናል፡፡
 • እኔን በክብር እንግድነት እንድገኝ የጋበዛችሁኝ ስብሰባ አይደል?
 • ከደጋፊዎቻችን መብዛት በተነሳ ግፊያ የኬክ ቤቱ ሁለት ብርጭቆዎች ከመሰበራቸው ውጪ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፡፡
 • እ. . .
 • በመካከላችን የነበረውን የአስተዳደርና የፋይናንስ ችግር ሳይቀር በሰላማዊ መንገድ ነው የፈታነው፡፡
 • አሁን ምን እያልክ ነው ታዲያ?
 • እንደ እኛ ሰላማዊ ፓርቲ የነበረባት አገር እንደዚህ ከውጭ እያመጣችሁ ስታበጣብጡ ሳይ አዝኜ ነው፡፡
 • ምን ይደረግ እያልክ ነው?
 • እኔማ ከፖለቲካ ሕይወት መገለል ፈልጌያለሁ፡፡
 • ስለዚህ ፖለቲካው በቃኝ እያልክ ነው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ግን እስከ ዛሬ ላገለገልኩበት ጥሩ ክፈያ እፈልጋለሁ፡፡
 • ተቆራጭ ይደረግልህ አልነበር እንዴ?
 • እስከ ዛሬ የታለልኩት ይበቃል ክቡር ሚኒስትር፡፡ አሁን ቋሚ ሀብት ነው የምፈልገው፡፡
 • የምን ቋሚ ሀብት?
 • ሰሞኑን ወደ መሬት ባንክ ከገቡት መካከል እኔም ድርሻዬን እፈልጋለሁ፡፡
 • ምን ያህል መሬት?
 • 10,000 ካሬ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ድሮ ድሮ በምን እንደማደንቅህ ታውቃለህ?
 • በምንድነው የምታደንቂኝ?
 • በዓል፣ ኮንፈረንስና ስብሰባ አስታከህ የሚገርም የቢዝነስ ሐሳቦች ስለነበሩህ አደንቅህ ነበር፡፡
 • አሁንስ?
 • አሁንማ አረጀህ መሰለኝ፡፡
 • ስሚ እኔ የቢዝነስ ሐሳብ ከማመንጨት መቼም ቢሆን ሰንፌ አላውቅም፡፡
 • ታዲያ የት አሉ ሐሳቦችህ?
 • ይኸውልሽ በዚህ ወር የሚከበሩትን ሁለቱን በዓላት በአሪፍ ለማክበር ተዘጋጅቻለሁ፡፡
 • ከመስቀል ውጪ ሌላ በዓል አለ እንዴ?
 • የኢሕአዴግ ጉባዔን ረሳሽው?
 • አሁን ጥያቄው ምን ዓይነት የቢዝነስ ሐሳብ አለህ የሚለው ነው?
 • እንደ ባለፈው ደግሜ አልሸወድም፡፡
 • ባለፈው በምንድነው የተሸወድከው?
 • የቀለም ቢዝነሱ እኮ ዓይኔ እያየ ነው ያመለጠኝ፡፡
 • ታዲያ አሁን ምን አሰብክ?
 • ኢትዮጵያ ውስጥ የጨርቅ ቢዝነስ እየሞቀ እንደሚሄድ ገብቶኛል፡፡
 • አልገባኝም?
 • ስሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ወደ አገር ቤት ከገቡ በኋላ ሁሉም በዓርማዎቻቸው ፉክክር ይዘዋል፡፡
 • እሱማ ስንት ሰው እየጨረሰ ነው፡፡
 • አየሽ ሕዝቡ የሚደግፈውን ፓርቲ ዓርማ በሸሚዝ፣ በሱሪ፣ በቀሚስ ብትይ በሻሽ ማድረግ ይፈልጋል፡፡
 • ጥሩ ሐሳብ ይመስላል፡፡
 • እሱ ብቻ ሳይሆን ሲፈለግ የሚለበስ፣ ካልሆነ አልጋ ልብስ የሚሆን ነገር ማዘጋጀት እንችላለን፡፡
 • ምን እናድርግ እያልከኝ ነው?
 • አሁን እንደ ምንም ብለን ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሼድ ብንይዝ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
 • እንደዚያ ከሆነማ ከቻይና የስፌት ማሽኖችን በአስቸኳይ ማስጫን አለብን፡፡
 • አንቺ እኮ ሐሳብ ማዳበር ትችይበታለሽ፡፡
 • እኔ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡
 • የምን ጥያቄ?
 • እኔም አንተም የፋሽኑ ዓላማም ብዙም አይገባንም ብዬ ነው፡፡
 • ምን ችግር አለው?
 • ማለቴ በዚህ የጨርቅ ቢዝነስ የተለያዩ ልብሶችን የምናመርት ከሆነ ስለፋሽን ብዙ ዕውቀት የለንም ብዬ ነዋ፡፡
 • ለዚህ ሥራ ፋሽን ማወቅ አያስፈልግም፡፡
 • ምን ነካህ? ሰው እኮ ሸሚዝና ቀሚስ ስለሰፋህ ብቻ ልብስ የሚገዛ መሰለህ እንዴ?
 • ነገርኩሽ እኮ ሰው የእኛን ልብስ የሚገዛው ለፋሽን ብሎ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ለምንድነው የሚገዛው?
 • ለባንዲራው!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ በቅርቡ ታስሮ የተፈታ ወጣት ይደውልላቸዋል]

 • ሄሎ ማን ልበል?
 • አያውቁኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ፈልገህ ነው?
 • አገሪቱ ውስጥ የሚፈጸመው ድርጊት አሳዝኖኝ ነው፡፡
 • ምንድነው ያሳዘነህ?
 • አገሪቱ ውስጥ ለውጥ መጣ ብለን ጨፍረን ሳንጨርስ ምን አድርገን ነው ሌላ ጣጣ የምታመጡብን?
 • ስማ ይኸው ዴሞክራሲ አላችሁ ሁሉን ነገር ለቀቅነው፣ አሁን ደግሞ ምን ፈለጋችሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር የድጋፍ ዜማችንን ሳንጨርስ፣ የተቃውሞ ዜማ እንድናወጣ እያደረጋችሁን እኮ ነው፡፡
 • ሕዝቡ ወርቅ ስታነጥፍለት ፋንድያ ይላል የተባለው እውነት ነው ማለት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንዲያውም ሕዝቡ ፋንድያ ተነጥፎለት አንድ ቀን ወርቅ ይሆናል ብሎ እየጠበቀ ነው፡፡
 • ለጊዜው ተረጋጋ፣ ስድቡንም አቆየው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በዚህች አገር መዝናናት እንኳን አይቻልም ማለት ነው?
 • ከዚህ በላይ እንዴት መዝናናት ፈለግህ?
 • ይኸው ከሥራ በኋላ እንኳን ቢራ መጠጣት አልቻልንም፡፡
 • አንተ ቢራ መጠጣት ምን ያደርግልሃል?
 • ተገድጄ ነው የምጠጣው ክቡር ሚኒስትር?
 • ማን ነው ያስገደደህ?
 • ያው ፀሐዩ መንግሥታችን ለዜጎቹ ቤት መሥራት ስለከበደው በቢራ ቤት ካገኘን ብዬ ነው የምጠጣው?
 • በቢራ ቤት ይገኛል ያለህ ማነው?
 • ማለቴ የቢራ ቆርኪ ፍቄ ቤት ከደረሰኝ በሚል ልማታዊ አስተሳሰብ ነው ቢራ የምጠጣው፡፡
 • ለመሆኑ ምን ሆነህ ነው?
 • ቢራ ስጠጣ ታሰርኩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አደገኛ ቦዘኔ ነህ ማለት ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ሥርዓት ያለኝ ኩሩ ዜጋ ነኝ፡፡
 • ለዚያ ነው የታሰርከው?
 • ነገርኩዎት እኮ ከጓደኞቼ ጋር ስዝናና ነው የታሰርኩት፡፡
 • ለመሆኑ አሁን ይኸው ተለቀሃል አይደል እንዴ?
 • እኔማ የደወልኩልዎት አንድ ነገር ልጠይቅዎት ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • አገር ውስጥ የገቡት ፓርቲዎች እናንተው ፈቅዳችሁ አይደል እንዴ የገቡት?
 • እሱማ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ብለን ነው፡፡
 • ታዲያ የፈለጉትን ፓርቲ መደገፍ አይቻልም?
 • ይኼማ ዴሞክራሲያዊ መብትህ ነው፡፡
 • ከታሰርኩ በኋላ የግንቦት 7 ደጋፊ መሆኔን ጠየቁኝ፡፡
 • ምን አልካቸው  ታዲያ?
 • አዎን ካልኳቸው ሌላ ችግር ውስጥ እንዳይከቱኝ ብዬ የሌላ ደጋፊ ነኝ አልኳቸው፡፡
 • የማን ደጋፊ?
 • የግንቦት 20!

[ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አድማ በማድረግ ታግደው ከነበሩ ሠራተኞች ከተመለሱት ውስጥ ተወካያቸው ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር እያወራ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ሊያነጋግሩኝ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሠግናለሁ፡፡
 • ምንም ችግር የለውም፣ ዘመኑ የይቅርታና የምሕረት ስለሆነ ብታጠፉም ከእናንተ ጋር ለመደመር ዝግጁ ነን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ እኮ ምንም አላጠፋንም፡፡
 • ለዚያ ነው ከሥራ የታገዳችሁት?
 • አሁንም ቢሆን እኛ የጠየቅነው ሕጋዊ መብታችንን ነው፡፡
 • የምን ሕጋዊ መብት?
 • የሚከፈለን ደመወዝ ይጨመር ማለት መብታችን መስሎኝ?
 • ቢሆንም የመሥሪያ ቤቱን ሰላም በሚያውክ መንገድ መሆን አልነበረበትማ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ እኮ መሥሪያ ቤቱ በወንዝና በጅረት እየተደራጀ ጥቅማ ጥቅማችንን ማስጠበቅ አልቻልንም ብለን ነው የጠየቅነው፡፡
 • ነገርኩህ እኮ ዘመኑ የፍቅርና የመደመር ስለሆነ ለጊዜው ጥፋታችሁን ምሕረት አድርገንላችኋል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁንም ጥያቄያችን በአግባቡ ካልተለመሰ ዘለቄታዊ መፍትሔ አይገኝም፡፡
 • አሁንም ምሕረት ተደርጎላችሁ መሥሪያ ቤቱን ለመበጥበጥ ትፈልጋላችሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ እኮ እንደ ዜጋ እናንተ ከላይ ያላችሁት አመራሮች የምታገኙትን እንደ ቤት ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች ይሰጡን ነው ያልነው፡፡
 • የምን ቤት ነው?
 • ሁላችንም ኑሮ ስለከበደን መንግሥት ቤት እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡
 • እኔ እኮ ያልገባኝ ይኼን አመፅ ለማስነሳት የምትሞክሩት ደግሞ በፍፁም የማትግባቡ ሰዎች ናችሁ እኮ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ ሌላ ጥያቄ የለንም፣ ጥያቄያችን መብታችን እንዲከበርልን ነው፡፡
 • አሁንማ ሲገባኝ እናንተ ከዚያም በላይ አጀንዳ አላችሁ፡፡
 • ምን ዓይነት አጀንዳ?
 • መፈንቅለ ሚኒስትር!