Skip to main content
x
የተጠያቂነት ዳር ድንበር በግልጽ መሰመር አለበት!

የተጠያቂነት ዳር ድንበር በግልጽ መሰመር አለበት!

የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ተጠያቂነት እንዳለበት የተደነገገው በሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ በወረቀት ላይ የሠፈረው ተግባራዊ ባለመሆኑ ግን የተጠያቂነት ዳር ድንበሩ አይታወቅም ነበር፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የአገር ሀብት ዝርፊያ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሰሞኑን እየተካሄደ ካለው ክስ ወይም ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ምክንያት የሚገለጽ ሳይሆን፣ ለዓመታት ብዙ የተባለበት ችግር ነው፡፡ የአገር ሀብት ዝርፊያን በተመለከተ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለዓመታት ሲያወጣቸው በነበሩ ሪፖርቶች አማካይነት ለፓርላማው እየቀረበ ብዙ ተብሎበታል፡፡ በተለይ በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ይቀርቡ የነበሩ ሪፖርቶች አስደንጋጭ ናቸው፡፡ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ካለመወራረዱም በላይ፣ ከፍተኛ ብክነትና ዝርፊያ እንደሚታይ ሪፖርቶቹ ጠቋሚ ነበሩ፡፡ ሪፖርቶቹ በየጊዜው ከፓርላማው በተጨማሪ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ዕርምጃ ለመውሰድ የደፈረ ግን የለም፡፡ ዋና ኦዲተሩ በተደጋጋሚ ዕርምጃ እንዲወሰድ ቢወተውቱም ሰሚ አልነበረም፡፡ ይህ ሁሉ ጥፋት ለምን ጨመረ ተብለው በአንድ ወቅት በፓርላማ የተጠየቁት ዋና ኦዲተሩ፣ ‹‹ዕርምጃ ስላልተወሰደ ነው ጥፋቱ የጨመረው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ በአገሪቱ ጠያቂና ተጠያቂ የሌለ እስኪመስል ድረስ የአገር ሀብት ባክኗል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደግሞ ከአገር አልፈው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዋነኛ መነጋገሪያ እንደነበሩ የታወቀ ነው፡፡

እንደሚታወቀው አገርን በሥርዓት ለማስተዳደር፣ የእያንዳንዱ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት በተቋቋመበት ሕግ መሠረት ኃላፊነቱና ተጠያቂነቱ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የእያንዳንዱ ተቋም ተሿሚም ሥልጣንና ኃላፊነቱ በሕግ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ሕግ ከወረቀት ጌጥነት ለማለፍ ባለመቻሉ፣ በአገር ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ ብዙዎቹ ተቋማትና ተሿሚዎች በሕጉ መሠረት ኃላፊነታቸውን መወጣት አቅቷቸው የደረሰው ጉዳት አስከፊ ነው፡፡ በየቦታው አድርባይነትና አስመሳይነት ተንሠራፍተው ተቋማት የጥቂቶች መጫወቻ ሲሆኑ፣ ሕግ እየተጣሰ ዜጎች ያለ ጥፋታቸው ሲቀጠቀጡና በእስር ሲማቅቁ፣ ድርጊቱን የሚቃወሙ እየታፈኑ የደረሱበት ሲጠፋ፣ ወዘተ ነበር፡፡ በሥልጣን መባለግ መብዛቱንና አደጋ እንደሚያስከትል ሲያሳስቡ የኖሩ እንደ ዕብድ ሲሳቅባቸው መታዘብም ተችሏል፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሚና ተደበላልቀው አገርና ሕዝብ ሲታመሱና ብሶቶች ሲሰሙ የጠላት ወሬ ነው እየተባለ ስላቁ በርክቶ ነበር፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ተደፍጥጠው ሕገወጦች እንዳሻቸው ሲሆኑ፣ የሕግ የበላይነት ተደርምሶ አገር ወደ ገደል እየተነዳች ነበር፡፡ ይህ አዲስ ታሪክ ሳይሆን የታለፈበት ነው፡፡ ተጠያቂነት ጠፍቶ ሕገወጥነት ሲፈነጭ ነበር፡፡

ከፌዴራል መንግሥት ባልተናነሰ የክልሎች ጉዳይም ያው ነው፡፡ ክልሎች ውስጥ ይፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘግናኝ በመሆናቸው፣ ብዙዎች ሸሽተው ይከትሙ የነበሩት አዲስ አበባ ነው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል መስተዳድር ድረስ ዜጎችን ማፈን፣ ማሰቃየትና መግደል የተለመደ ነበር፡፡ የግለሰቦችን ሀብት ወርሶ መክበርም እንዲሁ፡፡ መብታቸውን የጠየቁ ዜጎችን ከማሳደድ ጀምሮ በላባቸው ያፈሩትን ሀብት በመንጠቅ የከበሩ ወረበሎች፣ የራሳቸውን ሚሊሻና እስር ቤት እንዳደራጁ ጭምር ይታወቃል፡፡ ብሔርን የዓላማ ማስፈጸሚያ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ውንብድና የፈጸሙ ግለሰቦች በክልሎችም ነበሩ፡፡ የመንግሥት መሬት ከመቸብቸብ ጀምሮ ደን የሚመነጥሩና የማዕድን ሥፍራዎችን የሚዘርፉ ነበሩ፡፡ የተመደበላቸውን በጀት ከቢጤዎቻቸው ጋር ከመከፋፈል ጀምሮ፣ በየቦታው ለማይገነቡ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች የመሠረት ድንጋይ እየኮለኮሉ ሀብት ያጋበሱ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ በክልሎች ውስጥ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችና ዝርፊያዎች ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው፡፡ ተሸፋፍኖ ማለፍ አያዋጣም፡፡ ሕዝብ በሚገባ ያውቃልና፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተፈጸሙ አስከፊ የዝርፊያ ድርጊቶች በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ ሪፖርትም ቀርቦባቸዋል፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታዎች የተፈጸሙ አሳዛኝ ተግባራት ብዙ የሚባልባቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የተፈጸሙ ነውረኛ ድርጊቶች ወደፊት ብዙ እንደሚባልባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በመጥፋቱና ሕገወጥነት በመግነኑ አገር ተሽመድምዳለች፡፡ ጥቂቶች እየከበሩ ሚሊዮኖች የሚራቡባት ኢትዮጵያ የሰቆቃ ምድር ሆናለች፡፡ ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው አገር ለከፋ ችግር ተዳርጋለች፡፡ የአስፈጻሚው ጡንቻ በርትቶ ፓርላማ መጫወቻ በሆነባት ኢትዮጵያ፣ ሕግ ተርጓሚው ነፃነቱ ተገፎና በራሱም ችግር ምክንያት ሕገወጥነት መስፈኑ እዚህ አድርሷል፡፡ ሕግ ካልተከበረ ሕገወጥነት እንደሚነግሥ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሕግ አክብሮ ማስከበር ባለመቻሉ የአገር ጉድ እየተዘከዘከ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ ሌላ ጉድ ይሰማል እየተባለም ነው፡፡

የተጠያቂነትና ዳር ድንበር ተለይቶ ባለመሰመሩና ሥልጣን በሕግ ባለመገራቱ ምክንያት ብቻ፣ ከፍተኛ የአገር ሕመም ነው ያጋጠመው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግሥትን ሥራ የሚያከናውኑ ተቋማትና ተሿሚዎች በሕግ የተሰጣቸው ሥልጣን አለ፡፡ ከሥልጣናቸው ቀጥሎም ኃላፊነታቸው ተዘርዝሯል፡፡ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን የሚናገሩ ወገኖች ካሉ ለኅሊናቸው መተው ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎች በዚህ መንገድ ሥራቸውን አላከናወኑም፡፡ ግለሰቦች ፍርኃት አንግሠው ተቋማትን መጫወቻ ሲያደርጉ፣ አድርባዮችና አስመሳዮች ደግሞ አጋጣሚውን በመጠቀም ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ፈጽመዋል፡፡ ‹‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ሲማር ሞኝ ደግሞ ከራሱም ውድቀት አይማርም፤›› እንዲሉ፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ላይ የተፈጸሙ በደሎች ወደፊት መደገም የለባቸውም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚኖሩባት አገር ለመገንባት መነሳት እንጂ፣ ብሔር ላይ እየተለጠፉ ራስን መከላከልም ሆነ ቢጤዎችን ከፍትሕ ለማሸሽ መሞከር በሕግ ማስጠየቅ አለበት፡፡ ወደፊትም በሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ይህንን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› እየተባባሉ ድብብቆሽ መጫወት ሕገወጥነት ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሠባት አገር ለመገንባት መነሳት እንጂ፣ የብሔር ካርታ እየመዘዙ መቆመር አያዋጣም፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲከበር እንጂ፣ ሕግ እንዲጣስ ማደፋፈር ሕገወጥነት ነው፡፡ የተጠያቂነት ዳር ድንበር በግልጽ ይሰመር የሚባለው ለዚህ ነው!