Skip to main content
x
‹‹በግድ መምህር ሁን ብለን የምንለፋው ወደ ሌላ ትምህርት ዘርፍ መግባት ያልቻለውን ነው››

‹‹በግድ መምህር ሁን ብለን የምንለፋው ወደ ሌላ ትምህርት ዘርፍ መግባት ያልቻለውን ነው››

ዶ/ር ኤልአዛር ታደሰ፣ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ በ2010 ዓ.ም. በግልና በመንግሥት ትምህርት ተቋማት ያደረገውን የኢንስፔክሽን ሥራ ከሳምንት በፊት ይፋ ባደረገበት ወቅት በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተጠኑ ጥናቶች ውጤትም ተገልጸው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት እያሽቆለቆለ መምጣትና ዩኒቨርሲቲው መምህራንን የሚያሠለጥንበት ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ከሚማሩት ሥርዓተ ትምህርት ጋር ምን ያህል የተጣጣመ ነው፡፡ የሚለው በጥናቱ ታይቷል በጥናቱ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሥርዓት ትምህርተ ኤክስፐርቶችና የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ጥናቱን ያስተባበሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኤልአዛር ታደሰ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት መቀነስ ላይ ዩኒቨርስቲው ጥናት ለመሥራት ያነሳሳው ምንድነው?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ጥናቱን እንድንሠራ የጠየቀን የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት እየቀነሰ ስለመምጣቱ መረጃ ስለነበራቸው በዩኒቨርሲቲው ሥርዓተ ትምህርት ባለሙያ፣ አመራሮችና የመምህራን አሠልጣኞች በተሳተፉበት ጥናቱ ተካሂዷል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ሥራ የተጀመረው መቼ ነው? በጥናቱስ የምን ያህል ዓመት ውጤት ተካቷል?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ጥናቱ በ2010 ዓ.ም. ኅዳር ላይ ነው የተጀመረው፡፡ ጥናቱ ሁለት ጉዳዮችን አካቷል፡፡ አንደኛው በ2010 ዓ.ም. የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ የእነሱ መምህራን፣ የሚማሩባቸውን ትምህርት ቤቶችና ወላጆች የተካተቱበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም. ያለውን የስምንተኛ ክፍል ውጤት ማለትም በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ውጤት ታይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ናሙና ያደረግነው በአዲስ አበባ ከሚገኙት አሥር ክፍለ ከተሞች አራቱን ማለትም ቦሌ፣ ጉለሌ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ናሙና የወስድነው 28 የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ነው፡፡ በዚህም ከ28 ትምህርት ቤቶች አፄ ቴዎድሮስ የተባለ ትምህርት ቤት ብቻ ነው፡፡ የሁሉንም ትምህርት ቤቶች ጥምር ውጤት 50 በመቶና ከዚያ በላይ ያመጡትን ያሳልፍ የነበረው ሌሎቹ 50 በመቶ አያመጡም ነበር፡፡ በየዓመቱም ላለፉት አሥር ዓመታት ውጤቱ እያሽቆለቆለ ይሄድ ነበር፡፡ በመሆኑም ማለፊያውን መቀነስ ነበር አማራጩ፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት 50 በመቶና ከዚያ በላይ አማካይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ያለፉት በአፄ ቴዎድሮስ ትምህርት ቤት ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የስምንተኛ ብሔራዊ መልቀቂያ ውጤት ላይ የተገኘው መረጃ ነው፡፡ ከመምህር፣ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች ጋር የተያያዘው ውጤት ምን ያሳያል?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ለመምህራንና ለተማሪዎች ቃለመጠይቅና መጠይቅ አድርገናል፡፡ በዚህም 295 መምህራን፣ 393 ተማሪዎች 112 የትምህርት ቤት አመራሮች፣ 14 ሱፐር ቫይዘሮች 56 የወላጅ ተማሪ መምህር ኅብረት አባላት ጋር የቡድን ውይይት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ከመምህራን ጋር የተደረገው ውይይት፣ ቃለመጠይቅና የጽሑፍ ጥያቄ መልስ ምን አሳየ?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- የመምህራኑ ለሥራው ካላቸው ፍላጎት ጋር ይያያዛል፡፡ አብዛኞቹ መምህራን መምህርነትን የመጀመሪያ ምርጫ አድርገው የገቡበት አይደለም፡፡ ባጣ ቆየኝ አይነት ነው፡፡ ተነሳሽነትም የላቸውም፡፡ በመጠይቁ ላይ ያየነው የዕውቀት፣ የማስተማር ዕውቀትና ክህሎት ላይ ከፍተት መኖሩን ነው፡፡ አስተማሪ ለመሆን ሥልጠና የወሰዱ ቢኖሩም አንድ ሰው ዕውቀቱ የሚዳብረው መጀመሪያ ለሙያው ፍላጎት ሲኖረው ነው፡፡ ብዙዎቹ መምህራን ሌላ ትምህርት እየተማሩ ነው፡፡ አካውንቲንግ፣ ነርሲንግና ሌላም እየተማሩ ነው እንጂ የያዙትን ሙያ እያሳደጉ፣ እየሠለጠኑ አይደለም፡፡ ፍላጎቱም የለም፡፡ ይህም ቀጥታ ለተማሪዎች የሚያካፍሉትን ዕውቀት ያሳንሳል፣ የማስተማር ፍላጎታቸውንም ይገድለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መምህርነት እንደመሸጋገሪያ እየተቆጠረ ነው ማለት ያቻላል?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ይህ የሚመራን መጀመሪያ እንዴት ለመምህርነት ተመለመሉ ወደሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ መግባት ያልቻለ ነው ወደመምህርነት የሚመጣው፡፡ ይህ ችግር ባልተቀረፈበት ነው በግድ መምህር ካልሆንክ ብለን የምንለፋው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደመምህርነት የመግቢያው ነጥብ ዝቅተኛ መሆን በተደጋጋሚ የሚነሳ ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ዩኒቨርሲቲያችሁ ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ኮተቤ መምህራን በማሠልጠን የቆየ ተቋም ነው፡፡ የቆዩ መምህራንም አሉት፡፡ መምህርነታቸውን የሚወዱና የሚኮሩበትም ናቸው፡፡ ይኼንን ለተማሪዎች ለማስተላለፍ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ፣ ያስተምራሉ፡፡ ችግሩ ግን መጀመሪያውንም ሙያውን የማይፈልጉና ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች የሚመደቡ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህንም ለማብቃት ግን ትግል እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ በኩል የተማረ ኃይል አገሪቷን መምራት አለበት ይባላል፡፡ በሌላ በኩል የተሟላ ብቃትና ፍላጎት የሌለው መምህር ተማሪ እንዲያሠልጥን ማድረጉ አይቃረንም?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ትምህርት የሌሎች ሙያዎች እናት ነው፡፡ በመሆኑም ወደመምህርነት የሚመጣ ሰው ተወዳዳሪና ብቁ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም መምህር በማኅበራዊ ሕይወት የሚሰጠውን ሥፍራ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ የደመወዝ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ቅቡልነት፣ መምህር የመሆን ፍላጎት፣ ክብርና ሌሎችንም ያካተተ መምህርነት የሚወደድበት ፖሊሲ ሊኖረን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ያሠለጥናለ፡፡ እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ ምን እተየሠራ ነው? ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተጀመረ ሥራስ አለ?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- በመምህራን ደረጃ የተለያዩ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ አሁን ባለው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ዩኒቨርሲቲያችን ሁለት ምሁራን አሳትፏል፡፡ በዚህ ተሳትፎ ያሉ ችግሮች የሚፈቱበት ሐሳብ ይቀርባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የሚመጡልንን ተማሪዎች ለማብቃት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ይህ ክፍተት መኖሩ ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በወላጆች በኩል የታየው ችግር ምን ነበር?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- በወላጆች በኩል በሚያሳዝን መልኩ፤ የትምህርት ቤትና የወላጅ ወይም የማኅበረሰብ ግንኙነት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የለም ማለት ይቻላል፡፡ በጣም ዝቅተኛ ግንኙነት ነው ያለው፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ ነው ከወላጅ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያለው፡፡ ትምህርት ቤቱ ከሌሎች በተለየ ውጤታማ የሆነበትንም ማጥናት አለብን ብለናል፡፡ ባጠቃላይ ባየናቸው ትምህርት ቤቶች ወላጅና ትምህርት ቤቱ አለመገናኘት ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ የልጆችን ትምህርት የመከታተል ሁኔታ ዝቅተኛ መሆኑን አይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ ትምህርት ቤቶች የነበራቸው አስተዋፅኦ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- የትምህርት ቤት አስተዳደር ሥርዓቱ አለ፡፡ መቆጣጠር፣ መደገፍ፣ መከታተል የሚል ሥርዓት አለ፡፡ ነገር ግን በብዛት የሚያተኩረው መቆጣጠር የሚለው ላይ ነው፡፡ ድጋፍ ማድረጉና ግብረ መልስ መስጠቱ ላይ ክፍተት አለ፡፡ ተማሪ መጣ አልመጣም የሚለው ላይ እንጂ ምን ተማረ? ምን አገኘ? መምህራኑ እንዴት አስተማረ? ምን ሥልጠና ያስፈልጋል? የት ጋር ክፍተት የት ጋር ጥንካሬ አለ? ለሚለው የግብረ መልስ ሥርዓት ቢኖርም ተግባራዊነቱ ይጎድላል፡፡ መንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ ሠርቷል፡፡ ይህም አንድ ክፍል ብዙ ተማሪ እንዳይኖር በሚል ነው፡፡ ሆኖም ያጠናናቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአንድ ከፍል በርካታ ተማሪ አይተናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ለማስተማር ይቸግራል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከተማሪ በኩል ያለው ክፍተት ምን ነበር?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ተማሪዎች የመማር ማስተማሩን ሒደት በሚያውኩ አካባቢዎች ይማራሉ የሚለውን ተማሪዎች ራሳቸው ተናግረውታል፡፡ በትምህርት ቤት ዙሪያ ጫት ቤቶች፣ ፑል ቤቶችና ሌሎችም መኖራቸው፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን አላግባብ መጠቀም፣ ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት ማነስ ተነስተዋል፡፡ የተማረ የት ደረሰ የሚል አመለካከት መኖር፣ የተመረቁ ተማዎች ሥራ አጥተው ዓመትና ሁለት ዓመት መቆየታቸውን በቤትና ከጎረቤት ማየታቸው ቤተሰብ ቶሎ ሥራ ወደሚያስገኝ ሥራ እንዲገቡ እንደሚፈልጉ፣ ቶሎ ደርሰው ቤተሰብ ለመርዳት ነጋዴ፣ ደላላ፣ ሹፌር፣ መሆን እንደሚመርጡና ባጭሩ ገንዘብ ወደሚገኝበት ማድላታቸው በጥናቱ ታይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዘ ጥናት ተደርጓል? ይኼንን ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የሠራነው ጥናት ለተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገብ ግብዓት ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጀ ትምህርት ቤት ለማስተማር መምህራን በዚያው ልክ ነው የሚሠለጥኑት፡፡ መምህራን የሚሠለጥኑበት ሥርዓተ ትምህርትና ተመርቀው ሄደው የሚያስተምሩበት ሥርዓተ ትምህርት ምን ያህል የተቆራኘ ነው? የሚለውን አጥንተናል፡፡ ለምሳሌ አንድ መምህር አካባቢ ሳይንስ የሚያሠለጥንበት ሥርዓተ ትምህርትና የሠለጠነው ትምህርት ምን ያህል የተጣጣሙ ናቸው የሚለውን አይተናል፡፡ ውጤቱም የመጣጣሙ ልክ መካከለኛ መሆኑን ነው ያሳየው፡፡ መንግሥት የሳይንስ ትምህርን የማስፋፋትና የመደገፍ ዕቅድ አለው፡፡ ሆኖም መምህሩ የሠለጠነበትና ተማሪዎች የሚማሩበት ሥርዓተ ትምህርት ሲታይ ቁርኝቱ ዝቅተኛ ነው፡፡ በ28ቱ ትምህርት ቤቶች በሁለተኛና አራተኛ ክፍል ሥርዓተ ትምህርት ላይ ነው ጥናቱ የተሠራው፡፡ ሒሳብ ትምህርት ላይ ያለው ቁርኝት ጥሩ፣ ኤስቴቲክስ የሚባሉት ላይ መካከለኛ፣ አካባቢ ሳይንስ ላይ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በይዘት፣ በዓላማ፣ በጊዜ፣ በማስተማሪያ ዘዴዎች አይጣጣምም ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ልጆቹ ከታች በተገቢው ሳይዘጋጁ ስምንተኛ ክፍል ይደርሱና ይወድቃሉ ወደሚል እሳቤ አድርሶናለ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ስምንተኛ ክፍል ላይ ለአዲስ አበባ ተማሪዎች የሚዘጋጀው ፈተና መጠናት እንዳለበት አይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን አስፈለገ?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- የፈተና ክብደትና ቅለት ማለትም የክብደቱ ደረጀ መታየት አለበት፡፡ ፈተናው የሚመጣው ባለው መስፈርት ልክ ነው ወይ? የሚለው መታየት አለበት፡፡ የእኛም ትኩረት አቅጣጫ ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቶቹ ተጠንተዋል፡፡ በቀጣይ ምን ይደረጋል?

ዶ/ር ኤልአዛር፡- ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የራሱን ድርሻ ወስዷል፡፡ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ ከዚህ ቀደም እንደምናደርገው አሁንም እናደርጋለን፡፡ በየትምህርት ክፍሉ ይኼን እናደርጋለን፡፡ የእኛ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ በኤጀንሲውና በትምህርት ቢሮው በኩል የራሳቸውን ድርሻ ወስደዋል፡፡ አብረን የምናስተካክለው ነው፡፡ እየተሠራ ያለው የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ብዙ ጥያቄዎችን ሊመልስልን ይችላል፡፡ ሰባተኛና ስምነተኛ ክፍሎች ከዝቅተኛ ደረጃ ወደከፍተኛ ደረጃ መሸጋገሪያ ድልድይ ናቸው፡፡ ይህ ድልድይ ደካማ የሆነበትን ሁኔታ ነው ያየነው፡፡ የሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል መምህራን ኮተቤ የሚማሩበትና ሄደው የሚያስተምሩበት ሥርዓተ ትምህርት 30 በመቶው ብቻ ነው ሙሉ ለሙሉ የተጣጣመ፡፡ ሄደው የሚያስተምሩትን የሚሠለጥኑት ጥቂት ሲሆኑ 70 በመቶ ያህሉ ባብዛኛው ሳይንስ ትምህርቶች ከሥርዓተ ትምህርቱ ጋር የተጣጣሙ አይደሉም፡፡ ይህ ማለት የሰባትና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን ማስተማር የሚችል እየሠለጠነ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቢሮው ዘጠኝና አሥረኛ ለማስተማር የሠለጠኑ መምህራንን ሰባትና ስምንት እንዲያሠለጥኑ እያደረገ ነው፡፡ ይህን የፖሊሲ ክፍተት ፎኖተ ካርታው ይፈታዋል ብለን እናስባለን፡፡ በሌላ በኩል በ1994 ዓ.ም. የወጣው የትምህርት ፖሊሲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢው በሚነገር ቋንቋ ይማር ይላል፡፡ ሆኖም እየተደረገ ያለው በእንግሊዝኛ ነው፡፡ ይኼንንም የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተካርታው ይፈታዋል ብለን እናስባለን፡፡