Skip to main content
x

ንግድና ፖለቲካ

በተስፋዬ ታደሰ    

የበለፀገ ኢኮኖሚና የዳበረ ዴሞክራሲ ያላቸው አገሮች አንዴ ጦረኛ፣ ሌላ ምሁር፣ ከዚያ ደግሞ ዘረኛ የሆነ መሪ ሊኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ አሜሪካ እንደ ጆርጅ ቡሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍጋኒስታን፣ኢራቅ፣ፓኪስታን፣ ወዘተ ዜጎችን ለሞት፣ሥቃይናስደት የዳረገ ጦረኛ ፕሬዚዳንት ነበራት። ከእሱ ቀጥሎ ደግሞ ገና ለፕሬዚዳንትነት በተመረጠ ማግሥት የዓለም የሰላም ኖቬል ሽልማትን የተሸለመው ባራክ ኦባማ መርቷል። በአሜሪካ የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዚዳንት የተተካው ግን የመጨረሻ የነጭ አከራካሪና ዘረኛ በሆነው ዶናልድ ትራምፕ ነው።

በዚህ መልኩ ፕሬዚዳን ጆርጅ ቡሽ ያበላሸውን ገጽታ ባራክ ኦባማ ሲገነባ፣ ሬዚዳን ባራክ ኦባማ የገነባውን ገጽታ ዶናልድ ትራምፕ መልሶ ያፈርሳል። ያም ሆኖ ግን የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የፖለቲካ አመራር ብቃት በአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታና በሕዝቡ ሕይወት ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ውስን ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበለፀጉ ኢኮኖሚና የዳበረ ፖለቲካዊ ሥርዓት በሌላቸው አገሮች ግን፣ የመሪዎች የአመራር ብቃት የህልውና ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የደሃ አገሮች መሪዎች የፖለቲካ አመራር ብቃት በአገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ከማረጋገጥ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ተያያዥነት አለው።

ዶናልድ ትራምፕ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ከምርጫ ሒደቱ አንስቶ አብላጫ ድምፅ አግኝተው ሥልጣን በተረከቡበት ወቅት ባደረጓቸው ንግግሮች፣ ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች፣ በተከተሉት የአመራር ፍልስፍና የዓለም መነጋገሪያ ሆነው መሰንበታቸው ማንም የሚዘነጋው አይደለም፡፡ የምርጫ ሒደቱ አወዛጋቢነት እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ አሸናፊነታቸውን ተከትሎ ሥልጣን በተረከቡበት ወቅት የወሰዷቸው ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች አነጋጋሪ፣ አከራካሪ፣ አወዛጋቢና ቁጣ ያስነሳም ነበር፡፡ ሰውን በሃይማኖቱ መርጠው የሰባት ሙስሊም አገሮች ዜጎችና የሁሉምገሮች ስደተኞች ዩናይትድ ስቴት እንዳይገቡ ማገዳቸው ዓለምን ያስቆጣ፣ አሜሪካኖችን ያሳሰበ፣ ለአደባባይልፍም የጋበዘ ነበር፡፡ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መስተዳድር ዩናይትድ ስቴት ከውጪ በምታስገባው ብረትና አሉሙንየም ምርት ላይ ጫን ያለ አዲስ ቀረጥ መጣሉም ይታወሳል፡፡

ትራምፕ አሜሪካን ፈርስት (አሜሪካ ትቅደም) እያሉ አፍሪካውያንን ያስቆጣ ፀያፍ ንግግር ማድረጋቸው፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን የንግድ መስመር ማጥበባቸው፣ ከዚህ ቀደም አሜሪካ ከምትታወቅበት ለጋስነት እጇን መሰብሰባቸው፣ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የተገነባው የአሜሪካን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲልና ተራ መነጋገሪያ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ንግድ አንድ አገር የሚያስፈልጋትን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያመጣ ሕጋዊነትና ድንበር ዘለልነት እንጂ፣ አጥር አይፈልግም፡፡ ከዚህ አኳያ ትራምፕ አሜሪካ ትቅደም በማለት ባራመዱት ግለኛ አስተሳሰብ ሌሎች አገሮችን በማግለል፣ በተለያየ መንገድ ጫና አሳድሮ አሜሪካን ብቻ ይዞ የበላይ ለመሆን ያደረጉት ጥረትና የወሰዷቸው ዕርምጃዎች በአገሪቱ ንግድ ላይ አሉታዊ ውጤት መፍጠሩ አይቀርም፡፡

ትራምፕ ከምርጫ ቅስቀሳ አንስቶ ሥልጣን እስከ ያዙበት ጥቂት ወራት ድረስ ዓለምን አነጋገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሀላ ከፈጸሙበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ዓለምን በማዕበል አናወጡ፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱ መሪዎች ዓለምን የደረሱበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ ትራምፕ ከጅምራቸው አሜሪካንን የሚጎረብጥ አመራር፣ የአመራር ፍልስፍና በመከተላቸው አሜሪካን አይመሯትም የሚል መጠራጠርን በመፍጠር፣ በማወዛገብ፣ ግራ በማጋባት፣ በማስከፋት፣ የአሜሪካን ሕዝብ ሳይቀር በተቃውሞ ሠልፍ በማስወጣት የዓለምን ልብ ያንጠለጠሉ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ግን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አቃፊነትን፣ አንድነትን፣ መደመርን፣ ይቅር ባይነትን በመስበክ ነው የዓለምን ነፍስ የመገቡት፡፡

በምርጫ ሳይሆን ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አገሪቷን ከገባችበት ከፍተኛ ውጥረት ለማውጣት ባደረገው የአመራር ለውጥ በድንገት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመጡት  ዓብይ (ዶ/ር) የዚችን አገር በሽታ የላብራቶሪ ውጤት ከእነ መድኃኒቱ ይዘው ደርሰውላታል፡፡ ፍቅር፣ አንድነትና መደመር በተባሉት መድኃኒታቸው የጠወለጉ ሕይወቶችና የመነመኑ ተስፋዎች ለምልመዋል፣ ብዙ የታሰሩ ነገሮች ተፈተዋል፡፡

ከታሰሩት ነገሮች ውስጥ የቁም እስረኞች የነበሩት የአገራችን ሚዲያዎች (በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች) በነበረባቸው የድርጅትና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የተቋቋሙበትን ዓላማ ስተው ውሸትና ውዳሴ ላይ ብቻ ያቀነቅኑ የነበሩ፣ አሁን ሀቅ ላይ የተመሠረተና ሚዛናዊ ዘገባ በመዘገብ ሚዲያ፣ ሚዲያ መሽተት ጀምረዋል፡፡

ሌሎቹ የቁም እስረኞች የኢትዮጵያ ዜጎች አንደበቶች ናቸው:: እየተፈጸመና እየተፈጸመባቸው ያለውን በደል፣ ጭቆና፣ የፍትሕ መዛባት፣ አድልኦ፣ ሙስና፣ ሌብነት፣ የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት፣ ወዘተ ‹‹ብዙ ነገር እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን›› ብለው ታፍነው የነበሩ አሁን የመናገር ዕድልም፣ አድማጭም አግኝተዋል፡፡ ሌሎቹ እስረኞች አጥፍተውም ሳያጠፉም ብቻ በሰበብ አስባቡ እስር ቤት (ማረሚያ ቤት) ወይም ወህኒ ቤት እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ የታሰሩት ወገኖች ናቸው፡፡ የታሰሩት ሰዎች ጥፋተኛና ወንጀለኛ ነበሩ፣ አልነበሩም የሚለው የጽሑፌ ዓላማ ስላልሆነ ለፍትሕ አካላት ትቼዋለሁ፡፡ በዶ/ር ዓብይ የመጀመርያዎች ጥቂት የሥልጣን ቀናት ውስጥ ግን የወንጀለኛነት ፍርድ ተፈርዶባቸውና ሳይፈረድባቸውም ጭምር፣ ለበርካታ ዓመታት በእስር ቤት የኖሩ የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ሳይቀሩ በይቅርታና በምሕረት ከእስር ተለቀዋል፡፡

ሌላው እስረኛ የአገራችን ንግድ ነው፡፡ ንግድና የውጭ ምንዛሪ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ከሌሎች የአፍሪካና የዓለም አገሮች ጋር ተፎካካሪ ሆና፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆና እንድትገኝ የሚያስችላት ዋነኛ መዘውር ነው፡፡ ሆኖም ቢሮክራሲው የበዛ፣ ሕገወጥነት ያጠቃው፣ በአድርባይነትና በኋላቀር አሠራር የታነቀ ስለሆነ፣ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያክል ፋይዳ አላገኘችም፡፡ ዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ተቀዳሚ ካደረጓቸው ተግባራቸው ውስጥ በጠቀስኳቸውና ባልጠቀስኳቸው ምክንያቶች የታሰረውን የንግድ ሥርዓት ማፍታታት አንዱ ነበር፡፡ ገና ከጅምራቸው ከተባበሩት ኤምሬትስ መንግሥት ጋር ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሦስት ቢሊዮን ዶላር አግኝተው፣ በዘመናዊው ሕክምና በማይታወቀው ‹‹የምች›› በሽታ ለተመታው የመንግሥት ካዝና ደርሰውለታል፡፡

በማንኛውም ምክንያት የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው የሚገኝ የአገራችን ዜጎች ወደ ባንኮች ሄደው እንዲመነዝሩ ባደረጉት አገራዊ ጥሪ በጣም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መመንዘሩ ሌላው ስኬታቸው ነው፡፡ በውጭ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ማኪያቶ አንድ ዶላር ለአገራቸው ልማት እንዲያበረክቱ ባደረጉት ጥሪ፣ በቀን አሥር ዶላር ለኢትዮጵያ ቃል ተገብቶላታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በሕገወጥ መንገድ (ጥቁር ገበያ) የሚመነዝሩ አካላትን ሱቆች በመዝጋት ሕገወጥነትን በማቀጨጭ፣ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ እንዲነግሥና የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን እንዲጎለብት የተሠራው ጅምር ውጤትም የታየበት ነው፡፡

ከአገረ ኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላምና በተደረገው ስምምነት የጎሪጥ ይተያዩ የነበሩት ሁለቱ አገሮች በእህትነት ዓይን እየተያዩ፣ በጋራ አብሮ ለመልማትና ለማደግ ከመወሰናቸውም በተጨማሪ፣ አሰብና ምፅዋ ወደብን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ የወጪ ንግዳችን ያሉበትን ውጣ ውረዶችና የቤት ሥራዎች በማቃለል የወጪ ንግድ አማራጫችንን ለማስፋትና የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ለማሳደግ የተገኘ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸው ለአገራችን ባዘነቡት የፍቅር፣ የአንድነት፣ የዴሞክራሲና የመተሳሰብ ዝናብ ከሕፃን እስከ አረጋውያን ባሉ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ ሰርገው ገብተዋል፡፡ ይህም ሳይበቃ የኤርትራን መንግሥት በፍቅርና በይቅርታ አሸንፈው አገረ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ደምረዋታል፡፡ የደቡብ ሱዳኖችን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ዶ/ር ሪክ ማቻርን አጨባብጠዋቸዋል፡፡ 

 ውድ የጽሑፌ አንባቢያን የተነሳሁበትን አልዘነጋሁም፡፡ ፖለቲካ የጨዋታ ሜዳ ነው፡፡  ሜዳው ምቹና የተስተካከለ ከሆነ ጨዋታዎችን በጥሩ ሁኔታ ማካሄድ ይቻላል፡፡ የጨዋታ ሜዳው ከጠበበ፣ ድንጋይ ካለው፣ እሾህ ካለው፣ ካልተስተካከለ ተጨዋቾች ይጎዳሉ፣ አመርቂ ጨዋታም መጫወት አይቻልም፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በተከተሉት የመደመር ፍልስፍና ከአገር እስከ ጎረቤት አገሮች ድረስ የፈጠሩት ፖለቲካዊ ሰላም፣ አንድነትና በጋራ የመልማት ስምምነቶች ቀጣይነታቸው የሚረጋገጠው በንግድ ግንኙነት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን አገሪቱን፣ ጎረቤት አገሮችንና ምሥራቅ አፍሪካን ጭምር የሰላም ቀጣና ለማድረግ ከጅምሩ አንስቶ የተከናወኑ ሥራዎችና የታዩት ለውጦች፣ ለአገራችን ተወዳዳሪነትና ዕድገት ወሳኝ ለሆነው የወጪ ንግዳችን ጥሩ መደላድል ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለንግዱ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ስለሆነ፣ በዚህ ምቹ ሁኔታ ውስጥ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች እያስተካከልን ወደፊት ልናራምደው እንችላለን፡፡ ከዚህ አኳያ የአገር ውስጥና የወጪ ንግዳችን ያለበትን ቢሮክራሲዎች፣ ኋላቀርነትና ማነቆዎች በማፍታታት ለአገሪቱ ማስገኘት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያስገኝ እንዲችል የንግድ ሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የንግዱን ማኅበረሰብ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት የዳረጉ የቅድመ ንግድ ሥራ ፈቃድ ብቃት ማረጋገጫና የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመርያዎች በመሻሻል ላይ ሲሆኑ፣ እነዚህ መመርያዎች ተሻሽለው ወደ ተግባር ሲወርዱ የንግድ አሠራሩን ቀላልና ቀልጣፋ በማድረግ ከዓለም የንግድ ሥርዓት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት፣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የግል ባለሀብቱን በማበረታታት ፓልም የምግብ ዘይት አቅራቢዎች በአገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዲያመርቱና ለዘይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማዳን፣ ከፍጆታም አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲቻል በዚህ ዘርፍ ላይ መሰማራት የሚችሉትን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ለመለየት የሚያስችል መመርያ የተዘጋጀ ሲሆን፣ መንግሥት ከመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጥ ሥርጭት የሚወጣበት ስትራቴጂም እየተነደፈ ይገኛል፡፡

ምንም እንኳን አሁን የተፈጠረው አገራዊ መነቃቃት ለንግዱ መጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ቢሆንም፣ በተለመደው አሠራር በመሥራት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል አገሪቱ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ በንግዱ ዘርፍ መድረስ የሚገባት ደረጃ ላይ ለማድረስ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥና የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ማሳለጥ፣ ሕወጥ ንግድን በማስቀረት ሕጋዊ ንግድ እንዲሰፍን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር፣ የንግዱን ዘርፍ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም መገንባት፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ማስወገድና የወጪ ምርቶችን በጥራትና በመጠን የሚያሳድጉ ተግባራትን መፈጸም በሚሉ ስድስት አጀንዳዎች ላይ አገራዊ የንግድ ልማት ንቅናቄ ዕቅድ በንግድ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በ2011 በጀት ዓመት ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ይህ የንግድ ልማት የንቅናቄ ዕቅድ የንግዱ ዘርፍ በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አጋማሽ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንዳያመጣ ካደረጉት ማነቆዎች በመነሳት በተመረጡ ስድስት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ “ዘመናዊና ፍትሐዊ ንግድ ለአገራችን ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ታጅቦ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሳጠቃልለው የንግዱን ዘርፍ ካለበት ችግር በማላቀቅ ኅብረተሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚያደርግና በወጪ ንግድ ግኝት የአገራችንን ኢኮኖሚ የሚጠግን የንግድ ዘርፍ እንዲኖረን፣ የማይመለከተንና ድርሻ የሌለን ኢትዮጵያዊ የለንምና ሚናችን አንድ ጠብታም ብትሆን እሷኑ ሳንሰስት ተወጥተን በስኬት እንገናኝ እላለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡