Skip to main content
x
አቀንጭራነትን ለመከላከል

አቀንጭራነትን ለመከላከል

አሪ ሄንድሪክ ሃቪላር (ዶ/ር) በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የማይክሮባያል ሪስክ አሲስመንት ኤንደ ኢፒዲሞሎጂ ኦፍ ፍድቦርን ዲሲስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በዩኤስኤአይዲ ‹‹ሊድ ዘ ፊውቸር›› ፕሮግራም እና በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በሚደገፈውና በእንስሳት አያያዝ በንፁህ ሥፍራ ከመኖር ጋር በተያያዘው ፕሮጀክት፣ ባለፈው ክረምት ከኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን ተመራማሪዎች ጋር ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታ፣ በመቀንጨርና (Stunting) በተመጣጠነ ምግብ ዙሪያ ስለሚታዩ ፈተናዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሳሙኤል ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ በጥናቱ ዘርፍ ከተለያዩ አጋሮች ጋር ተጣምሮ ይሠራል? ቢያብራሩልን?

አሪ ሄንድሪክ (ዶ/ር)፡- በዩኤስኤአይዲ የሚደገፈው ‹‹ፊድ ዘ ፊውቸር ኢኖቬሽን ላብ ፎር ላይቭስቶክ›› ሥርዓት በቁም ከብት ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በሰባት ፕሮጀክቶች ይሳተፋል፡፡ ከፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ማለትም የአንድ ዓመት ከግማሽ እንዲሁም እስከ አራት ዓመት የሚቆዩ አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የሚደጎሙ ያሉ ሲሆን፣ በየዓመቱም ፕሮጀክቶቹ ስለደረሱበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንመክራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከእንስሳት አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚኖረው ብክለትና የሚያስከትለው የጤና እክል ላይ በኢትዮጵያ ስላለው ሥራ ቢገልጹልን?

አሪ ሄንድሪክ (ዶ/ር)፡- ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብቻ የታቀደ ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የቁም ከብት ሥርዓቱን በማዘመን ድሆች በቋሚነት የተሻለ ገቢ የተመጣጠነ ምግብና ጤና በዘላቂነት የሚያገኙበት ሥርዓት እንዲኖር ማመቻቸት ነው፡፡ ዋና ትኩረት የሰጠነው ማኅበረሰቡ በተለይም እናቶችና ታዳጊዎች የእንስሳት ተዋፅኦ የሚመገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ይኼንን ለማድረግ አንዱ አካሄድ የእንቁላል ማስፈልፈል እንዲጨምር ማድረግ ነው፡፡ እንቁላል በከፍተኛ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ ይዘት አለው፡፡ በኢኳዶር የተደረገ ጥናት የሚያሳየው ሕፃናትን በየቀኑ ለስድስት ወር ያህል አንድ፣ አንድ እንቁላል ማብላት የመቀንጨር አጋጣሚን በግማሽ መነሱን ነው፡፡ የእንቁላል ምርትን ማብዛትም በኢትዮጵያ ስለቁም ከብት በተዘጋጀው መሪ ዕቅድ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዶሮ አርቢዎች ጋር ተያይዞ የሕፃናት ጤና አደጋ ውስጥ የሚወድቅበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዶሮዎች ጋር አብሮ መኖርና ማደር በራሱ ለቅንጨራ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ዶሮዎች ቻምፒሎባክተር ለተባለው ባክቴሪያ መራቢያ ናቸው፡፡ ይህ የልጆች የሆድ ዕቃን በመጉዳት ለቅንጨራ ምክንያት ይሆናል፡፡  በጥናትም ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም እኛ የምንመክረው የዶሮ ማርባት ሥራው በጥንቃቄ መያዝና ንፅህናው በተጠበቀ መልኩ መመራት እንዳለበት ነው፡፡ በተለይ የዶሮ ኩስ በአግባቡ የሚወገድበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱ ዓላማ ምንድን ነው?

አሪ ሄንድሪክ (ዶ/ር)፡- የዶሮ እንቁላል የሚመገቡ ታዳጊ ልጆች ከማይመገቡት በተለየ ዕድገታቸው እንደሚፈጥንና ዘላቂ ጠቀሜታ እንደሚያገኙ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በኢትዮጵያ ያደረግነው ጥናትም በቤት ውስጥ የዶሮ እርባታን በማዘመን ለልጆች የሚሆን በርካታ እንቁላል ማግኘት እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ የዶሮ ኩስም እንዴት መወገድ እንደሚችልና ሕፃናትን ከብክለቱ በመጠበቅ የሕፃናቱን ጤና ማሻሻልና ዕድገታቸው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማምጣት እንደሚቻል አይተናል፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ የዶሮና የቁም እንስሳት እርባታውን ማሳደግ፣ ከስድስት እስከ 18 ወራት ያሉ ሕፃናት ከእንስሳትና ዶሮ በሚመጣ እዳሪና ሽታ እንዳይጋለጡ ቅድሞ መከላከልና ሥልጠና መስጠት፣ የግል ንፅህና እንዲጠበቅና ሕፃናትን በባክቴሪያ ከተበከለ አየር መጠበቅ፣ በቤት ውስጥ እንቁላል የሚመገቡበትን ጊዜ ማብዛትና መሠረታዊ የተመጣጠነ ምግብና የአካባቢና የግል ንፅህና (የዋሽ) ሥልጠና መስጠት ናቸው፡፡ ይህ ከስድስት እስከ 18 ወር ያሉ ልጆችን ዕድገት መልካም ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የተለያዩ ፕሮጀክቶች አሏችሁ? ተመሳሳይ ችግር ታስተውላላችሁ? የኢትዮጵያ በምን ይለያል?

አሪ ሄንድሪክ (ዶ/ር)፡- በስምንት አገሮች እንሠራለን፡፡ ሁሉም የተመረጡት የፃናት መቀንጨር በብዛት ስለሚታይባቸው ነው፡፡ አገሮቹ የተለያዩ እንደመሆናቸው የተለያዩ አካሄዶችን ተከትለን ቅድሚያ የሚፈልጉትንና ፈተናዎችን ለማየት ሞክረናል፡፡ ከ2015 እስከ 2016 በሠራነው ሥራ ሁሉም አገሮች ተመሳሳይ ችግርና ቅድሚያ የሚፈልጓቸው ፍላጎቶች እንዳሏቸው ተገንዝበናል፡፡ የቁም እንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ በኩል የምግብ አቅርቦትና የጥራት ችግር በሁሉም አለ፡፡ የእንስሳት በሽታም እንዲሁ፡፡ የከብት አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ከፍተት አለ፡፡ እኛ በምንሠራባቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች በሙሉ አዳዲስ አካሄዶችን ለመቀበል የሚጓጉና የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አንዴ ቴክኖሎጂው ጥሩ መሆኑንና ችግራቸውን እንደሚፈታ ካመኑበት ይቀበላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በምሥራቃዊ ክፍል፤ ሐረር ነበሩ፡፡ ምን ነበር ሥራዎት?

አሪ ሄንድሪክ (ዶ/ር)፡- ከፍሎሪዳ፣ ከኦሃዩና ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሁለት ሳምንታት ቆይታ አድርገዋል፡፡ በመጠናት ላይ ባለው የኅብረተሰብ ጥናት ዙሪያ ተወያይተናል፡፡ በቅርቡ የመረጃ ማሰባሰቡ ይጀመራል፡፡ በመረጃ አሰባሰብ፣ በሥነ ምግባር፣ በቃለ መጠይቅ በኤሌክትሮኒክስ መረጃ የመሰብሰብ ዘዴን፣ የሕፃናት ጤና ዳሰሳ፣ የማይክሮባዮሎጂካል ቤተ ሙከራና በጥራት ሥልጠና ዙሪያ መክረናል፡፡ ሥራው በጥልቅ የተከናወነና የሁሉም ቁርጠኝነት የታየበት ነበር፡፡ እርስ በርስ ለመማርም አስችሏል፡፡ ለአሜሪካ ተመራማሪዎች በገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን አኗኗር ለመማር፣ የአርሶ አደሩንና የቤተሰቡን ፈተናዎች ለማየትና በቴክኖሎጂ ሕይወታቸውን እንዴት መለወጥ እንደሚቻል ለመገንዘብ መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ አካባቢው ሕዝብ የበዛበት የሚኖርበት፣ የውኃና የመሬት እጥረት ያለበትና ለአየር ንብረት ለውጡ ችግሮች የተጋለጠ መሆኑን አይተናል፡፡ በአባቶች የሚመራ፣ ከፍተኛ ድህነት የሚታይበት እንዲሁም የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ዕድገት እየመጣለት ያለ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ካለፉት 10 እና 15 ዓመታት ወዲህ ጫት ኢኮኖሚውን ማለትም ለቤተሰቦች የገቢ ምንጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም ከገበያ ምግብ የመግዛት ዕድላቸውን አስፍቷል፡፡ ሆኖም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በከፍተኛ መጠን ይታያል፡፡ የእንስሳት ተዋፅኦ መመገብም ዝቅተኛ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ስታርች (ኃይል ሰጪ) የበዛበትን የአካባቢውን ዋና ምግብ የሚመገብ ሲሆን፣ የተመጣጠነ ምግብ ይዘት ያላቸውን ገንቢ ምግቦች የመመገብ ባህሉ እናሳ ነው፣ ወይም አይመገብም ለማለት ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- የዶሮ እርባታውን ዘርፍ በማሻሻል ሕፃናት እንቁላል እንዲመገቡና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የማስቻል ጥረታችሁን ቢነግሩን?

አሪ ሄንድሪክ (ዶ/ር)፡- ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት እንቁላል በተመጣጠነ ምግብ ይዘት የበለፀገ ነው፡፡ በመሆኑም ታዳጊ ሕፃናት እንቁላል እንዲበሉ ማመቻቸት የተመጣጠነ ምግብ አወሳሰዳቸውን ያሻሽለዋል፡፡ ሆኖም ይኼንን ግብ ለመምታት የተለያዩ እክሎች አሉ፡፡ ፕሮጀክታችን ከከብት እዳሪ አስተዳደርና ንፅህና ጋር ያለውን ችግር እየፈታ ነው፡፡ ሥራችን ውጤታማ እንዲሆን ተሳታፊዎች ሁሉ በመከላከል ሥራው እንዲሳተፉ የሥልጠና ሞዴል አዘጋጅተናል፡፡ ይህ በአጠቃላይ እንቁላል መመገብን ጨምሮ የሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ችግርን ይደርሳል፡፡ ሰዎች እንቁላልን የቅንጦት ምግብ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም ሸጠው ለቤተሰብ ሌላ ቀለብ ይገዛዙበታል፡፡ ንፅህናን በተመለከተ የዶሮ ኩስ ብቻ ሳይሆን የእንስሳትና የሰው እዳሪ አወጋገድም መሠልጠን አለበት፡፡ በመሆኑም ሥልጠናችን የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ ትምህርቶችን ያካተተና እንስሳትን እንዴት ማስተዳደር ብሎም ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ያካተተ ነው፡፡