Skip to main content
x
‹‹ግብርናውን ለማበልፀግ ቴክኖሎጂዎችን ከነምክረ ሐሳባቸው አሟልቶ መተግበር ያስፈልጋል››

‹‹ግብርናውን ለማበልፀግ ቴክኖሎጂዎችን ከነምክረ ሐሳባቸው አሟልቶ መተግበር ያስፈልጋል››

አቶ ፍሥሐ ዘገየ፣ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ

በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ምርምሮች አዎንታዊ ሚና አላቸው፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም የግብርናውን ዘርፍ ለማበልፀግ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በየጊዜው ያወጣል፡፡ አቶ ፍሥሐ ዘገየ፣ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ ናቸው፡፡ በሰብል ምርምሮችና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር:- በዋና ዋናዎቹ የግብርና ዘርፎች ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ቢያብራሩልን?

አቶ ፍሥሐ፡- ሰብል፣ እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ልማቱ ዋና ዋናዎቹ የግብርና ዘርፎች ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂ ስናወጣም በተለይ በእነዚህ ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ግብዓት የሚሆኑትን ቴክኖሎጂዎችን ነው፡፡ የቴክኖሎጂዎቹ ዋና ዓላማ ችግር መፍታት ነው፡፡ የአርሶ አደሩ፣ የአርብቶ አደሩና በዘርፉ የተሠማሩ አካላት ፍላጎት ምንድን ነው? ምን ችግር አለባቸው? ብለን እናያለን፡፡ አንዱ ችግር ከምርታማነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው ከተባይና ከበሽታ ጋር ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ከአፈር ለምነትና ከሚመረተው ምርት ጋር ያሉ የጥራት ችግሮችም ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ከጥራት ጋር በተያያዘ ዳቦ ከአሠራሩ በተጨማሪ እናቶች እንደሚፈልጉት መልካም እንዲሆን የስንዴው ባህሪ ወሳኝ ነው፡፡ እኛ ከሰጠናቸው የስንዴ ዝርያ ቁብሳ የሚባል አለ፡፡ አርሶ አደሮች የዚህን ስንዴ ዳቦ ጥሩ ነው ይላሉ፡፡ ጥራቱን በዚህ መልኩም እናያለን፡፡ ለምሳሌ ከጥራጥሬ ብንወስድ ወደ ውጭ የሚላኩ አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ካላሟላን ዋጋ ይጥላል፣ ተፈላጊነቱ ይቀንሳል፡፡ ጥራት ስንል ተፈላጊ ባህሪያት ማለትም በጣዕም፣ በቀለምና በተለያዩ መለኪያዎች የሚገለጽ ነው፡፡ ይህ ለእንስሳቱም ሆነ ለተፈጥሮ ሀብቱ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡-  በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብቱ ዙሪያ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ፍሥሐ፡- በእንስሳት ዘርፍ የተሻሉ ዝርያዎች፣ በወተትና በሥጋ ከብቶች፣ በፍየል በበግና በዶሮ ዝርያዎች ላይ እንሠራለን፡፡ ከሥነ ምግብና ከጤና ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የእንስሳትን ምርታማነት የሚያሳድጉ ምርምሮችን እንሠራለን፡፡ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን እናወጣለን፡፡  የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችንም እንሰጣለን፡፡ አንድ አርሶ አደር የተሻሻሉ ዝርያዎችን ካገኘ በኋላ እንዴት ይይዛቸዋል? የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ምርታማነት ዝርያው ብቻ አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ላይ የአፈር ለምነት፣ የመስኖ አጠቃቀም አካባቢ ጥበቃ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡-  የምርምር ዘዴዎቹን ቢገል ጹልን?

አቶ ፍሥሐ፡- ሁለት ዓይነት የምርምር ዘዴ እንከተላለን፡፡ አንደኛው ተለምዷዊ ሲሆን ሁለተኛው የባዮቴክኖሎጂ ነው፡፡ ምርምሩ የአገሪቱን የግብርና ልማት እንዲመራ መረጃዎችና ምክረ ሐሳቦች እናወጣለን፡፡

ሪፖርተር፡-  የምርምር ዘዴዎቹን ተከትላችሁ በሠራችሁት ሥራ ምን ውጤት ተገኘ?

አቶ ፍሥሐ፡- ተቋሙ ከተመሠረተ 50 ዓመት ሆኖታል፡፡ ከአጋር አካላቱ ጋር በመቀናጀት ከ1280 በላይ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ወጥተዋል፡፡ የእንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ሲጨመር ከ3ሺሕ በላይ ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎች ቀርበዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚረዱ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪው ግብዓትና ለውጭ ንግድ የሚሆኑ፣ ለተፈጥሮ ሀብት የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎችንና መረጃዎችን ያጠቃልላል፡፡

ሪፖርተር፡-  ከሰብል ጋር በተያያዘ የምርምር ዘርፎቹ ምን ይመስላሉ?

አቶ ፍሥሐ፡-  በሰብል የምርምር ሥራዎች የሚሠሩባቸው ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ እንደ ገብስ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ማሽላ ጤፍ የመሳሰሉት የብዕርና አገዳ ሰብሎች ላይ ምርምሮች በየጊዜው ይወጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ የሰብል ብዙኃነት ካላቸው ቀዳሚ 10 አገሮች አንዷ ናት፡፡ ሥነምህዳሩ ሰፊ ስለሆነ ብዙ የሰብል ዓይነት እናበቅላለን፡፡ ይህን ለእኛ የተሰጠ የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቡና ሻይ፣ ቅመማ ቅመም የመሳሰሉ አነቃቂ የሰብል ዓይነቶች፤ በጭነት ሰብሎች ጥጥና ባዮፊውል እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ላይ ጥናቶች ይሠራሉ፡፡ ዓላማው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በሽታን መከላከል፣ የተለያዩ ችግሮችን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ማውጣትና ምክረ ሐሳብና ቴክኖሎጂን ማቅረብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰብል ብቻ ብናይ ተቋሙ 1280 በላይ አጥንቶ ከነምክረሐሳቡ ለሚመለከተው አካል ያቀረባቸው ናቸው?

አቶ ፍሥሐ፡- አዎ፡፡ አንድ ዝርያ ከመውጣቱ በፊት ጽንሰ ሐሳቡ ላይ ባለሙያዎች ገምግመው ያፀድቁታል፡፡ ምርምሩ በተለያዩ ደረጃዎች ተሞክሮም ውጤታማ መሆኑ ሲረጋገጥ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ዝርያው ትክክል ነው ብሎ ያፀድቀዋል፡፡ የሚፀድቀው የዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ገምግሞ በሚያቀርበው መሠረት ነው፡፡ የሚወጡት የተሻሻሉ ዝርያዎችም ተቀባይነት አግኝተው የፀደቁ ናቸው፡፡ ከምርታማነት አኳያ ስንመለከት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ ሰብል ተብለው የተወሰዱት ስንዴና በቆሎ ናቸው፡፡ በቆሎ በምርምር ጣቢያ በሔክታር 130 ኩንታል መድረስ ችለናል፡፡ ከዚህ ውጪ የአገሪቱ ሥነ ምህዳርና የአፈር ሁኔታ ያለው ፀጋ ይለያያል፡፡ አንዳንድ ቦታ ምርት ሲሰጥ ሌላው የማይሰጥ አለ፡፡ ችግር ላለበትና ድርቅ የሚያጠቃውን ሥፍራ ተቋቁሞ ምርት የሚሰጥ ዝርያም አለ፡፡ አራት  ዋና ዋና የሥነ ምህዳር ዓይነቶች አሉ፡፡ እኛም የምናቀርበው ለእነዚህ ተስማሚ የሆነ ዝርያ ነው፡፡ ምንም እንኳን በምርምር ጣቢያ የበቆሎን ምርት በሔክታር 130 ኩንታል ብናደርስም፣ አገራዊ አማካይ ምርታማነት ሲታይ በሔክታር 34.3 ነው፡፡ ሞዴል አርሶ አደሮች እስከ 120 ኩንታል ያደርሳሉ፡፡ ይህ ማለት ቴክኖሎጂውን አሟጠው የተጠቀሙ ናቸው፡፡ ብዙ ግን አይደሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ልዩነቱ እንዴት ሊመጣ ቻለ?

አቶ ፍሥሐ፡- ቴክኖሎጂውን አሟጦ አለመጠቀም፣ ቴክኖሎጂውን አግኝቶ ምክረ ሐሳቡን ማለትም በሔክታር ላይ ምን ያህል ይዘራል፣ አንድ ዘር የትኛው አካባቢ ላይ በየትኛው ቀንና ወቅት ይዘራል፣ የአፈር አያያዙ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀሙ፣ አረምና ተባይ ላይ መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ሁሉ ምክረ ሐሳብ እንላቸዋለን፡፡ ቴክኖሎጂው ብቻውን ሳይሆን ከነምክረ ሐሳቡ ነው ውጤት የሚያመጣው፡፡ ስንዴ ሲታይ በምርምር ጣቢያ በሔክታር 80 ኩንታል ማድረስ ችለናል፡፡ አገራዊ ምርታማነቱ ሲታይ ግን በሔክታር 24 ኩንታል ነው፡፡ ሌሎች ሰብሎች ላይም እንዲሁ ነው፡፡ ድንች ቢታይ በሔክታር 500 ኩንታል የሚሰጡ ዝርያዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ ለምን በስፋት ተጠቅሞባቸው ለውጥ ማምጣት አልቻለም?

አቶ ፍሥሐ፡- ከምርምሩ ጀምሮ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ ብዙ የሚመለከታቸው ተዋንያን አሉ፡፡ የእነዚህ ቅንጅትና ውጤታማነት አርሶ አደሩ ጋር ደርሶ ውጤቱን ይወስነዋል፡፡ ሁለት አርሶ አደሮች እኩል መሬትና አንድ ዓይነት ዘር ኖሯቸው አንዱ በአግባቡ በመሥራቱና ሌላው ባለመሥራቱ ምክንያት ውጤቱ ላይ ልዩነት ይመጣል፡፡ ቴክኖሎጂውም በሚፈለገው መልኩ ሄዶ ውጤት እንዳያመጣ ያደረገው በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ያሉ ችግሮች፣ ክፍተቶች፣ ፈተናዎች ናቸው፡፡ መንግሥት ችግሮቹን ለይቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ምርምር ላይ ሲታይ የቅንጅት ችግር አለ ይባላል፡፡ ይህንን ለመፍታት ተቋሙ ምርምር ከሚሠሩ አካላት ጋር በጋራ ይሠራል፡፡ በክልል ካሉት ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ የአሠራሮች ክፍተት በምርታማነቱ ላይ ተፅዕኖ ቢያስከትሉም ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረው ሲነፃፀር ምርታማነቱ ከሦስት እስከ አራት ዕጥፍ ጨምሯል፡፡ ውጤት እያመጣ ነው፡፡ በምንፈልገው መልኩ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝቡ ቁጥርም የዛኑ ያህል ጨምሯል?

አቶ ፍሥሐ፡- ጨምሯል፡፡ ግን ለዛ የሚሆነውን የምግብ አቅርቦት እያመጣን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምግብ አቅርቦቱን እያመጣን ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ፍሥሐ፡- ተሟልቷል እያልን አይደለም፡፡ የዓለም የምግብ ድርጅት ያረጋገጠልን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የምርት መጠን በቂ ነው፡፡ ወደ ግለሰብ ደረጃ ሲመጣ የምግብ ዋስትና በሁሉም ግለሰብ ሕይወት ውስጥ አልተረጋገጠም፡፡ የምግብ ዋስትና ያረጋገጡ አርሶ አደሮች አሉ፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ እንዲሁም በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ ራሱን መቻሉ ብቻ ሳይሆን አገርን በመመገብ ራስን መቻል የሚለውስ?

አቶ ፍሥሐ፡- ምርታማነቱ ቢያድግም በቃ ብለን ወደምንፈልገው ደረጃ ደርሰናል የምንልበት ዓይደለም፡፡ ምንም እንኳን ዕድገቱ ቢኖርም ችግሮች ስላሉ እነሱን አርመን እየሠራን ለውጥ እናመጣለን፡፡ በበቆሎ ደረጃ ራሳችንን ችለናል፡፡ ስንዴ ላይ ግን ከውጭ እናስገባን፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቷ ለስንዴ ምርት ተስማሚ ናት ይባላል፡፡ ችግሩ ምንድነው?

አቶ ፍሥሐ፡- ስንዴ በሆቴል በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በቤትና በሌሎችም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከዚህ በአኳያ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ለማሟላት ለቆላማ አካባቢ የሚሆኑ ዝርያዎችን ጭምር በማውጣት እንደ ስኳር ኮርፖሬሽን ካሉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ ዝርያዎቹን ወደ ምርት እያስገባን እንገኛለን፡፡ ወደ ሥራው ከገባን ሦስት ዓመት ሆኖናል፡፡ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ ሠርተን ውጤታማ ሆነናል፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽኖቹ መሳሪያዎችም አቅምም አላቸው፡፡ ሰፋፊ እርሻ ሲታሰብ ሜካናይዜሽኑ ከባድ ነው፡፡ አርሶ አደሩ በተበጣጠሰ ሁኔታ ነው የሚሠራው፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች ላይ መሥራቱን ከገፋንበት የስንዴ ፍጆታችንን ማሟላት እንችላለን፡፡ በሌላውም ሰብል ላይ እንደዚሁ ምርምሩ የሚጠበቅበትን እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ በመሥራት ያልተፈቱ ችግሮችን እየተፈታን እንሄዳለን፡፡ 2009 ዓ.ም. ብቻ 48 የሰብል ዝርያ ቴክኖሎጂዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የቴምርና የፓልም ዝርዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የለቀቅናቸው ናቸው፡፡ በ2010 ዓ.ም. ላይም አማራጭ ዝርያዎችን አስመዝግበናል፡፡ ይህ አርሶ አደሩንም፣ ኢንቨስተሩንም ይጠቅማል፡፡ ለምግብ ዋስትናውም ያግዛል፡፡ በየዓመቱ አንድ ዝርያ ሲወጣም ከአሥር እስከ 20 በመቶ በተፈላጊ የባህሪያት ዝርዝር ብልጫ ያለው ነው፡፡ በዚህ መልኩ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ ዝርያዎች ተሻሽለዋል፡፡ እነዚህ ወደ ተግባር ተለውጠው ቢሆን፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈም ወደ ውጭ በብዛት መላክ በተቻለ ነበር፡፡ በተቋሙ በኩል ቴክኖሎጂው ከነምክረሐሳቡ ተሠርቷል፡፡ ሳይተገበር ሲቀር በናንተ በኩል ያለው ተፅዕኖ ምንድነው? ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ጋር ትመክራላችሁ ወይ?

አቶ ፍሥሐ፡- ዝርያዎቹ እንዲሄዱ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ በእርሶ አደር ማሳ ላይ ሠርቶ ማሳያ ይሠራል፡፡ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ አብረን ዓይተን ቴክኖሎጂው እንዲስፋፋ እንሠራለን፡፡ ቴክኖሎጂው በተዋረድ እታች እስካሉ አካላት ይደርሳል፡፡ ሆኖም አንድ ቴክኖሎጂ ከተቋሙ ተነስቶ ታች እስኪደርስ የሚሄድበት መንገድ አለ፡፡ በአንድ ጊዜ አገር አይሞላም፡፡ አርሶ አደሩ ጥቅሙን ማየት አለበት፡፡ አማራጭ እየሰፋ ሲመጣ ቴክኖሎጂዎችን የመቀበል ሁኔታ አለ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ መሟላት ያለባቸው መሠረተ ልማቶች አሉ፡፡ ብዙ አምርተው የገበያ ችግር የሚያጋጥማቸው አሉ፡፡ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበትን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አምርተው ዱቄት መሸጥ የሚፈልጉ አርሶ አደሮች ቢኖሩም መብራት የሚያጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ምርትና ምርታማነቱ አድጎ ሌሎች የሚጎትቱ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህ በአርሶ አደሩም ለተመራማሪውም ተፅዕኖ አለው፡፡ ሆኖም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በምግብ ዋስትናና ድህነት ቅነሳ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ልማትና በወጪ ንግድ፣ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት በሚየስችል መልኩ በተለይም በስትራቴጂያዊ የግብርና ምርቶች የምግብ ዋሰትናን ለማረጋገጥ ተቋሙ በቀጣይም ይሠራል፡፡