Skip to main content
x
የፖለቲካ ፓርቲዎች የስምና የመለያ ለውጦች ፋይዳና አንድምታ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የስምና የመለያ ለውጦች ፋይዳና አንድምታ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት፣ በግንባሩ አባል ድርጅቶች የተደረጉ ጉባዔዎች አዳዲስ ክስተቶች የታዩባቸውና ባልተለመደ ሁኔታ አባል ድርጅቶች አዲስ ዓርማና መጠሪያዎችን ያስተዋወቁባቸው ናቸው፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ብሎ ስሙን የቀየረው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አስቀድሞ ስያሜውንና ዓርማውን እንደሚቀይር የታወቀ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ቀድሞ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በመባል ይታወቅ የነበረው የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ ስያሜውን ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) መቀየሩን ይፋ አድርጓል፡፡

ምንም እንኳን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሐዋሳ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ አንዱ አጀንዳ የነበረው የፓርቲውን ስያሜ መቀየር ቢሆንም፣ ይህ የፓርቲውን ስያሜና ዓርማ የመቀየር አጀንዳ ውሳኔ ሳይሰጥበት ቀርቷል፡፡

ዓርማቸውንና ስያሜያቸውን የቀየሩት ኦዴፓና አዴፓ መሆናቸው በኢሕአዴግ ውስጥ የሚኖርን የኃይል አሠላለፍ የሚያሳይ እንደሆነ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡

ፓርቲዎች መጠሪያና መለያ ዓርማ (ብራንድ) ለምን ይቀይራሉ?

መለያ ወይም ብራንድ በንግዱ ዓለም በስፋት የሚታወቅ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ ተቋማት ራሳቸውን ቀላልና ለመያዝ በማያስቸግር መንገድ እንዲታወቁ የሚረዳቸውን ምልክት በመጠቀም፣ በተጠቃሚዎቻቸው ዘንድ ለመታወቅ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ለተጠቃሚዎች የእነዚህን ድርጅቶች ምርቶችና አገልግሎቶችን በዓርማቸው የመለየትና የመምረጥ ዕድል የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆይና በሰፊው ሲታወቅ ተዓማኒነትንም ይዞ ይመጣል፡፡ እነዚህ መለያዎች የድርጅቱ መጠሪያና መለያ ምልክትን የሚያካትቱ ሆነውም ይስተዋላሉ፡፡

ልክ እንደ ንግድ ድርጅቶች ፓርቲዎችም መለያዎችን (ብራንድ) በመያዝ የሚታወቁ ሲሆን፣ ፓርቲዎች ምልክቶቻቸውን፣ የያዙትን ዓላማ፣ የሚከተሉትን ርዕዮተ ዓለምና የወፊት ራዕያቸውን በሚያመላክት መንገድ ይቀርፃሉ፡፡ በእነዚህ መለያዎቻቸው ለመራጮቻቸው የፓርቲያቸውን ዕጩዎች የሚያስተዋውቁ ሲሆን፣ የርዕዮተ ዓለም ምልከታዎቻቸውንም ለመራጮቻቸው ያስተላልፉባቸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠቀሙባቸውን ምልክቶች መቀየራቸውም በዓለም የተለመደ ክስተት ሲሆን፣ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን የፓርቲዎች ዓርማ መቀየር የተለያዩ ተፅዕኖዎች ይኖሯቸዋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ሚ ሶን ኪምና ፍሬዴሪክ ሶልት የተባሉ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ፓርቲዎች ለምን ስምና ምልክታቸውን እንደሚቀይሩ፣ ከሚሸከሟቸው የመረጃ እሴቶች አኳያ ለረዥም ጊዜ የቆየ መለያ የተሻለ ያገለግላል በሚለው እሳቤ መሠረት የፓርቲዎች መለያዎች የመቀየር ዕድላቸው አናሳ እንደሆነ ቢጠቅሱም፣ ይህ ሲሆን ደግሞ በፓርቲ ውስጥ በሚፈጠር ፈተና በጊዜው ያለውን ሁኔታ ለማስቀጠል የማይቻልበት ችግር ሲገጥም የሚደረግ እንደሆነ የሚታሰብ ነው ይላሉ፡፡ ይህም ያልተረጋጋና ደካማ የፓርቲ ተቋማዊ ሥርዓት አለመኖሩን ያመለክታል ይላሉ፡፡

ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው የሚቆሙት የቢዝነስና የፐብሊክ ፖሊሲ እንዲሁም የብራንዲንግ ባለሙያው አቶ እሸቱ ዱብ፣ የቢዝነስና የፖለቲካ ማርኬቲንግ የሚዋዋሱት ጉዳይ እንዳለ ጠቅሰው ፖለቲካ ውስጥ ገበያ እንዳለ ያሰምራሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በገበያው ውስጥ የማሸነፍ ዕድላቸው ከብራንድ ጋር ተያያዥ ስለሆነ ትልቅ ዋጋ ያለው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ብራንዲንግ ልብና አዕምሮን የማሸነፍ ጉዳይ ነው፣ ራስንም ለአጠቃላይ ወቅቱ በሚጠይቀው ቦታ ላይ ማስቀመጥ ነው፤›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡

ስለዚህ በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ለ27 ዓመታት ይቅርና ለአምስት ዓመት የሚሠራም ስትራቴጂ ረዥም የሚባል ስለሆነ፣ ከጊዜው እኩል ለመራመድ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ፡፡ ይህም ከሚሠራባቸው አንደኛው ጉዳይ የመለያ ምልክት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ይኼንን ሲያብራሩም፣ በዴሞክራሲ ፓርቲዎች ሰዎችን ያስቀድማሉ፡፡ ስለዚህም ካለው የሕዝብ ፍላጎት ጋር ራስን አጣጥሞ መሄድ ስለሚያስፈልግ፣ እንዲህ ዓይነት የመለያ ለውጦችን ማድረግ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

ይሁንና ሚ ሶን ኪምና ፍሬዴሪክ ሶልት የፓርቲዎች የምርጫ ውድቀት ከመለያ ለውጦች ጋርም ግንኙነት እንዳለው ያሳያሉ፡፡ ፓርቲዎች ልክ የንግድ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸው እንዲሸጥ እንደሚፎካከሩ ሁሉ፣ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ፉክክር ውስጥ ስለሚኖሩ የፓርቲ መለያዎች፣ የፖለቲካ መለያዎች፣ የርዕዮተ ዓለም መለያዎችና የመለያ መሪዎች ወይንም ‹ብራንድ ሊደርስ› የሚባሉት ቃላት በፓርቲ ጥናቶች ውስጥ በስፋት እየተስተዋሉ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የስምና የመለያ ለውጦች ፋይዳና አንድምታ

የኦዴፓና የአዴፓ የስምና የመለያ ለውጦች ምን ያመላክታሉ?

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ስያሜውን ለመቀየር ያነሳሳው ምክንያት፣ የፖለቲካ መሠረቱ የሆኑት የኦሮሚያ አርሶ አደሮችንና የከተማ ነዋሪዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማሳተፍና ለማገልገል እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ቀድሞ ሲገለገልበት የነበረው ዓርማና መጠሪያ የፖለቲካ ተልዕኮን የማያመለክት፣ በግለሰብ ደረጃም ለተለያዩ የንግድ ተግባራት ለሚቋቋሙ መገልገያ በመሆኑ ለመቀየር ማስፈለጉን አክሎ፣ ድርጅት የሚለውን ስያሜ ለመተካት የተለመዱት አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜዎች ማለትም ንቅናቄ፣ ትግልና ግንባር የሚሉት መጠሪያዎች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተግባራትን ከመግለጽ ይልቅ፣ ውስን የሆነ የፖለቲካ ተግባርንና የትጥቅ ትግልን የሚያመላክቱ በመሆናቸው ፓርቲ የሚለውን ስም መምረጡን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የድርጅቱን መዝሙርም በመቀየር፣ አሁን ፓርቲው የቆመለትን ዓላማ ማንፀባረቅ በሚችል አዲስ መዝሙር ተክቶታል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በተመሳሳይ በመለያው ላይ ለውጥ በማድረግ፣ በድርጅቱ ልሳናትና በዓርማው ላይም ለውጥ አድርጓል፡፡

እንዲህ ዓይነት ለውጦች በፖለቲካው የተለመዱ እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ እሸቱ፣ በዋናነት አዲስ ጉልበትን ለድርጅቱ በመስጠት ለማጠንከር ሲባል የሚደረግ ነው ሲሉም የመለያ ለውጥ የማድረግን ፋይዳ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የስትራቴጂ አቅጣጫ ለውጥ ሲሆን ያንን ፍላጎት ለማሳየት የሚያገለግል ነው፡፡ ይህም ከዕይታዊ ይዘቶቹ በዘለለ በመሪዎች ለውጥም እየታየ ነው፡፡ ሁሉም ከ70 በመቶ በላይ አመራሮችን ቀይረዋል፡፡ በፊት ለውጥና በሰዎቹ ዕድሜ ብቻ ግን የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡ በዚህ ውስጥ ግን በአዳዲስና በሚታደሱ ሐሳቦች መካከል የሕዝቡን ፍላጎት የሚያስጠብቁ አቋሞችን መያዝ አለባቸው፤›› ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ስለዚህም እነዚህ ለውጦች የአሁኑንና የወደፊቱን በማመላከት መቃኘት አለበት ይላሉ፡፡

ኦዴፓ ቀድሞ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሲያገለግሉ ከቆዩት 81 አባላት መካከል 16ቱን ብቻ በአዲሱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሆነው እንዲቀጥሉ በመወሰን  ሕወሓትም ደግሞ ከ55 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ በአዳዲስ አባላት የቀየረ ሲሆን፣ አዴፓም መጠነ ሰፊ ለውጥ በማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴውን መሥርቷል፡፡

በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዘጠነኛ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ንግግር ያሰሙት ሊቀመንበሩ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተማሩ፣ ድርጅቱ ለመምራት የተዘጋጁና ብቃት ያላቸውን ወጣት አመራሮችን ማምጣቱንና ኢትዮጵያን ወደ ፊት ማራማድ የሚያስችለውን ቁመና ተላብሷል ብለዋል፡፡

የተደረገው የአመራር ለውጥም የድርጅቱ ስያሜና መለያ ለውጥ (ሪብራንዲንግ) መሆኑንና ይህም በአቅጣጫም ጭምር ሊታይ እንደሚችል አቶ እሸቱ ያመለክታሉ፡፡ ከሕወሓት ውጪ ያሉት ሦስቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ለጉባዔዎቻቸው የያዟቸው መፈክሮች ድርጅቶቹ ለውጥን ለመቀበል ያላቸውን ፍላጎትና ዝግጁነት የሚያመላክት ሲሆን፣ ሓርነት (ነፃነት) የሚለውን የድርጅት ስም ይዘው ለመቀጠል የወሰኑት ሕወሓቶች አሁንም ያስፈልጋል ብለው በማመን ነው? ወይስ በሌላው እየታየ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴ አንፃር ለመቆም ሲባል ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የስምና የመለያ ለውጦች ፋይዳና አንድምታ

ለኢሕአዴግ ይህ ለውጥ ምን ማለት ነው?

ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ የሚካሄደውን የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ ግንባሩ ዓርማውንም ሆነ መጠሪያውን የመቀየር ዕቅድ እንደሌለውና የድርጅቱ ጉባዔም አጀንዳ እንዳልሆን ቢናገሩም፣ የሁለቱ ድርጅቶች የመለያ ቅያሪ ብሎም በደኢሕዴን በአጀንዳነት የተያዘ መሆኑ በኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ ሊነሳ የሚችለው አንዱ ጉዳይ የድርጅቱን ስምና ዓርማ መቀየር፣ የድርጅቱን ፕሮግራምም መለወጥ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ወ/ሮ ፈትለ ወርቅም በመግለጫቸው ጉባዔው የፈለገውን አጀንዳ ማስያዝ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ይህ ግን የ11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ሲያጠናቅቅ ጉባዔተኞቹ እጅ ለእጅ ተያይዘው የ‹ማንወጣው ተራራ የለም፣ የማንሻገረው ወንዝም እንዲሁ፣ ብርድ ቁር ቢሆን፣ ሐሩር ፀሐይ ቢወርድ መስመር ነው ኃይላችን› እያሉ ሲዘምሩ ለተስተዋሉት የሕወሓት ሰዎች ግን ይህ የሚዋጥላቸው እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡

በእሑድ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት የሕግ ባለሙያው አቶ መርሐ ጽድቅ መኰንን ዓባይነህ፣ ‹‹ለመሆኑ በኢሕአዴግ ተጠባብያን እሳቤ ወገንተኝነቱ ለጭቁን ሕዝቦች ነው የሚባልለት አብዮታዊ ዴሞክራሲ በቁሙ ሲወሰድ ምን ማለት ይሆን? በግዕዝ ልሳን አበየ ለሚለው ቃል የአማርኛ ቋንቋ ምትኩ እምቢ አለ፣ አወከ፣ አመፀ…ነው፡፡ ከዚህ ሥርወ ቃል ስንነሳ አብዮታዊ የተሰኘው ቅጽል እምቢተኛን፣ ሁከት ፈጣሪን ወይም አመፅ ያረገዘን አሉታዊ ሁኔታ ከወዲሁ ያጠይቃል፡፡ ሆኖም ዴሞክራሲ በባህሪው ፈቃጅ እንጂ አስገዳጅ፣ እንቢተኛና ሁከት አነሳሽ ወይም አመፀኛ ሊሆን አይችልምና ሳንፈልገው ተጭኖብን ከመቆየቱ የተነሳ፣ ርዕዮቱን ያላንዳች ጥያቄ ተቀብለነውና ተለማምደነው ካልሆነ በስተቀር የዴሞክራሲ አብዮተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚቀነቀንለት ብቻ ሳይሆን እምብዛም የሚታወቅ ነገር አይደለም፤›› ሲሉ የሕወሓትን ፕሮግራም ይተቻሉ፡፡

ስለዚህም ጥብቅ ብሎ ከመያዝ ይልቅ ለውጥን ለመቀበል መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ያትታሉ፡፡

በተመሳሳይ የመለያ ለውጥ ማድረግ ከስትራቴጂና ከፖለቲካ አቅጣጫ ተለይቶ ሊታይ አይችልም የሚሉት አቶ እሸቱ፣ የኦዴፓና የአዴፓ ጥምረት በትልቁ ግንባር ላይ እነሱ ያደረጉት ዓይነት ለውጥ እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል ይላሉ፡፡

‹‹ሁለቱ ፓርቲዎች ዘንድ ያለው ጥምረትና የድርጊት ውህደት ወደ ሌሎቹ አባል ድርጅቶች ማስተላለፍ ከተቻለ፣ ለረዥም ጊዜ የኢሕአዴግ ሐሳብ የነበረውን ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የማደግ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህም የብሔር ማንነት ላይ የተመረኮዘ ግንኙነት ሳይሆን ሙያዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ይህ የማይሆንና ሁለቱ ተነጥለው የሚጓዙ ከሆነ፣ በመጨሻረው የኢሕአዴግን መከፋፈል ሊያስከትል ይችላል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የስምና የመለያ ለውጦች ፋይዳና አንድምታ

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት አዴፓ (የቀድሞው ብአዴን) አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራሙን ለመቀየር ውይይት ማድረጉን ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ፓርቲውን አንድ ላይ ከሚያስሩት ገመዶች አንዱን መበጠስ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ተመሳሳይ መስመር የሚከተሉ ከሆነ ጥንካሬን ያመጣል ይላሉ፡፡ ‹‹ይሁንና አሁን ይህ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በብሔር ማንነትና በብሔራዊ (ኢትዮጵያዊ) ማንነት መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ ማስኬድ ከባድ ስለሚሆን፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የብሔራዊና የብሔር ማንነትን በተመለከተ ኢሕአዴግም በእኩል አልሠራሁበትም ብሎ ያመነው ተግባር ቢሆንም፣ ጉዳዩ ግን ከዚህም የላቀና በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ባሉ ድንጋጌዎች የተተከለ ችግር ስላለው፣ እንዲህ ዓይነት ምልከታዎች ወደ ዋናው ምንጭ እንዳይኬድ ሊያግዱ ይችላሉ የሚሉም አሉ፡፡ አቶ መርሐ ጽድቅም አንዱ ናቸው፡፡

‹‹ይበልጥ የሚያስገርመው በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ብሔራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጣጣምና ሚዛናቸውን በመጠበቅ ደንግጎልን እያለ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ባለ ዋጋነት ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ሳንሠራ ቆይተናል (ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ) ሲሉ የተናዘዙበት የመግለጫው ክፍል ነው፡፡ ከማስተዛዘኛነት የማያልፈው ይህ ዓይነቱ አስተያየት በሕገ መንግሥቱ ይዘት ላይ እንዳናተኩርና ጥልቀት ያለው ፍተሻ እንዳናደርግ የማዘናጋት አደጋ ይኖረዋል፡፡

‹‹ሕገ መንግሥታችን በመግቢያው ላይ ቀና ቀናውን ሐረግ ጽፎ ቢያስነብበንም ቅሉ፣ በተለይ በራሱ ቋንቋ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እያለ ለሚጠራቸውና አንደኛውን ከሌላው በውል ለይቶ እንኳ ግልጽ ትርጓሜ ላልሰጣቸው ቡድኖች በአፍ መፍቻ ልሳን የመናገርና የመጻፍ፣ ባህልና ታሪክን የማበልፀግና በራስ ገዝ ተቋማት የመተዳደር መብቶችና ነፃነቶችን በመዘርዘር ብቻ አያቆምም፡፡ ከዚህ በብዙ አልፎ ፌዴሬሽኑን የመሠረቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች ያለ ገደብ የተረጋገጠላቸውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተጠቅመው በፈለጉ ጊዜ እስከ መገንጠልና የየራሳቸውን ትንንሽ መንግሥታት እስከ መመሥረት የሚዘልቅ ነፃነት እንዳላቸው በማያሻማ ሁኔታ ያውጅላቸዋል፡፡ ስለሆነም የአገራዊ አንድነታችን መሸርሸር ምክንያቱ ወ/ሮ ፈትለወርቅ እንደሚሉት ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ አንድነት ከብሔራዊ ማንነት ያነሰ ትኩረት ሰጥቶ መቆየቱ ሳይሆን፣ ቀድሞ ነገር ሕገ መንግሥቱ ራሱ ከኢትዮጵያዊ አንድነት ይልቅ፣ ለብሔራዊ ማንነት ክፉኛ አዳልቶ መደንገጉ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፤›› ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ነገር ግን እነዚህ ለውጦች ግባቸውን እንዲመቱ ጥንቃቄዎች ያስፈልጋሉ ሲሉም አቶ እሸቱ ያሳስባሉ፡፡ ‹‹እነዚህ የመለያ ለውጦች የዕይታዊ ለውጦች ብቻ እንዳይሆኑ አዳዲስ ሐሳቦችን የሚያፈልቁ ሰዎች ያስፈልጋሉ፣ ከሰዎቹም በላይ እነዚህን ሐሳቦች የሚያስተናግድ ተቋማዊ ሥርዓት ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በጥብቅ የሚያምን ስብስብ ውስጥ ለውጡን ማስረፅ ከባድ እንደሆነ በማስረዳት፣ ዋናው የዚህ ለውጥ መለኪያው አዲስ አስተሳሰቦች መስተናገድ መቻላቸው ነው፡፡

‹‹የአገሪቱ ዕድገት በኢኮኖሚ ብቻ ሳይወሰን በዴሞክራሲና በአመራር መዳበር አለበት፤›› ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ፖሊሲያችን ጥሩ ቢሆንም አፈጻጸሙ ነው ችግር ብሎ ፖሊሲን ከአፈጻጸም ውጪ ማየት ልክ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን አቶ እሸቱ የኢሕአዴግ የ27 ዓመታት ፕሮግራም ጊዜውን ጨርሷልና መተካት አለበት ቢሉም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መለያ ለውጥ ላይ ጥናት ያከናወኑት ኪምና ሶልት ግን፣ የቆየ መለያ ከፍተኛ ታዋቂነት ስለሚኖረው የፓርቲዎችን ስም መቀየር ትልቅና ከፍተኛ አደገኛ ውሳኔ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የድርጅቶቹ ስሞች የብራንዱ ዋነኛ ምሰሶዎች ሲሆኑ፣ ይኼንን መቀየር ምሰሶውን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን ፓርቲውን ማጥፋትም ጭምር ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ በፖለቲካም ሆነ በገበያ የስምና የመለያ ለውጥ ዓመታትን የፈጀው የፓርቲው ዕውቅና ግንባታና መልካም ስም ይዞ ይጠፋል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን ዕድሜ ጠገብ መለያዎችና ዓርማዎች ከኋላቸው አዳፋ ታሪክ ካላቸው፣ የሚከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ መለወጥ አለባቸው የሚሉ አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝብን የሚስብ የፖለቲካ አጀንዳና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አመራሮችን ወደፊት ማምጣት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ለወጣቶች ትኩረት በመስጠት የፖለቲካ ፓርቲውን ለዘመኑ በሚመጥን ደረጃ ማደራጀት ዓርማና መለያን በሚገባ ለማስረፅ ይረዳል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ከፓርቲዎቹ የስምና የዓርማ ለውጥ ጋር አብረው በተለወጡት በርካታ ነባር አመራሮች ምትክ ወደፊት የመጡት ወጣት አመራሮች፣ ብዙም የፖለቲካ ልምድና ብስለት የላቸውም ብለው የሚተቹም አሉ፡፡ ይሁንና ወጣቶቹን ከበሳሎቹ ጋር በማቀናጀት በትክክለኛው ጎዳና ላይ መራመድ ከተቻለ፣ ከበፊቶቹ አመራሮች በተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተስፋ መሰነቅ እንደሚገባ የሚከራከሩ አሉ፡፡