Skip to main content
x
ጠመንጃ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት አለበት!

ጠመንጃ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት አለበት!

በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለመቀላቀል የተለያዩ አማፂ ኃይሎች፣ ከኤርትራ በየተራ ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ አማፂ ኃይሎች ከዚህ ቀደም ትጥቅ አንግበው በረሃ የገቡት፣ በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዳናደርግ ስለገፋን የትጥቅ ትግል ይሻለናል ብለው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገር መምራት ከጀመሩ ወዲህ አማፅያኑ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን እንዲንቀሳቀሱ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት፣ ጠመንጃ ከፖለቲካው ዓውድ እንዲርቅ ሙሉ ፍላጎት ታይቷል፡፡ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት የተመቸ መደላድል እንዲፈጠር በርካታ አመርቂ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ትጥቅ ያነገቡ አማፂያንም ደጋፊዎቻቸው አደባባይ በማጨናነቅ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ እነሱም ባደረጓቸው ንግግሮች ካሁን በኋላ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለመቀላቀል መወሰናቸውን በግልጽ አስታውቀዋል፡፡ እዚህ ላይ እንደ ትልቅ ጎደሎ የሚወሳው መንግሥትና አማፂያኑ ያደረጉዋቸው ድርድሮችና ስምምነቶች ግልጽ አለመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ማንኛውም አማፂ ኃይል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለመቀላቀል ከፈለገ፣ ትጥቁን በመፍታት ሠራዊቱን ወደ ተዘጋጀለት ካምፕ እንዲገባ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ታጥቆ ሰላም የማስከበርና የሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ጠመንጃ አንግቦ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ መንጎማለል አይችልም፡፡

መንግሥት አሁንም ከአማፂ ኃይሎች ጋር ያደረገውን ድርድርና ስምምነት ለሕዝብ በግልጽ ማሳወቅ አለበት፡፡ ማንኛውም አማፂ ኃይል ትጥቅ ፈቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈልገውን ጨዋነትና ዲሲፒሊን በግልጽ ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት እንደመሆኑ መጠን፣ ከማንኛውም ወገን ጋር የሚያደርገው ድርድርና ስምምነት ሕግን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰሞኑን በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ትጥቁን እንደማይፈታ ሲነገር ተሰምቷል፡፡ ኦነግ ለምን ትጥቁን አይፈታም? ከመንግሥት ጋር  ያደረገው ድርድርና ስምምነት ምንድነው? ይህ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ይሁንና ኦነግ አገር ቤት በይፋ በተመለሰበት ወቅት አቶ ዳውድ ባደረጉት ንግግር፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለመቀላቀል ድርጅታቸው ቆርጦ መመለሱን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ትጥቅ ፍታ አልፈታም ጭቅጭቅ ውስጥ የሚያስገባ ምን ጉዳይ ተገኘ? ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቆርጦ የተመለሰ አማፂ ትጥቅ አልፈታም ካለ፣ ገና ያልተወራረደ የፖለቲካ ሒሳብ አለ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ከኦነግ በተጨማሪ ሌሎች አማፂ የነበሩ ኃይሎችም ያልተገባ ፉክክር ውስጥ ገብተው የበለጠ ችግር ከመፈጠሩ በፊት፣ መንግሥት ፈጣንና አሳማኝ ምላሽ ይጠበቅበታል፡፡ ትጥቅ አልፈታም ያለ አማፂ ቡድን ምን አስፈራው? ምን ዓይነት ሥጋቶች ቢኖሩት ነው ትጥቅ አልፈታም የሚለው? ከዚህ በስተጀርባስ ምን ዓይነት ዓላማ አንግቧል? የውጭ ኃይሎች ሥውር እጅ ላለመመኖሩ ምን ማረጋገጫ አለ? ወዘተ በማለት በጠረጴዛ ዙሪያ በግልጽ መነጋገር ይገባል፡፡

መንግሥት ትጥቅ ሳይፈቱ የሚንጎራደዱ የፖለቲካ ኃይሎች ምክንያታቸው ምን እንደሆነ አውቆ ለሕዝብ ከማሳወቅ ባለፈ፣ በአንድ አገር ውስጥ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይል በስተቀር ማንም የፖለቲካ ኃይል ትጥቅ እንደማይኖረው አስረግጦ ማስገንዘብ አለበት፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ መጠናከርና መጎልበት ሲባል ትዕግሥትና መለሳለስ መኖሩ ከሞላ ጎደል መልካም ቢሆንም፣ ሕግ የማይገዛውን ግን አደብ እንዲገዛ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በመለሳለስ እሹሩሩ ማብዛት እንደ ድክመት ይቆጠራል፡፡ ፍቅርና ይቅር ባይነትን እየሰበኩ ብቻ አገርን በሰላም ማስተዳደር አይቻልም፡፡ የፍቅርና የይቅር ባይነት አንዱ ዓላማ አመፃንና ሥርዓተ አልበኝነትን ለማስወገድ ጭምር ነው፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ በፍትሐዊነትና በእኩልነት የሚፎካከሩበትን የፖለቲካ ምኅዳር የማስተካከል ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ እግረ መንገዱንም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ግራ መጋባቶች፣ ጥርጣሬዎችና ሥጋቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ መንግሥት የሕዝብንም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎችን አመኔታ ለማግኘት ተጨባጭ የለውጥ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ መደላድሉን ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ሥጋትና ጥርጣሬ መወገድ አለባቸው፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ ሥፍራዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚያስተውሉ የፖለቲካ ኃይሎች ትጥቃችንን ፈተን ለአደጋ ብንጋለጥስ ብለው የሥጋት ጥያቄዎችን ቢያነሱ፣ መንግሥት ግጭቶች ሙሉ በሙሉ ተወግደው ሰላምና መረጋጋቱ አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ የአስተዳደርና የፀጥታ መዋቅሮቹን ሙሉ በሙሉ ማንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ችግር ያለባቸው መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰጉ ደካሞችን በጠንካራ አመራሮችና ፈጻሚዎች በመለወጥ፣ አገሪቱን የማስተዳደር አቅሙን በሚገባ ማሳየት አለበት፡፡ መንግሥት መለሳለሱ እንደ ድክመት እየተቆጠረ ትጥቅ አልፈታም የሚባል ከሆነ፣ ወደ አገር ቤት የተመለሱ አማፂያን በሥርዓት ትጥቃቸውን ፈተው ሥምሪት ካልተደረገላቸው፣ ድርድሮችና ስምምነቶች ግልጽ ባለመሆናቸው ብቻ ውዥንብር ቢፈጠር፣ አንፃራዊውን ሰላም የሚያደፈርሱ ፍጥጫዎችና ግብግቦች ቢያጋጥሙ፣ ወዘተ የታሰበው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች እንደስተዋለው የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂነትን በመፍራት ግዳጃቸውን ላለመወጣት ካቅማሙ፣ የተጀመረውን ለውጥ ችግር ውስጥ ይከቱታል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች በሕጉ መሠረት ግዳጃቸውን በአግባቡ ካልተወጡ ደግሞ፣ ራሳቸውን ያስታጠቁ ኃይሎች መፈንጨት ይጀምራሉ፡፡ መንግሥት ይኼንን ጉዳይ በአንክሮ ሊያስብበት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት የውጭ ወራሪ ኃይሎችን ስትመክት የኖረች አገር ናት፡፡ በዚህ ምክንያት አሁንም ታሪካዊ ጠላቶች አሉዋት፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ያሸመቁ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ትልቅ ትኩረት ያሻዋል፡፡ የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ይኼንን አጋጣሚ በመጠቀም ትርምስ አይፈጥሩም ማለት የዋህነት ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ሁሌም አኩራፊ እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ አኩራፊዎች በብልኃት ካልተያዙ ደግሞ ችግር ይፈጠራል፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙዎቹ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ትግል ተሳታፊ ያልሆኑት፣ ሥልጣን በያዙ ወገኖች ከመጠን በላይ በመገፋታቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፖለቲካ ብልጠትና ብልኃት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ብልጠትና ብልኃት ግን አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ የሚያደርግ ሳይሆን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ወገን አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሚችለው ግልጽ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ድርድርና ስምምነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በኢትዮጵያ ምድር ሥልጣን በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን፣ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ከሆነው የሕዝብ ድምፅ እንዲገኝ ያስችላል፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድ ደግሞ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲከናወን የሚያግዙ በርካታ ሥራዎች ከፊት ይጠብቃሉ፡፡ እነዚህን ሥራዎች ተጋግዞ ለማከናወን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ታጥቆ መንጎራደድ ለአምባገነናዊ ሥርዓት ያመቻቻል፡፡

ኢትዮጵያ በተጀመረው ለውጥ አማካይነት ወደፊት መገስገስ አለባት፡፡ ይህ ግስጋሴ ጠንካራ የዴሞክራሲና የሲቪክ ተቋማት እንዲያብቡ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በስፋት ሥራ ላይ እንዲውል፣ ኢትዮጵያዊያን የፈለጉትን የመደገፍ ያልፈለጉትን የመቃወም ነፃነት እንዲጎናፀፉ፣ ለአገር የሚጠቅም ሐሳብ ያላቸው ወገኖች ያለምንም መሸማቀቅ እንዲንቀሳቀሱ፣ ወዘተ ማድረግ ከተቻለ ቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና አሳማኝ ሆኖ ይከናወናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆነው መቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህ ሒደት ግን ጠመንጃን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማስወጣት አለበት፡፡ ጠመንጃ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ጠመንጃ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሕዝብና አገር የሚጠብቁበት እንጂ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንግበው የሚንጎማለሉበት መሆን የለበትም፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለውጡ ተቀልብሶ ለአምባገነንነት እጅ መስጠት ይመጣል፡፡ ያኔ በፀፀት ፀጉርን እየነጩና ጥርስን እያፋጩ ቢነፋረቁ ዋጋ የለውም፡፡ ጠመንጃ ነውጠኝነትንና ሥርዓተ አልበኝነት ከማራባት ውጪ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጠንቅ ነው፡፡ ስለዚህ ጠመንጃ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት አለበት!