Skip to main content
x
‹‹የተፈጥሮ ሀብት ችግር ሳይሆን የአመራር እርግማን ነው ያለው›› አቶ ሙስጠፋ ኡመር መሐመድ፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

‹‹የተፈጥሮ ሀብት ችግር ሳይሆን የአመራር እርግማን ነው ያለው›› አቶ ሙስጠፋ ኡመር መሐመድ፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

አቶ ሙስጠፋ ኡመር መሐመድ በቅርቡ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው መሰየማቸው ይታወሳል፡፡ ከክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ 175 ኪሎ ሜትር ያህል በምትርቀው ደገሃቡር በ1966 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ሙስጠፋ፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደገሃቡር የተማሩ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ሐረር በሚገኘው መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ወደ ሥራው መስክ በመሰማራት፣ በተለይም በትምህርት ቢሮ በኤክስፐርትነት ጀምረው ምትክል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም ሴቭ ዘ ቺልድረንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ የሥራ መስኮች አገልግለዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም. ከአገር የተሰደዱት አቶ ሙስጠፋ እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ (የእርሻ ምጣኔ ሀብት) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊትም ለ11 ዓመታት ያህል በተለይ ከሰብዓዊ ዕርዳታ ጋር በሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (UNOCHA) ሠራተኛ በመሆን በዚምባብዌ፣ በኬንያ፣ በሶማሊያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የሚያደርሱትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም በርካታ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ አሁን ክልሉ ስለሚገኙበት የፀጥታ ሁኔታ፣ አጠቃላይ አገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችንና እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት በክልሉ በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ በዋና ከተማዋ ጅግጅጋ የተለያዩ የፀጥታና የፖለቲካ ችግሮች ካጋጠሙና በክልሉም ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን በክልሉ ያለው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ምን ይመስላል?

አቶ ሙስጠፋ፡- ይጠበቅ ከነበረው በተቃራኒ መንገድ በክልሉ በአሁን ወቅት ያለው የፀጥታና የሰላም ሁኔታ የተረጋጋ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ከተፈጠሩት ችግሮች አንፃር ሲጠበቅ የነበረው ክልሉን ማስተዳደር ከባድና አስቸጋሪ ሥራ እንደሚሆን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን የክልሉ ፀጥታ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተረጋጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት በክልሉ ያለው የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ነው፡፡ ከክልል እስከ ወረዳ ደረጃ የሚደርሰው የጎሳዎች እንቅስቃሴም ከጎናችን መቆማቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያከናወንነው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አሳታፊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኅብረተሰቡ ላይ ውሳኔ ከመጫን ባለፈ ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መንገድ መከወን ትንሽ አስቸጋሪ፣ እንዲሁም የሚያለፋ ነው፡፡ ነገር ግን የኅብረተሰቡ ስሜት ምን እንደሆነ ስለምናውቅ የፖለቲካ ዕርምጃችንን የጀመርነው ከጎሳ መሪዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙ ልሂቃን ጋር ሰፋፊ ውይይቶችን በማድረግ ነው፡፡ ይህ ሒደት እርግጥ ነው የተወሰነ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ ነገር ግን ከተገኘው ውጤት አንፃር ውጤቱ አስደሳች ከመሆኑም በላይ ክልሉን የተረጋጋ አድርጎታል፡፡

ሪፖርተር፡- በሐምሌ ወር መጨረሻ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ በክልሉ የሚገኙ የሌሎች ብሔር አባላት የግድያ ወንጀል የተፈጸመ ሲሆን፣ አብያተ ክርስቲያንን ጨምሮ የበርካታ ዜጎች ንብረት ላይ ውድመት ገጥሞ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የነበረው ሁኔታ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች እጅግ አስፈሪ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አሁን ምን ያህል የተረጋጋ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ሙስጠፋ፡- ከዚህ አንፃር ስንመለከተው የመጀመርያ ሥራችን የነበረው ግጭቱን ማስቆምና ቀጣይ ግጭቶች እንዳይከሰቱ ማረጋገጥ ነበር፡፡ ይህንንም ማሳካት ችለናል፡፡ በክልሉ የሚገኙ የሌሎች ብሔር ተወላጆችን፣ እንዲሁም በጎሳዎች መካከል ያለውን ትስስር በተመለከተ ደግሞ በአንድ ጀንበር የሚያልቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ለማስተካከል እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ የመጀመርያው እንቅስቃሴ ደግሞ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭትና ብጥብጥ መሠረታዊ ምክንያት መለየት ነው፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ተፈጥሮ የነበረው የብሔሮች ጥቃት ምክንያቱ ያን ያህል ሥር የሰደደ አልነበረም፡፡ አብዛኛው የጥቃቱ መንስዔ ፖለቲካዊ ምክንያት የነበረው ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ጊዜ ግጭት ካጋጠመ በኋላ የተለያዩ የድንጋጤና ያለመረጋጋት ስሜቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህንም ለመቆጣጠርና ለማስተካከል እየሠራን ነው፡፡ እነዚህንም ነገሮች በሦስት ዋና ዋና መንገዶች እያስተካከልናቸው እንገኛለን፡፡ የመጀመርያው ሕዝቡን ማወያየትና ማረጋጋት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከሶማሌም ሆነ ከሌሎች ብሔር ተወላጆች፣ እንዲሁም ከጎሳ መሪዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይቶችና ምክክሮች አከናውነናል፡፡ በነገራችን ላይ በሶማሌዎችና በሌሎች ብሔሮች መካከል የተሰተው ግጭት የአጠቃላይ ግጭቱ ትንሹ ክፍል ነው፡፡ ክልሉን ሲያስተዳደር በነበረው የቀድሞ አመራር በሚከተለው የሸፍጥ ፖለቲካ የተነሳ በጎሳዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ነበር፡፡ በክልሉ በሚገኙ ወደ 20 የሚደርሱ ሥፍራዎች የጎሳ ግጭት ሊቀሰቀስ ጫፍ ደርሶ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ያ ሁኔታ ለእኛ እጅግ አሳሳቢው ነገር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው የጅግጅጋ ሁኔታ ሕግና ሥርዓትን ወደነበረበት የመመለስ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህንንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ማሳካት ችለናል፡፡ አሁን ለተጎጂዎች በቂ የሆነ ዕርዳታ ማድረስና ጥቃት የደረሰባቸው በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሔሮች አባላት ላይ ጥቃት የተፈጸመው ሶማሌዎች ስለሚጠሏቸው ሳይሆን፣ በክልሉ የነበረው አስተዳደር ሶማሌዎችንም ጭምር ሲገድል መቆየቱንና ግድያው ወደ እነርሱ መሸጋገሩን ማረጋገጥ ነበር፡፡ በእርግጥ በርካታ ሶማሌዎች በቀድሞ አስተዳደር ላይ የተለያዩ ቅሬታዎችን ያሰሙ ነበር፡፡ የቀድሞው አስተዳደር በ11 ዓመታት ቆይታው ወደ አሥር ሺሕ ያህል ሶማሌዎች እንዲገደሉ፣ በርካታ ሴቶች ተገደው እንዲደፈሩ፣ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከክልሉ እንዲሰደዱ ምክንያት ነበር፡፡     

ሪፖርተር፡- የክልሉን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በቅርብ የሚከታተሉ በርካታ የፖለቲካ አስተያየት ሰጪዎችና ፖለቲከኞች በክልሉ ተከስቶ የነበረው ግጭት ፖለቲካዊ ምክንያት አለው ይላሉ፡፡ እርስዎም ከላይ እንደገለጹት የክልሉ ፀጥታ ችግር መንስዔው ፖለቲካዊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መንስዔው ይህ እንደሆነ ከታወቀ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ምን እየሠሩ ነው?

አቶ ሙስጠፋ፡- እርግጥ ነው ፖለቲካዊ መንስዔ አላቸው ሲባል ከፖለቲካዊ ችግሮች የተለየ እንደሆነ ማየት አለብን፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የተወሰኑት መፍትሔ አግኝተዋል፣ የተወሰኑ ደግሞ ገና አልተፈቱም፡፡ እነዚህ ሁሉ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ይፈልጋሉ፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደርን ለምሳሌ ብንወስድ፣ በሶማሌ ክልል ያሉ ሰዎች እውነተኛ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ጥያቄ በተለያዩ ተፅዕኖዎች፣ እንዲሁም ከክልሉ ውጪ ባሉ የመቆጣጠርያ መንገዶች ለክልሉ ሕዝብ ተነፍጎት የነበረ ነው፡፡ በፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል፣ በብሔራዊ ደረጃ ስለሚገኝ ውክልና፣ እንዲሁም የክልሉ ነዋሪዎች ከብሔራዊ የሀብት መጠን ላይ ድርሻቸውን የመጋራት ጥያቄዎች እውነተኛና ሕጋዊ የሕዝባችን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች ለግጭትና አለመረጋጋት መነሻ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ስለዚህ በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ሳቢያ የሚነሱ ግጭቶች ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የክልላችን ነዋሪዎች ጥያቄን በተመለከተ ጥያቄዎቹ በዋነኛነት የነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የዴሞክራሲ መጎልበት፣ እንዲሁም የዜግነት መብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ከቻልን በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ አገኙ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ጥያቄውን ከሚገባው በላይ አናወሳስበው፣ የሕዝቡ ጥያቄ በጣም ቀላል ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ እንዲሁም ከመንግሥት የሚፈልጉትን አገልግሎቶች መገኘታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡       

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከብሔር ጋር የተያያዙ በርካታ ግጭቶ እየተከሰቱ ነው፡፡ ዜጎች ባላቸው የብሔር ማንነት ሳቢያ ለዓመታት ከኖሩባቸው የመኖሪያ ሥፍራዎች የመባረር ዕጣ እየገጠማቸው፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ቀላል ነው ማለት ይቻላል? የተወሳሰበ ጥያቄ አይመስልዎትም?

አቶ ሙስጠፋ፡- ለጭቆና፣ እንዲሁም የሕዝቦችን የራስ በራስ መተዳደር መብት እንዲገደብ እየተሟገትክ ነው?

ሪፖርተር፡- በፍፁም፡፡ ለጭቆና እንዲሁም ሕዝቦች ራሳቸውን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲገደብ እየተሟገትኩ አይደለም፡፡ ወደፊትም አልሟገትም፡፡

አቶ ሙስጠፋ፡- እያልኩህ ያለሁት ነገር ፍፁም አምባገነን ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ የሽግግር ሒደት ውስጥ ከላይ የጠቀስካቸው ነገሮች መፈጠራቸው ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ወቅት መንገራገጭ ሊያጋጥም ይችላል፡፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ የሽሽግሩ ሒደት ዘለቄታዊ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ የሚፈጠር አለመረጋጋት እንደሆነ ማየት ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የምትመለከተው ነገርም ከጭቆና ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር ወቅት የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ውጤት ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄው እነዚህ ነገሮች በአግባቡ ተይዘዋል ወይ የሚለው ነው፡፡ ምናልባት ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ደግሞ የተለያዩ ክልሎች በተለያየ መንገድ እየፈቱት ነው፡፡ ነገር ግን ዋነኛው የመፍትሔ መንገድ የዜጎች የቡድንና የግለሰብ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ እንደምረዳው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ነው፡፡ ለጊዜው ለድርድር የቀረበ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ስህተት አለ የሚል ስሜት ካለ፣ መፍትሔው ይህንን በመገደብ ወይም የክልሎችን ሥልጣን በመቁረጥ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥቱና የፖለቲካ ፕሮጀክቱ ላይ መወያየት ነው የሚሆነው፡፡ ክልሎች ያላቸው ሥልጣን ላይ ብቻ ከማተኮር ጉዳዩን ጥቅል በሆነ መንገድ ብንመለከተው የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብትን አያያዝ አስመልክቶ የክልሉ ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ ሲፈጸሙ ስለነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በርካታ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የክልሉን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል ምን ያህል ቁርጠኛ ነዎት? ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት ያለዎት ፈቃደኛነት ምን ያህል ነው?

አቶ ሙስጠፋ፡- ወደ ክልሉ የአመራር ኃላፊነት ካመጡኝ አንደኛው ምክንያት ከሰብዓዊ መብቶች መከበር ጋር ያለኝ የግል ታሪኬ ነው፡፡ ስለሆነም በክልሉ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ከሚገፋፉኝ ዓበይት ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡ የክልሉ ነዋሪዎች የሰብዓዊ መብቶችን ካለማጣጣማቸውም በላይ፣ ከፍተኛ በሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሰለባ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበራቸውን ከማረጋገጥ አንፃር ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት የነበሩ ጉዳዮችን አስመልክቶ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች እየወሰድን ነው፡፡ ለምሳሌ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ጋር በቅርቡ የሰላም ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ ግንባሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን የተስማማ ሲሆን፣ በክልሉ ላይ በጠላትነት ላለመተያየት የጋራ ስምምነት ፈጽመናል፡፡ ይህ በራሱ በክልሉ ሲታዩ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከማረቅ አንፃር ከፍተኛ እመርታ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ከፍተኛ ሥራዎች እያከናወንን እንገኛለን፡፡ በዚህም መሠረት የፍትሕ ሥርዓቱ በሥርዓት እንዲያገለግል፣ እንዲሁም ዜጎች ፍትሕ የሚያገኙበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ በፖለቲካው መስክም ከዚህ ቀደም ለአፈናና ለመልሶ ማጥቃት መነሻ የሆኑትን መሠረታዊ ምክንያቶች ለመፍታት እየሞከርን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ለኦብነግ ጉዳይ መፍትሔ ሰጥተናል፡፡ እርግጥ ነው በክልላችን የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ሁኔታ የከፋ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ጥሰቱን ወደ ፊት ለማምጣትና ለማጋለጥ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው አስተዳደር ዝግ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ይከሰቱ የነበሩ ጥሰቶች ተደብቀው ቆይተዋል፡፡ እኛ አሁን ይህንን እያጋለጥን እንገኛለን፡፡ ስለሆነም ላረጋግጥልህ የምፈልገው ዋነኛው ጉዳይ እኛ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆናችንንና ከመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር፣ የሕዝባችንን በነፃነት የመኖር መብት ለማረጋገጥ በጋራ እንደምንሠራ ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- ሰብዓዊ መብቶችን በክልሉ ከማረጋገጥ አንፃር በምታደርጉት የእስካሁን ጥረት አስተዳደርዎ የገጠሙት ፈተናዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ሙስጠፋ፡- በአሁኑ ጊዜ የገጠመን ዋነኛው ፈተና የክልሉ ተወላጅ በሆኑም ባልሆኑም፣ ፀረ ለውጥ ኃይል አካላት የሚሰነዘሩ የተለያዩ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ይህ ፀረ ለውጥ ኃይል ራሱን በተለያየ መልክ የሚገለጽና ዋነኛው ፈተናችን ነው፡፡ በቀዳሚነት እንቅስቃሴያቸውን በፕሮፓጋንዳ መንገድ ይገልጹታል፡፡ በፕሮፓጋንዳቸው አማካይነት በክልሉ ምንም ነገር እየተሠራ እንዳልሆነ የሐሰት መረጃ ይነዛሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች የተለያዩ ትስስሮችን በመጠቀም የሚፈጥሯቸውን ወሬዎች በመንዛት የተጀመረውን የለውጥ ሒደት አዝጋሚ እንደሆን እየሠሩ ነው፡፡፡ ከእነዚህ ኃይሎች በተጨማሪም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የጥፋት ኃይሎች፣ በክልሉ በተፈጠረው የአመራር ክፍተት በመጠቀም የተለያዩ ብጥብጦች ለመፍጠር እየሞከሩ ነው፡፡ አስተዳደሩ ተንኮታኩቶ ነበር፡፡ በርካታ የፀጥታ አባላትና አዛዦች ሥራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ በርካታ የሲቪል ሠራተኞችም ወይ አገር ጥለው ተሰደዋል፣ አሊያም ዳግም ታስረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአመራር ክፍተት እንዲፈጠርና ሥርዓቱ እንዲንኮታኮት በር ከፍቶ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ለምሳሌ ብንወስድ አልሸባብ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት በመጠቀም ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ሙከራ አድርጓል፡፡ በርካታ ኮንትሮባንዲስቶች አጋጣሚውን በመጠቀም የጦር መሣሪያ  ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየሞከሩ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሰብዓዊ መብትን ከማስከበርም ሆነ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ከማረጋገጥ አኳያ የገጠሙን ዋናዎቹ ፈተናዎች እነዚህ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተጠናቀቀው የኢሕአዴግ ጉባዔ ለውይይት ይቀርባል ከተባሉት አጀንዳዎች መካከል የአጋር ፓርቲዎች ጉዳይ ነበር፡፡ የእርስዎ ፓርቲ ደግሞ ከእነዚህ አጋር ፓርቲዎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚኖራችሁን ሚና እንዴት ለመጫወት አስባችኋል?

አቶ ሙስጠፋ፡- አጋር ፓርቲ ለመሆን እኛ አይደለንም የወሰንነው፡፡ አጋር ፓርቲ ለመሆን አልመረጥንም፡፡ በሕዝብ ብዛት ቁጥር ብትመለከተው እኛ ሦስተኛ ነን፡፡ በቆዳ ስፋት ደግሞ ከአገሪቱ የመጀመርያ ነን፡፡ ከመነሻው እኛን አጋር ፓርቲ የማድረግ ምድራዊም ሆነ መለኮታዊ ምክንያት የለም፡፡ አሁን አጠቃላይ የአገሪቱ ብሔራዊ ፖለቲካ ላይ የድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ ይህን ለማድረግ ኢሕአዴግን መቀላቀል ከሆነ ይህንን እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግን መቀላቀል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፣ የራሳችንን ድርሻ በብሔራዊ ፖለቲካው መወጣት ሌላው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ዕድሉን መነፈጋችን ብቻ ሳይሆን፣ እኛ ለዚህ በቁርጠኝነት አለመታገላችን ሌላው ምክንያት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ እርስዎ በሚያስተዳድሩት ክልል ነዳጅ መገኘቱ ታውቋል፡፡ ሆኖም የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጉድለት ባላቸው በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች መገኘት ከበረከት ይልቅ መርገምትን ያመጣል የሚባል ነገር አለ፡፡ እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? የተገኘው የተፈጥሮ ሀብት ለኢትዮጵያ በረከትን ወይስ መርገምትን የሚያመጣ ይመስልዎታል?

አቶ ሙስጠፋ፡- የተፈጥሮ ሀብት መርገምት ነው የሚለውን ሀልዩት ፈጽሞ አልቀበለውም፡፡ ሁልጊዜም የማስበው የአመራር መርገምት እንዳለ ነው፡፡ በናይጄሪያ፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቬኒዙዌላ ወይም በሌላ አገር የተፈጥሮ ሀብት መገኘት ለግጭት መነሻ፣ ለኋላቀርነት አሊያም ለመልካም አስተዳደር ዕጦት ምንጭ የሚሆነው ከአመራርነት አኳያ ነው፡፡ እርግጥ ነው ተፈጥሮ ሀብት ለዕድገት አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በረከትም ሆነ መርገምት እንዲሆን የሚያደርገው የአመራር ብቃት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በሶማሌ ክልል የተገኘው የተፈጥሮ ሀብት በክልልም ሆነ በብሔራዊ ደረጃ ያለው አመራር በአግባቡ ከተጠቀመበት በእርግጠኝነት ለሁሉም በረከት ይሆናል፡፡ ነገር ግን አመራሩ ይህን ለማድረግ ከተነሳው እርግማን ይሆናል፡፡ ነገር ግን የተፈጥሮ ሀብት እርግማን የሚለውን ትርክት ተረት እንደሆነ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው አመራር የተፈጥሮ ሀብቱን ወደ በረከት የመቀየር ብቃት አለው ብለው ያምናሉ?

አቶ ሙስጠፋ፡- እንደምገምተው የለውጥ ኃይሉን የሚመራው የኢሕአዴግ ክንፍ፣ ለአገሪቱ መልካም ነገሮችን የማድረግ ሐሳብ አለው፡፡ አመራር ለመስጠት የሚያስችል ትክክለኛ ሐሳብ፣ አመለካከት፣ እንዲሁም ፀባይ አለው፡፡ ስለሆነም በብሔራዊ ደረጃ ያለው አመራር የተፈጥሮ ሀብቱን ወደ በረከት የመቀየር አቅም እንዳለው በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በክልል ደረጃም ቢሆን ይህን ራዕይ ለማሳካትና ለመደገፍ ቁርተኞች ነን፡፡ ስለሆነም ይህ እኔን የሚያሳስበኝ ጉዳይ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው እንዳልከው ከተፈጥሮ ሀብት መገኘት ጋር በርካታ ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን የተለያዩ ፍላጎቶች መምራትና ማስተዳደር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም በአገሪቱ አመራር ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ተቋማትን እንደ አዲስ ከማዋቀር፣ ከማደራጀት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ከማሻሻል፣ እንዲሁም ሌሎች የተቆለሉ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር ያዘጋጁት ዕቅድ ምንድነው? ከሦስት ወይም ከአምስት ዓመት በኋላ የምትኖረው ሶማሌ ክልል በእርስዎ ዕይታ ምን ትመስላለች?

አቶ ሙስጠፋ፡- በመጀመርያ ደረጃ የሶማሌ ሕዝብ ያለ ምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ የሚኖርበት ክልል መፍጠር እንፈልጋለን፡፡ እዚህ ላይ ፍርኃት ለሚለው አፅንኦት መስጠት እፈልጋሁ፡፡ ምክንያቱም ላለፉት 27 ዓመታትና ከዚያም በላይ ፍርኃትና መሸማቀቅ የክልሉ ነዋሪዎች መለያ ስለነበር ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝባችን የፖለቲካ ሥርዓትን መፍራት እንደሌለበት እንዲሰማው እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የክልላችን ሕዝብ ሐሳብን ነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ እንዲሁም የማምለክ መብቱን በመጠቀም ነፃ እንዲሆንም እንፈልጋለን፡፡ የክልሉ ሕዝብ በክልሉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፍ ማድረግም እንደሁ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ የመገለል ስሜት ነው የሚሰማው፡፡ በተለይ የተማረው የክልሉ ሕዝብ ወደ ዳር እንደተገፋ ነው የሚቆጥረው፡፡ ስለዚህ እኛ የተማረውንና ልሂቅ የሆነውን የክልሉን ሕዝብ ወደ ፊት ለማምጣት ነው የምንሠራው፡፡ በቅርቡ ያቋቋምነው ካቢኔ 96 በመቶ የሚሆኑት አባላት የማስተርስና ከዚያ በላይ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም ልሂቁን ወደፊት ለማምጣት የምናደርገው ጥረት ማሳያ ነው፡፡ በዚህ አቅም በብሔራዊ ደረጃ ባሉ በፖለቲካዊ፣ በልማትና በሌሎች ጉዳዮች በከፍተኛ ሁኔታ መወዳደር ይቻላል፡፡ በመጨረሻም ክልላችን ኢንቨስተሮችን እንዲስብ እንሠራለን፡፡ እስካሁን ክልሉ እንደ ጦር ቀጣና ነው የሚቆጠረው፡፡ ነገር ግን በክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ስለሚገኙ ኢንቨስተሮች መጥተው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡