Skip to main content
x

በመደናበር ወይስ በፍልስፍና እየተመራን ነው?

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ውድ አንባቢያን ለመሆኑ ከሚኒስትሮቻችን፣ ከፕሬዚዳንቶቻችን፣ ከፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት የትኛው ነው ፈላስፋ? ወይም ይኼ ነው ተብሎ በሚታወቅ ፍልስፍና የሚመራው ማነው? ለመሆኑ አንድ የፖለቲካ ሰው ወደ ሥልጣን ሲያመራ ፍልስፍና የሚባል ነገር በአዕምሮው ውስጥ አለ? አመራሮቹ በፍልስፍናስ በኩል አልፈው ያውቃሉ? አገር ለመምራት የሚረዱ የፍልስፍና መጻሕፍት ሳያቋርጡ ያነባሉ? "ደግሞ ሰው ለመግዛት ፍልስፍና አያስፈልግም!" ይላሉ? እርግጥ ነው ሁሉም ፈላስፎች፣ የፍልስፍና ተከታዮች፣ በፍልስፍና በኩል አድርገው ያለፉ ሊሆኑ ይችላሉ። አጠቃላዩን ሁኔታ ስናየው ግን አይመስልም። ስለዚህ ትልቁ ችግራችን የፍልስፍና ድህነት ሳይሆን ይቀራል? እንደተለመደው ሐሳብ ለመሰንዘር ያህል ግን ዛሬ የበለፀጉት አገሮች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሯቸው እጅግ ከተሻለ የኑሮ ደረጃ የደረሱት፣ መሪዎቻቸው ፍልስፍናን እንደ ዋነኛ መሣሪያቸው አድርገው በመነሳታቸው ሲሆን፣ የፍልስፍና ድህነት ባለባቸው አገሮች ጠበብት ‹‹መንግሥት እንደ ሳይንስ በፍልስፍና ዕጦት እየተሰቃየ ነው፤›› በማለት የሚያስጠነቅቁትም፣ የፍልስፍና ዕውቀት የሌላቸው የፖለቲካ መሪዎች ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ የራሳቸውን ዓላማ በጭፍን እንዳያራምዱ ነው፡፡ ያለ ፍልስፍና ፖለቲካው ብቻውን አፍራሽ ተፅዕኖ ያለው ባዶ ጩኸት ስለሚሆን ነው፡፡ እንደ ቶማስ ጀፈርሰን (አሜሪካ) ያሉ ታላላቅ መሪዎች ተብለው የሚነገርላቸው የፖለቲካ ሰዎች፣ አንድም ራሳቸው ፈላስፎች ያለበለዚያም ፈላስፎችን ጎናቸው ያደረጉ ወይም ሁለቱም ሁኔታዎች በማመቻቸታቸው እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡

ኧርቪን ኤድማን የተባሉ ፈላስፋ "ዘ ፊሎዞፊ ኩዌስት" በሚል ርዕስ በ1947 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ ‹‹በፍልስፍና አዕምሮን ማንቃት ከጠባብነትና በምኞት ዓለም ከመኖር ያድናል፡፡. . . (ፍልስፍና) ሰዎችን እርስ በርስ የሚግባቡ፣ አንዳቸው የሌላው አባል የአንድ ዓለም ዜጎችና ወንድማማቾች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤›› ሲሉን፣ ቪክቶር ሁጎም ‹‹ፍልስፍና የሐሳብ አጉሊ መነጽር ነው፤›› በማለት አስፈላጊነቱን ያጎላዋል፡፡ ከእነዚህ ሊቃውንት በግልጽ እንደምንረዳው ፖለቲካ ያለ ፍልስፍና አፉ ሳይታሰር እንደ ተዘቀዘቀ ስልቻ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ሐሳብ እየተደረደረ በየደረሰበት ፏ ብትን የማለቱና ምኞት ሆኖ የመቅረቱ ጉዳይም ሚስጥር ይኼው ነው። ፍልስፍና ያላስተሳሰራቸው የፖለቲካ መሪዎች ሥልጣን ቢያስተሳስራቸው እንኳን መበታተናቸው ከቶ አይቀርም። ታላቁ ፈላስፋ ዣን ዣክ ሩሶ (1712-1778) ‹‹አንድ አናፂ አንድን ትልቅ ሕንፃ ከመገንባቱ በፊት መሬቱ የሕንፃውን ክብደት መሸከም መቻሉን አስቀድሞ ማወቅ እንዳለበት ሁሉ፣ አንድ ጥሩ ሕግ አውጪ አካል ጥሩ የሆኑ ሕጎችን ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ይደግፈው እንደሆነ መረዳት ይኖርበታል፤›› ሲል በቀላል ምሳሌ ፍልስፍናዊ አመለካከቱን ያቀርባል፡፡ ይኼው ፈላስፋ ነፃ ያልሆነ ሕዝብ እኩል ሊሆን እንደማይችልና እኩል ካልሆነ ደግሞ አመፅ ማስነሳቱን እንደማይተው “ሶሻል ኮንትራክት” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ ይተነትናል፡፡ ፕሌቶም የፖለቲካ መሪዎች (ንጉሦች) ፈላስፎች መሆን እንዳለባቸው በአራት ነጥብ የመዝጋቱን ትክክለኛነትም ብዙ ፈላስፎች ይደግፉታል፡፡ ይህ ሰው ጥሩ የጦር መሪዎች፣ ድል በድል የተጎናፀፉ ፋኖዎች፣ ወኔያም መኮንኖች፣ የፖለቲካ መሪዎች ይሆናሉ ቢል ኖሮ ተቀባይነትን ባላገኘ ነበር፡፡ ወታደራዊ መሪ ኢኮኖሚን አንኮታኩቶ ሕዝብን ለሥቃይና ለብጥብጥ እንደሚዳርግ የምናውቀው በመሆኑ፣ እዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አያስፈልግም፡፡

ይሁንና የማንም ‘ቲፎዞ’ ሳንሆን ከቀና አመለካከት ተነስተን፣ ‹‹ፍልስፍና ለምን ያስፈልገናል? ለመሆኑ ያለፍልስፍና ማደግ አይቻልም? ሕይወት ራስዋን የቻለች የፍልስፍና መስክ ሆና እያለ ለምን የግሪካውያን፣ የሮማውያን፣ የሌሎች ምዕራባውያንና ምሥራቃውያን አገሮች ፍልስፍናን በማጥናት ጊዜያችንን እናባክናለን?" የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ ወደነዚህ ጥያቄዎች በተለይም ፍልስፍና ለምን ያስፈልገናል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቅርቡ ከሆነው ድርጊት በመነሳት መመልከት እንችላለን፡፡. . . ለምሳሌ መንግሥት ሕዝብን በአንድ ምክንያት ተነስቶ ድጋፉን እንዲሰጠው ሲጠይቀው ‹‹ሆ›› ብሎ የሚወጣ ለምንድነው? ግብር እንዲቀነስለት? ከሥራ እንዳያባርረው? እንዳይቀየመው? ጥናታዊ የዘመቻ ባህል በልቦናው ውስጥ ስለተቀረፀበት? የታፈነ ስሜቱን የሚገልጽበትን ጊዜ ሲጠብቅ ስለነበረ? ከዚህ ቀደም የነበረውን መንግሥት ደግፈው የወጡት ስላናደዱት? ወይስ ምንድነው? ይህ በዝርዝር ካልታወቀ "ሕዝብ ሆ ብሎ ስለወጣልኝ ወዶኛል" ወደሚል ዝንባሌ ማምራት እጅግ በጣም አደገኛ ግምት ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የታላቋ ብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትርን አንዲት ደጋፊያቸው፣ ‹‹ይህ ሁሉ ሕዝብ ንግግርህን አፉን ከፍቶ ሲያዳምጥና ከዳር እስከ ዳር ሲያጨበጭብልህ ምን ይሰማሀል?" ስትለው “ነገ አንዳች ነገር ባጠፋ ተዘቅዝቆ ይሰቀል ሲለኝ፤›› ሲል የሰጠው በትምህርታዊነቱ ሲጠቀስ ይኖራል። እውነቱን ለመናገር እንኳን ተራ ሰው ያመኑት የቅርብ ሰው እንኳን በፍልስፍና የማይመራ ከሆነ አደገኛ ነው። 

ይህም ሁሉ ደግሞ የኢትዮጵያ ፍልስፍና በዩኒቨርሲቲ ገዳም ውስጥ ገብቶ ዓለም በቃኝ ማለቱ ነው። በእርግጥም ‹‹ከኋላ ቀርነትም እርስ በርስ ብጥብጥም ያድነናል›› ብለን የምናምንበት ዩኒቨርሲቲ አሸልቦ ካልሆነ በስተቀር መጥፎ የፖለቲካ አዝማሚያ ሲያይ፣ ‹‹ይህ አካሄድ ፈጽሞ ጥሩ አይደለም፣ ጥሩ የፖለቲካ አካሄድ ሲታይ ደግሞ ይህኼኛው መልካም ነው፤›› በማለት በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያና በማኅበራዊ ሚዲያ ጉድለቱን አንድ በአንድ እየቀነሰ ባስተማረን፣ ሃይ ባለን ነበር፡፡ ‹‹የጨነቀው እርጉዝ ያገባል›› በሚሉት ዓይነት መንገድ ሰዎች ወደ ሥልጣን ሲመጡና ትንሽ ሰላም፣ ትንሽ መረጋጋት፣ ትንሽ ዴሞክራሲ፣ ትንሽ ነፃነት ስትኖር እርሷም እልም ድርግም እንዳትል  በዝምታ ባልተመለከተ ነበር፡፡ ለነገሩ አውሮፓና አሜሪካ ከትልልቅ የዕድገት ደረጃ የደረሱት እኮ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያልተቆጠበ ጥረት በማድረጋቸው ነው። በአንፃሩም የፖለቲካ መሪዎችና ምሁራን በመገናኛ ብዙኃን ምን አሉ? ብለው ስለሚከታተሉ፣ ስለሚማሩ፣ ስህተታቸውን ስለሚያርሙ፣ አመለካከታቸውን ስለሚያዳብሩ ነው። እንደገና ልመለስባቸውና ለመሆኑ የእኛ ምሁራን፣ ላራሽፋኮ (1613-1680) ‹‹ፍልስፍና ያለፈውንና የወደፊቱን መጥፎ ነገር ታሸንፋለች፣ በአሁኑ ወቅት ግን መጥፎ ነገር ያሸንፋታል፤›› እንዳለው፣ ወቅቱ እስኪያልፍ ያለውን ሁኔታ እየከተቡልን ወይስ እንደ አገራቸው፣ እንደ ባህላቸው፣ እንደ ሠልፍና እንደ ምኑና ምናምኑ ጥሪ ካልተደረገላቸው ቀብራራ ፈላስፎቻችን ወደ አደባባይ ላይዘልቁ ነው? ወይስ መማር ሌላ በአደባባይ መናገርና ለአደባባይ መጻፍ ሌላ በመሆኑ ነው? ወይስ ኦስትሪያዊው ታላቁ የሥነ ልቦና ምሁር ሲግመን ፍሮይድ (1856-1939) ‹‹የምሁራን ድምፅ ለስላሳ ነው፣ ነገር ግን እስኪሰማ ድረስ እረፍት የለውም፡፡ አንድን ሐሳብ በግድ ለማጤን የሚደረገውን ሙከራ ያላሰነሰ ጥረት በማድረግ የተሳካ ውጤት ያስገኛል. . . ›› ያለውን አልሰሙም ይሆን?

ያም ሆነ ይህ የሚጠቅመን እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 22 ቀን 1561 ዮርክ ሻየር በሚባለው የለንደን ክፍለ ከተማ የተወለደው ዝነኛ ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከን፣ ‹‹እኔ የተወለድኩት ለሰው ልጅ መልካም አገልግሎት ለመስጠት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ሕዝብ መብት መጠበቅ ያሉ የሰው ልጅ የደስታ ምንጭ የመሳሰሉት መልካም ነገሮች ሁሉ እንክብካቤ ሊደረግባቸው፣ እንደ ውኃና አየር ሁሉም እኩል ሊጠቀምባቸው እንደሚገባም አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም ለሰው ልጅ የሚበጁ ነገሮችን ለማከናወን እንዴት ተፈጥሮዬን ማስተካከል እንዳለብኝ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በዚህም ጥያቄ ሁኔታዎችን ስንዳስስ ኪነ ጥበብን ከማሳደግና ከመፍጠር የተሻለ የሰው ልጅን ብልፅግና (ሥልጣኔ) የሚመጣ ሥራ አላገኘሁም ካለ በኋላ፣ ‹‹ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ልጅን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያወጣ ሐሳብ የሚያመነጭ እውነተኛ ሰውን የዓለማችን የበላይ የሚያደርግ፣ የነፃነት ሻምፒዮንና በአሁኑ ጊዜ ባርያ አድርጎ ከያዘው ችግር (ፍላጎት) አስወጋጅ የሚል መጠሪያ ሊሰጠው ይገባል፤›› ያለውን መሆኑን እኛ እንድናስታውሳቸው ይሆን?

እንዲያው ለነገሩ እንደ ፍራንሲስ ቤከን ሁሉ ቀደም ሲል ፕሌቶ፣ አርስቶትል፣ በኋላም ስፒኖዛ፣ ቮልቴር፣ ኢማኑኤል ካንት፣ ሄርበርት ስፔንሰርና ፍሬድሪክ ኒሼ፣ በቅርቡ ዘመናዊ የአስተሳሰብ ብርሃናቸውን ፈንጥቀውልን ካለፉት አውሮፓውያን ፈላስፎች ሄነሪ ቤርጋሰን፣ ቤንዴዩ ክረችና ከአሜሪካ ጆርጅ ሳንታያ፣ ዊልያም ጀምስና ጆን ዲዩ፣ የአገራቸውንና የዓለምን አስተሳሰብ ወደ ተሻለ አቅጣጫ መምራታቸውን ለአሁኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆናቸውን እያወቅን በጭፍን የምንመራው እስከ መቼ ነው?

ያም ሆነ ይህ ፈላስፎቻችን ሕዝብን ለማስተማር ፈለጉም አልፈለጉም፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ የሰላም ጥያቄ ሲነሳ ፍልስፍና የሌላቸው የፖለቲካ ሰዎች ‹‹በእኛ ጥረት  የሰላም አየር ከተነፈሳችሁ ሌላ ምን ትፈልጋላችሁ? ዴሞክራሲውን እንደሆን ለእኛ ተውት። ከእኛ ወዲያ ጎራሽ ማዕድ አበላሽ. . . ›› የሚለው አመለካከት ባለፉት 27 ዓመታት ምን ጠቀመን? ለመሆኑ ሰዎች መንፈሳዊ፣ ሞራላዊና ማዕምራዊ (ምሁራዊ) ሰላም አያስፈልጋቸውም? ዛሬ መንፈሳዊ አመለካከትን በተመለከተ አንዱ የሌላውን በሚያከብርበት ሳይሆን፣ ሌላው አንዱን እያንኳሰሰ የሚታበይበት እንዲሁም አንዱ በሌላው ላይ ''መጣሁብህና መጣብኝ" የሚል ስሜት ሲፎካከር አይሰማምን? ማነው ይኼንን ፉክክር በፍልስፍና ላይ በተመሠረተ አመራር አስተባብሮ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያሲዘው? እርግጥ ነው ለተወሰኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ሰላም ማለት የጦር መሣሪያ ተኩስ የሌለበት ሁኔታ መኖር ማለት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድነት ላይ በተመሠረተ ልዩነቱ፣ በብሔረሰብ ድብልቅነቱ፣ በቆየና በተወው ፖለቲካዊ አመለካከቱ ነፃ ካልሆነ፣ ለዚህ የኅብረተሰብ ክፍል የሚስማማ ሁኔታ ካልተመቻቸና በሚቀጥለው ምርጫ ማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት በነፃ ተወዳድሮ አሸናፊው ሥልጣን የሚይዝበት ሁኔታ ካልፈነጠቀ፣ ሌላው ቀርቶ ለራሱ ለኢሕአዴግ አባላት ምን ያህል አስደሳች ይሆናል? ካልሆነስ ከወዲሁ ሁኔታዎች ሊመከርባቸውና ሊዘከርባቸው አይገባምን? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሕዝብ ‹‹እኔ ነፃ ነኝ›› የሚለው በፖለቲካ ድርጅቶች ግፊት ከሆነ ለነፃነቱ ምን ያህል ነፃ ነው? መንግሥት እውነት ነፃና ትክክለኛ መንግሥት ከሆነ፣ እነዚህ አነስተኛ የሕዝብ መብቶች የመገናኛ ብዙኃኑን በቁጥጥር ሥር ባደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲረገጡ ማስከበር አልነበረበትምን? እንግዲያውማ እኛ የዛሬዎቹ ጎልማሶችና አዛውንቶች እንደምናውቀውና ከደርግ የአሥራ ሰባት ዓመታት አገዛዝ እንደተማርነው. . . ‹‹ሴቱንም፣ ወጣቱንም፣ ገበሬውንም፣ ሠራተኛውንም. . . በሰበብ አስባቡ እየሰበሰበ አንዱ በሌላው ላይ እንዳይተኛ የሚያደርግ አስተዳደር ዛሬም ምን ጊዜም አምባገነን ነው፤›› ብንል ኢሕአዴግንም ሆነ ሌላውን በመጥላታችንና በመውደዳችን ምክንያት ሳይሆን፣ በመሥጋታችንና በመፍራታችን ነው፡፡ ከመፍራትና ከመሥጋት በመነጨ ስሜት ተነስተን የምንሰጠው አስተያየት ደግሞ፣ ከምቀኝነት ወይም ከወደቀው መንግሥት ናፋቂነት ሊቆጠርብን አይገባም፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል በፊት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ "እስቲ ያለፈውን ፊልም ተመልሳችሁ እዩት" ማለታቸው እኮ እውነት ነበር፡፡ እስቲ ይህ አባባል ሐሰት ከሆነ አሁንም አሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን የፊልም ክምችት ክፍል እንመርምር፡፡ ሠልፉም ሆነ አደረጃጀቱ ከአሁኑ የሚለየው በምንድነው?

ፈላስፋውና ሳይንቲስቱ ራስል (1872-1970) አስተሳሰብን አላነበብንም እንዳይሆን እንጂ፣ ‹‹ሰላም የሠፈነ ቢመስል እንኳን የጦርነት አደጋ ባንዣበበበት አገር ምን ጊዜም የመንግሥት ቁጥጥር ኃይል ነው፤›› ሲል ያስጠነቀቀው ለዚህ አልነበረምን? ስለሕዝብ ነፃነት አጥብቀው ከተከራከሩት ዕውቅ ፈላስፎች አንዱ የሆነው ጆን ሎክ፣ ‹‹ከፍተኛ የሕዝብ ነፃነት ፍላጎትና መንግሥት ከሚሰጠው እጅግ አነስተኛ ፍላጎት ጋር መታረቅ አለበት፤›› ሲል የመከረው ነፃነትና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ሠፍኖ የተሻለ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲገኝ፣ ሕዝብ የሚፈልገውን እንዲሾምና እንዲሽር አልነበረምን? ሕዝብን እንደፈለገ የሚነዳ የፖለቲካ ፓርቲ ሲኖር ግን፣ በሌላው አገር ሁሉ አልፀደቀምና በእኛም አገር ደርሶ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ ዕውቁ ጸሐፊ ተውኔት ሼክስፒርም ‹‹ጁሊየስ ቄሳር›› በሚል ርዕስ በደረሰው ተውኔት ‹‹ሕዝቦች ሆይ ፓምፔም፣ ጁሊየስ ቄሳርም፣ ብሩተስም፣ ማርክ አንቶኒዮስም ያው አምባገነን መሪዎቻችሁ ናቸው፤›› ይለናል፡፡ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ገጽታውን እስካላሳየ ድረስ መባል ያለበትም እንደዚህ መሆን ይኖርበታል፡፡

በእርግጥም ፀረ ኢሕአዴግ ለመሆን ስለተፈለገ ሳይሆን ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ፣ እንዲለወጡ፣ በሀቅም በዚች አገር ላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲዘረጋ ካለን ምኞት ተነስተን የምንሰጠው አስተያየት ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ፣ ሕዝብ እኮ ‹‹ተሠለፍ›› ሲባል የመንግሥትን እገዛ ለመፈጸም ሲል የሚሠለፈውን ያህል፣ ‹‹ነፃ ሆነህ አስተያየትህን ስጥ›› ሲባልም የሰላ ሒሱን የሚሰነዝር መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጎጃም ውስጥ ሕዝቡን ሰብስበው ረጅም ዲስኩር ካደረጉ በኋላ ለጉብኝት ሲሄዱ አንዱን ገበሬ በድንገት ይዘውት ‹‹ታዲያስ ምን ይሰማሃል?›› ቢሉት፣ ያንን ያህል ሲናገሩ የነበሩ ሰው ከሕዝቡ ጋር ሲቀላቀሉ መለየት አልቻለምና ‹‹እንግዲህ ተናግሯል እናያለና፤›› በማለት ሐሳቡን በነፃ እንደሰጠው ሁሉ፣ ኢሕአዴግም በ1982 ወይም በ1983 ዓ.ም. ኩታ በርና አካባቢዋን በተቆጣጠረበት ጊዜ ካድሬዎቹ ሕዝቡን ይሰብስቡና ለረዥም ጊዜ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ ‹‹የደርግ ከላሾች፣ በራዥች፣ ንዑስ ከበርቴዎች፣ አቀባባይ ከበርቴዎች፣. . .  ወዘተ.›› እያሉ የእነሱ አመለካከት ግን ፍትሕን፣ ዴሞክራሲን፣ እኩልነትንና ነፃነትን እንደሚያመጣ ይሰብካሉ፡፡ በመጨረሻም ሕዝቡ ጥያቄ ወይም አስተያየት እንዳለው ይጠይቃሉ፡፡ ወዲያውም አንድ ሰው እጁን ያወጣና አስተያየት እንዳለው ሲገልጽ እንዲናገር ይፈቀድለታል፡፡ ሰውየውም፣ ‹‹መቼም የተናገራችሁትን ሁሉ ሰምተናል ጥሩ ነው፡፡ እኔ ግን ነገር ዓለሙን ሳየው በዚች አገር ላይ ሽማግሌ ጠፍቷል፤›› ካለ በኋላ ለምን ሽማግሌ እንደጠፋ ሲያብራራ፣ ‹‹አሁን ያልከንን ነገር ሁሉ የደርግ ካድሬዎችም ይነግሩን ነበር፡፡ ነገረ ሥራችሁን ሁሉ ሳየው ወንድማማቾች ትመስሉኛላችሁ፡፡ ታዲያ የምትሉን ሁሉ አንድ ከሆነ ምን አጣላችሁ? የተጣላችሁስ ቢሆን ካልጠፋ በስተቀር ሽማግሌ ሊያስታርቃችሁ አይገባምን?›› ሲል አስተያየቱን ሲሰጥ ሁሉም በጭብጨባ ስምምነቱን ገለጸ፡፡

እንግዲህ ይህ ሕዝብ ትናንት ኢሕአፓ፣ ወያኔ፣ ሻዕቢያ፣ ቀኝ መንገደኛ ወዘተ. መጣብህ እያለ፣ ልጆችህን ስጠኝ እንጂ አንተን አኖርሃለሁ እያለ ደርግ ፍዳውን ሲያሳየው የነበረና ከመብቱና ከነፃነቱ አንዳንድ መናኛ ነገሮች ስለተደረጉለት ሳይሆን፣ ስለታሰቡለት እየተጎተተ የሥራ ጊዜውን ማባከን አለበትን? ለመሆኑ በደርግ ኢሕድሪ መንግሥት ለቁጥር የሚያስቸግር የድጋፍ ሠልፍ ከቶ ምን ተገኘ? የሚለው ጥያቄ ግን በጥልቀት መዳሰስና የአካሄድ ለውጥ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ከልብ ያልሆነ አሠራር አይጠቅምምና!!!

‹‹ከማርክሳዊ ሌኒናዊ አስተሳሰብ ተነስተን የብዙ ፓርቲዎች መኖር የሕዝብና የአገር ጥቅም አያስከብርምና እንደ ኢሕአዴግ ያለ አንድና ጠንካራ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ይበቃል፡፡ እስካሁን የተገኘው ዴሞክራሲያዊ ድል ሁሉ በእሱ አይደለምን?›› ብለን እንዳንተወው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እየተከተልን ነው፡፡ የነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት ደግሞ የነፃ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የነፃ ፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ዘረኛ፣ ወዘተ. ሳይባል ሁሉንም አስተሳሰብ ያለገደብ የሚያስተናግድ ሥርዓት ነው፡፡ ጠንካራ ጠንካራውን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት የተለያየ ስም እየሰጣችሁ፣ ደካማውን ደግሞ መቼም የትም አይደርስምና ‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላህ ግፋው›› ዓይነት አስተናግዱት የሚሰኝ ፍልስፍናም የለም፡፡ እኛ የነገሩ አካሄድ የሚገርመንና ችግር እንዳያመጣ የምንሠጋ ሰዎች ደግሞ ሞርቲ መርዱራንድ የተባለ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ፣ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ወደ አገራችን በመጣበት ጊዜ ‹‹ክሬዚ ካምፔይን›› በሚል ርዕስ ባጠናቀረው የዘገባ መጽሐፍ (1936) ኢትዮጵያውያን አርበኞች፣ ውኃውን ወረው የፋሺስት ጦር እንዳይጠጣው ይመርዙት ስለነበርና በዚህም ምክንያት ጉዳት ስለደረሰበት ‹‹እንደ ወታደር መዋጋት አለባቸው እንጂ፣ እንደ መራዦች መሆን የለባቸውም፤›› በማለት ጄኔራል ሳኒቲ መናገሩን ጠቅሶ፣ ‹‹ይህ አባባል እነሱ በጋዝ መርዝ ከሚጨፈጭፉት ድርጊት ጋር እንዴት እንደሚገናዘብ ለሚያስበው በጣም የሚያስገርም ይሆናል፤›› በማለት አስተያየቱን እንዳሠፈረው አካሄድ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ ስንወተውት፣ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ልንባል አይገባም፡፡ የእብሪተኛ መሪዎች ሁሉ ስህተት ይኼው ነበር፡፡

ይህም ብቻ አይደለም ዓለማችን ‹‹ነፃ እናወጣችኋለን፣ እኩልነታችሁን እናረጋግጣለን፣ ፍትሕና ርትዕ እናሠፍናለን፣ ዴሞክራሲም ይረጋገጣል. . . ›› የሚሉ በርካታ አምባገነኖችን ኢትዮጵያ ታውቃለች፡፡ ‹‹ወርቅ ቢያቀርቡለት ፋንድያ ነው›› የሚል ተብሎ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከመነቀፉ በፊት፣ ማለትም የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ጥሎ ሥልጣን በጨበጠበት ጊዜ ሕዝብ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ የሚያስጎመጁ ዲስኩሮች ተደርገውለት ነበር፡፡ ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ መኮንን ያለው ወታደር ሁሉ፣ ‹‹ሕዝብ ከተባበረና ትከሻ ለትከሻ ከተደጋገፈ እውነትም የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት እናደርጋታለን፤›› ብሎን ነበር፡፡ የጎደለው ድጋፍም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሥልጣን ከከረሜላ፣ ከስኳርም፣ ከማርም የበለጠ ይጥማልና የደርግ አባል የሆነ ሁሉ ሥልጣኑን የሚያደራጅለት ወዳጅ ዘመዱን መጎተት ጀመረ፡፡ በአምቻ በጋብቻ ተሳሰረ፡፡ በፊውዳል መኳንንትና መሳፍንት ምትክ ወታደራዊ መኳንንትና መሳፍንት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማየት በቃን፡፡ የእኛዎቹን ወታደራዊ መኳንንትና መሳፍንት በተራቸው ወደ እስር ቤት፣ ወይም ወደ ስደት፣ ወይም ወደ ሞት ሲያዘግሙ ሽርጣቸውን በጎፈሬያቸው ላይ ሸብ ያደረጉ ከሲታ፣ ዙሪያ ምላሻቸውን ቦምብ የታጠቁ ኢሕአዴጎች ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ብዙ እጅግ ብዙ ተስፋ መስጠታቸው ሳይረሳን በቀበሌም፣ በወረዳም፣ በክልልም፣ የተመረጡት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ዘውዳዊና ደርጋዊው መሳፍንትና መኳንንት ወደ ገዥነት መለወጥ ከመሠረታዊ ፍላጎት ባሻገር ማየት ጀመሩ፡፡ ተቃዋሚ ኃይሎች ከተቃዋሚዎቹ ደግሞ ጠንካራዎቹ እንዲንቀሳቀሱ ሲፈልጉ ሥልጣን ከከረሜላም፣ ከስኳርም፣ ከማርም ትጥማለችና ‹‹ቀልቀሎ ስልቻ ስልቻ፣ ቀልቀሎ›› እንዲሉ አሁንም፤

በትግሬም እኛ

በአማራም እኛ

በኦሮሞም እኛ

በጉራጌም እኛ

በሲዳማም እኛ

በሌሎችም እኛ

ከዚህ የተለየ የእናንተ አማርኛ

መሆን ነው ነፍጠኛ

መሆን ትምክህተኛ ይባልልናል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ግን ዴሞክራሲን በትክክል በሚያራምዱት አገሮች የሚታይ አይሁን እንጂ ከዚያ መለስ በእኛዎቹ ዘውዳውያን፣ ደርጋውያን/ኢሕዲሪያውያን፣ ኢሕአዴጋውያን ብቻ የተንፀባረቀ አይደለም፡፡ ሞሎቫን ዲጂላስ የተባሉ የዩጎዝላቪያ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ ‹‹ዘ ኒው ክላስ›› በሚል ርዕስ በ1958 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ ‹‹በሩሲያም ሆነ በሌሎቹ የኮሙዩኒስት ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ሁሉም ነገር ሌኒን፣ ስታሊን፣ ትሮትስኪና ቡካሪን ከጠበቁት የተለየ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግሥት ዴሞክራሲ ተጠናክሮ የፈላጭ ቆራጭ መንግሥት አገዛዝ ይወገዳል ብለው ነበር፡፡ በመፈጸም ላይ ያለው ግን ግልባጩ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕድገት ተገኝቶ የሕዝብ ማኅበራዊ ሕይወት እንደሚሻሻል አምነው ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ጠበቁት ሊሆን አልቻለም፤›› ካሉ በኋላ፣ ይኼም የሆነው አዲሱ የወዛደር/ላብአደር መደብ ከፊውዳሉ መደብ እንደተነሳው ዘውዳዊ መደብ ልፍለጥ ልቁረጥ በማለቱ ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ የአዲሱ መደብ ሌላ ችግር ካፒታሊስትም፣ ወዛደርም፣ ላባደርም፣ ሠራተኛም ለመሆን የማይችል ነገር ግን በሠራተኛው ላይ የተለጠፈና በስሙ የሚገዛ እንደሆነም ያስገነዝባሉ፡፡ የአዲሱ መደብ ዕጣ ፈንታ ከ40 ዓመታት በኋላ ምን እንደሆነም ዛሬ ከአገራቸው ዩጎዝላቪያ የበለጠ ማስረጃ አይኖርም፡፡ ይህ ግን የጥሩ ነገር ምሳሌ ሊሆን ከቶ አይቻልም፡፡

‹‹ብዙ ሲናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል›› እንደሚባለው፣ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ዘርዝሮ መናገር ይቸግራል፡፡ ሁሉን መዘርዘር አስቸጋሪ ነው፡፡ ወደ ማጠቃለያው እንሂድ። አሜሪካዊው ፈላስፋ ጆን ዲዩ (1859-1952) ‹‹ሪኮንስትራክሽን ኢን ፊሎዞፊ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ (1920 ገጽ 140) ያሠፈረውን ልብ ብለን እንመልከተው፡፡ ‹‹መጥፎ ሰው የሚባለው ሰው ምን ያህል ጥሩ የነበረ ቢሆን ከዕለት ወደ ዕለት ጥሩነቱ እየቀነሰ ሲሆን፣ ጥሩ ነው የሚባለው ሰው ደግሞ ምንም ያህል ፋይዳቢስ የነበረ ቢሆን ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ጥሩነት እያደገ የሚሄድ እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ግንዛቤ ያለው ራሱንና ሌሎቹን ሊገመግም ይችላል፤›› ይላል፡፡ የዚህ ፈላስፋ አመለካከት ትክክል ነው ብሎ የሚያምን መሻሻልን ያመጣል፡፡ ካለማወቅ ባርነትም ራስን ማላቀቅና ራስን በተሻለ ሁኔታ መቅረፅ ነው፡፡ የሰዎች የወደ ፊት ብሩህ ተስፋ የሚመሠረተውም ከመጥፎ ወደ ጥሩ በመጓጓዝ እንጂ፣ ከጥሩ ወደ መጥፎም ሆነ ከመጥፎ ወደ መጥፎ በመሸጋገር ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ ደርግ መሬት ላራሹ በማድረጉ በገበሬው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ በግድ በአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጁና በመንደር ተሰባሰቡ በማለቱ፣ አብዮቱ የመሬት ባለቤት አድርጎሃልና ለአብዮቱ ህልውና ዝመት ብሎ በማስገደዱ ወዶ እስኪሰለቸው ድረስ አንገፍግፎታል፡፡ የሕዝብ መንገፍገፍም ደርግን ከጥሩ ወደ መጥፎ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡

ወቅቱ ዛሬ ነውና የአሁኑ መንግሥትም በዚህ መነጽር ራሱን ይመርምር፡፡ ሕዝብን በእርግጥም ነፃ የማድረግ ፍልስፍና ይጨምር፡፡ እስካሁን ምን ሠራሁ? በዚህ የሥራ ሒደት ምን አጠፋሁ? ብሎ ራሱን ይጠይቅ፡፡ ተቀናቃኝን ማንጓጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለማጥፋት መሞከር የትም እንደማያደርስ የሚያውቅን ሕዝብ በፕሮፓጋንዳ ሞገድ ለማጥለቅለቅ ቢሞከርም ፍንክች እንደማይል መታወቅ ይኖርበታል፡፡  ‹‹ያለ ፍልስፍና የሚያስተዳድር መሪ በእውር ፈረስ የሚመራ ጋሪ›› ተብሎ የሚመሰለውም ለዚሁ ነው፡፡ ሕዝብ የሚመራው በፍልስፍና ጥበብ ነውና ካለፈው ጥፋት ለመማር ያብቃን፣ አሜን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡