Skip to main content
x
የማያመልጡት ጭስ

የማያመልጡት ጭስ

ለመጀመርያ ጊዜ ትምባሆ መጠቀም የጀመሩት ሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ነባር ነዋሪዎች ወይም ቀይ ህንዶች ናቸው፡፡ ክርስቶፈር ኮሎምቦስ የተባለው አሳሽ ሰሜን አሜሪካ ‹ጭስ የሚበሉ ሰዎች አየሁ ወይም አገኘሁ ብሏል፡፡ በዘመኑ አውሮፓ ውስጥ እሱ እንደሚለው ጭስ መብላት አልተለመደም ነበርና ክስተቱ ለሁሉም እንግዳ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግራ ራሱ ጭሱን ሞክሮት በትምባሆ ሱስ ተጠልፎ ይህንኑ ልምድ ወደ አውሮፓና ስፔን እንዳሸጋገረው፣ ቀኝ ገዥዎች ደግሞ ወደ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ እንዳሸጋገሩት ታሪካዊ ዳራው ያስረዳል፡፡ የ700 ዓመታት ታሪክ ያለው ትምባሆ ወደ አፍሪካ የገባው በ17ኛው ክፍለ ዘመን በፖርቱጋሎች አማካይነት ነበር፡፡

ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይካትሪክ ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ የሱስና ተያያዥ ችግሮች ሕክምና መከላከልና ተሃድሶ የመሳሰሉትን በካናዳ ዩኒቨርሲቲ ቶሮንቶ ተጨማሪ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ እንዲሁም ሱስና ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተመለከተ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡  ‹‹ትምባሆን ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሱሱ ነው፡፡ ሱስ በአንድ ባህሪ ተፅዕኖ ሥር መውደቅ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሱስ መገለጫዎች ወይም ሳይንሳዊ ትርጓሜዎች አራት ናቸው፡፡ ተደጋጋሚነት አንደኛው  መገለጫው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ውስጣዊ ግፊት ነው፡፡ ይህም ማለት እንደተነሳ መታጠበቢያ ቤት ከመሄድና ቁርስ ከመብላቱ በፊት ትምባሆ እንዲያጨስ ግፊት የሚያድርበት ነው፡፡ ሦስተኛው መገለጫ በራስ ላይ ቁጥጥር ማጣት ነው፡፡ በግልጽ የሚታዩ ጉዳቶች መፈጠር የሱስ ደረጃው አራተኛ ላይ መድረሱን ያመለክታል፡፡

ሰዎች ትምባሆን የሚጠቀሙት ለመዝናኛነት ሲሆን፣ በመነሻው ላይ የተለያዩ ምክንያቶች ይኑራቸው እንጂ አንዴ ከገቡበት በኋላ ሱሳቸውን ማስታገስ ቀዳሚ ኢላማቸው ይሆናል፡፡ ያላጨሱ እንደሆነ የመበሳጨት፣ እንቅልፍ የማጣት፣ ሥራ መሥራት አለመቻል፣ በአጠቃላይ ምቾትና ዕረፍት የማጣት ነገር እንደሚታይባቸው ከዶ/ር ሰለሞን ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሲጋራ ማጨስን መቆጣጠር አለመቻል፣ ተደጋጋሚ ወይም ሰቅሶ የሚይዝ የማጨስ ፍላጎት ማሳየት፣ ውድ ጊዜን ሲጋራ በማጨስ ማሳለፍን፣ ሥራ መሥራትና ትምህርት መማር አለመቻል፣ በሲጋራ ማጨስ ጉዳይ ግጭት ውስጥ መግባት (ከሥራ ባልደረቦችና ከቤተሰብ ጋር)፣ ውስብስብ የጤና ችግሮችና የመሳሰሉት የሲጋራ ሱስ የሚያስከትላቸው ቀውሶች ናቸው፡፡

ትምባሆ በውስጡ የሚገኘው ኒኮቲን ከሌሎች አደንዛዥ ዕፆች ከፍተኛ የሆነ፣ እንዲሁም ከኮኬይንና ሄሮይን ከሚባሉትም በላቀ ሁኔታ አንድ ሰው በሱስ እንዲያዝ የማድረግ ኃይል አለው፡፡ ‹‹በአገራችን ሞኖፖሊ የሆነ አንድ የትምባሆ ኩባንያ አለ፡፡ ሞኖፖሊ ስለሆነ እንደ ልብ በውድድር የተለያዩ የትምባሆ ኩባንያዎች እንዳይገቡ ይከለክልልናል የሚል ሐሳብ አለ፡፡ ነገር ግን ሞኖፖሊው በራሱ በአሁኑ ሰዓት ዕድገቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ሞኖፖሊውን ተቆጣጣረነዋል ቢባልም እውነት ለመናገር ይኼን ያህል ቁጥጥር አለ ለማለት አይቻልም፤›› ይላሉ፡፡

የአገሪቱ ሌላው ትልቁ ችግር በኮንትሮባንድ የሚገባው ሲጋራ ነው፡፡ በየዓመቱ ወደ አሥር ቢሊዮን ሲጋራዎች ይጨሳሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ በኮንትሮባንድ የሚገባ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ሲጋራ ውስጡ ምን እንዳለ ያልተፈተሸ ከመሆኑ ባሻገር የመጠቀሚያ ቁኑ ያለፈበትም ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳቱ ሁለት እጥፍ ነው፡፡ ሲጋራው በራሱ ጎጂ መሆኑ አንዱ ጉዳት ሲሆን፣ በኮንትሮባንድ በመግባቱ የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ችግር ደግሞ ሌላው ነው፡፡

ሲጋራን ከሥልጣኔ ጋር የማያያዝ ነገር ስላለ ወጣቶች በቀላሉ ሊጀምሩት ይችላሉ፡፡ ሲጋራና ሌሎች ሱስ አስያዥ ነገሮችን የሚጀምሩትም በብዛት ከ20 ዓመት የዕድሜ ክልል በታች ያሉ ወጣቶች እንደሆኑ፣ እነዚህ ወጣቶች ለእንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የሚጋለጡት ለምንድነው የሚለውን ከማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከአንጎል ዕድገትም ጋር ማየቱ ተገቢ እንደሆነ ነው ተባባሪው ፕሮፌሰር የተናገሩት፡፡

አንጎል ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ አንደኛው የስሜት ዕድገት ክፍል ሲባል፣ ሌላው ደግሞ ተቆጣጣሪው ክፍል ነው፡፡ ልጆች መጎርመስ ሲጀምሩ የስሜት ዕድገት ክፍሉ ቶሎ ይበስላል፡፡ ስሜታዊና ደስታን የሚገልጽ ነገሮች ላይ ሰፍ ብሎ የመሞከር ነገር ይታይባቸዋል፡፡ ሁለተኛውና ተቆጣጣሪው የአንጎል ክፍል ግን ብስለቱ በጣም ዘገምተኛ ሲሆን፣ ዕድገቱ ሊቀንስ የሚችለው እስከ 20 እና 25 ዓመት ድረስ ባለው ዕድሜ ክልል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ወጣቶቹ በቀላሉ ስሜት ሰጪ ለሆኑ ነገሮች ሳያመዛዝኑ ሲሸነፉ ይታያል፡፡ በመሆኑም ቤተሰብና ሌላው አካል እንደእነዚህ ዓይነት ወጣቶችን በቅርብ መከታተልና መቆጣጠር እንዳለበት፣ ራሳቸውን ይችላሉ፣ ያስባሉ፣ ለምን ጣልቃ እገባለሁ ማለት ስህተት መሆኑን፣ ምክንያቱም የዕድገት ደረጃው ነገሮችን እንዲያመዛዝን እንደማይፈቅድለት ምሁራን ይመክራሉ፡፡ ይህንንም ሲሉ ቅርብ የወላጅ ክትትል ያላቸው ልጆች በሱስ የመያዝ ዕድላቸው ከሌሎቹ አንፃር በጣም አነስተኛ እንደሆነ በመግለፅ ነው፡፡

በአሜሪካ በብዛት፣ በእኛም አገር በተወሰነ መልኩ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ትምባሆ ከማጨስ ለመላቀቅ ከሚሞክሩ ሰዎች መካከል በራሳቸው ተሳክቶላቸው መተው የሚችሉ ስምንት በመቶ ያህሉ ናቸው፡፡ የባለሙያ ዕገዛ ምክርና መድኃኒት ሲጨመርበት የሚተው ሰዎች መጠን ግን በሦስት እጥፍ ከዚያም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል፡፡  

ባደጉ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ሕክምናዎችን የሚሰጡ የትምባሆ ማቆሚያ ክሊኒኮች አሉ፡፡ ተገቢው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ መድኃኒቶችና የምክር አገልግሎቶች ተሰጥቷቸው ከማጨስ እንዲላቀቁ ይደረጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ትምባሆን ሊተኩ የሚችሉ ቅመማ ቅመሞች (ማስቲካ፣ እንደ ከረሜላ የሚመጠጥ፣ እንዲሁም በክንድ የሚለጠፍ) እና አምሮትን የሚቀንሱ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ‹‹ቫሬን ክሊን›› የሚባል ትምባሆን እንዲተካ የሚያደርግ፣ በኪኒን መልክ የተዘጋጀና በጣም ውድ የሆነ መድኃኒት ይገኝበታል፡፡ አንድ ሰው ያንን መድኃኒት በሚውጥበት ጊዜ አንጎሉ ትምባሆን እንዳገኘ ይሰማዋል፡፡

ከፍ ብለው በዝርዝር ከተጠቀሱት መድኃኒቶች መካከል ሦስት ያህሉን አስፈላጊ መድኃኒቶች ተብለው ከምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦ ኤጀንሲ ዝርዝር ውስጥ ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ግዥ እየተካሄደ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የሕክምና አገልግሎቱና የሠለጠነ ባለሙያም የለም፡፡ 

የትምባሆ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኮሚቴ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ የትምባሆ ቁጥጥርን እያስተባበረ ይገኛል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የትምባሆ ቁጥጥርና የአደገኛ መድኃኒቶች ቁጥጥር ክፍል ባለሙያ አቶ ባህሩ ዘውዴ ናቸው፡፡

ይህ ዓይነቱ ኮሚቴ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች፣ በሐረሪ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎችም እንደተቋቋመ በቀሩትም ክልሎች የማቋቋሙ ሥራ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡

በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ የተቋቋሙትና ወደፊትም የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ሥልጣናና ተግባራቸው በዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ፍሬም ወርክ ኮንቬንሽን ኦን ቶባኮ ኮንትሮል ላይ የተቀመጡትን የፍላጎትና አቅርቦት ቅነሳ ስትራጂዎችን ማስተግበርና በ2007 ዓ.ም. የፀደቀውን የትምባሆ ቁጥጥር አዋጅን ላይ የተካተቱትን ድንጋጌዎች ማስፈጸም ይሆናል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከስትራቴጂዎች አንደኛው ፍላጎትን መቀነስ ነው፡፡ ይህንን ለመቀነስ ደግሞ ታክስና ዋጋን መጨመር ሌላውስ ትራቴጂ ነው፡፡ ታክስ በተጨመረ ቁጥር ዋጋ ከፍ እያለ ይሄዳል፣ ዋጋው ከፍ ሲል ደግሞ ሰው የመግዛት አቅሙ እየወረደና እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ለዚህም ምን ዓይነት ታክስ ነው መጣል ያለበት የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል በዓለም ጤና ድርጅትና በገንዘብ ሚኒስቴር ተጠንቷል፡፡

በጥናቱም መሠረት የኤክሳይዝና ሚክስድ ታክሶች ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከእነዚህም ጥናቶች መካከል የትኛውን ተግባራዊ ብናደርግ ይሻላል? የሚለው ሌላ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ መቼ ተጠናቆ ነው ተግባራዊ የሚሆነው? ለትምባሆ የተለየ ታክስ ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው? ሲል ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ባህሩ ሲመልሱ፣ ‹‹የተለየ ታክስ ያስፈለገበት ምክንያት ከቅንጦት ሸቀጦች መካከል ትምባሆ አንዱ በመሆኑ ነው፡፡ በየቀኑ በምንጠቀምባቸው ምግቦች ላይ የሚቆረጠውን ታክስ፣ ትምባሆ ላይ ከተጣለ ፍላጎትን የመቀነስ አቅሙ የወረደ ይሆናል፡፡ በተረፈ ጥናቱ በሒደት ላይ ነው ያለው፡፡ በከፍተኛ የሥልጣን ዕርከን ላይ ያሉትን ኃላፊዎች ውሳኔ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ የማስተባበር አቅማችን ጠንካራ ከሆነ ግን ቶሎ ወደ ተግባር መግባት እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡       

ሱስ የሚድን በሽታ እንደመሆኑ መጠን በትምባሆ ሱስ የተያዙ አጫሾችን በሕክምና ለማላቀቅ ወይም ለማዳን እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ በዚህም የተነሳ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በዓለም ጤና ድርጅትና በኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዕገዛና ድጋፍ አማካይነት ወደ 50 የሚጠጉ ባለሙያዎችን በዚህ ሕክምና ዙሪያ ማሠልጠን ቢቻልም እስከዛሬ ድረስ ወደ ሥራ እንዳልገቡ አቶ ባህሩ ገልጸዋል፡፡

ዋና መሥሪያ ቤቱ አሜሪካ የሚገኘው ካምፔን ቶባኮ ፍሪ ኪድስ (ከትምባሆ ነፃ የሆኑ ሕፃናትን የመፍጠር ዘመቻ) የሕግ አማካሪና የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ደረጀ ሺመልስ እንደገለጹት፣ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም. ተቀብላ፣ በ2007 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 822/2008 አፅድቃ የአገሪቱ የሕግ አካል አድርጋዋለች፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ኮንቬንሽኑን የማስፈጸም ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ኮንቬንሽኑ ሁሉን አቀፍ የሆነ በሳይንስ የተረጋገጠ፣ በጥናት የተመሰከረለት የቁጥጥርና የማስተማር ሥርዓቶችን ያካተተ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አቅርቦትንና ፍላጎት  ቁጥጥር የሚደረግበት ድንጋጌዎች ተካትተዋል፡፡ ከተካቱትም ድንጋጌዎች መካከል የትምባሆ ፍላጎትን ለመቀነስ ትምባሆ በሕፃናትና ለሕፃናት እንዳይሸጥ፣ ማንኛውም ዓይነት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የትምባሆ ማስታወቂያ እንዲከለከሉ፣ በትምባሆ ማሸጊያዎች ላይ የትምባሆን አደገኛነት የሚገልጹ፣ ገዳይነቱንና ለበሽታ አጋላጭነቱን የሚያመላክቱ ሥዕላዊ መግለጫዎችና የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲደረግ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡

አቶ ዳግም ዓለማየሁ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፣ ባለሥልጣናኑ ኮንቬንሽኑን ለማስፈጸም የሚረዳ የትምባሆ ቁጥጥር መመርያ አውጥቷል፡፡ ይህ ዓይነቱን የሽግግር መመርያ ወደ ወንጀል ድንጋጌ ማስገባትና የገንዘብ ቅጣት ማስጣል ግን አይችልም፡፡ የቁጥጥር ግዴታዎችን ሙሉ ለሙሉ ባካተተ መንገድ ጠንካራ የማስፈጸሚያ ሥልቶችን የያዘ አዋጅ ተረቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቁ ላይ ተወያይቶ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደመራውና በቅርቡ ፀድቆ ይወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት፡፡   

በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የትምባሆ አጠቃቀም አስመልክቶ በ2008 ዓ.ም. የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፣  ዕድሜያቸው 15 እና ከዚያ በላይ ከሆኑ ዜጎች መካከል 3.2 ሚሊዮን ወይም አምስት ከመቶ ያህሉ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ሲጋራ የማያጨሱ ሰዎች ሲጋራ ከሚያጨሱ ሰዎች በሚወጣ የሲጋራ ጭስ በስራ ቦታቸው 6.4 ሚሊዮን ወይም 29.3 በመቶ፣ በቤት ውስጥ ደግሞ 8.5 ሚሊዮን ወይም 12.6 በመቶ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው ‹‹ከሲጋራ ጭስ ነፃ›› የሚለው መመሪያ የሲጋራ ማጨሻ ቦታዎችን የመለየት ግዴታ ጥሎ ነበር፡፡ መመሪያው ይበልጥ ጠንካራ በሆነ አዲሱ መመሪያ ተሻሽሏል፡፡ በአዲሱ መመሪያ መሠረት የሲጋራ ማጨሻ ቦታ በምንም ዓይነት መልኩ መኖርም መዘጋጀትም እንደሌለበት የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ባለሙያ አስማማው በዛብህ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው በየትኛውም ሥፍራና ቦታ የሲጋራ ማጨሻ ቦታ ከተዘጋጀ ጭሱ በአየር ውስጥ በመትነን አካባቢን መበከሉ ስለማይቀር ነው፡፡ ከጤና አኳያም ሲታይ በትምባሆ ጪስ ከሚያደርሰው ጉዳት ሊድን የሚችል የሰውነት ክፍል እንደሌለ ዶክተር አስማማው አስረድተዋል፡፡