Skip to main content
x
‹‹ወደብ አልባ አገር ሆኖ ባህር ኃይል መገንባት ይከብዳል››

‹‹ወደብ አልባ አገር ሆኖ ባህር ኃይል መገንባት ይከብዳል››

ካፒቴን አየለ ኃይሌ፣ የቀድሞ ባህር ኃይል አካዴሚ ዋና አዛዥና የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የሥልጠና ማዕከል መሥራች

ካፒቴን አየለ ኃይሌ የተወለዱት የቀድሞው ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ኤጀርሳ ጎሮ ለመድረስ ሦስት ኪሎ ሜትር ሲቀረው በሚገኘውና ልዩ ስሙ ጣጤሳ በተባለው መንደር ነው፡፡ የሦስት ዓመት ሕፃን እያሉ አባታቸው በጦር ሜዳ በፋሺስት ጣሊያን ጦር ተረሽነዋል፡፡ አባቶቻቸው በጦር ሜዳ ለተሰውባቸው ልጆች ተብሎ በተቋቋመው ሐረር ልዑል ራስ መኮንን የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከዚያም በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል፡፡ ወደ እንግሊዝ አገር አቅንተው ሮያል ማሪን ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ገብተው በማሪን ኢንጂነሪንግ፣ እንዲሁም በዚሁ አገር በሚገኘው ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በወቅቱ በዓለም ለመጀመርያ ጊዜ የተጀመረውን ሲስተምስ ኤንድ ማኔጅመንት ትምህርት ተከታትለው በክብር ተመርቀዋል፡፡ በሥራ ዓለምም የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በ1948 ዓ.ም. ሲቋቋም የመጀመርያው ምልምል ሆነው ገብተዋል፡፡ በልዩ ልዩ ክፍሎችም ካገለገሉ በኋላ የባህር ኃይል ኮሌጅ ዋና አዣዥ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ቀጥሎም የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን በአዲስ መልክ ለማዋቀር በተካሄደው እንቅስቃሴ የጎላ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በተጨማሪ ሌላ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ኢንስፔክተር ጄኔራል ሆነው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ተወጥተዋል፡፡ በአንድ ወቅት የሸቀጥ ዋጋ መናርን ክስተት ለማወቅ እንዲቻል በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ ተሳትፈው ሙያዊ ዕገዛ አድርገዋል፡፡ በኮሚሽነር ማዕረግ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢንስቲትዩቱን በዘመናዊ መንገድ እንደገና ካዳራጁ በኋላ ቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢንስቲትዩቱን ማሠልጠኛ ማዕከል አቋቁመዋል፡፡ ልደታ አካባቢ የሚገኘውን የምርታማነት ማሻሻያ ማዕከልን እንደ አዲስ አደራጅተዋል፡፡ ምሕረት ሞገስና ታደሰ ገብረ ማርያም ከካፒቴን አየለ ኃይሌ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡   

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ ትምህርት ከተከታተሉበት እንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደተመለሱና በወቅቱ ያጋጠመዎት መሰናክል ካለ ቢያብራሩልን?

ካፒቴን አየለ፡- የአፄው ሥርዓት የተለወጠው እንግሊዝ እያለሁ ነው፡፡ ለሥራ ትፈለጋለህና ቶሎ እንድትመጣ ተባልኩ፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን እዚያው ትቼ ወደ አገር ቤት መጣሁ፡፡ እንደመጣሁም የገባሁት የድሮ ክፍሌ ባህር ኃይል ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ ጥሩ ሆነው አልጠበቁኝም፡፡ አዲዩ ነህ ተብዬ መኖሪያ ቤት ስለተነፈገኝ ለስምንት ዓመታት ያህል ሆቴል ውስጥ ቆይቻለሁ፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን ተመልሼ እንዳላይም ፓስፖርት ተከለከልኩ፡፡ ባለቤቴ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ትሠራ ነበር፡፡ እሷንም ከኢኤልኤፍ (ጀብሃ) አባላት ጋር ግንኙነት አለሽ ብለው ፓስፖርቷን ነጠቋት፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ግን ለባለቤቴና ለልጆቼ ጥገኝነት ፈቀደላቸው፡፡ መኖሪያ ቤትም በነፃ ሰጣቸው፡፡ እኔ ደግሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘንድ ቀርቤ ተጠየቅኩ፡፡ ውጭ አገር የተማርኩት በራሴ ገንዘብ ሳይሆን በመንግሥት ገንዘብ ነው፡፡ ያ የመንግሥት ገንዘብ ደግሞ ከግብር ከፋዮች የተሰበሰበ ነው፡፡ እንግሊዝ የምሠራበት ድርጅት ይከፈለኝ የነበረው ደመወዝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከፈለው አሥር እጥፍ የበለጠ ነበር፡፡ ጥቅሜን ብቻ ባይ ኖሮ ሌሎች እንደሚያደርጉት እዚያው እቀር ነበር፡፡ ነገር ግን የግብር ከፋዮች ውለታ አለብኝ ብዬ ተመለስኩ እንጂ እዚህ አገር እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም ወይም ዘመድ የለኝም ብዬ ነገርኳቸው፡፡ ይህንን በጥሞና ካዳመጡና ለትንሽ ቀናት ያህል ከቆዩ በኋላ መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እንዳገለግልና በስተመጨረሻ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩትን በዘመናዊ መንገድ እንዳደራጅና በኢንስቲትዩቱ ማሠልጠኛ ማዕከልም እንዳቋቁም ጠየቁኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንስቲትዩቱ ማሠልጠኛ ማዕከል መቼና እንዴት ተቋቋመ?

ካፒቴን አየለ፡- የኢንስቲትዩቱ ማሠልጠኛ ማዕከል የተቋቋመው በ1976 ዓ.ም. ኅዳር ሲሆን፣ በአፍሪካ ‹‹የልቀት ማዕከል›› (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ) ተብሎ ተመርጦ ነበር፡፡ ይህንንም የመረጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ነው፡፡ ሊመረጥ የቻለውም በአፍሪካ አገሮች የሚገኙትን ተመሳሳይ ተቋማትን ከጎበኘና ከዳሰሰ በኋላ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ በዘመናዊ መልክ እንዲደራጅ ያስፈለገበት ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አዘቅት ውስጥ በመውደቁ ነው፡፡ ማኔጅመንት ደግሞ ለሀብታሞች ብቻ ሳይሆን፣ ደሃዎችም በድህነታቸው ያላቸውን ፋይናንስ እንዴት አድርገው መጠቀም አለባቸው የሚለውን ለመመለስ ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባት ይመስለኛል ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በአንድ ወቅት ጠርተውኝ፣ ‹‹ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ታቋቁምልኛለህ ወይ?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ጥያቄውንም ተቀብዬ ኢንስቲትዩቱን ለማቋቋም በቃሁ፡፡ ኢንስቲትዩቱ ዋናው ትኩረቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ ተመርቆ ወደ ሥራ እንደገባ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹ከእኔ ጀምሮ ሥልጠና ስጠን› ብለው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ መካከለኛ ማኔጀሮች (መምርያ ኃላፊ፣ ዳይሬክተር)፣ ከዚም ዝቅተኛ ማኔጀሮች (የክፍል ኃላፊና ሌሎችም) ሁሉ ሥልጠና እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የአፍሪካ የማኔጅመንት አሶሴሽን ስብሰባ በሐራሬ ዚምባብዌ ተካሂዶ ነበር፡፡ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ገብርኤል ሙጋቤ ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ እንዳሉት ሁሉ ሚስተር ሙጋቤም የኢንስቲትዩቱን ኃላፊ በስም ጠርተው ‹‹እኔንም እንድታሠለጥነኝ እፈልጋለሁ፤›› ብለው ተናገሩ፡፡ የሁለቱን አገሮች የቀድሞ መሪዎች ተመሳሳይ ንግግሮች እስከ ዛሬ ሳስበው ይገርመኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በሠልጣኞች ወይም በአጠቃላይ በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ያሉት ችግሮች ምንድን ነበሩ?

ካፒቴን አየለ፡- ትልቁና ብዙ አሠራሮችን ለብልሽት የዳረገው በሥራና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የመንግሥትና የፖለቲካ ሹመኞች ጣልቃ ገብነት መኖሩ ነው፡፡ ተገቢ ዕውቀት ያለው በተገቢ ቦታ አለመመደቡ ሌላው ችግር ሲሆን፣ የበላይ ኃላፊዎች ወይም ከላይ የሚቀመጡት አቅምና ብቃት የሌላቸው፣ ለፖለቲካው ታማኝ የሆኑ ብቻ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አወሳስበውታል፡፡ ለፖለቲካው ብቻ ታማኝ የሆነ ሰው ደግሞ የመሥሪያ ቤቱን የሥራ አካሄድና ያለበትን ችግር አያውቀውም፡፡ ከታች ያሉት ሊያስረዱት ቢሞክሩም አይቀበላቸውም፡፡ አንድ ጉዳይ ለመወሰን ባለሥልጣኑ ከስብሰባ እስከሚመጣ ወይም ከሄደበት አገር እስከሚመለስ ድረስ ይወዘፋል፡፡ ባለሥልጣኑም ከሄደበት ሲመጣ ጉዳዩ በኮሚቴ ነው የሚታየው፣ አንዳንዴ ኮሚቴው ላይሟላ ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ በሥራው ላይ መጓተትን፣ ባለጉዳይ ማጉላላትን ያስከትላል፡፡ ውሳኔውም የተዓማኒነትና የአግባብነት ችግሮች ይታዩባቸዋል፡፡ እርግጥ ነው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የተማሩና በጣም የበሰሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ ሙያውና ዕውቀቱ እያላቸው ለመወሰን ይፈራሉ፡፡ በአጠቃላይ በደርግ ሥርዓት የነበሩ ባለሥልጣናት ትኩረታቸው ከፖለቲካ አንፃር ምን እባላለሁ በሚል የራሳቸውን ደኅንነት የመጠበቅ እንጂ፣ ስለዕድገት እምብዛም አይጨነቁም፡፡ በእርግጥ አገራቸውን በጣም ይወዳሉ፡፡ እንዲያውም በብዛት ስለአገር ፍቅር ይናገራሉ፡፡ መተማመንም አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- የጠቃቀሷቸው ችግሮች እርስዎንም ገጥመዎት ነበር?

ካፒቴን አየለ፡- በእኔ ሥራ አካሄድ ላይ የገጠሙኝ ችግሮች ሥራን ከአብዮቱ ወይም ከፖለቲካው አንፃር አያይም የሚል ሐሜትና ጣልቃ ገብነት ናቸው፡፡ ሐሜቱ የተነሳው ሥልጠና የሚሰጡ በሳል ባለሙያዎች ከአሜሪካና ከእንግሊዝ አገሮች ነበር የምናስመጣው፡፡ በአንፃሩም የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ወደ ተጠቀሱት አገሮች ሄደው የሚገባውን ሥልጠና ተከታትለው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር፡፡ በመካከሉ ሥራ አስኪያጁ ኢንስቲትዩቱን ከፖለቲካው ወይም ከአብዮቱ አንፃር አያየውም ተባልኩ፡፡ ትኩረቱና ግንኙነቱ ከካፒታሊስት አገሮች ጋር እንጂ፣ ከሶሻሊስቶችና ከኮሙዩኒስቶች ጋር አይደለም እባል ነበር፡፡ በኢንስቲትዩቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተቀመጠው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ነገር ግን ኢንስቲትዩቱ እንደ ተመሠረተ ፕሬዚዳንቱ ካላቸው ጉጉትና ፍላጎት የተነሳ በየጊዜው እየጠሩኝ ስለኢንስቲትዩቱ እንቅስቃሴ እንወያይ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቁሜ በአዋጁ መሠረት የሥራ ግንኙነቴን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ጋር አደረግኩና በዚሁ ቀጠለ፡፡ ለሥልጠናም የሚመጡትን ተጠሪነታችሁ እንደ የዕድገት ደረጃችሁ በቅርብ ላለው ኃላፊ እንጂ፣ አልፋችሁ መሄድ የላባችሁም እያልኩ ማስተማሩን ተያያዝኩት፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ለመጀመርያ ጊዜ የተሰጠ ነው ያሉትን ‹‹ሲስተምስ ኤንድ ማኔጅመንት›› እንዴት ሊማሩ ቻሉ?

ካፒቴን አየለ፡- የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ለንደን በነበሩበት ጊዜ ስለትምህርቱ ሰዎች ሲያወሩ ይሰማሉ፡፡ ከለንደን ሆነው በስልክ ‹‹ሲስተምስ ኤንድ ማኔጅመንት›› ለመጀመርያ ጊዜ በሲቲ ዩኒቨርሲቲ ሊጀመር ነውና አንተ እንድትገባ ፈልጌያለሁና ጻፍላቸውና ቀጥል አሉኝ፡፡ እንደተነገረኝ ጻፍኩላቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊ ድሮ መርከበኛ የነበረና ካፒቴን ማክስ ሰርሰን ይባላል፡፡ ይህ ካፒቴን እኔ ቀደም ሲል የተማርኩበት ሮያል ማሪን ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ይማር ነበርና እኔም የኮሌጁ ተማሪ መሆኔን ስነግረው ያለቅድመ ሁኔታ እቀበልሃለሁ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ ቢያንስ አንድ ዓመት ያህል በኃላፊነትዎ ላይ ቆይተዋል፡፡

ካፒቴን አየለ፡- አዎ! ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ምን ማየት ችለዋል? የጠቃቀሷቸው ዓይነት ተመሳሳይ ችግሮች ቀጥለው ነበር? ምን ተገነዘቡ? ኃላፊ እንደ መሆንዎ መጠን ምን የመፍትሔ ሐሳብ አቀረቡ፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘው ቢያነሱልን የምንፈልገው ‹ታይም ማኔጅመንት› ላይ መንግሥት ባለፈው ጥናት አጥንቶ አንድ ሠራተኛ ከተመደበለት በቀን ሦስት ሰዓት አይሠራም የሚልና ሌሎችንም ችግሮች አውጥቷል፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው መስተካከል የሚቻለው?

ካፒቴን አየለ፡- ኢሕአዴግ የገባው ሕዝቡ መንግሥት ላይ ባጉረመረመበትና ደርግን በጣለበት ወቅት ነው፡፡ እኔም ከኢሕአዴግ ሹመኞች ጋር አብሬ ለመሥራት ተንቀሳቅሼያለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ ስዬ አብርሃ ምንድነው የምትመክረን ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ እኔም እናንተ አሁን በመምጣታችሁ ሕዝብ በጣም ደስ ብሎታል፡፡ በዚህም መንፈስ ተቀብሏችኋል፡፡ ይህንን መወደዳችሁን ግን እንዳታጡ ተጠንቀቁ አልኳቸው፡፡ እሳቸውም በጣም ጥሩ ምክር ነው የመከርከን አሉኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አድራጎታቸው ሁሉ ሰው እንዲጠላቸው አድርጓል፡፡ በሥራ ላይ የሰው አመዳደባቸው የበፊቱ ሥርዓት ደርግ ይሠራበት እንደነበረው ዓይነት ለፓርቲው ታማኝ የሆነውን እንጂ፣ ለመሥሪያ ቤቱ ታማኝነት ያለው ሰው አይደለም፡፡ የኃላፊነት አመዳደብ በማኔጅመንት ዓይን የሚታየው ታማኝነቱ ለተሰጠው መሥሪያ ቤት ኃላፊነት እንዲሆን ነው እንጂ ለሌላ እንዲሆን አይደለም፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ ማኔጅመንት ሊሠራ አይችልም፡፡ ይህንን ችግር ደጋግመን ነግረናቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ እሺ ይበሉ እንጂ እሺታቸው በፍርኃት የታጀበ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔም ብዙ ሳልቆይ ኢንስቲትዩቱን ለቀቅኩ፡፡ ሥራን በአግባቡ ለማከናወን የጊዜ አጠቃቀማችን እንዴት ነው? ምን ያህል ጊዜ በሥራ ላይ እናጠፋለን? የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ ከሰኞ እስከ ዓርብ በቀን ስምንት ሰዓት መሥራትና ቅዳሜና እሑድ ማረፍ ግድ ሲሆን፣ በተለይ ቅዳሜ የገበያ (ሾፒንግ) ቀን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በደርግም ሆነ በአሁኑ ሥርዓት ለሥራ የተመደበው ሰዓት በሆነና ባልሆነ ምክንያት ሲስተጓጎልና ሲባክን ይስተዋላል፡፡ ይህም ራሱን የቻለ ሌብነት ከመሆኑም በላይ በድህነት ውስጥ ተዘፍቀን እንድንቀር ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የሥራ ባህል እንዲዳብርና ሰዓትም እንዲከበር የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ግድ ይላል፡፡       

ሪፖርተር፡- በኢንስቲትዩቱ የተመደቡት አሠልጣኞች ኢትዮጵያውያን ወይስ የውጭ አገር ሰዎች ናቸው? በደርግ ሥርዓት የነበረው ጣልቃ ገብነት እስከ ወዲያኛው ቀጠለ ወይስ ቆመ?

ካፒቴን አየለ፡- ኢንስቲትዩቱ ለሥልጠናና ለስብሰባ በሚያስፈልጉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በሚገባ የተደራጁ ምቹ የሥልጠና ክፍሎች፣ የመመገቢያ አዳራሽና ካፍቴሪያ ያሉት ሲሆን፣ ንፅህናቸውን የጠበቁ የመኝታና ንፅህና መጠበቂያ ክፍሎች አሉት፡፡ ይህንንም ያሟላነው ዩኤንዲፒ ባደረገልን የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ኢንስቲትቱን መርቀው በከፈቱበት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንደዚህ ተሳካ?›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሠልጣኞቹ ወይም አስተማሪዎቹ በንጉሡ ጊዜ የተማሩና በዓለም ላይ ከፍተኛ ዝናን ያተረፉ እንደ እነ አቶ ተፈራ ደግፌ ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በደርግ ሥርዓት የነበረው ጣልቃ ገብነት ቅይጥ (ሚክስድ) ኢኮኖሚ ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ ነው፡፡       

ሪፖርተር፡- የኢንስቲትዩቱን ማሠልጠኛ ማዕከል ለማቋቋም ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ለምን ተመረጠ?

ካፒቴን አየለ፡- የአመራረጡን ሁኔታ አላውቅም፡፡ የመረጡት ግን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ማሠልጠኛው አሁን ባለበት ቦታ ላይ ‹ፖይንት ፎር› በተባለ የአሜሪካ ድርጅት የሚደገፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓለማያ ኮሌጅ የእርሻ ምርምር ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ይህንን ኢንስቲትዩት ከተመለከቱ በኋላ የእርሻ ኢንስቲትዩቱን ወደ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እንድትለውጠው ሰጥቼሃለሁ፣ ወይም ፈቅጄልሃለሁ አሉኝ፡፡ ቦታውንም ከእነ ሕንፃው ስንወስደው ዩኒቨርሲቲው ትንሽ አጉረምርሞ ነበር፡፡ እኛም ዩኤንዲፒ በሰጠን ገንዘብ በጥሩ ሁኔታ ስላስፋፋነው ብዙም ሳይቆይ በዓለም ተወዳጅነቱን ሊያተርፍ በቅቷል፡፡ ማኔጀሮቹ ሥልጠና ሲገቡ ሥልጠናውን በጥሞና እንዲከታተሉ ከተፈለገ፣ ከቤተሰብ ወይም ከአዲስ አበባ ራቅ እንዲሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ውስጥ ከተደረገ ትኩረታቸውን በሥልጠናው ላይ ከማሳለፍ ይልቅ፣ ቤተሰባቸውንና የራሳቸውን ጉዳይ በማሰላሰል ሥልጠናውን በሚገባ ሳይከታተሉ ይቀርና ችግር ይፈጠራል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ማዕከሉ ቢሾፍቱ ላይ እንዲሆን ያደረጉት በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ማሠልጠኛው ደግሞ ራሱን የቻለ መኝታና ምግብ ቤት ስላለው ምቹነቱን በይበልጥ አጠናክሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንስቲትዩቱን የለቀቁት ለጡረታ መውጫዎ ሳይደርስ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

ካፒቴን አየለ፡- የለቀቅኩት ማንም ሳያስገድደኝ በገዛ ፈቃዴ ነው፡፡ እንዲህ እንዲሆን ያደረኩበትም ምክንያት የበላይ ኃላፊዎች ጣልቃ ገብነት እየባሰና እየጠነረከ በመምጣቱ በዚህም የተነሳ መግባባት እንዳልተቻለ፣ አልፎ አልፎም ሥርዓተ አልበኝነት በመስፈኑና መደማመጥ ባለመቻሉ የተነሳ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ብዙ መንገዶችና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተሠርተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ብዙ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሚገባቸውን ካሳ እንኳን በሚገባ አላገኙም፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ካፒቴን አየለ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ልማት ላይ ማተኮር ጥሩ ሆኖ ነገር ግን ተጠቃሚው ማን ነው? ለልማት በሚፈለገው ቦታ ላይ ያሉት ቤቶች ሲፈርሱ የሚጎዳ አለ ወይ? የሚጎዳ ካለ እንዴት ይካሳል የሚለው በቅድሚያ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን እንኳን በአንድ አካባቢ ያለ የግለሰብ ቦታ ለልማት ከተፈለገ፣  ተመጣጣኝ የሆነ ሌላ ቦታ ለባለቤቱ ወይም ለባለ ንብረቱ ከሰጡት፣ በላዩም ላይ ቤት ከሠሩለትና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞችን ካከበሩለት በኋላ ነው የቀድሞውን ቤት አፍርሰው ቦታውን ላሰቡት ዓላማ የሚያውሉት፡፡ ከዚህ አንፃር የሚከናወን ልማት የሚያስገኘው ውጤት የሚውለው ለሕዝቡ እስከሆነ ድረስ የሕዝቡ የመኖር ዋስትናው ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ሁልጊዜ የሚታየው ነገር ቢኖር ጥቂት ሰዎች የሚረኩበትና የሚደሰቱበት፣ ሕንፃዎች መገንባታቸውና መንገዶች መሠራታቸው እንጂ በግንባታው ሳቢያ አብዛኛው ሕዝብ መጎዳቱን የመገንዘብ ወይም የመረዳት ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በደርግ ዘመን በሸቀጥ ዋጋ መናር ላይ ጥናት አሠርታችሁ ነበር፡፡ የጥናቱን አፈጻጸምና የደረሳችሁበትን ድምዳሜ ያስረዱናል?

ካፒቴን አየለ፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የንግድ ሚኒስቴር ኢንስፔክተር የሚባሉ አሉ፡፡ ኢንስፔክተሮቹ ከደመወዛቸው ሌላ አበል አላቸው፡፡ በዚህም ፒያሳና መርካቶ፣ በሌሎችም ሥፍራዎች በሚገኙ ንግድ መደብሮች እየተዘዋወሩ ደስ ያላቸውንና የፈለጉትን ሸቀጥ ይገዛሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢንስፔክተር ሸሚስ ለመግዛት ቢፈልግ ዋጋው 35 ብር ሆኖ ሳለ ነጋዴው ግን 60 ብር አድርጎት ይሸጥለታል፡፡ ኢንስፔክተሩም ሳይከራከር ይገዛዋል፡፡ በሌላውም ቀን ይሄዳል በዚያው ዋጋ ይሸጥለታል፡፡ ነገር ግን በዓመቱ የገቢ ግብር ሲመጣ ነጋዴው በሚሸጥበት ዋጋ የተተመነ ግብር እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ እንዳይከራከር መረጃ አለ፡፡ በደርግ ሥርዓት ጊዜ ግን ይህ ዓይነቱ አካሄድ ወይም ውሎ አበል ክፍያ የአድኃሪያን አስተሳሰብ ነው ብሎ አበሉን ከለከለ፡፡ በዚህ ምክንያት ነጋዴዎችን የሚቆጣጠር ጠፋ፡፡ እንደፈለጋቸው መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ሸማቹ ኅብረተሰብ ተጎዳ፡፡ ኑሮም ተወደደ፡፡ ሸማቹ ከቀበሌ ሕዝብ ሱቅ የገዛውን ሸቀጥ ራሱ መጠቀም ሲገባው ጉሊት ቁጭ ብሎ መቸርቸሩን ተያያዘው፡፡ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ሸማቹ ወይም ተጠቃሚው ነጋዴ ሆነ ወይም ወደ ነጋዴነት ዞረ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በችግር የተነሳ ነው ብዬ የጥናቱን ውጤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቤ ነበር፣ ነገር ግን ምንም የፈየደው የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ችግር አሁንም አለ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ካፒቴን አየለ፡- ይህ ከነፃ ኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው፡፡ የነፃ ኢኮኖሚን አስተሳሰብ ያመጣው ጆን አዳምስ ራሱ ነፃ ኢኮኖሚ የሚሠራ አይደለም ብሏል፡፡ ነፃ ኢኮኖሚ በእንደ እኛ አገር አይሠራም፡፡ በነፃ ኢኮኖሚ ምክንያት ተጠቃሚ የሚሆነው ሕዝቡ ሳይሆን መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ራሱ ነጋዴ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ማስወገድ የሚቻለው የሸማቾች ጥበቃ ሲኖር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለምርታማነት ማሻሻያው ቢነግሩን?

ካፒቴን አየለ፡- ቀደም ሲል ‹‹ናሽናል ፕሮዳክቲቭ ሴንተር›› በሚል መጠሪያ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር ነበር የተቋቋመው፡፡ የሥራውም እንቅስቃሴ ብረታ ብረቶችን በመጠገን ላይ ያተኮረ ወርክሾፕ ነበር፡፡ ከተረከብነው በኋላ ከዩኤንዲፒ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ኢንስቲትዩቱን በአዲስ መልክ አደራጀው፡፡ መጠሪያውም፣ ‹‹የምርታማነት ማሻሻያ ማዕከል›› ተባለ፡፡ ስያሜውንም ያወጣሁለት እኔ ነኝ፡፡ በአዲስ መልክ ያደራጀነውም ከፖላንድ ከመጣ አንድ ኢንጂነር ጋር በመሆን ነው፡፡ የማዕከሉ ዓላማ በትንሽ ወጪ ብዙ ማምረት ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም በተለያዩ ተቋማት ወይም ፋብሪካዎች የሚገኙ የወርክሾፕ ማኔጀሮችን ያሠለጥናል፡፡ የሥልጠናውም መሠረተ ሐሳብ የተሰበረ ብረትን ለመበየድና ለመጠገን የሚውለው ገንዘብና ጊዜ፣ የተበየደው ወይም የተጠገነው ብረት ምን ያህል አካክሶታል በሚለው ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኤርትራ በ1974 ዓ.ም. በተካሄደው ቀይ ኮከብ ሁለገብ አብዮታዊ ዘመቻ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ዘመቻው ሁለገብ ቢሆንም በተለይ የወታደራዊው እንቅስቃሴ አልተሳካም፡፡ ምክንያቶቹን ቢያብራሩልን?

ካፒቴን አየለ፡- ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው፡፡ ጥቂቱን ብቻ ልንገራችሁ፡፡ በአልጌና፣ በናቅፋና በከርከበት ዕዞች ሥር ለውጊያ ከተሠለፈው ጦር መካከል አብዛኞቹ ልምድና ብቃት የሌላቸው፣ በግዳጅ ታፍሰው አጫጭር ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ የተሠለፉ ወጣቶች ናቸው፡፡ አንድ የወገን ጦር ድል ሊቀዳጅ የሚችልበት በርካታ አካሄዶች ቢኖሩም፣ ስለጠላቱ ምንነት ማወቅና ጣላቱን አምርሮ መጥላት በጠላቱ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀትና ድሉን ለመጨበጥ ታላቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ታፍሶ ሥልጠና ከገባ በኋላ የተሠለፈው ጦር ግን ጠላቱን አያውቀውም፡፡ ለምን እንደሚዋጋ የሚገልጽ ዓላማም የለውም፡፡ የቀሰመውም ሥልጠና የይድረስ ይድረስ ከመሆኑም በላይ እሱንም ቢሆን ሳያጠናቅቅ የተሰማራ ነው፡፡ በዚህ በኩል ስማቸውን ልገልጽ ከማልፈልገው አንድ ጄኔራል ጋር ተጣልቼ ነበር፡፡ የጥሉም መንስዔ ያመጣችሁት ጦር በወጣቶች የተገነባ ቢሆንም፣ በቂ ሥልጠና አልወሰደምና ውጊያ ውስጥ ሲገባ ችግር ይፈጥራል አልኩ፡፡ ጄኔራሉ ደግሞ፣ ‹የለም በዒላማ ተኩስ ልምምድ ላይ እያንዳንዱ ምልምል አሥር ጥይቶች ተሰጥቶት በስድስት ጥይቶች ዒላማውን መትቷል፡፡ ይህም ለውጊያ ዝግጁ የሚያደርገው ማስረጃ ነው› አሉኝ፡፡ የዒላማ ተኩስ አንድ የቆመ ነገርን አልሞ መምታት ነው፡፡ የቆመውም ነገር ስለማይንቀሳቀስ ለዒላማ ምቹ ነው፡፡ ውጊያ ውስጥ ከገባ ግን ቆሞ የሚጠብቅ ጠላት የለም፣ ይንቀሳቀሳል፡፡ የሚንቀሳቀሰውን አካል ደግሞ አልሞ መምታት ያስቸግራል፡፡ ከዚህ አኳያ በስድስት ጥይቶች የቆመን ዒላማ መምታት ለውጊያ ብቁ ያደርገዋል መባሉ ተረት ተረት ነው የሚሆነው ብያቸው ነበር፡፡ ምንም ሳይመልሱልኝ ትተውኝ ሄዱ፡፡ መደበኛው ጦር ደግሞ ከ17 ዓመታት በላይ ያህል ሳህል ተራራ ላይ መዋል፣ ማደሩና መዋጋቱ ሰልችቶታል፡፡ እንደማንኛውም ሰው ልጆች፣ ሚስት፣ በአጠቃላይ ቤተሰብ አለው፡፡ ስለዚህ የቤተሰቡም ናፍቆት ይቆጠቁው ነበር፡፡        

ሪፖርተር፡- አሁን መንግሥት የባህር ኃይል እንደገና ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ካፒቴን አየለ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ከባህር ኃይል ባልደረቦች መካከል ከአንዳንዶች ጋር ተወያይተናል፡፡ በመጀመርያ ወደብ አልባ አገር ሆኖ ባህር ኃይል መገንባት ይከብዳል፡፡ የንግድ መርከብ ከሆነ ግን ይቻላል፡፡ ባህር ኃይል ደግሞ ያለመርከብ ምንም ማለት አይደለም፡፡ መርከበኛ በመርከብ እንጂ በእግረኛ የሚዋጋ አይደለም፡፡ የመርከቦች ማቆሚያና ሠራዊቱን ማሠልጠኛ ቦታ ከየት ይመጣል? በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት በዓመት አንድ ጊዜ በጥር ወር የባህር ኃይል ቀን ይከበራል፡፡ በበዓሉ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ይገኛሉ፡፡ ከመላው ዓለም ከሚገኙት ባህር ኃይሎች መካከል አብዛኞቹ አዛዦች የየራሳችን የጦር መርከብ ይዘው በመምጣት በበዓሉ ይታደማሉ፡፡ ይህም ሥነ ሥርዓት ‹ሚኒ ዩናይትድ ኔሽንስ› (ትንሹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) የሚል ቅፅል ስም ነበረው፡፡ በዕለቱም መርከቦቻችን በባህራችን ላይ የባህር ላይ ውጊያ ያካሂዳሉ፡፡ ተኩስ ከየአቅጣጫው ይከፈታል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ‹ሔዝ ሚጂሲቲ ሺፕ› በተባለችው መርከብ ላይ ቁጭ ብለው በጦር ሜዳ መነጽር የውጊያውን ሥርዓት ይከታተላሉ፡፡ አሁን ባህር ኃይል ቢቋቋም ማን ባህር ላይ ሆኖ ነው የተኩስ ልምምድ የሚያደርገው? በሚከራይ ባህር ላይ ባህር ኃይልን ማቋቋም የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ ከኤርትራ ወደቦች መካከል በአንደኛው ላይ እናቋቁም ቢባል እንኳን በሁለቱ አገሮች መካከል አንድ ቀን ጠብ ቢፈጠር የሚያስከትለውን ጉዳት ማየት ይገባል፡፡