Skip to main content
x
አገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስና የጀግኒት ፕሮግራም በይፋ ይጀመራል

አገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስና የጀግኒት ፕሮግራም በይፋ ይጀመራል

ሴቶች በሰላምና በልማት ዘርፎች የሚወጡትን ሚናና አበርክቶ ለማጉላትና በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለመዱትን አላስፈላጊ አመለካከቶች፣ አስተሳሰቦችና ተግባራት ለመለወጥ አገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስና ጀግኒት የሚል የማኅበረሰብ ንቅናቄ ፕሮግራም በይፋ ይጀመራል፡፡

በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ረዳት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሴቶች እንደ ሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ሚና የሚያጎላና በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችን ለመፍታት ተፅዕኖ ያለው ሥራ እንዲያከናውኑ በየክልሉ ባሉ መዋቅሮች በተዘረጋው አሠራር የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

ሴቶች በልማቱና በሰላም ያላቸው ሚና ትልቅ ቢሆንም ይህ ጎልቶ የሚታይ ባለመሆኑ ይህንን አመለካከት ለመቀየርና በሰላም መንገሥ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ለማጉላት አገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በወቅታዊ ግጭቶች ምክንያት የሚከሰቱ መፈናቅሎችና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች የሚኖራቸውን ሚና የሚያጎለብት የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ኮንፍረንስ መዘጋጀቱን አስመልክቶ አሥሩ ሴት ሚኒስትሮች ትላንት በሂልተን አዲስ አበባ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር በሚዘጋጀውና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በይፋ በሚጀመረው የሴቶች ሰላም ኮንፍረንስና ጀግኒት ፕሮግራም ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኛሉ ተብሏል፡፡