Skip to main content
x

ቋንቋ የማን ነው?       

በአሰፋ አደፍርስ    

ቋንቋ የማንም ንብረት አይደለም፡፡ መገናኛ፣ መግባቢያና መገበያያ እንጂ! ይህንን የተረዱ የአውሮፓ ተገዥ የነበሩት ብዙ የአፍሪካ አገሮች ነፃነት ካገኙና በ1950ዎቹና 60ዎቹ ላይ ራሳቸውን ማስተዳደር እንደጀመሩ፣ ወደየቋንቋቸው ቢሰማሩ ለብዙ ዓመታት የልጅ ልጆቻቸው ገና የእነሱ የተባለውን ቋንቋ ተምረው እስኪግባቡ ድረስ፣ ከልማትና ከቴክኖሎጂ ተለያይተው የባሰውኑ ወደ ኋላ እንዳይቀሩ አስበው ያንን በግፍ ይገዛቸው በነበረው ሕዝብ ቋንቋ መጠቀሙን ሲመርጡ ያነሱት ጥያቄ ለመሆኑ ቋንቋ የማን ነው? ብለው ነበር፡፡

እዚህ ላይ “ቋንቋ የማን ነው?” ብለው የጻፉትን ምሁር ታከለ ታደሰ (ዶ/ር) አስታወሰኩኝ። ያችን መጽሐፍ ማንበቡ ይጠቅማልና ሁሉም ቢያነብ መልካም ነው እላለሁ። እንግሊዝኛን ቀላቅሎ መናገርን እንደ ዕውቀት በመቁጠር ዛሬ ባለሥልጣኖቻችንም ሆኑ የመንደር ሰው ሁሉ፣ በማይዘልቀውና ትርጉምንም በማያውቀው እንግሊዝኛ መጫት ሲያስገባ እናያለን። ለምን ቢባል እንግሊዝ በቴክኖሎጂ ቀደምትና የሠለጠነች በመሆኗ፣ ቀጥሎም ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ የማይሆናት  ዕድሜ ያላት አሜሪካ (የእንግሊዝ የበኩር ልጅ) በዴሞክራሲ የቀደመች፣ በሥልጣኔ የላቀችና የሁሉ እኩል  አገር በመሆኗ በእንግሊዝኛ ስለተናገሩ እንግሊዝ ወይም አሜሪካ የሆኑ መስሏቸው በዚያ ቋንቋ ሲንተባተቡ ይታያል።

በነገራችን ላይ እንግሊዝኛ በቃርሚያ የተገኘ ቋንቋ እንጂ የሺሕ ዓመታት ቋንቋ አይይደለም፡፡ ላስረዳ እንግሊዝኛ ለ980 ዓመታት አንግሎ ሳክሶን ይባላል፡፡ ከጀርመን፣ ከግሪክና ከላቲን በመውጣጣት በብዛትም ከጀርመን የተቃረመ ቋንቋ ነው። ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በ1720 ይህ ቅልቅል ሕዝብ በተሰባሰበ የሰው ልጆች አዕምሮ በመጠቀም፣ በኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ የመጀመርያ በመሆን የዓለም መሪ ለመሆን ችሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንግሊዝ ቀድማ በመሄድ የኢንዱስትሪን ሥልጣኔ በማምጣት ለሰው ልጆች መልካም አርዓያ ሆናለች፣ ይህንን አንክድም። በተመሳሳይ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታ የበይ ተመልካች ሆናለች። ለምን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ለደግነቷ ክፍያ ሆኖ እናገኛለን። ደግ ለዋሉት ደግን የማይመልሱ የዓረብ አገሮች ለኢትዮጵያ የመከራና የሥቃይ አቅራቢ ጎረቤት በመሆን፣ የነበራትን የሥልጣኔ ጉዞ ወደ ኋላ ለመጎተታቸው ራሳቸው የሚመሰክሩት ታሪክ ነው።

የነብዩ መሐመድ አንድ ልጅና ባለቤታቸው ከመካና መዲና የዓረብ ባለሥልጣናት ግድያና ግርፊያ እንዲድኑ፣ ወደ እንግዳ ተቀባይዋ ፍትሕ የማይዛባበት ንጉሧ ዘንድ በጥገኝነት እንዲከለሉ ከ70 የማያንሱ ተከታዮች በማድረግ ወደ ደጓ አገር ኢትዮጵያ መላካቸው የታወቀ ነው። ነብዩ መሐመድ ያ ደግ ንጉሥ መሞቱን በሰሙ ጊዜ የሞተው ንጉሥ የኢትዮያ ብቻ ሳይሆኑ የእኛም ናቸው በማለት፣ ለሰባት ቀናት ተከታዮቻቸው ጭምር ሐዘን እንዲቀመጡ ማዘዛቸው ይነገራል።

ይህንን ሁሉ ውለታ የረሱ ዓረቦች ኢትዮጵያን በማጥቃትና በየጊዜው በመተንኮስ ኢትዮጵያን ወደ ጦር ሜዳ በመሠለፍ ወሰናቸውን በመጠበቅና በማስጠበቅ፣ የቀደምቱ የሥልጣኔ ጉዞ ወደ ኋላ ተጎትቶ ሁሌ ወደ ጦር ሜዳ መዝመት ሆነ፡፡ የአክሱም ሥልጣኔ ወደ ኋላ ለመጎተት በቅቶ ሌሎች እየተራመዱ፣ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ መቅረትና ነፃነቷን ማስጠበቅ ቅድሚያ ተግባሯ ሆነ፡፡ እነሆ አሁን ላለችበት ኋላ ቀርነት ተገደደች። ከምንም በላይ ነፃነት ይበልጣልና በነፃነቷ ኮርታ አንገቷን ቀና አድርጋ ለዛሬው ትውልድ አስረክባለች፡፡

የራሷ የሆነ ፊደል ያላት፣ የራሷ የሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች ያሏት ኩሩዋ ኢትዮጵያ፣ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ የምትተርፍ የነፃነት ታጋይ ስለሆነች አፍሪካዊያን የኢትዮጵያን ፊደል የአፍሪካ እናድርግ ያሉበትም ጊዜ ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም የመጀመርያው ጥያቄ የኢትዮጵያን ፊደል በኅብረት ለመላው አፍሪካ እንጠቀም ሲባል፣ እነዚያው ተንኮለኞች አድበስብሰው እንዲያልፉ አድርገውት ተዳፍኖ ቀረ።

ታላቁ ኢትዮጵያ ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ ለግርማዊ ጃንሆይ አንድ ሐሳብ እንዳቀረቡም፣ አብሯቸው ከነበሩት ታላላቅ ሰዎች የሰማሁትን ላካፍል ወደድኩኝ። አቶ ይልማ ለጃንሆይ ያቀረቡት ሐሳብ እንደሚከተለው ነበር። አማርኛ ቋንቋ መባሉ ቀርቶ ኢትዮጵኛ ቢባል ሁሉንም ስለሚያጠቃልል ይህ ቢሆንስ ብለው ሐሳብ አቅርበው፣ ንጉሠ ነገሥቱም በሐሳቡ ተስማምተው ኮሚቴ እንዲመረጥና በጉዳዩ እንዲወያዩበትና ወደ ፍፃሜ እንዲደርስ ተደርጎ የሚከትሉት ሰዎች በጉዳዩ እንዲመከሩበት ተደርጎ ነበር፡፡

አቶ ይልማ ደሬሳ፣ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ አቶ አዲስ ዓለማየሁ፣ ቢትወደድ ሐረጎት ዓባይ፣ አቶ ምናሴ ለማና ደጃዝማች አስፍሐ ተመርጠው ጥናታቸውን ጨርሰው አማርኛ ከመባል ይልቅ ኢትዮጵኛ እንዲባል ወስነው፣ ይህ ወደ ፓርላማ ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት በንጉሡና በክቡራን ከላይ በተጠቀሱት ሰዎች ተገምግሞ አልቆ ወደዚያ በሚመራበት ጊዜ፣ ሥር ነቀል የተባለው የኮሙዩኒስት ለውጥ መጥቶ ሁሉንም ነቅሎ እነሆ ዛሬ  ወደ ደረስንበት ችግር ውስጥ ጥሎን አልፏል።

ይህ ለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ ራሷን በመከላከል የኖረች አገራችን እንደ ሌሎቹ በልማት ወደፊት ባለመጓዟና በመከራ የታጠረች በመሆኗ፣ ከክብሯ ይልቅ ወደ ኋላ ቀርነቷ ብቻ ስለሚታይ የመለያየትና የግልን ብቻ ማስቀደም እንደ ምርጫ በመቆጠሩ ነው።                                                                          

ዛሬ ቋንቋችንን በየፊናችን እናድርግ ብንል ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም፡፡ ለምሳሌ አዳማ ፍርድ ቤት የተፈረደን ፍርድ ወደ አዲስ አበባ ለአቤቱታ ለማቅረብ ቢያስፈልግ፣ ከኦሮሚኛ ወደ አማርኛ ለማስተርጎም ለጠበቃ ከሚከፈለው በላይ ለትርጉም ሊከፈል ነው፡፡ መክፈል ያልቻለ አልቅሶ መተው እንጂ ሌላ መንገድ የለውም። ከሃያ ዓመታት በፊት ሁሉ ተግባብቶ ይኖር ነበር፡፡ አሁን ግን ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ተገንዝባችኋል? ያውም በጠላትነት ወደ ኋላ ልንቀር ምክንያት በሆኑ አገሮች ፊደል የራስን ትተን ወደዚያ ስንሸጋገር የሚገርም ነው።                                         

ፊደሉ እንኳ የተለመደው ኢትዮጵኛ ሆኖ ቋንቋ እንኳ ቢለውጥ ባማረበትና በተሻለ ነበር። በፈረንጆቹ ፊደል መጻፉ ይቀላል የሚሉ አሉ፡፡ ግን እስኪ አንድ ቃል በሁለትም ጽፈን እንይ፡፡ አሉባልታ = Aalubaalta የት ላይ ነው የተሻለው? በአምስት ፊደል ከመጨረስ አሥር መሆኑ ነው የተሻለው? ፍረዱ። ዓለም በጥላቻ አይመራም። ከጠላንም ሊያጠፉን ወይም ባሪያ ሊያደርጉን ይፈልጉ የነበሩትን እንጂ እንዴት ራሳችንን እንጠላለን? ሰከን ብለን አመዛዝነን እንመልከት። ቸር ይግጠመን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻ [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡