Skip to main content
x
‹‹ኢትዮጵያን አንድ ላይ ሆነን የምናሳድግበት ጉዳዮች ላይ ከተስማማን ሁሉም ነገር ቀላል ነው›› አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ የኖክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ነዳጅ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

‹‹ኢትዮጵያን አንድ ላይ ሆነን የምናሳድግበት ጉዳዮች ላይ ከተስማማን ሁሉም ነገር ቀላል ነው›› አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ የኖክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ነዳጅ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

አቶ ታደሰ ጥላሁን የናሽናል ኦይል ኩባንያ (ኖክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ  ከ40 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነቶች ሠርተዋል፡፡ መጀመርያ ተቀጥረው የሠሩት በአዲስ አበባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ነው፡፡ በሥራው ዓለም በአብዛኛው ጊዜ ያሳለፉት ግን ሼል ኩባንያ ውስጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ቀደም ሲል የዚሁ ኩባንያ ሠራተኛ ሆነው በ11 አገሮች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉም ነበር፡፡ ሼል ኩባንያ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ ናሽናል ኦይል ኩባንያን (ኖክ) ከ15 ዓመታት በፊት ከሁለት ከሸሪኮቻቸው ጋር በማቋቋም፣ ኩባንያውን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ ነው፡፡ ኖክ በዘርፉ ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ከሁለት መቶ በላይ ማደያዎች አሉት፡፡ በተመሳሳይም በጂቡቲ ኖክ ጂቡቲ የተባለ ኩባንያ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የነዳጅ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት በመሆንም እያገለገሉ ነው፡፡ በትምህርት ዝግጅታቸው በመጀመርያ ከአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ፣ ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲግሪ አላቸው፡፡ አቶ ታደሰ ከአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴና የንግድ ኅብረተሰቡን በሚመለከቱ መድረኮች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን በመስጠትም የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የሁለቱን ምክር ቤቶች ሥራ መጀመርንና የ2011 ዓ.ም. የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር በመንተራስና  ተያያዥ ጉዳዮችን በማካተት ዳዊት ታዬ አቶ ታደሰን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የመንግሥትን የ2011 ዓ.ም. የትኩረት አቅጣጫዎችን ያመላከቱበትን ንግግር አቅርበዋል፡፡ በጥቅሉ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያቀረቡት ንግግር ምን አመላከተዎ? እንዴትስ አገኙት?

አቶ ታደሰ፡- ክቡር ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግግራቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና አጠቃላይ የአገሪቱን ሁኔታ በሙሉ ዳሰዋል ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ በኢኮኖሚ ዘርፍ መከናወን የሚገባቸውን ነገሮች ጠቁመዋል፡፡ የአገሪቱን ችግሮች በጥልቀት የዳሰሰ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን የፈነጠቀና በተለይ ለኢኮኖሚው ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት የሰጠ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ዘርፍ የበለጠ ለማነቃቃት በርካታ የፖሊሲና ተዛማጅ ለውጦች እንደሚደረጉ መግለጻቸው፣ ኅብረተሰቡን ለሥራ በይበልጥ የሚያነቃቃና ብሩህ ተስፋን ይጭራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በእኔ አስተያየት ከዚሁ ጋር በተያያዘ አፈጻጸሙ ላይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሲሆን፣ ይህንን በተመለከተ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት እንዳመለከቱት አስፈጻሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በየዘርፉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መከታተል እንዲቻል፣ አገሪቱን እንደ አንድ ኮርፖሬት ተቋም ወስዶ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባቸው ተግባራት ተለይተው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ለእነዚህ ትኩረት ለሚሰጣቸው ዘርፎች ብልህ፣ ግልጽ፣ ሊለካና ሊከናወን የሚችል፣ እንዲሁም  በጊዜ የተገደበ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ስትራቴጂ ለመንደፍም ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው እሳቸው ያነሱዋቸውን ነጥቦች በየመልኩና በየዘርፉ የት ቦታ ሊከናወኑ ይችላሉ የሚለውን በየዘርፉ ዓይቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው ዋናው ነገር፡፡ እንደምታውቀው በየዓመቱ እንዲህ ይደረጋል ተብሎ በፓርላማ ይነገራል፡፡ ነገር ግን እነዚያ የተባሉት በሙሉ ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ እኔና አንተም መነጋገር ያለብን እንዴት ተግባራዊ መሆን አለበት የሚለው ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዋናው ነጥብ ይህ ነው፡፡ በጥቅል ይተገበራሉ የተባሉ ዕቅዶች እንዴት ነው ተግባራዊ መሆን ያለባቸው? እስካሁን ድረስ በየዓመቱ በፓርላማው በበጀት ዓመቱ የሚከናወኑ ናቸው ተብለው የሚገለጹ መሪ ዕቅዶች ሥራ ላይ ሲውሉ አይታይም፡፡ ሥራ ላይ ላለመዋላቸው ብዙ ምክንያቶች እንደሚነሱ ቢታወቅም፣ እንደ ረዥም ጊዜ የሥራ ልምድዎ ዕቅዶች እንዴት መተግበር ይችላሉ? የተባሉትን ነገሮችስ  እንዴት ወደ መሬት ማውረድ ይቻላል? የትኩረት አቅጣጨዎቹ እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ያምናሉ?

አቶ ታደሰ፡- ለእያንዳንዱ የትኩረት አቅጣጫ በጀት መመደብ ያስፈልጋል፡፡ የእያንዳንዱ የትኩረት አቅጣጫ ግብና አፈጻጸም በመጠንና በጊዜ ገደብ ተለይቶ ሊቀመጥ ይገባዋል፡፡ እነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚተገብሩት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስገነዘቡት፣ የአፈጻጸም ስኮር ካርድ ማዘጋጀትና በየደረጃው ከሚገመግሟቸው አካላት ጋር መፈራረም ይኖርባቸዋል፡፡ ክትትል፣ ቁጥጥርና ግምገማው ከፍተኛ ዲሲፕሊን በተላበሰ መንገድ በየሦስት ወሩ መካሄድ አለበት፡፡ ዓመታዊው ግምገማው የሩብ ዓመቶቹን የግምገማ ውጤት በግብዓትነት ቢወሰድና በየዓመቱ የሚዘጉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ከዕቅዱ ጋር ተገናዝቦ ቢገመገም፣ እንዲሁም ከዓመት በላይ የሚወስዱትን ለሚቀጥለው ዓመት ግምገማ ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህና ተመሳሳይ ነጥቦችን ያካተተ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም የአስተዳደር ሥርዓት ፓርላማው በባለቤትነት ሊይዘውና ለክትትል መሣሪያነት ሊጠቀምበት የሚገባ ሲሆን፣ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ይፋ ቢደረግ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ያጎለብታል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ያስፈልጋል እንጂ ንግግር ብቻ በራሱ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ንግግሮችን ወደ ተግባር መለወጥ ላይ ችግሮች እንዳሉ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ በተግባርም የሚታይ ነው፡፡ ለዚህ ምን ዓይነት ሥርዓት ቢቀረፅ ይሻላል የሚለው ጉዳይ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ብዙ ጊዜ የሚታወቁት አስፈጻሚ የሚባሉት የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ በግል ዘርፉ ውስጥ ያሉና ሌሎች ባለሙያዎች፣ መንግሥት እተገብራቸዋለሁ በሚላቸው ዕቅዶች ላይ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት ዕድል ቢኖርስ? በተለይ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዴት እየተከናወኑ እንደሆነ የመንግሥትን ሪፖርት ከማዳመጥ በተጨማሪ የገለልተኛ ወገኖች ተሳትፎ ቢኖርስ?

አቶ ታደሰ፡- ከዚህ ቀደም ብዙ ነገር ዓይተህ ይሆናል፡፡ አንድ ፕሮጀክት ላይ መጀመርያ ፕሮጀክቱን የሚመራው ኤጀንሲ ወይም አካል መታወቅ አለበት፡፡ ይህንን በዚህ በዚህ መንገድ ትሠራለህ፣ ለዚህ ደግሞ ይህንን ያህል በጀት ተይዞልሃል፣ ማጠናቀቅ ያለብህም በዚህ ጊዜ ነው መባል አለበት፡፡ ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚገኘው ጥቅም ይኼ ነው ተብሎ በትክክል ከታወቀ፣ ያ አመራር የሚያስፈልገውን ዕርዳታ ሊሰጡ የሚችሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በኃላፊነት መሥራት ያለበት ራሱ ነው፡፡ ምክንያቱም  ከሌላ ቦታ አንድ ሰው አምጥተህ ቁጥጥር ያደርጋል ብትል ምናልባት ኃላፊነቱን የሚያደበዝዝ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ወስዶ ኃላፊነቱን የሚቆጣጠር የበላይ አለቃ መኖር አለበት፡፡ በእኔ እምነት ለእያንዳንዱ ሚኒስትር አለቃው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደግሞ ፓርላማው ይቆጣጠራል፡፡ እንዲህ ያለው ሰንሰለታዊ አሠራር መቀመጥ አለበት፡፡ ሌሎች ድጋፍ የሚሰጡ ካሉ እሰየው ነው፡፡ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ ግን በኃላፊነት ተጠያቂው ሚኒስትሩ መሆን አለበት፡፡ ሚኒስትሩን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደግሞ ፓርላማው መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡   

ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንቱ ካደረጉት ንግግርም ሆነ በዚህ ወቅት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የሚሏቸው  የኢኮኖሚው ክፍሎች የትኞቹ መሆን አለባቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ ታደሰ፡- አገራችን የተሻለ ጥቅም የምታገኝባቸውን ዋና ዋና ተግባራት በይበልጥ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ በምግብ ራሳችንን እንድንችል የሚረዱ፣ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ጠቀሜታ ያላቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ከእነዚህም ተግባራት መካከል የመስኖ እርሻ ልማት በቀዳሚነት መቀመጥ አለበት፡፡ ልማት ሊካሄድባቸው የሚችሉትን ቦታዎች በፍጥነት በመምረጥ ወደ ሥራ መግባት፣ ራስን ለመቻልና ለምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ የስኳር ልማት ዘርፍ አገራችን ካላት አመቺ የአየር ንብረት፣ ተስማሚ መሬትና ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ምቹነት አንፃር በቂ ትኩረትና ክትትል በማድረግ በአፋጣኝ ወደ ተግባር መሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ኃይል ማመንጨት ሥራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ዘርፍ በተፈጥሮ እጅግ የታደለች በመሆኑ፣ ይህንን ዘርፍ በፍጥነት በማጎልበት ለአጎራባች አገሮች አስተማማኝ የኃይል አቅራቢ የመሆን ዕድላችንን ከወዲሁ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ዋናና ተግባራት በዘመናዊ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት መመራት ያለባቸው ሲሆን፣ አፈጻጸማቸውንም በአግባቡ ለመከታተል አስፈጻሚ አካላት የመገምገሚያ ስኮር ካርድ ውስጥ መካተት ይኖርባቸዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይህንን ሒደት በባለቤትነት ሊመሩ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በግልጽ እንደሚታወቀው ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ንግድና ኢንቨስትመንት ተቀዛቅዟል፡፡ የግል ዘርፉም ተዳክሟል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በፓርላማ ንግግራቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ ችግር ሲባል የማገገማያና የማስተካከያ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል፡፡ እንደ አንድ የንግድ ኅብረተሰብ አባል ምን ዓይነት ዕርምጃዎች ይጠብቃሉ?  

አቶ ታደሰ፡- የግል ዘርፉ በእርግጥም ተዳክሞ ነበር፡፡ አንድ የግሉ ዘርፍ ተዋናይ ወደ  አንድ ቦታ ሄዶ ሠርቶ ትርፋማ ለመሆንና ራሱንም አገሪቱንም ለመጥቀም አንዳንድ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ግብዓቶች ሊሟሉለት ይገባል፡፡  

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ግብዓቶች?

አቶ ታደሰ፡- አንዱ ካፒታል ነው፡፡ የሰው ኃይልና መሬት ያስፈልጋሉ፡፡ ቀሪዎቹ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ማኔጅመንት ሲስተሙንና የመሳሰሉትን የሚያከናውን ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ሊያግዝ የሚችልበት በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የግሉ ዘርፍ አባል አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ይዞ ሲቀርብ አዋጭነቱ ከታወቀ፣ መሬት በቀላሉ ውጣ ውረድ ሳይኖ ሊመቻችለት ይገባል፡፡ የታክስ ተመላሽ የሚያስፈልገው ከሆነ ይህንን እንዴት ማግኘት እንደሚችል የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከተደረገ አዋጭ ሥራዎችን ማከናወን ይኖርበታል ብዬ ነው የማምነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የግል ዘርፉ ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግለት ተገልጿል፡፡ በምላሹ የግል ዘርፉ አስተዋጽኦ ምን መሆን አለበት? የንግድ ኅብረተሰቡን የሚመሩ ተቋማትስ?

አቶ ታደሰ፡- ከዚህ ቀደም የግል ዘርፉ ብዥታ ነበረበት፡፡ አንደኛ ልማታዊ ባለሀብት  ብለው ራሳቸውን ያደራጁ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቻምበር (ንግድ ምክር ቤት) አለ፡፡ እንዲያውም የቻምበርን ሚና የሚያዳክም አደረጃጀት አለ፡፡ አሁን ግን እንዲህ ያለው ነገር የሚፈለግ አይመስለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸውን በተረከቡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የንግድ ኅብረተሰቡን ያነጋገሩት በቻምበሩ በኩል ነው፡፡ ስለዚህ ቻምበር የግል ዘርፉን ችግር አጥንቶ የፖሊሲ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የግል ዘርፉ የሚደገፍበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ዘርፍ ይህ ይጎለዋል፣ በዚህ ዘርፉ ደግሞ ይህ ይቀረዋል ብሎ በትክክል አስጠንቶ ለመንግሥት ማቅረብ አለበት፡፡ ይህንን የሚያደርገው አባላቱን አወያይቶ በሁሉም የንግድ ኀብረተሰብ ስም መሆን አለበት፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም በግል መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በእያንዳንዱ ዘርፍ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ውስጥ ምን ችግር አለ? የሚለውን በባለሙያ በማስጠናት፣ በማወያየትና ችግሩን በመለየት ቁልጭ ባለ ቋንቋ ግልጽ በሆነ መንገድ ለመንግሥት አቅርቦ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ቻምበር መሥራት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የግሉ ዘርፍ የሥራ ባህልም መነሳት አለበት፡፡ የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የግል ዘርፉ ሚና ከፍተኛ ነው ከተባለ የሥራ ባህሉ ወሳኝነት አለው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የግሉ ዘርፍ ወደ ዕድገት ለመራመድ የሚያስችል ቁመና ላይ ነው ያለው ማለት ይቻላል? በአጠቃላይ ዲሲፕሊኑ እንዴት ይታያል?

አቶ ታደሰ፡- ደስ የማይል ነገር ዓይተናል፡፡ ዲሲፕሊናችን ሞቷል፡፡ ምክንያቱም ያላግባብ የመበልፀግ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ በአቋራጭ በቶሎ የመበልፀግ ስሜት ይታይ ነበር፡፡ የፖለቲካውን ድጋፍ በማግኘት በአቋራጭ እየገቡ የተጠቀሙ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሙያተኞች ወይም የግል ዘርፉ አባላት ትንሽ የተዳከሙ ይመስለኛል፡፡ ሞራላቸውም የተነካ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያ ነገር መለወጥ አለበት፡፡ በሰከነ መንገድ መሥራት ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት የሚያቀርበው ሐሳብ መደመጥ አለበት፡፡ ለአገሪቱ  የሚከፍለው ታክስና ምን ያህል ሠራተኞች እንደ ቀጠረ በማየት ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡ በዚያ መንገድ ሞራሉ ሊገነባ ይችላል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡም ለሥራ ቀልጠፍ ማለት ይችላል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ችግር የሥራ አጦች ቁጥር መበራከት ነው፡፡ ችግር እያመጣ ያለው የሥራ ዕጦት ነው፡፡ ይህንን የሥራ ዕጦት እንዴት እንደሚቀረፍ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ነገር አብዛኛው የንግድ ኅብረተሰባችን ሰፊ የጉልበት ሥራ የሚያመጣ ኢንዱስትሪ መምረጥ አለበት፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስኖን ጠቅሰዋል፡፡ የመስኖ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ መከናወን አለበት፡፡ መስኖ ይህችን አገር ከድህነት ለማውጣት የሚችል አቅም አለ፡፡  በአፋር፣ በሱማሌና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለመስኖ ልማት የሚሆን ከፍተኛ ዕድል አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰፊ ዕድል መንግሥትና የግል ዘርፉ በሰፊው ሊገቡበት  ይገባል፡፡ የመስኖ ልማት ሥራን ትኩረት ሰጥቶ በማከናወን ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብርና አሁንም የአገሪቱ ወሳኝ ዘርፍ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው በኢኮኖሚው ሥር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ለማረጋገጥ እንደሚሠራና ለዚህም በግብርናው ዘርፍ እንደ ሜካናይዜሽን ያሉ ሥራዎች እንደሚጠበቁ አመልክተዋል፡፡ ግን ይህ ገለጻቸው እንዴት መሬት ላይ ሊወርድ ይችላል ብለው የሚጠየቁ አሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ወገኖች ግብርናውን ለማዘመን ያስችላሉ የተባሉ ወሳኝ ጉዳዮች አልተገለጹም ይላሉ፡፡ ገበሬው መሬቱን ተጠቅሞ የበለጠ ምርታማ እንዲሆን፣ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን ገዝቶ ለመጠቀም የሚችልበት ዕድል የለም፡፡ ብደር ለማግኘት እንኳን አይችልም፡፡ ግብርናውን እናሳድጋለን ከተባለ ከሚነገረው በላይ ምንድነው መደረግ ያለበት ብለው ያምናሉ? እንዲያውም ዘንድሮ መጀመር ያለበትስ?

አቶ ታደሰ፡- እንደሚታወቀው የእያንዳንዱ የገበሬ ማሳ ታርሶ የትም አያደርስም፡፡ ገበሬው ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለገበያ አውጥቶ ኅብረተሰባችንን ይመግባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ለሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች ቦታዎች መርጦ ማልማቱ፣ ከራስ ፍጆታ በላይ ለአካባቢያችን አገሮች ኤክስፖርት አድርገን የምንጠቀምበት ትልቅ ዕድል አለ፡፡ ይህ አካሄድ ሊለውጠን ይችላል እንጂ እያንዳንዱ ገበሬ መሬት በመቆፈር አገሪቱን እየጎዳ ይሄዳል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው ጉዳት ምክንያት ይሆናል፡፡ እንዲያውም እስከተቻለ ድረስ ገበሬውንና መሬቱን መለያየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ አባባልዎን ያብራሩልኝ?

አቶ ታደሰ፡- ለምሳሌ ገበሬው ዛፍ እየተከለ አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር የሚከፈለው ነገር ቢኖር መሬቱ ዕረፍት እንዲያገኝ ይረዳል፡፡ ገበሬው አንድ ላይ የሚያርስበት ሁኔታ ተፈጥሮ ‹ኮሙዩኒቲ ፋርሚንግ› (የኅብረት እርሻ) መተገበር ይሻላል እንጂ፣ እያንዳንዱ ገበሬ መሬት እየቆፈረ የሚያከናውነው ገበሬውንም አገርንም የሚጠቅም አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ሰፋፊ እርሻዎች ጉዳይ ከተነሳ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱት ከስኳር ፋብሪካዎች ጋር በተጓዳኝ ያሉት የሸንኮራ አገዳ እርሻዎች ናቸው፡፡ የሸንኮራ አገዳ ልማትን በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም፡፡ ቢያንስ ከሸንኮራ አገዳ ልማት በአግባቡ ተጠቃሚ ለመሆን፣  ሰፋፊ እርሻዎችን በአግባቡ ለመጠቀም ምን መደረግ አለበት?

አቶ ታደሰ፡- የስኳር ፕሮጀክትን ከወሰድክ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ መንግሥት የራሱ እርሻ ይኖረዋል፡፡ ፋብሪካውም አለ፡፡ ነገር ግን የስኳር ፕሮጀክትና እርሻው የመንግሥት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አብዛኛው እዚያ አካባቢ ያለ ገበሬ ሸንኮራ አገዳ አምርቶ፣ ለመንግሥት የስኳር ፋብሪካዎች ያቀርባል፡፡ በዚያ ይጠቀማል፡፡  የእርሻዎቹ ጠቀሜታ ለገበሬውም ጭምር ነው፡፡ የጎረቤት አገሮች እንዲህ እየሠሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሥራ ‹አውት ሶርስ› (ኮንትራት በመስጠት) አድርገህ መሥራት አለብህ፡፡ እንዲህ ያለውን አሠራር በመዘርጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ በስኳር ብቻ ይህች አገር ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በስኳር ምርት ተጠቃሚ መሆን ሲገባት አልሆነችም፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ የሚመረተው ስኳር የጥራት ደረጃ ተፈላጊ መሆኑ ታውቆ ተገቢው ትኩረት እየተሰጠው አይደለም፡፡ ለምን?

አቶ ታደሰ፡- በስኳር ምርት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ስኳር የጥራት ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን፣ በአፈሩ ምክንያት በኢትዮጵያ የሚመረተው ስኳር የጥራት ደረጃ ተፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የስኳር የማምረቻ ዋጋ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከገበያ አንፃርም አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ብታቀርበው ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ነው፡፡ እንዲህ ባሉና በሌሎች ምክንያቶች በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ አዋጭ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡  

ሪፖርተር፡-  በፕሬዚዳንቱ  ንግግር ሌላው ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራበታል የተባለው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ካፒታል አሰባስበው በአዋጭ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ የሚለው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአክሲዮን ማኅበር ተደራጅተው ካፒታል በማሰባሰብ ወደ ሥራ ለመግባት የተደረጉ ሙከራዎች ሲሰነካከሉ ታይተዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ ሥራ ላይ ለማዋል ምን መደረግ አለበት?

አቶ ታደሰ፡- ኢትዮጵያውያን ከተደራጁ በአሁኑ ጊዜ ካፒታል አለ፡፡ የውጭ ካፒታል አለ፡፡ አዋጭነቱ ታይቶ ብድር ሊሰጡ የሚችሉ የውጭ ተቋማት አሉ፡፡ ዋናው ነገር መደራጀታቸው ነው፡፡ ካፒታል አሰባስበው ሊሠሩ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን ተደራጅተውና ቦታ አግኝተው በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ የሚገቡትን ዕድል ካገኙ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት እንደ ከፍተኛ ችግር ከሚጠቀሰው ውስጥ የካፒታል ወይም የገንዘብ ችግር ነው፡፡ እርስዎ እንደገለጹልኝ ደግሞ የውጭ ካፒታል ወይም ከውጭ የሚገኝ ብድር አለ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ ለኢንቨስትመንት ይዋል ተብሎ የሚሰናዳውን ገንዘብ ከባንክ በመውሰድ፣ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ባለመቻሉ የተበላሸ የብድር መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን መጥቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ የሚቀርቡ ካፒታሎችን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል?

አቶ ታደሰ፡- ችግሩ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ነው፡፡ ሰዎች ያላቅማቸው ገንዘብ ወስደዋል፡፡ ይመረታል የተባለው ሳይመረት ገንዘቡ ለሌላ ነገር ውሏል፡፡ በዚህ ምክንያት ከመንግሥት የተወሰደው ካፒታል ሳይመለስ ችግር ውስጥ ተገብቷል፡፡ አሁን እንዲህ ባለው ሁኔታ አይደለም የምናወራው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ፖሊሲውን ከቀየረና ለምሳሌ እኔ ከውጭ ካፒታል መበደር የምችል ከሆነ ችግሩ ምንድነው? የፕሮጀክቱ አዋጭነት ታይቶ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ መበደር የምችል ከሆነ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ማረጋገጫ ከሰጠ መበደር የሚቻልበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ የውጭ ድርጅቶች አዋጭ ለሆኑ ፕሮጀክቶችና ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚቋቋሙ ኩባንያዎች ብድር ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ፈንድ አለ፡፡ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማት ብድር ለማቅረብ ዝግጁ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያራምደው ፖሊሲ፣ የግል ኩባንያዎች ከውጭ የሚያገኙዋቸውን ብድሮች የማይደግፍ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ብድር ቢገኝ እንኳ በኢትዮጵያ መንግሥት ይሁንታ አያሰጥም፡፡ እንዲህ ያሉ የውጭ ብድሮች ሲገኙ ብድራቸው በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል በመሆኑ መንግሥት ፍራቻ አለው፡፡ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለዕዳ መክፈያ ያዳግታል ከሚል ሥጋት የመነጨ ነው፡፡ ይህ ከሆነ እንዲህ ያለው የውጭ ብድር እንዴት ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል? ምን ዓይነት መፍትሔ ይኖረዋል?

አቶ ታደሰ፡- ትክክል ነው፡፡ ለዚህ ሊሆን የሚችለው መልስ የፕሮጀክቱ አዋጭነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ፕሮጀክትህ የወጪ ንግድ ላይ የተመሠረተ ከሆነና አምርተህ ለውጭ ገበያ የምታቀርብ ከሆነ፣ መልሰህ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ነው፡፡ ስንዴ አምርተህ ለውጭ ገበያ የምታቀርብ ከሆነ፣ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ታደርጋለህ፡፡ ክፍያው ይፈጸማል፡፡ ይህ ችግር አይደለም፡፡ አሁን እኮ የዓለም ገበያ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ራሳችንን ነጥለን ማየት አንችልም፡፡ ለዚህ ባለ ካፒታሉ የሰጠውን ብድር በውጭ ምንዛሪ ማግኘት አለበት፡፡ ይህ መከልከል የለበትም፡፡ ዋናው ነገር አዋጭነቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምን ታገኛለች? ለኢትዮጵያ የሚቀረው ነገር ምንድነው? ብሎ መታየት አለበት እንጂ መከልከል የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ አሁን በፋይናንስ ዘርፍ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ሪፎርም፣  ሊመለከታቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ የውጭ ብድርን መፍቀድ መሆን አለበት ብለው ያምናሉ ማለት ነው?

አቶ ታደሰ፡- በትክክል!

ሪፖርተር፡- በፋይናንስ ዘርፍ መሆን አለበት ብለው የሚያስቡት ነገር አለ? አሁን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከታሰበው አንፃር የፋይናንስ ዘርፉ እንዴት ባለ ፖሊሲ መቃኘት አለበት? በፋይናንስ ዘርፍ የመንግሥት ትኩረት ምን መሆን አለበት፡፡

አቶ ታደሰ፡- በዚህ ረገድ ባለሙያዎች ሊተነትኑት የሚችሉት ነገር እንዳለ ሆኖ፣ በእኔ እምነት ግን አዋጭ የሆነ ቢዝነስ በሚመጣበት ጊዜ በተለይ የውጭ ገበያን ያለመ ኢንቨስትመንት መሆኑ ከታመነ ፋይናንስ ማግኘት አለባቸው፡፡ እንዲህ ያለ የተመቻቸ ነገር ካለ ብዙ ኩባንያዎች ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ ፋይናንስ ስንል ፈንዱን የማቅረብ ነገር ነው፡፡ ኩባንያው ለሚፈልገው ኢንቨስትመንት በሚፈልገው መንገድ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ካፒታሉን ማግኘቱ ችግር የለውም፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም የተሳሳተ አመለካከት ነበር፡፡ ይህም የግል ዘርፍ ጉዳይ እንደ ግል ጉዳይ ተደርጎ ነበር የሚወሰደው፡፡ ግን አይደለም፡፡ የግል ዘርፍ ማለት ባለቤትነቱ ሌላ ይሁን እንጂ እንደ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም የሚሠራ ነው፡፡ ሠራተኛ ይቀጥራል፡፡ ታክስ ይከፍላል፡፡ ራሱንም ኅብረተሰቡንም ይጠቅማል፡፡ በዚህ መልኩ መታየት አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለኢትዮጵያ የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ ሲታሰብ በአብዛኛው ያደላው የንግድ ሥራ ላይ ነው፡፡ ብዙዎች እርሻ ውስጥ የሉም፡፡ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመግባት መነሳሳት የለም፡፡ ንግድ ላይ ብቻ የበለጠ የማተኮሩ ነገር መለወጥ የለበትም? ከንግድ ውጪ ባሉ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶች ላይ ተገብቶ እንዳይሠራ አሉ የሚባሉ ማነቆዎችን መፍታት አይችልም?

አቶ ታደሰ፡- በደንብ መፍታት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ግን በአብዛኛው ንግድ ላይ ስለተሰማራ መጥፎ ነው ብዬ አልገምትም፡፡ በብዙ አገሮች ላይ የሚሆነው በተለይ አሜሪካን ብታይ በአገልግሎት ኢንዱስትሪ ብቻ 60 እና 70 በመቶ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ራሱን የቻለ ነው፡፡ በቀላሉ ለማምረት የሚያስችል አቅጣጫ ካለ ሰዎች የማይገቡበት ምክንያት የለም፡፡ እስካሁን የተቸገሩት አዋጭ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በስኳር ፕሮጀክት ውስጥ መንግሥት እኔ እሠራለሁ ስላለ እንጂ፣ የግሉ ዘርፍ ሊሠራው ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም እኮ የነበሩትን የስኳር ፋብሪካዎች ያቋቋሙት የግል ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ካፒታሉ እስከተገኘና በሽርክናም ቢሆን ለግል ዘርፉ ለምን አይፈቀድም? የግል ዘርፉ የአክሲዮን ኩባንያ አቋቁሞ ሥራውን ሊያከናውን ይችላል፡፡ እርሻም እንዲሁ ነው፡፡ መከልከል የለበትም፡፡ ነፃ መሆን አለበት፡፡ ወደ እነዚህ ዘርፎች ሲገባ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ባለሙያዎች መግባባት አለባቸው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጭፍን አይደለም መሠራት ያለበት፡፡ ቴክኖሎጂውና ሳይንሱ መኖር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ የውይይት መድረክ ላይ የግል ዘርፉን ሚና በተመለከተ አስተያየት ሲሰጡ፣ ‹‹የግል ዘርፉ ታክስ ይከፍላል፡፡ መንግሥት በሰበሰበው ታክስ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ይሠራል፡፡ ለምሳሌ መንገድ ይሠራል፡፡ ነገር ግን ከታክስ ከፋዩ የተሰበሰበው ገንዘብ እንዴት እየተሠራበት እንደሆነ የሚጠይቅበት አሠራር የለም፡፡ በታክስ መልክ የግል ዘርፉ አባላት የምንከፍለው ገንዘብ በትክክል ሥራ ላይ ስለመዋሉ የምንቆጣጠርበት አሠራረ አልተዘረጋም፤›› ማለትዎን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ ጠቀሜታው ምንድነው?

አቶ ታደሰ፡- አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን አስተያየት የሰጠሁበት ምክንያት አለኝ፡፡ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተለይ ወሳኝ በሚባሉ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያሉ ተቋማት በቦርድ ይተዳደራሉ፡፡ የመንገዶች ባለሥልጣን በአገሪቱ ውስጥ በሚገነቡት መንገዶች ኃላፊ ነው፡፡ እዚህ ተቋም ውስጥ ያሉት የቦርድ አባላት የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ መሆን አለባቸው ብዬ አልጠብቅም፡፡ ቦርዱ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች መግባት መለባቸው፡፡ ከቻምበር ሊሆን ይችላል፣ ጉዳዩን በቀጥታ የሚያውቁ የግል ዘርፉ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግን መግባት አለባቸው፡፡ ዕውቀቱ ያላቸው የግል ዘርፉ ተወካዮች ሊካተቱ ይገባል፡፡ የግል ዘርፉን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ወይም የሚያነቃቁ፣ እንዲሁም የቢዝነስ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ሊካተቱበት ይገባል፡፡ አየር መንገዱ ውስጥም እንዲህ መሆን አለበት፡፡ የአየር መንገዱ ቦርድ አባላት የመንግሥት ሰዎች ናቸው፡፡ ግን መሆን አለበት? ንግድ ባንክም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ሊወከል ይገባል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው ነገር ሊያስገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ምንድነው?

አቶ ታደሰ፡- ሁሉንም ነገር መንግሥት ያውቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የግል ዘርፉ ቢዝነስ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣን ይበልጥ የግል ዘርፉ ውስጥ ያለው ስለሥራው ያውቃል፡፡ ለምሳሌ እኔን ስለአየር መንገዱ ብትጠይቀኝ ለአየር መንገዱ 50 በመቶ ነዳጅ የማቀርበው እኔ ነኝ፡፡ ምን ችግር እንደሚያጋጥም ላውቅ እችላለሁ፡፡ እዚያ ቦርድ ውስጥ የግል ዘርፍ እንዲኖር እጠብቃለሁ፡፡ የንግድ ባንክ 80 በመቶ የሚሆነው ሀብት የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ የግል ዘርፉን የሚወክል የቦርድ አባል እንዲኖር እጠብቃለሁ፡፡ ብዝኃነት ያለው ቦርድ ቢኖር እመርጣለሁ፡፡ የተለያዩ ሰዎች በመኖራቸው በቦርድ ስብሰባ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ ባንክን ከወሰድክ ገንዘቡ እኮ የሚመጣው ከግል ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ 11 የሚሆኑ አገሮች ሠርተዋል፡፡ በእነዚህ አገሮች በኖሩበት ወቅት ያዩዋቸውና ይኼ ነገር አገሬ ላይ ቢኖር ብለው የተመኙት ነገር አለ? አሁንስ ያለውን ለውጥ እንዴት ያዩታል?

አቶ ታደሰ፡- እኔ ከሁሉም በላይ የሚያመኝ ነገር ቢኖር አሁን የተጀመረው ዓይነት ሰዎች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ እስካሁን አለመኖሩ ነው፡፡ ሰዎች ይፈራራሉ፡፡ ባለመታደል ሰዎች በዘር፣ በእምነትና በመሳሰሉት ይፈራሩ ነበር፡፡ በግልጽ አይነጋገሩም ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር አሁን የሰበርነው ይመስለኛል፡፡ አንዱ የምመኘው እንዲህ ያለውን ነገር ነበር፡፡ አሁን ይህ ተፈጥሯል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን አሁን አንድ ጥያቄ ብንጠይቅ ቆመው በድፍረት የሚመልሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት መድረክ ስለተፈጠረ መነቃቃት ታያለህ፣ ትራንስፎርም የምናደርግበት ወቅት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ነበር የምመኘው፡፡ ለውጥ እያየሁ በመሆኑም ደስ ብሎኛል፡፡ ፖለቲካውና ኢኮኖሚው ተነጣጥለው አይታዩም፡፡ ተደጋጋፊዎች ናቸው፡፡ የፖለቲካው አቅጣጫ በትክክል የማይጓዝ ከሆነ ኢኮኖሚውም ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ አሁን ዋናው ነገር ሁላችንም በጋራ አንድ አገር አንድ የኢኮኖሚ ሲስተም መፈጠር አለበት ብለናል፡፡ ይህ ካልሆነ ልናድግ አንችልም፡፡ የዘርና የሃይማኖት ልዩነቶች ጠፍተው  እንደ አንድ አገርና እንደ አንድ ሕዝብ ነፃ ሆነን የምንጓዝ ከሆነ አብዛኛዎቹ ችግሮቻችን ይፈታሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለባት፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እንደ ዜጋ የሚያስቆጭ ነገር አለ፡፡ ይህም በመከራ የተገኘ የውጭ ምንዛሪ አገሪቱ ማውጣት ለሌለባት እዚሁ በቀላሉ ልታመርታቸው ትችል ለነበሩ እንደ ስንዴና ዘይት ላሉ ምርቶች ታወጣለች፡፡ እንዲያውም የስንዴ ፍላጎቷን ማሟላት ባለመቻሏ፣ ከውጭ ለምታስገባው ስንዴ እንኳን የውጭ ምንዛሪ ጠፍቶ ለወራት የሚጠበቅበትም ጊዜ አለ፡፡ ግን ኢትዮጵያ ስንዴ፣ ዱቄትና የምግብ ዘይት ማስገባት የሚገባት አገር ነበረች?

አቶ ታደሰ፡- የሚያሳፍርህና የሚያሳዝንህ አንዱ ነገር ይህ ነው፡፡ አርሲን ወይም ባሌን ወይም ሌላውንም አካባቢ ብትወስድ፣ ስንዴ በብዛት አምርተህ ለአገር ብቻ ሳይሆን እንደ መካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አገሮች የምናቀርብበት ዕድል አለን፣ ሀብት አለን፡፡ ይህንን ባማድረጋችን ሊቆጨን ይገባል፡፡ ይህ ዕድል እያመለጠን ነው፡፡ ውኃ ከመሬት ማውጣት እንችላለን፡፡ ጅረቶቻችንን መገደብ እንችላለን፡፡ ለም መሬት አለን፡፡ ይህ ሁሉ መልካም ዕድሎች እየለየን በመከራ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ለስንዴ መግዣ ማዋላችን ሊቆጨን ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ኅብረተሰብ ጉዳዩን የራሴ ነው ብሎ መነጋገር አለበት፡፡ እኔ እንዲውም ይህ ጉዳይ ፓርላማ ውስጥ መወያያ ሊሆን ይገባል እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለራሷ የሚሆን ስንዴ ማምረት እንዳለባት ቀላል ነገር ነው መባሉን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ትክክልም ነው፡፡ የቅለቱን ያህል ቢያንስ በዚህ ዓመት በስንዴና በዘይት ራስን ለመቻልና ከውጭ ላለማምጣት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን መደረግ አለበት? ዘንድሮ ባይቻል በሚቀጥለው ዓመት ለስንዴና ለዘይት የውጭ ምንዛሪ ላለማውጣት ምን ይደረግ?

አቶ ታደሰ፡- ብልኃት የታከለበት ፕሮግራም ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ማለት ቀላል፣ የሚለካ፣ በጣም የሚታይና የጊዜ ሰሌዳ ያለው ፕሮግራም ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ፕሮራም ይህንን እናደርጋለን፣ ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጉን እነዚህ ነገሮች ናቸው፣ በዚህ ዓመት እንዲህ ማድረግ እንችላለን ከተባለ፣ ዕቅዱ ወጥቶ ዕቅዱ ላይ ከተፈራረምን ይህንን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ሌላ ታሪክ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለውን ለውጥ እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ታደሰ፡- እኔ በበኩሌ ዘርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ መዋቅር ማየት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም በሐሳብና በርዕዮተ ዓለም ነው እንጂ መስማማት ያለብን፣ አንተ የእኔ ወገን ነህ ብዬ አንተን መደገፍ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ አንተ ምን ሐሳብ አለህ? ጥሩ ሐሳብ ካለህ ከሐሳብህ ጋር የምንግባባ ከሆነ ነው የምደግፍህ እንጂ፣ ከዚህ ውጪ መሆን የለበትም፡፡ መከፋፈል የለብንም፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወዘተ. የሆንከው ፈልገህ አይደለም፡፡ ምንም የምታደርገው ነገር የለም፡፡ ይህ ሳትፈልግ የሆንከው ነገር እንዳለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያን አንድ ላይ ሆነን የምናሳድግበት ጉዳዮች ላይ ከተግባባን ሁሉም ነገር ቀላል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ብዙ ነገር አለ፡፡ ዝናብ የሚዘንብባት፣ ጥሩ አየር ያላት፣ ያለ አየር ማሞቂያና ማቀዝቀዣ እንዲህ ባለው ቢሮ ውስጥ የምትቀመጥባት አገር አለችን፡፡ ናይጄሪያ ብትሄድ ያለ ኤር ኮንዲሽነር መቀመጥ አትችልም፡፡ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ልናመርት የምንችልባት አገር አለችን፡፡ ከዚህ የበለጠ ምንድነው የምንፈልገው? ሌላም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሁልጊዜ የዜግነት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን ይባላል፡፡ እርስዎም ለአገርዎ መልካም ነገር እየተመኙ ነው፡፡ ከምኞት ባለፈ እንደ አንድ ዜጋ እያደረግኩ ነው፣ ባደርገው ደግሞ ደስ ይለኛል ብለው የሚያስቡት ነገር አለ?

አቶ ታደሰ፡- እኔ እንደ ምሳሌ ልጠቅስልህ የምችለው አንድ ትልቅ ፕሮጀክት አለኝ፡፡ የራሴን ኤንጂኦ አቋቁሜያለሁ፡፡ የተወለድኩበት አካባቢ የጀመርኩት ነው፡፡ ለጊዜው ስድስት መቶ ሰዎች የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው እርሻ ላይ ነው፡፡ በዚያ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በእርሻ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ይህንን እርሻቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያመርቱበት የሚረዳ ነው፡፡ ምርጥ ዘር እናቀርብላቸዋለን፡፡ መኖ እናቀርባለን፡፡ የተሻሉ አምራቾች እንዲሆኑ እናስተምራለን፡፡ ይህንን ጅምር ለማስፋት እንሠራለን፡፡ ይህንን በማድረግ የሚገኘውን ውጤት ማየት እፈልጋለሁ፡፡