Skip to main content
x
‹‹በአንድ ክፍለ ከተማ ዓይነ ሥውር ለመሆን አፋፍ የደረሱ ሰባ ሕፃናት አጋጠሙን››

‹‹በአንድ ክፍለ ከተማ ዓይነ ሥውር ለመሆን አፋፍ የደረሱ ሰባ ሕፃናት አጋጠሙን››

አቶ ብርሃኑ በላይ፣ የቱጌዘር በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ

አቶ ብርሃኑ በላይ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው የቱጌዘር በጎ አድራጎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ቱጌዘር እ.ኤ.አ. በ2013 የተመሠረተ ሲሆን፣ የመሠረቱትም ኢትዮጵያውያንና ጀርመናውያን ናቸው፡፡ ቱጌዘር የተሰኘው የድርጅቱ ስያሜ አንድም ሁለቱ አገሮች አንድን ዓላማ ለማሳካት በአንድነት መቆማቸውን ለማሳየት በሌላ በኩል ደግሞ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው በዓይነ ሥራውን ላይ ቢሆንም ግቡን ለመምታት ከዓይናማዎች ጋር በአንድነት እንደሚሠራ ለማሳየትም ነው፡፡ አብዛኛውን የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከጀርመን ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የሆላንድ ኤምባሲም ድጎማ ያገኛል፡፡ ዓይነ ሥውር ኢትዮጵያውያን በልማት እንዲካተቱ፣ ከሌላው ዜጋ እኩል መብታቸው እንዲከበር የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውነው ድርጅቱ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት ይታወቃል፡፡ ዓይናማዎች በዓይነ ሥውራን እግር ሆነው የሚያሳልፉበት የጨለማ ውስጥ የእራት ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ ይህንን ፕሮግራም ከቀናት በፊት በቢርጋርደን  አዘጋጅተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ድርጅቱ ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ዓይነ ሥውራን ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ አጠቃላይ እንቅስቃሴውንና ዓይነ ሥውራንን በልማት ማካተትን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ብርሃኑ በላይን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በዋናነት የሚያከናውናቸው ተግባራት ምን ምን ናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡- የኛ ድርጅት የሚተገብራቸው አራት ዓይነት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው ለዓይነ ሥውራን ዜጎች አጠቃላይ የሆነ ድጋፍ የሚሰጥበት ነው፡፡ በተለይም የአቅም ግንባታ ሥራ ያከናውናል፡፡ ዓይነ ሥውራን ኮምፒውተር ለመጠቀም ይቸገራሉ፡፡ መጽሐፍ ለማንበብ ኢሜይል ለመላላክ ዓይናማዎች ካላገዟቸው ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህም መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ክህሎት እንዲኖራቸው እናስተምራቸዋለን፡፡ ያለን መደበኛው ኮምፒውተር ቢሆንም ውስጡ ስፒች ሶፍትዌር ስላለው የተመቸ ነው፡፡ በየዓመቱም 15 የሚሆኑ ዓይነ ሥውራንን እየተቀበልን የትራንስፖርት እንዳይቸገሩ እየከፈልናቸው እናሠለጥናቸዋለን፡፡ ለሴቶችም ቅድሚያ ሰጥተን እናሠለጥናለን፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ከሠለጠኑ በኋላ በየመንግሥት ትምህርት ቤቱ እንደነሱ ያሉ ዓይነ ሥውር ተማሪዎችን እንዲያሠለጥኑ ይደረጋል፡፡ ዓይነ ሥውራኑ  በኮምፒውተር ትምህርት ክፍለ ጊዜ የሚያስተምራቸው ስለሌለ ክፍል ለቀው እንዲወጡ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ግን በተወሰነ መልኩም ቢሆን የኛ ሠልጣኞች እንዲረዷቸው እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራቸው ደመወዝ እንከፍላቸዋለን፡፡ ተማሪዎቻችን አራት ጊዜ የብቃት ምዘና ፈተና ወስደው መቶ በመቶ ነው ያለፉት፡፡ በድርጅታችን ለዓይነ ሥውራን ብቻ ሳይሆን ሌላ የአካል ጉዳት ላለባቸውም የሚሆን ሪሶርስ ሴንተር አለን፡፡ እዚህ እየመጡ መጽሐፍ በኮምፒውተር አማካይነት ማግኘት፣ ኢንተርኔት መጠቀምና የተለያዩ ሥራዎችን በነፃ መሥራት ይችላሉ፡፡ እስከ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ መጻሕፍት በሶፍት ኮፒ አለን፡፡ መጻሕፍቱ ለዓይነ ሥውራን እንዲሆኑ ተደርገው በድምፅ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አሁን ያለንበት ቦታ ለአብዛኞቹ ዓይነ ሥውራን ተደራሽ ስላልሆነ ወደ ስድስት ኪሎ አካባቢ ልንወስደው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር ውስጥ ሪሶርስ ሴንተር እንድናቋቁም ተጠይቀን እያቋቋምን ነው፡፡ አፍንጮ በር አካባቢ በሚገኘው የትምህርት ቢሮ ሴንትራል ብሬል ላይብረሪ ውስጥ ዲጂታል ላይብረሪ ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ከሦስት ወራት በፊት ተፈራርመናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥልጠና ባለፈ የምታደርጉት ድጋፍ ካለ?

አቶ ብርሀኑ፡- እዚሁ ግቢያችን ውስጥ የሚገኘው የሴቶች ማረፊያ አለ፡፡ ሴቶች ዓይነ ሥውር ስለሆኑ ብቻ ለተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ በሚደርስባቸው ጥቃት ከትምህርት የሚቀሩ ብዙ አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሴቶችን እየተቀበልን በግቢያችን ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ከእኛ ዘንድ  በሚቆዩበት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ፣ ያቆሙትን ትምህርት እንዲቀጥሉ እናደርጋለን፡፡ የኮሌጅ ትምህርት ጨርሰው ሥራ እንዲይዙ ያደረግናቸውም አሉ፡፡ ዘንድሮ ሁለት ሴቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ አልፈውልናል፡፡ አራቱ ደግሞ ከአሥረኛ ወደ 11ኛ ክፍል ተዛውረዋል፡፡ እስካሁን በአራት ዙር ከ25 የሚበልጡ ሴቶችን በዚህ መልኩ ረድተናል፡፡ በማዕከላችን ብዙ ሴቶችን መቀበል አንችልም፡፡ ከማኅበረ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ (ሳይኮ ሶሻል ሰፖርት) ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች የሚያስፈልጋቸው ስለሆነ ለበርካቶች በአንዴ ድጋ ለማድረግ የአቅም ውስንነት አለብን፡፡  ሌላ ልጆቻቸውን ይዘው የሚገቡም አሉ፡፡ ድጋፍ የምናደርገው ለልጆቻቸው ጭምር ነው፡፡ የሕፃናት ማቆያ ስላለን አስፈላጊው እንክብካቤ ያገኛሉ፡፡ በማዕከሉ የማይኖሩ ዓይነ ሥውር ሴቶች ቢሆኑም ልጆቻቸውን ይዘው ለልመና እንዳይዳረጉ እኛ ጋ እያስቀመጧቸው ወደ ሥራ እንዲሄዱ እናደርጋለን፡፡ እዚህ ተቀምጠው እንዲማሩ የሚደረጉ ሴቶች ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የመቋቋሚያ ገንዘብና በየወሩ ደግሞ እንደየደረጃው ከ1,000 እስከ 1,500 ብር እንደጉማቸዋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዓይነ ሥውር ሴቶች ከሌላው በተለየ ምን ያህል ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡- ከኛ የሚመጡት አደጋው ከደረሰባቸው በኋላ ነው፡፡ የምንቀበለውም ሠራተኛ ማኅበራዊ ጉዳይ የሚልክልንን እንዲሁም እኛ በራሳችን ጎዳና ላይ ሲለምኑ የምናገኛቸውን ነው፡፡ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሴቶቹን መልምሎ በመስጠት ረገድ በጣም ይተባበረናል፡፡ ዓይነ ሥውር ሴቶች ለፆታዊ ጥቃት ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው ስንል ከሚያጋጥሙ ገዳዮች በመነሳት ነው፡፡ መንገድ ላይ የሚያገኟቸው እንምራችሁ ብለው ወደ ሌላ ቦታ እየመሩ ወስደው ይደፍሯቸዋል፡፡ እኛ ባደረግነው ጥናት ደግሞ ሽሮሜዳ አካባቢ ቤት ተከራይተው የሚያስቀመጧቸውና እንደፈለጉ የሚገናኟቸው ሲያሻቸውም የሚደፍሯቸው ወንዶች  አሉ፡፡ ከኛ ያሉት ግን ተማሪ የነበሩ ነገር ግን ተደፍረው የልጅ እናት የሆኑና ትምህርታቸውን ያቋረጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ ይገኝባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓይነ ሥውራንን በሥራ እንዲሳተፉ ድርጅታችሁ ምን ይሠራል?

አቶ ብርሃኑ፡- ዓይነ ሥውራን ዓይነ ሥውር በመሆናቸው ምክንያት ሥራ አያገኙም፡፡ ስለዚህም የኛ ድርጅት የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆኑ ዓይነ ሥውራውንን እየተከታተለ ሥራ ያስይዛል፡፡ ይህንን የምንሠራው ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር እየተዋዋልን ነው፡፡ ትምህርት ቢሮን አነጋግረን ሰሞኑን 21 ዓይነ ሥውራን ወደ ማስተማሩ ሥራ አስገብተናል፡፡ ዓይነ ሥውራን ትምህርት ቢኖራቸውም ማየት ስለማይችሉ የተለያዩ አድሎዎች ይደረጉባቸዋል፡፡ በቂ ድጋፍ ከተደረገላቸው መሥራት ይችላሉ እያልን የማሳመን ሥራ እየሠራን እስካሁን በርካቶች ወደ ሥራ ዓለም እንዲገቡ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- መሥራት ይችላሉ ብሎ የማሳመን ሥራው ምን ያህል ከባድ ነው?

አቶ ብርሃኑ፡- አራተኛው ፕሮጀክታችን የሚመጣው እዚህ ጋ ነው፡፡ ኢቨንት ኤንድ ኢንካውንተርስ የምንለው ይህ ፕሮጀክት ዓይነ ሥውራን መሥራት እንቸሚችሉ ግንዛቤ መፍጠር የሚቻልባቸውን ፕሮግራሞች ያዘጋጃል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ያዘጋጀነው በዓይነ ሥውራን አስተናጋጅነት የቀረበው የጨለማ ውስጥ የእራት ዝግጅት የዚህ አካል ነው፡፡ በሌላው ዓለም ዓይነ ስውራን በዚህ ሙያ ተሰማርተው ሬስቶራንት ይከፍታሉ፡፡ እኛ ግን እዚህ የምናዘጋጀው ዓይነ ሥውራን ጥቂት ዕርዳታ ከተደረገላቸው መሥራት እንደሚችሉ ለማሳየት ነው፡፡ የእራት ፕሮግራም እያዘጋጀን በጨለማ ክፍል ውስጥ በዓይነ ሥውራን አስተናጋጅነት ሲስተናገዱ ያላቸውን አመለካከት ይቀይራል፡፡ ተመግበው ሲወጡ በቂ ግንዛቤ አልነበረንም፣ አሁን መረዳት ችለናል የሚሉንና የኛ ወዳጆች የሚሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ዓይነ ሥውራን በፋሽን መድረኮች በመሳተፍ፣ ሙዚቃ በመጫወት ምንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ እኛ የራሳችን የሙዚቃ ቡድን አለን፡፡ የኛ ልጆች በብሔራዊ ቴአትርና በተለያዩ መድረኮች ሥራቸውን በማቅረብ አድናቆት አግኝተዋል፤ እስከ ጂቡቲ ድረስም ተጋብዘዋል፡፡ ይኼ ራሱ ሌላ ግንዛቤ መፍጠሪያ መንገድ ነው፡፡ በእኛ ግቢ ውስጥ የሚገኙ ዓይነ ሥውራን የሠሯቸውን የተለያዩ ምርቶች፣ ሥዕሎች እንሸጣለን፡፡ እግረ መንዱንም መሥራት እንደሚችሉ የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ መቅጠር የሚችሉ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በየፕሮግራሞቻችን እየጋበዝን መሥራት እንደሚችሉ እናሳያለን፡፡ አሁን ብዙ የግንዛቤ ለውጥ መፍጠር ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓይነ ሥውራንን የመቅጠር ፍላጎት ያላቸው ጥቂት የመንግሥት ድርጅቶች እንጂ የግል ድርጅቶች አለመሆናቸው ይወሳል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ብርሃኑ፡- ልክ ነው የግል ድርጅቶች ዘንድ ችግር አለ፡፡ ነገር ግን ያለውን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ ትግል እያደረግን ነው፡፡ ለውጥም እያየን ነው፡፡ ለምሳሌ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አካባቢ ዓይነ ሥውራንን በምርት ሥራ ላይ የሚያሠለጥን ድርጅት አለ፡፡ የኛ ልጆችን ተቀብለው እንዲያሠለጥኑ፣ በሠራተኛነትም እንዲቀበሏቸው አድርገናል፡፡ የአገር ጥበብ የሚባል ሌላ ዓይነ ሥውራንን የሚቀበል በምንጣፍ ሥራ የተሰማራ ድርጅትም አለ፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ዘርፎች የተሰማሩ ድርጅቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በአብዛኛው በክፍለ ከተማዎች ላይ የሥራ ቅጥሮች ሲወጡ የእኛ ልጆች እያስቀጠርን ነው፡፡ ኮምፒውተር ሲማሩ የነበሩ የሕግ፣ የሶሾሎጂ ምሩቃንና በሌሎችም የትምህርት አይነቶች የተመረቁትንም በመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ እንዲቀጠሩ እያደረግን ነው፡፡ በምናዘጋጃቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ መቅጠር የሚችሉ የመንግሥት አካላትና ግለሰቦች እንዲገኙ በማድረግ ያለውን ክፍተት በተቻለን መጠን ለማጥበብ እንጥራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች በጥቅሉ ምን ያህል ለዓይነ ሥውራን ተደራሽ ናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡-  በእኛ አገር በጣም ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ በውጭ አገር የተለያዩ ድርጅቶች ዓይነ ሥውራንን እንዲቀጥሩ መንግሥት ያስገድዳል፣ የሚገለገሉበትን ኮምፒውተርም ይሰጣል፡፡ የሚሰጠው ኮምፒውተር አንድ ሰው አስቀጠረ ማለት ነው፡፡ እኛ አገር እንደዚህ ዓይነት አሠራር የለም፡፡ እኛ ቱጌዘሮች እየሞከርነው ያለ ከባለድርሻ ድርጅቶች ጋር የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ ይኸውም በአዲስ አበባ ላይ ብቻ የተወሰኑ አገልግሎቶች ወደ ክልሎችም እንዲደርሱ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ዓይነ ሥውራን አሉ፡፡ አብዛኞቹ ትምህርት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ ቢመጡም የሚማሩበት ብሬይል በበቂ ስለማያገኙ፣ የሚያነብላቸውም ሰው ስለማይኖር ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ይህንን ችግር በመጠኑም ቢሆን ሊቀርፉ የሚችሉ ከጀርመን ላይፕዚንግ ከተማ ኅዳር ላይ የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ሰዎቹ ለዓይነ ሥውራን ተማሪዎች ትምህርት ለማዳረስ የሚረዳ ፕሮግራም ለማስጀመር የሚመጡ ሲሆን፣ ስቱዲዮ እንድናቋቁም ይረዱናል፡፡ መጻሕፍትን በድምፅ የምታዘጋጅልን አንዲት ሴትም  ትመጣለች፡፡ አስፈላጊውን ሥልጠናም ትሰጠናለች፡፡ ይህም በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ ወደፊት መንግሥት ሊያስብበት የሚገባና እየሞከረ ያለው ነገርም አለ፡፡ ትምህርት ቢሮ ከእኛ ጋር በመሆን መጻሕፍትን በማዕከላዊ የብሬይል ላይብረሪ ዳውንሎድ አድርገው በድምፅ ማድመጥ የሚችሉበትን ሁኔታም ለማመቻቸት እየሞከርን ነው፡፡ እኛ መሥራት የምንችለው በአዲስ አበባ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን እስከ ሰበታ ለመድረስ ሞክረናል፡፡ በሰበታ የዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት አለ፡፡ ለትምህርት እንዲረዳቸው ኮምፒውተር እንሰጣለን፡፡ በልዩ ፕሮግራሞች ሌሎች አካባቢዎችን ለመድረስ እንሞክራለን፡፡ ነገር ግን እስካሁን አዲስ አበባና ዙሪያዋን እንጂ ሌሎች አካባቢዎችን መድረስ አልቻልንም፡፡ በመንግሥትም በኩል ተሠርቷል የሚባል ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- አሉ የሚባሉ የተደራሽነት ችግሮችን በቴክኖሎጂ የመፍታት ነገርስ ምን ያህል ነው?

አቶ ብርሃኑ፡- በአገራችን አልተለመደም ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ በነጭ ብትር እየተመራሁ ያለፍኩበት መንገድ ነገ ተቆፍሮ ሊጠብቀኝ ይችላል፡፡ ተናቦ የመሥራት ነገር የለም፡፡ ዓይነ ሥውራን ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ገደል ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የእኛ ድርጅት ባለድርሻ አካላትን አንድ ላይ በማምጣት ላለው ችግር ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በብትር እየተመሩ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን አሽከርካሪዎች ሲያዩ ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ የትምህርታቸው አንድ አካል እንዲሆን ሐሳብ አንስተናል፡፡ በመንገዶች ላይ ስለሚደረጉ ቁፋሮዎችም እንደዚሁ ተወያይተናል፡፡ መንገድ ሲሠራ ዓይነ ሥውራን የሚያውቁባቸው መንገዶች ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ በውጭ አገሮች ዓይነ ሥውር መንገደኞች በድምፅ በመታገዝ ነው መንገድ የሚሻገሩት፡፡ በኛ ግን ይህ የለም፡፡ በአጠቃላይ ከቴክኖሎጂ አኳያ አብዛኛው ነገር ተደራሽ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓይን ጤና ምን ያህል ትኩረት ይሰጣል?

አቶ ብርሃኑ፡- በየክፍለ ከተማው እየሄድን ስለዓይነ ሥውርነት ገለጻ እንሰጣለን፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዓይነ ሥውር ለመሆን አፋፍ የደረሱ 70 ሕፃናት አጋጠሙን፡፡ ወላጆቻቸው ‹‹ዕርዱን ልጆቻችን እያዩ የሚያዩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፣ ለማሳከም አቅም የለንም አሉን፡፡›› እኛ በድርጅታችን ሜዲካል ሚሽን (የሕክምና ልዑካን) የሚባል በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች ያሉት ቡድን አቋቁመናል፡፡ ሰባዎቹ ልጆችም እንዲታከሙ የተደረገው ቡድኑን በመጠቀም ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር የኛ ፕሮግራም አይደለም፤ እያየን ግን ማለፍ አንችልም፡፡ በኛ አገር ለዓይን ጤና ብዙም ቦታ የተሰጠው አይመስልም፡፡ በንፅህና ችግር የሚያጋጥሙ ሕመሞች ቀላል አይደሉም፡፡ ከታመሙ በኋላ በቀላል ሕክምና መዳን ሲቻል አደገኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ይሆናል፡፡ የግንዛቤ ማነስና ቸልተኝነት ነው ዋናው ችግር፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ያሉበት ችግሮች ምን ምን ናቸው?

አቶ ብርሃኑ፡- ቱጌዘር ከተቋቋመ ስድስት ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩትን ደርሷል፡፡ ትልቁ ችግሩ ቤት ነው፡፡ በየወሩ 69,000 ብር ለቤት ኪራይ እንከፍላለን፡፡ ቦታውም ለዓይነ ሥውራን የተመቸ አይደለም፡፡ ግቢው በቂያችንም አይደለም፡፡ መጠለያው እዚሁ ነው፡፡ የልጆች ማቆያ፣ ኮምፒውተር መማሪያ ሁሉ እዚሁ ስለሆነ የመረባበሽ ነገርም አለው፡፡