Skip to main content
x
አገር ፀንታ የምትቆመው ቅንነትና ሰፋ ያለ ዕይታ ሲኖር ነው!

አገር ፀንታ የምትቆመው ቅንነትና ሰፋ ያለ ዕይታ ሲኖር ነው!

በአሁኑ ጊዜ ውስብስቡን የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት የአገር ፍቅር፣ ዕውቀት፣ ብስለት፣ ቅንነትና ሰፋ ያለ ዕይታ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ድረስ በታሪኩ የሚታወቀው ለአገሩ ባለው ጥልቅ ፍቅርና ተወዳዳሪ በሌለው አስተዋይነቱ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ የያዘን ሕዝብ አንድ ላይ አስተባብሮ መምራት ከተቻለ አንፀባራቂ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል፣ ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ድል ህያው ምስክር ነው፡፡ ሕዝባችን ዘመናትን አብሮ ያሳለፈው በጋራ አገሩን ሲጠብቅ ነው፡፡ ይህንን ታሪካዊ ሕዝብ በአግባቡ መርቶ ለልማት ማሠለፍ ቢቻል ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ የምድር ገነት ትሆን ነበር፡፡ ይህ ዕድል በመታጣቱ ግን ኢትዮጵያ የድህነት፣ ከዚያም አልፋ ተርፋ የረሃብና የጠኔ ተምሳሌት ናት፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ውርደት ውስጥ ለመውጣትና በአደባባይ ቀና ብሎ ለመሄድ፣ ለዘመናት ከሚያናጥሩት ኋላቀርና አሳፋሪ ድርጊቶች መገላገል ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት የሚታዩ የነውጠኝነት ባህሪ ያላቸው ድርጊቶች ለአገርም ለሕዝብም ጠንቅ እየሆኑ ነው፡፡ ቅንነትና ሰፋ ያለ ዕይታ የሌላቸው በእብሪት የተሞሉ ድርጊቶች ለማንም እንደማይጠቅሙ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩ በተጀመረው የለውጥ ጎዳና ወደ ዴሞክራሲና ብልፅግና እንድትገሰግስ ይፈልጋል፡፡ ለውጡ በስኬት መከናወን የሚችለው ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ሰላም የሚሰፍነው ግን የአገር ጉዳይ ተዋንያን ሙሉ ተሳትፎ ሲታከልበት ነው፡፡ አንዱ እየገነባ ሌላው የሚያፈርስ ከሆነ ሰላም አይኖርም፡፡ ሰላም በሌለበት ደግሞ ዴሞክራሲም ዕድገትም አይታሰቡም፡፡ የአገር ህልውናም ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ከጠባብ የቡድን ጥቅም በላይ አገር የምትባል የጋራ ጎጆ መኖሯን የዘነጉ ወገኖች፣ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ ካልተገላገሉ የአገር ህልውና ችግር ይገጥመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ የጋራ እናት እንድትሆን ጥርስን ነክሶ ከመታገል ይልቅ፣ የጎራ ፖለቲካ ውስጥ ተወሽቆ አገርን ለማተራመስ መሞከር የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕይታ የተጋረደባቸው ኃይሎች የማንነትና የግዛት ትንቅንቅ በመጀመር የለውጡን ጉዞ እያደናቀፉ ነው፡፡ የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን የተወሰኑ ወገኖች ለማድረግ የሚደረገው መሯሯጥና የማኅበራዊ ሚዲያ የቃላት ጦርነት የለውጡን ዓላማ እየተፃረረ ነው፡፡ ልዩነትን አክብሮ ለአገር መፃኢ ዕድል ከመጨነቅ ይልቅ፣ ቀውስ ለመፍጠር የሚደረገው ጥድፊያ ከአጥፍቶ ጠፊነት ተለይቶ አይታም፡፡

ሕዝብ በሰላምና በእኩልነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሲገባ፣ አገርን መቀመቅ የሚከት ቀውስ መፍጠር ጤነኝነት አይደለም፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ ስለሆነች ለተጀመረው ለውጥ ቢቻል ደጋፊ መሆን፣ ካልተቻለ ደግሞ አደብ ገዝቶ የራስን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይሻላል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ አሸናፊ መሆን የሚቻለው የተሻለ አጀንዳ ይዞ ሕዝብን ከጎን ማሠለፍ ሲቻል ነው፡፡ በሕዝብ ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ነውጠኝነትና ሞገደኝነት የሚያጋልጡት አጀንዳ አልባነትን ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው የተሻለ ሐሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ፣ ሰላምና መረጋጋቱን እያደፈረሰ ደኅንነቱን የሚያቃውስ አይደለም፡፡ የአጀንዳ ወይም የሐሳብ እጥረት ያለባችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ስብስቦች ነውጥን በአማራጭነት ለመጠቀም ከምትሞክሩ፣ ምኅዳሩን ለቃችሁ ብትወጡ ለሕዝብ ውለታ እንደዋላችሁ ይቆጠራል፡፡ አገር እናንተን የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም፡፡ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለማኅበራዊ ፍትሕ ተስፋ የሰነቀ ሕዝባዊ ለውጥን ለማሰናከል መሞከር ከሕዝብ ጋር ያጋጫል፡፡ ሕዝብ ደግሞ በአገሩ ህልውና አይደራደርም፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን የሕዝብ የዘመናት ጥያቄዎች ይመለሳሉ፡፡ ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ በአገሩ ዴሞክራሲ ሰፍኖ በነፃነትና በእኩልነት መኖር ይፈልጋል፡፡ አገር ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ፀጋ ላይ ተቀምጣ ደሃ መሆኗ ስለሚያንገበግበው፣ ሠርቶ የሚያሠራ ብቁ አመራር ይፈልጋል፡፡ ይህ አመራር የሚገኘው ደግሞ በነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ነው፡፡ ይህንን አማላይ ምርጫ ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚወዳደሩበት ምኅዳር ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ፣ ነፍጥ ያነገቡ ሳይቀሩ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አገር ቤት ገብተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በእኩልነት በምርጫ ሕጋዊ ማዕቀፎችና በተለያዩ ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ ድርድር አድርገው፣ ሒደቱ ይመቻቻል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩት መንግሥት፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማሳመር በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ የተቸረው ጥረት አድርጓል፡፡ ይህንን ምሥጉን ተግባር በተቻለ አቅም በመረባረብ መደገፍ ሲገባ፣ ልፋቱን መና የሚያስቀር የዘቀጠ ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ሕዝብ ደግሞ በንቃት እየተከታተለ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር መጣላት ውጤቱ ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡

አሁን ዋናውና መሠረታዊው ጉዳይ የተጀመረው ለውጥ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አስተማማኝ እንዲሆን መሥራት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች ለለውጡ ስኬት መደጋገፍ አለባቸው፡፡ ይህ መደጋገፍ ለአገሪቱ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲኖረው፣ የተገኘው መልካም አጋጣሚ እንዳይመክን ያግዛል፡፡ በዚህ መሠረት መተባበር ሲቻል የሕዝብ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ይመለሳሉ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይጠናከራል፣ በአገር የጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይኖራል፣ የነገውን ቀና ጎዳና በኅብረት ለመተለም ይጠቅማል፡፡ ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር የሚቻለው የተለያዩ ዓላማዎች ያሏቸው የፖለቲካ ኃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር እንጂ፣ በጦርነት እንዳልሆነ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ በቂ ነው፡፡ ልዩነትን ማክበር የፖለቲካ የጥበብ መጀመርያ ሲሆን፣ ተደራድሮ የጋራ ውጤት ማግኘት ደግሞ ማሳረጊያው ነው፡፡ ሥራ ፈት ይመስል ለሕዝብ የማይጠቅም አጀንዳ እያራገቡ በሕይወቱ መቆመር፣ አገርን ቀውስ ውስጥ ከመክተት ውጪ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ቀናነትንና አርቆ አሳቢነትን የሚጠይቅ እንጂ፣ በጊዜያዊ ድል ተኩራርቶ የተገኘውን ሁሉ ጠራርጎ ለመውሰድ ማሰፍሰፍ አይደለም፡፡ በጊዜያዊ ድል የሚኩራሩ ምስኪኖች መጨረሻቸው ፀፀት ነው፡፡ አሁን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የሚታየው ከታሪክ ትምህርት ላለመቅሰም የሚደረገው ሁካታ፣ እንወክለዋለን የሚሉትን ወገን ጭምር የማይጠቅም ስለሆነ ቆም ብለው ቢያስቡ ይበጃቸዋል፡፡ ለትዝብት የሚዳርጉ ብዙ ነገሮችን ሕዝብ በሚገባ እያየ ነው፡፡

የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በቅጡ ሊያስቡበት የሚገባው ዋነኛ  ጉዳይ፣ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ሕገወጥነትን ማምከን መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልባቸው፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ መብቶች በተግባር ሥራ ላይ እንዲውሉላቸው፣ በነፃነት የፈለጉትን እንዲደግፉ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ በአገራቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑና አገራቸው እንድትመነደግ ጠንክሮ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ፈንታ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሡ የሚጎዱት ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞችና ንፁኃን ወገኖች ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙ ግጭቶች ሰለባ የሆኑት እነዚህ ምስኪን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊና ታላቅ አገር ሆና ሳለ በስግብግብነት ስሜት መራኮትና ቀውስ መቀስቀስ፣ የአምባገነኖች ተግባር እንጂ የዴሞክራቶች ተግባር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እንኳን ለገዛ ልጆቿ ለአፍሪካውያን የጋራ ቤት መሆኗን መዘንጋት ያስተዛዝባል፡፡ ይልቁንም ለሐሳብ ነፃነት ክብር ይሰጥ፣ የጋራ በሆኑ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገርና መደራደር ይለመድ፣ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ለሕዝብና ለአገር ህልውና ቅድሚያ ይሰጥ፡፡ ቅንነትና ሰፋ ያለ ዕይታ ይኑር፡፡ አገር ፀንታ መቆም የምትችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው!