Skip to main content
x
ስደተኞችን የመታደግ ፈተናዎች

ስደተኞችን የመታደግ ፈተናዎች

በዓለም ላይ አትራፊ ከሆኑ ወንጀሎች መካከል ከሕገወጥ የዕፅ ዝውውር ቀጥሎ ይጠቀሳል፡፡ ሰዎች እንደ ተራ ዕቃ በኮንቴይነር ታጭቀው በረሃ የሚያቋርጡበት፣ ኬላ የሚያሳብሩበት ረዣዥም እጅ ያላቸው ከኋላ ሆነው ሰዎችን የሚሸቅጡበት አደገኛ ወንጀል ነው፡፡ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የዓለምን ፖለቲካም እያናጋ ያለና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ረገድ በተምሳሌትነት የሚነሱ አገሮችን ጭምር ትዝብት ላይ እየጣለ ያለ አጋጣሚ ነው፡፡

ወዲህ የተሻለ ኑሮ ይኖራል በሚል አጉል ተስፋ፣ ወዲያ ደግሞ በእርስ በርስ ጦርነት አገራቸው ለታሪክ እንዳይተርፍ ሆኖ የወደመባቸው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ድንበር ያቆራርጣሉ፡፡ ወራት በሚፈጀው አደገኛው ጉዞ በረሃ ከሚበላቸው፣ ባህር ከሚውጣቸው ተርፈው ኬላዎች ላይ የሚደርሱ ጥቂት ናቸው፡፡

 በቀላሉ በማይረታው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የሚሳተፉ ቢያዙም ወንጀሉ ግን የሚገታ አልሆነም፡፡ በተያዙት እግር ተተክተው ዝውውሩን የሚያቀላጥፉ እሳት የላሱ ደላሎች ጠፍተው አይጠፉም፡፡ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም በዚህ ሲሏቸው በዚያ፣ በኬላ ሲመጡባቸው በጫካ ድብብቆሽ እየተጫወቱ ኑሮ የገፋቸውን ምስኪኖች እንደከብት ይነዳሉ፡፡ ሲላቸው አግተዋቸው ገንዘብ ይጠይቁባቸዋል፡፡ አልያም ደግሞ ተበላሽቶ እንደ ቆመ መኪና የአካል ክፍሎቻቸውን አውጥተው ይቸረችራሉ፡፡

በዚህ መልኩ አካላቸው የጎደለ፣ ኩላሊታቸውን ያጡ፣ ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም፡፡ የታገቱ ልጆቻቸውን ለማስፈታት ቤት ንብረታቸውን ሸጠው ባዶ እጃቸውን የቀሩም እንደዚሁ፡፡ ከዚህ ስደተኞች ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው የአገሮችን ድንበር ከሚያቋርጡበት አደገኛው ጉዞ ባሻገር በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ሰነዶችን ይዘው በቦሌ ኤርፖርት የሚወጡም አሉ፡፡ በሥራና በቱሪስት ቪዛ እንዲሁም በሃይማኖት ጉዞዎች አሳበው ያልፍልኛል ብለው ወደሚመኟቸው አገሮች ይገባሉ፡፡ ዕድለኞች አደገኛ የሚባለውንና በበረሃ የሚደረገውን ስደት የሚቀላቀሉ ደግሞ የተለያዩ መውጫዎችን ተጠቅመው  ባገኙት ቀዳዳ ይሾልካሉ፡፡

ከኢትዮጵያ በጅቡቲና በየመን አድርገው ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገቡበት አንደኛው የስደት መስመር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ላንድ፣ ቦሳሶ፣ የመን በኩል እንዲሁም በሶማሌ ላንድ በርበራ፣ የመን አቆራርጠው ሳዑዲ የሚገቡም አሉ፡፡ ይህ የጉዞ መስመር የምሥራቅ መውጫ በሮችን የሚከተል ሲሆን፣ የሰሜን ምዕራብ መውጫ በሮችን የሚከተሉ ደግሞ ወደ እስራኤልና ጣልያን ይገባሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ የመግባት ፍላጎት ያላቸውም የደቡብ መውጫዎችን እንደሚከተሉ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተደራጁና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ከተማ ደባልቄ ገልጸዋል፡፡

በአፋር ክልል የጋላፊን መስመር በመከተል፣ ወደ ጅቡቲ የሚመላለሱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በትራንስፖርትነት በመጠቀም፣ ድንበር አካባቢ ሌላ ተቀባይ ደላላ በማዘጋጀት ጨለማን ተገን አድርገው በባጃጅ እልም ይላሉ፡፡ መተማ ድንበር ላይ የሚገኙ ደላሎች ጨለማን ተገን አድርገው ስደተኞቹን የሱዳንን ድንበር ያሻግራሉ፡፡ በዚህ መስመር በግምት 100 ሰዎች በየቀኑ የሱዳንን ድንበር እንደሚሻገሩ ይነገራል፡፡

ወደ ደቡብ አፍሪካ መግባት የሚፈልጉም የሞያሌን ድንበር አልፈው ኬንያ እንደሚገቡ፣ ሶማሌ ክልል የሚገኙ መውጫዎችን ተጠቅመው ወደ ጅቡቲና ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገቡም ብዙ እንደሆኑ ኮማንደሩ አብራርተዋል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በስፋት የታየባቸው በአገሪቱ የሚገኙ ክፍሎች በደቡብ ክልል በከምባታ፣ በሀድያ፣ በስልጤ፣ በወላይታ ዞኖች ሲሆን፣ በአማራ ክልል ደግሞ በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞን እንዲሁም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በባሌ፣ በጅማ፣ በኢሉአባቦራ፣ በወለጋ ዞኖች፣ በትግራይ ክልል በምሥራቃዊና ደቡባዊ ዞኖች በስፋት ታይቷል፡፡ 

እነኚህ መውጫ በሮች በተለይም የዓረብ አገሮች ጉዞ ታግዶ በነበረበት ወቅት ትራፊክ እንደሚበዛባቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ የተጣለው ዕገዳ ከሳምንታት በፊት መነሳቱን ተከትሎ ብዙዎች በሕጋዊ መንገድ ለመሄድ ፓስፖርት በማውጣት ሒደት ላይ ናቸው፡፡

ከኢሚግሬሽን ቢሮ ፓስፖርት ለመውሰድ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ክፍያ ከፈጽሙ 56‚000 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ የሚለያይ ቢሆንም አንዳንዴ እስከ 95 በመቶ የሚሆኑ ፓስፖርት ፈላጊዎች የዓረብ አገር ተጓዦች ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ያለው አጋጣሚ የሚከሰተው በብዛት የዓረብ አገር ጉዞ መጀመሩን የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲለቀቅ እንደሆነ የሚናገሩት የኢሚግሬሽን ምክትል ኃላፊው አቶ መንግሥቱ አለማ ናቸው፡፡

የኤጀንሲዎች ግዴታ

ሕጋዊ ጉዞ በተጀመረባቸው የዓረብ አገሮች ሠራተኞችን ለመላክ እንቅስቃሴ የጀመሩ ጥቂት ኤጀንሲዎች ተፈላጊ የሥራ ዝርዝሮችን ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ዕገዳው ከመነሳቱ አስቀድመው ዝግጅት ያደረጉ ኤጀንሲዎች ሲሆኑ፣ ሠራተኞችን መመልመል የሚችሉት የሥራ ዝርዝራቸውን ባስገቡባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ብቻ ነው፡፡

ለምሳሌ ይህንን ያህል ሰው እፈልጋለሁ ብሎ አዲስ አበባ በሚገኘው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጥያቄ ያስገባ ኤጀንት ሰዎችን መመልመል የሚችለው ከአዲስ አበባ ይሆናል፡፡ ኤጀንሲዎቹ በየክልሎች ቢሮ እንዲከፍቱ ስለሚደረግ የሚከፍቷቸው ቢሮዎች በየአካባቢው ያሉ ወጣቶችን እንዲመለምሉ ይሆናል፡፡ ‹‹በክልሉ የሚገኙ ሰዎችን እዚህ አምጥቶ ማጉላላት አይቻልም፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚሰጠው ፓስፖርት ሕጋዊ ነው እያሉ ደላሎች ወጣቶችን እያታለሉ እዚህ እያመጡ ያጉላሏቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ቢሮ በየክልሉ እንዲከፍቱ የተደረገው፤›› የሚሉት በሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዳይሬክተር ጄኔራሉ አቶ ብርሃኑ አበራ ናቸው፡፡

ኤጀንሲዎቹ በብዛት ወደ ዓረብ አገር የሚሄዱ ሰዎች የሚበዙባቸውን ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎችና ድሬዳዋ ከተማ ላይ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ፡፡ ያስገቧቸው የሥራ ዕድሎች (ጆብ ኦፈር) በቢሮዎቹ ከፀደቁላቸው በኋላ ሠራተኞችን ወደ መመልመል ሥራ ይገባሉ፡፡ የሚመለምሉትም በተጠየቀው የሥራ መስክ ከቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ማዕከሎች አስፈላጊውን ሥልጠና የወሰዱትን ብቻ ነው፡፡

እነዚህ የሥልጠና ማዕከሎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሠልጣኞችን እየተቀበሉ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሥራው ዓይነት ከአንድ እስከ ሦስት ወራት የሚፈጀውን ሥልጠና በአዲስ አበባ የተከታተሉ 314 ሠልጣኞች የተመረቁት ከቀናት በፊት ነው፡፡ ሌሎችም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ማሠልጠኛ ማዕከላት ሠልጣኞችን በማስመረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ተገቢውን ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ወደ ተፈራረሙ ጆርዳን፣ ኳታር ወይም ሳዑዲ ዓረቢያ ይሄዳሉ፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑትም መዳረሻቸው ሳዑዲ ዓረቢያ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ፡፡

ለሥራ ወደ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች

ዕድሜያቸው 18 ዓመት የሞላቸው፣ ቢያንስ እስከ ስምንተኛ ክፍል የተማሩ፣ በሚሄዱበት አገር ለሥራ የሚያግዛቸው በቂ ክህሎት ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ያገኙና የብቃት ማረጋገጫ ወረቀት የወሰዱ፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ውላቸው ፀድቆና ልዩ መታወቂያ የወሰዱ ናቸው ለሥራ ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ ብቁ ይባላሉ፡፡

በቂ መረጃ ሳይኖራቸው፣ በተቃራኒ ደግሞ በደላሎች ተደፋፍረው አስፈላጊውን መመዘኛና መስፈርት ሳያሟሉ ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ ሙከራ ያደረጉም ነበሩ፡፡ በኤርፖርት የኢሚግሬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አይክፋው ጎሳዬ፣ መስፈርቱን ሳያሟሉና ወደ ቤሩት፣ ሳዑዲ፣ ግብፅና ሱዳን ለመብረር ሙከራ ያደረጉ 301 ሰዎች (የዓረብ አገር ጉዞ በተጀመረበት የመጀመርያው ቀን) ከኤርፖርት እንዲመለሱ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

እነዚህ ተመላሽ የተደረጉ ሰዎች ሕጋዊ ዶክመንት ያላቸው ነገር ግን በተባሉት አገሮች ለመግባት ማሟላት ያለባቸውን መመዘኛዎች ያላሟሉ እንዲሁም እንደ ግብፅና ሱዳን ያሉ አገሮችን ረግጠው የማለፍ ፍላጎት የነበራቸው እንደሆኑ አቶ አይክፋው ገልጸዋል፡፡ በሌላኛው ቀን ወደ ዓረብ አገር ሊሄዱ ሲሉ የተገኙ 115 ሰዎች ከኤርፖርት ሲመለሱ ‹‹ሕጋዊ ሆኖና መስፈርቱን አሟልቶ መሄድ ያለውን ጠቀሜታ አስረድተናቸው ስለነበር አጭበርብረው ለመውጣት ሙከራ የሚያደርጉ ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ወደ ኤርፖርት የሚሄዱ ቁጥራቸው መቀነሱ ምናልባትም ሌላ አማራጮችን እየተጠቀሙ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የሚፈጥር ነው፡፡ በአየር ትራንስፖርት መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ደላሎችን አማራጭ የሚያደርጉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ከጀርባው አቅም ያላቸው ሰዎች የሚመሩት ይህ ወንጀል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ማኅበረሰቡም ጭምር የሚሳተፍበት ነውና በቀላሉ መግታት ከባድ ነው፡፡ ከደላሎቹ ባሻገር ከዚህ ተግባር የሚያተርፉ የማኅበረሰቡ አካላትም አሉ፡፡ አቶ አይክፋው የታዘቡትን እንዲህ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከከተማ ወጣ ብለው የሚገኙ ዘዋራ ቦታዎች ላይ ቤት ሠርተው የሚቀመጡ አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሕገወጥ ስደተኛችን ዱካ እየተከተሉ ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ናቸው፡፡ እልም ያለ በረሃ ላይ ቤት ሠርተው ሲኖሩ አካባቢውን አቋርጠው ለሚያልፉ ስደተኞች አንድ ሊትር ውኃ እስከ 50 ብር ይሸጣሉ፡፡ አጋጣሚውን እንደ መልካም የንግድ ዕድል በመጠቀም በሶ በኩንታል እያስፈጩ በውድ ዋጋ ይሸጡላቸዋል፤››  በየኬላዎች ላይ የተጠናከረ ጥበቃ ስለሚኖር ጥበቃ በማይኖርባቸው ጫካዎች  አቆራርጠው ያልፋሉ፡፡ መውጫ መግቢያ በሮች ሲጠበቁ እነሱ በአንድ ጥግ ተሽሎክሉከው ያልፋሉ፡፡ በጉዞ ወቅት የሚያጋጥማቸው ስቃይና እንግልት እንዲሁም የፈለጉበት አገር ከገቡ በኋላ የሚያጋጥማቸው ነገር ‹‹የመሰቃየት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የክብርም ጉዳይ ነው፡፡ የሌላ አገር ሰዎች ተጎዱ ሲባል አንሰማም፡፡ ኢትዮጵያውያን  በሕገወጥ መንገድ ስለሚሄዱላቸው እንደ ዕቃ ነው የሚጫወቱባቸው፡፡ ለዚህ የሚዳርጋቸው ደግሞ ደላላ ነው፡፡ ስለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል፣ የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው እንዲሠሩ መደረግ አለበት፤›› ብለዋል አቶ አይክፋው፡፡

በሕገወጥ መንገድ በጎን የሚገቡ እንደ ልብ ስለሆኑም አገሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ‹‹መንግሥት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል ከተለያዩ ዓረብ አገሮች ጋር የሚያቀርበው የፍርርም ጥያቄ ዋጋ የለውም፡፡ አገሮች ምን አስጨንቆን ነው ምንፈርመው፣ ዜጎቻችሁ እንደሆነ እየመጡ ነው ይላሉ፤›› ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡