Skip to main content
x
ታላቅ አገር ለመገንባት ታላቅ አስተሳሰብ ያስፈልጋል!

ታላቅ አገር ለመገንባት ታላቅ አስተሳሰብ ያስፈልጋል!

ታዋቂዋ ዲፕሎማት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ የሴት ፕሬዚዳንት ተደርገው ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሾሙ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ታላቅ አገር የመገንባት ህልምን ዕውን ለማድረግ ከሰላም ውጪ ምንም አቋራጭም ሆነ አማራጭ የለም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ሰላማችንን አጥብቀን እንድንጠብቅ፣ ከሁሉም በላይ ሰላም ሲታወክ በምትጎዳው እናት ስም እጠይቃለሁ፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በመጀመርያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለዚህ ታሪካዊ ኃላፊነት በቅተው አገራቸውን ለበርካታ ዓመታት ካገለገሉበት ዲፕሎማነት በተጨማሪ፣ በርዕሰ ብሔርነት ለማገልገል በመመረጣቸው እንኳን ደስ ያለዎት እያልን፣ የተጣለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት በስኬት እንዲወጡ ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡ በተጨማሪም ላለፉት አምስት ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት አገልግለው በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትንና ለበርካታ ዓመታት አገራቸውን በተለያዩ ኃላፊነቶች በትጋት ያገለገሉትን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ  (ዶ/ር)፣ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያመሠገንን መልካሙን ሁሉ እንመኝላቸዋለን፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን መሆን የሚችሉት ለታላቅ አገር ግንባታ ታላቅ አስተሳሰብ መጎናፀፍ ሲቻል በመሆኑ፣ ይህንን የሥልጣን ሽግግር እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ በአፍሪካና በመላው ዓለም መነጋገሪያ የሆነው ይህ የሥልጣን ሽግግር ሰላም ምን ያህል ትልቅ ዋጋ እንዳለው አመላካች ነው፡፡ ታላቅ የመሆን ህልምም የሚሳካው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ታላቅ አገር ናት፡፡ ሰላሳ ሚሊዮን ያህል ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙባት ታላቅ አገር ስትሆን፣ በየዓመቱ 200 ሺሕ ያህል ወጣቶች ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይመረቃሉ፡፡ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አማካይነት ሥርዓተ ትምህርቱ ተስተካክሎ ብቁና ተወዳዳሪ ተመራቂዎች ማፍራት ሲቻል፣ ኢትዮጵያ የምርምር አገር በመሆን የቴክኖሎጂ በረከቶችን በቀላሉ በመቋደስ ከድህነትና ከኋላቀርነት በፍጥነት የመላቀቅ ተስፋ አላት፡፡ ይህ በወጣቶች ላይ የሚጣል ተስፋ ዕውን የሚሆነው ግን ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ደግሞ ለአገር የሚያስቡ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ኃይሎችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች፣ በብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መስማማት አለባቸው፡፡ ይህ ስምምነት የሚያስፈልገው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር የሚረዳ የፖለቲካ ዓውድ ለማደላደል ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍ ዓውድ ሰላም ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዳበረ አስተሳሰብ ውጤት የሆነ ዴሞክራሲያዊነትን መላበስ ይጠይቃል፡፡ ሰላምን በአስተማማኝነት ማስፈን የሚቻለውም፣ ከአድልኦ የፀዳ ከባቢ መፍጠር የሚያስችል የዳበረ አስተሳሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በሴቶችም ሆነ በወንዶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ከተመራ፣ ኢትዮጵያ ከድህነትና ከኋላቀርነት ተላቃ ወደ ብልፅግና ጎዳና እንደምታመራ ጠቁመዋል፡፡ የለውጥ ጉዞው ውስብስብና በርካታ ፈተናዎች ያሉበት እንደሚሆን ይጠበቃል ብለው፣ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ ቤት እንደሚገነባ ቤተሰብ እርስ በርስ በመደማመጥ፣ በመፈቃቀድ፣ በመተሳሰብና አንድነትን በማጠናከር ፈተናዎችን መሻገር እንደሚያስፈልግ በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ባሳለፉት የዲፕሎማሲ ልምዳቸው የብዙ አገሮችን የግጭትና የውድመት ታሪክ የሚያውቁት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ለሰላም ትልቅ አፅንኦት የሰጡት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ‹‹የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የሥልጣኔ ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ ድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ እንድትቆይ ያደረጋት የሰላም ዕጦት ነው፤›› ሲሉም የዘመናት የአገር ፈተናን አስታውሰዋል፡፡ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን ወሳኝነት አውስተዋል፡፡ መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ ሥር እንዲሰድ በኃላፊነት እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚል ማንኛውም ዜጋ ይህንን መልዕክት በአንክሮ ሊረዳው ይገባል፡፡ አገር የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ስለሆነ፡፡

የአገር ባለቤት ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ኃይሎች ለሕዝብ ፈቃድ መገዛት አለባቸው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚያዋጣው የሕዝብን ፍላጎት ተከትሎ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ነው፡፡ በተለይ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ ከውጭ የገቡም ሆነ አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ስብስቦች ለሰላም ትልቅ ቦታ መስጠት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስፈልገው ከሴራና ከአሻጥር የፀዳ የዳበረ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አምባነገንነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን የሚፀየፍ ሲሆን፣ ለሕግ የበላይነትና ለእኩልነት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ፍትሐዊ የሆነ የሰጥቶ መቀበል ግንኙነት እንዲኖር ይሠራል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች በገለልተኝነት የሚሠሩበት ምኅዳር ያመቻቻል፡፡ የፍርድ ቤቶች ነፃነት እንዲሰፍን ይታገላል፡፡ ሕገወጥና ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ የድርሻውን ይወጣል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ እንዲውልና በአጠቃላይ ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ ዴሞክራሲያዊ አሠራሮች እንዲሰፍኑም ይረባረባል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ሰላም አስተማማኝና ዘለቄታዊ ሆኖ አገርን ታላቅ ማድረግ ይቻላል፡፡

ዘወትር እንደምንለው የአገር ህልውና ለድርድር አይቀርብም፡፡ ማንኛውም ግሰለብ ሆነ የፖለቲካ ቡድን ከአገር በታች እንጂ በላይ አይደለም፡፡ ይህንን በመዘንጋት መኮፈስ ወይም እያወቁ እንዳላወቁ መሆን የዴሞክራትነት ባህሪ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን መገኘት ያለበት በሉዓላዊ ባለቤቱ የሕዝብ ድምፅ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ በጉልበት በማስፈራራት ሥልጣን መያዝ ዘመን ያለፈበት ኋላቀርነት ሲሆን፣ በዚህ መንገድ ሥልጣን ለመጨበጥ የሚያስቡ ካሉ የሚላተሙት ከሕዝብ ጋር እንደሆነ ማወቅ አለባቸው፡፡ አምባገነንነት ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ ጠመንጃ ካሁን በኋላ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት እንዳለበት፣ ሕዝብ በአደባባይ ፍላጎቱን በማሳወቅ አስጠንቅቋል፡፡ በጠመንጃ የሚመራ ወይም በሴራና በአሻጥር የሚዘወር ፖለቲካ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ አይመጥንም፡፡ ሥልጣን ከምርጫ ሳጥን እንጂ በአሻጥር ወይም በጉልበት ማግኘት እንደማይቻል መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ይህ መተማመን ወደ ውይይትና ድርድር እያደገ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሥራ ውስጥ መገባት አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ሰላም ይሰፍናል፡፡ የታላቅ አገር ግንባታ ፕሮጀክት ይጀመራል፡፡

‹‹ሰላም ለራስ፣ ሰላም ለጎረቤት፣ ሰላም ለመንደር፣ ሰላም ለወረዳዎች፣ ሰላም ለአገር በአጠቃላይ፣ ሰላም ለጎረቤት አገሮችና ለዳያስፖራዎች ይሁን፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹ሰላም ለማስፈን ትኩረት አደርጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ታላቅ ሐሳብ ዕውን ለማድረግ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የትምህርት ተቋማት፣ የሙያና የሲቪል ማኅበራትና በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ አገር የውርደት መገለጫ ከሆነው ተመፅዋችነት ወጥታ ወደ ብልፅግና መገስገስ የምትችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲያዊነት የምትሸጋረው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም ትልቅ ዋጋ ያለው ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ግን ሞትና ውድመት ይቀጥላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አዘቅት ውስጥ መግባት ለማንም አይጠቅምም፡፡ ይልቁንም ሁሉንም በእኩልነትና በፍትሐዊነት የምታስተናግድ የጋራ ታላቅ አገር ለመገንባት ታላቅ አስተሳሰብ ይዞ መነሳት የጊዜው ዋነኛ ጥያቄ ነው!