Skip to main content
x
‹‹በነዳጅ ላይ እየተከሰተ ያለው ችግር አሻጥር ነው›› አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹በነዳጅ ላይ እየተከሰተ ያለው ችግር አሻጥር ነው›› አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታወጣባቸው የገቢ ምርቶች ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነዳጅ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓመት እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ታወጣለች፡፡ በወቅታዊው የምንዛሪ ዋጋ ሥሌት አገሪቱ በዓመት ለነዳጅ ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ ታወጣለች ማለት ነው፡፡ የዚህን ያህል ዋጋ ተከፍሎበት የሚመጣው ነዳጅ ሥርጭት ግን ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተጠቃሚዎች ሲጉላሉ ይታያል፡፡ ነዳጅ የማይነካው ነገር የለምና የነዳጅ እጥረት ተፈጠረ ሲባል ብዙ ነገር ይናጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የመርከብ መዘግየት፣ ከወደብ ለማጓጓዝ የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቱ ደካማ መሆን በቶሎ ማከፋፈል አላስቻለም የሚሉ ምክንያቶች ሲሰጡ ነበር፡፡ በማደያዎች ነዳጅ ጠፋ ሲባል የመንገድ መበላሸት ገጥሞ ነው የተባለበትም ጊዜ አለ፡፡ አንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች ወርኃዊውን የነዳጅ የዋጋ ማስተካከያ ጊዜ ጠብቀው ቤንዚን የለንም በማለት፣ እጥረት የፈጠሩበት አጋጣሚም ይታወቃል፡፡ ሌሎች ምክንያቶችም ሲሰሙ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጊዜ እየጠበቀ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ባሉ ማደያዎች ነዳጅ ለማግኘት እየገጠመ ያለው ፈተና መንስዔ፣ ሕገወጥ የቤንዚን ንግድ መስፋፋት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ሕገወጥ ነጋዴዎችና ተባባሪያቸው በመመሳሰጠር ቤንዚንን ከነዳጅ ማደያዎች ያለቦታው እየቸረቸሩ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡ ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ኪዮስክ ድረስ ገብቶ እየተቸረቸረ መሆኑ በሥርጭቱ ላይ ፈተና እየሆነ ነው፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ዋነኛ መንስዔ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ችግሩ ይህ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያስፈልጋል ከሚባለው ነዳጅ በላይ እስከማቅረብ ቢደረስም፣ ሕገወጥ ንግዱ የነዳጅ እደላውን እየፈተነ ችግሩም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ የነዳጅ ሥርጭት የቁጥጥር ሥራ ባለቤት ያጣ ሆኗል ብለው ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ችግሮችንም ይጠቅሳሉ፡፡ የሰሞኑን የነዳጅ እጥረት መንደርደሪያ በማድረግ በአጠቃላይ የነዳጅ ሥርጭትና ችግሮች ላይ ዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያምን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለመቅዳት እየተቸገሩ ነው፡፡ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የለም ይላሉ፡፡ ነዳጅ ለመቅዳት መንገድ በመዝጋት ጭምር ወረፋ እየተጠበቀ ነው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም በነዳጅ ዕጦት ሥራቸው እየተስተጓጎለ ነው፡፡ መንገደኞችም እየተጉላሉ ነው፡፡ ይኼ የነዳጅ ችግር ምክንያቱ ምንድነው? የአቅርቦት ችግር ነው?

አቶ ታደሰ፡- አቅርቦት ላይ ችግር የለም፡፡ ሙሉ በሙሉ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ድርጅታችን በአግባቡ ነዳጅ አቅርቧል፡፡ በበቂ ሁኔታ ነዳጅ ማቅረብ ችለናል፡፡ እንዲያውም ለወር ከሚያስፈልጉ ከመጠን በላይ ያቀረብንበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁን በየቦታው የምናየው ቤንዚን ለመቅዳት የተፈጠረው ችግር አሻጥርና ሰው ሠራሽ ነው፡፡ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ድርጊት ነው ብለን ነው የምንገምተው፡፡

ሪፖርተር፡- አሻጥር ብለው የሚገልጹት ለምንድነው? እንዴት ዓይነት አሻጥር?

አቶ ታደሰ፡- ምክንያቱም በሎጂስቲክስ ዙሪያ ያለ ችግር አለ፡፡ በእርግጥ የአገራችን የነዳጅ አቅርቦት በጣም ኋላቀር ነው፡፡ ኋላቀር ነው ሲባል እስከ ሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር በመኪና ተነድቶ ነዳጅ የሚቀርብባቸው አገሮች በጣም ጥቀቂቶች ናቸው፡፡ ነዳጅ በቧንቧ፣ በባቡርና በመሳሰሉት መንገዶች ነው የሚቀርበው፡፡ የእኛ አንዱና ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡ የነዳጅ ሎጂስቲክስ ፈተና ነው፡፡ ምክንያቱም የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉት ተዋንያን ብዙ ናቸው፡፡ ትራንስፖርተሩ አለ፣ ሾፌሩ አለ፣ ጂቡቲ ላይ የእያንዳንዱ የነዳጅ ድርጅት ተወካይ አለ፡፡ እነሱ ራሳቸውን የቻሉ ንጉሦች ናቸው፡፡ ኖክ የራሱን አስቀምጧል፡፡ ቶታል የራሱን አስቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ወደ ሻሽመኔ ተብሎ ከእኛ የወጣ ነዳጅ ልክ ሾፌሩ ዘንድ ሲደርስ ተሰርዞ አዳማ ሊባል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ የማድረግ መብት አላቸው?

አቶ ታደሰ፡- በዚህ ዓይነት ነው የምንሠራው፡፡ አሁን በተጫነው መዳረሻ መሠረት በቀጥታ እዚያ ለመድረሱ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለውን ተግባር ማረጋገጥ የማትችሉ ከሆነ የእናንተ ኃላፊነት ምንድነው ታዲያ? ያስመጣችሁትን ነዳጅ በትክክል መሠራጨቱን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

አቶ ታደሰ፡- የእኛ ኃላፊነት በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ድርጅት ያቋቋመው ለአገሪቱ የሚበቃውን ነዳጅ በዓይነትና በጥራት እስከ ወደብ ድረስ አምጥቶ ለአከፋፋይ ኩባንያዎች ለመስጠት ነው፡፡ የእኛ ተልዕኮ እዚያ ላይ ነው የሚያበቃው፡፡ ከዚያ በኋላ የወሰድከውን ነዳጅ የት አደረስክ? ለማን ሸጥክ? እንዴት ሸጥክ? የሚለውን የሚቆጣጠረው ሌላ አካል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የመቆጣጠር ኃላፊነት የማነው?

አቶ ታደሰ፡- አሁን እዚህ ላይ ክፍተት አለ፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ዘንድ ብትሄድ እኔ የዋጋ ተመን አወጣለሁ እንጂ እኔን አይመለከተኝም፣ የሚመለከተው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን ነው ይላል፡፡ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒቴርን ብትጠይቅ ደግሞ መሠረተ ልማትንና ጥራቱን ነው የምቆጣጠረው እንጂ ሌላው አይመለከተኝም ይላል፡፡ ስለዚህ ሥርጭት ላይ ያለው አሠራር ክፍተት አለበት ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው የንግድ ፈቃድ ሲያወጣ በንግድ ፈቃዱ መሠረት ለገበያ የሚያቀርበውን ምርት ወይም ሸቀጥ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ በትክክል ለማድረስ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ የንግድ ፈቃዱን መመለስ አለበት፡፡ በነዳጅ በኩል ግን ችግር ታያለህ፡፡ ስለዚህ ይኼ ክፍተት በመኖሩ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ ፈተና እየሆነ ነው፡፡ አንድ መኪና ከጂቡቲ ተነስቶ አዲስ አበባ ለመድረስ ስንት ቀን ይፈጃል? ለሚለው ምንም የጊዜ ገደብ እንዲቀመጥ የተደረገ ነገር የለም፡፡ በሦስት ወይም በአራት ቀናት ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ወለንጪቲ አቁመው ይመጣሉ ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- ወለንጪቲ ነዳጅ የያዘ ተሽከርካሪ አቁሞ የመምጣቱ ምክንያት ምንድነው?

አቶ ታደሰ፡- ምንም ቁጥጥር እየተደረገ ባለመሆኑ ነው፡፡ ማንም ተቆጣጣሪ የለም፡፡ ተከታታይ የሌለው ሆኗል፡፡ የዛሬ ሁለትና ሦስት ዓመት እኮ ቶታልና ኦይል ሊቢያ ነዳጅ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጂፒኤስ መቆጣጠሪያ ነበራቸው፡፡ መኪኖቹ የት እንደደረሱ፣ የት እንደቆሙ ያውቁ ነበር፡፡ አሁን አንድ ከጂቡቲ ወጥቶ ወደ ፈለገበት ሲሄድ የት እንደደረሰ ወይም የት እንዳለ አይታወቅም፡፡ ነዳጅ ትልቅ ሀብትና ንብረት ነው፡፡ እዚህ ኅብረተሰቡ ነዳጅ ይመጣልኛል ብሎ ይጠብቃል፡፡ ግን የቁጥጥር መላላት ነዳጅ በአግባቡ እንዳይሠራጭ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ላይ እየተከሰተ ያለው ችግር አሻጥር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አሻጥር መገለጫው ምንድነው?

አቶ ታደሰ፡- ብዙ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ሰው የራሱ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል፡፡ አንደኛው ሕገወጥ ንግድ ነው፡፡ ቤንዚን ከማደያዎች በበርሜል ተሞልቶ ይወጣና በሕገወጥ መንገድ ይቸረቸራል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሰሞን ከተለያዩ ማደያዎች በሕገወጥ መንገድ በበርሜሎች የተሞላ ቤንዚን ሊወጣ ሲል ይዟል፡፡ ከአንድ ማደያ እንኳን እስከ 43 በርሜል የሚሆን ቤንዚን ተጭኖ በአይሱዙ ሲጫን ተይዟል፡፡ የቃሊቲ ፖሊስም እንዲሁ ወደ 28 በርሜል ቤንዚን ተጭኖ ሊወጣ ሲል ተይዟል፡፡ ይህ በአጋጣሚ የተያዘ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት አጥተን ለንግድ ሚኒስቴርና ለማዕድን ሚኒስቴር የላክነው ነገር ነበር፡፡ ይህም ጥናት በሐዋሳ፣ በሻሸመኔ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በወላይታ ሶዶ፣ በአጋሮና በመሳሰሉት ከተሞች የቤንዚን ሥርጭት እንዴት ነው? የሚለውን ይዘን ያደረግነው ጥናት ነው፡፡ ጥናቱ ያመለከተን በእነኚህ ከተሞች በየቦታው ነዳጅ እንደ ተራ ዕቃ እየተሸጠ መሆኑን ነው፡፡ አንድ ሊትር ቤንዚን 25 እና 30 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት ከነዳጅ ማደያዎች ውጪ በኪዮስኮችና በተለያዩ ቦታዎች በሕገወጥ መንገድ የሚሸጥ ነው?

አቶ ታደሰ፡- አዎ! በሱቆች ይሸጣል፡፡ ማደያዎች ማታ ሸኝተው (ሸጠው) ያድራሉ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር አዲስ አበባ ውስጥ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እንዲህ ያለው ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አዲስ አበባ ገባ፡፡ በዚህ ምክንያት ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር ብዙ ተነጋግረን ብዙ ቦታ ደርሰናል፡፡ ግን በሕገወጥ መንገድ ነዳጅ ይዘው የተገኙት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ አንችልም፡፡ የኛ ሥራ አይደለም፡፡ እንደ ነገርኩህ የእኛ ሥራ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ሱዳንና ጂቡቲ ላይ ካሠራጨን ሥራችንን ጨረስን ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ እንዲህ ሲሰቃይ እኛንም ያመናል፡፡ በጣም እያመመን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ነጋዴ የንግድ ፈቃድ ካወጣ በኋላ ፈቃድ በትክክል ስለመሥራቱ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ስለአሠራሩ ሊጠይቀው ይችላል፡፡ እናንተ ደግሞ የሥራ ግንኙነታችሁ ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ አከፋፍሉ ብላችሁ የሰጣችሁትን ነዳጅ በትክክል ስለመሠራጨቱ ማረጋገጥና ተጠያቂ የሚያደርግ አሠራር እንዴት አይኖራችሁም? ሊኖራችሁስ አይገባም ነበር?

አቶ ታደሰ፡- እኛ የለንም፡፡ የነዳጅ ኩባንያው ይህንን ያህል ቤንዚን ስጡኝ ብሎ ይጠይቀናል፡፡ በዚያ መሠረት እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ 300 መኪኖች በቀን ከጂቡቲ ይጭናሉ፡፡ 300 ተሽከርካሪዎች የሚጠይቁት ቤንዚን ነው፡፡ ናፍጣ አይጠይቁም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው? ናፍጣ በበቂ መጠን ስለሚቀርብ ነው? ቤንዚን ከናፍጣ በተለየ ፍላጎቱ የመጨረውና ለሕገወጥ ንግድ ይበልጥ የተጋለጠው ለምንድነው? በድንገት ሕገወጥ ንግዱ የተስፋፋው ለምንስ ይመስለዎታል?

አቶ ታደሰ፡- ቤንዚን የተለየ የሆነበት ሁኔታ አለ፡፡ ትልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ይኖረዋል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውጥረት በመፍጠር ሰውን ለማስኮረፍ የሚደረግም ይመስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቤንዚን ምቹ ነው፡፡ ምክንያቱም በሦስትና በአራት ሊትር ብዙ ኪሎ ሜትሮች ትጠቀማለህ፡፡ ለምሳሌ ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎቹ ሁለት ሊትር ቢያገኙ ግማሽ ቀን ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ቪትስ የሚባሉትና ሌሎች ትናንሽ ተሽከርካሪዎች አምስትና ስድስት ሊትር ቢያገኙ ቀኑን ሙሉ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ናፍጣን እንዲህ ባለው ሁኔታ ልትጠቀምበት አትችልም፡፡ ሲኖትራክን ብትወስድ ጉራንጉር ውስጥ ገብቶ አንድና ሁለት ሊትር ናፍጣ ሊቀዳ አይችልም፡፡ ምቹ አይሆንለትም፡፡ ቢቀዳም 70 እና 80 ሊትር ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው ሁኔታ ቤንዚን ለሕገወጥ ንግድ ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ሁለተኛ ሕዝብንም ለማስመረር የሚሠራ ይሆናል የሚል ግንዛቤ አለኝ፡፡ ምክንያቱም የዛሬ ሁለትና ሦስት ወር ያልነበረ ነገር አሁን የመጣበት ሆን ተብሎም ይሆናል፡፡  ሐምሌ፣ ነሐሴና መስከረም ላይ ምንም ችግር አልነበረም፡፡ አሁን ይኼ ነገር የተከሰተው ልክ ከጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ ነው፡፡ እስካሁን አልበርድ አለ፡፡ ቢቸግረን ሥርጭቱን እየጨመርን መጣን፡፡ ከመጠባበቂያ ዴፖ ጭምር አውጥተን ለሁለትና ለሦስት ቀናት ተጨማሪ ቤንዚን አሠራጨን፡፡ ከዚያ ለሁትና ለሦስት ቀናት አየነው፡፡ ግን ተመልሶ ያው ነው፡፡ ማቆሚያ ጠፋ፡፡  ስለዚህ ሰው ሠራሽ ችግሩ ብሷል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምታሠራጩትን ነዳጅ መጠን ጨምራችሁም ምንም የተለየ ነገር አለመኖሩን ካረጋገጣችሁ በኋላ ቀጣዩ ዕርምጃችሁ ምን ሆነ? ምንስ አደረጋችሁ?

አቶ ታደሰ፡- የእኛ ዕርምጃ ሳይሆን የሚመለከተው አካል ተግባር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እሺ ዕርምጃ መውሰድ አለበት የተባለው አካል ዕርምጃ እንዲወስድ ምን አደረጋችሁ? የሚመለከተው አካልስ?

አቶ ታደሰ፡- እኛማ መረጃውን እንሰጣቸዋለን፡፡ እከሌ የሚባለው ኩባንያ በቀን ይህንን ያህል ነዳጅ ጭኗል፡፡ በተለይ ለዚህ ከተማ ብሎ ይህንን ያህል ቤንዚን ጭኖ ሄዷል እንላለን፡፡ እንዲህ ያለውን መረጃ በየቀኑ እንሰጣለን፡፡ አሁን አሁን ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ያልተለመደ ነገር ታያለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ያልተለመደ ነገር?

አቶ ታደሰ፡- እዚህ መረጃ ላይ እንደምታየው (የዕለቱን የነዳጅ የሥርጭት ሰንጠረዥ እያሳዩ) ለምሳሌ ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. አንድ ኩባንያ ለወላይታ ሶዶ 49 ሺሕ ሊትር ጫነ፡፡ በዚያው ቀን 45 ሺሕ ሊትር ጫነ፡፡ እንደገና በሦስተኛው ቀን አሁንም ለወላይታ ሶዶ 46 ሺሕ ሊትር ጫነ፡፡  ስለዚህ እንዲህ ያለውን መረጃ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እንልካን፡፡ ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላትም ይላካል፡፡ ሌላም ምሳሌ ልጥቀስልህ፡፡ ከሰሞኑ ኅዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም. አንድ የነዳጅ ኩባንያ ለሻሸመኔ 46 ሊትር ጫነ፡፡ እንደገና በዚሁ ቀን 46 ሺሕ ሊትር ለሻሸመኔ ብሎ ተጫነ፡፡ ይህንን ያህል ለምን ጫንክ ብለን ብንጠይቅ እዚያ ሁለትና ሦስት ማደያዎች አሉኝ ሊል ይችላል፡፡ እዚያ ያሉት ደንበኞቼ ይህንን ያህል ናቸው ሊል ይችላል፡፡ ግን እዚያ ያለው የንግድ መምርያ ሊያጠራጥሩ የሚችሉ ጭነቶችን ማየት አለበት፡፡ አሁን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተዋረድ ስላልተዋቀረ፣ የንግድ መምርያዎችን ወይም የንግድ ቢሮዎችን ወኪል አድርጓል፡፡ በእነሱ አማካይነት ይህ ነገር በአግባቡ ሄዷል ወይ ማለት ነበረበት፡፡ ግን አይልም፡፡ አሁን ቢቸግረን ያደረግነውን ነገር ልንገርህ፡፡ ድሬዳዋ በጣም ችግር ነበር፡፡ ከንቲባው የንግድ ቢሮም ኃላፊ ነው፡፡ ሁልጊዜ የባጃጅ ሾፌሮች እኔን ያስቸግሩኛል ምን አባቴ ላድርግ? ይላል፡፡ በጣም ለሥራ ተነሳሽነት አላቸው፡፡ ከዚያ እኛ ለእናንተ የሚላከውን ተቆጣጠሩ አልን፡፡ ለእነሱ የሚላከውን መረጃ እናደርሳቸዋለን፡፡ ቶታል ወይም ኖክ ይህንን ያህል ጭኗል ብለን እንነግራቸዋለን፡፡ እነሱም ይከታተላሉ፡፡ ልክ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ቤንዚን ያዘጋሉ፡፡ ሄደው ከዲስፔንሰር ቆጣሪው ላይ ይመዘግቡና ጠዋት በአንድ ሰዓት ቆጣሪው ያለ መንቀሳቀሱን ዓይተው ይከፍታሉ፡፡ እንዲህ እያደረጉ መሥራት ከጀመሩ ወዲህ ችግሩ ጠፋ፡፡ ይኸው ያለ ችግር መሥራት ከጀመሩ ስድስት ወራት ሆኗቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከገለጻዎት መረዳት እንደቻልኩት የነዳጅ ሥርጭት አስቸጋሪ መሆኑን፣ የነዳጅ ሥርጭት ነባለቤት እያጣና ተቆጣሪ የሌለው ሆኗል እያሉኝ ነው ማለት ነው?

አቶ ታደሰ፡- አዎ! ባለቤት በማጣቱ እየተፈጠረ ያለ ችግር ነው፡፡ ባለቤት የለውም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ በየማደያው የነዳጅ እጥረት ተፈጠረ እያሉ እየጮኸ ነው፡፡ የነዳጅ አቅርቦት ችግር አለ እያለ በሚዲያው ብሶቱን እየተናገረ ነው፡፡ ሕዝቡ መጮሁ ትክክል ነው፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ግን ምን እየተሠራ እንደሆነ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ይጉላላል፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ በትክክል ምላሽ መሰጠት ያለበት ነገር መንግሥት ወይም የእናንተ ድርጅት በቂ የሆነ ነዳጅ እያቀረበ ነው? ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት  የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን በሚመጥን ደረጃ እየቀረበ ስላልሆነ የነዳጅ እጥረት መፈጠሩን የሚገልጹ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ታደሰ፡- ይኼውልህ (አኃዛዊ መረጃዎችን እያመላከቱ) የናፍጣ ከስምንት እስከ አሥር በመቶ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ቤንዚን በ13 በመቶ ነው የሚጨምረው፡፡ ይህንን መረጃ ይዘን ነው የምናቀርበው፡፡ መረጃውንም በደመ ነፍስ አይደለም የምንሠራው፡፡ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን በምናገኘው መረጃ ላይ ተመሥርተን ነው የምናቅደው፡፡ አሁን ያለው የመኪኖች ቁጥር በ17 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ነው የእነሱ ስትስቲክስ የሚያሳየው፡፡ ከዚህ ውስጥ የቤንዚን መኪኖችና ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች እየበዙ ስለመጡ፣ የቤንዚንም ፍላጎት በዚያው መጠን በ13 በመቶ እየጨመረ መጣ፡፡ ስለዚህ እኛም ይህንኑ ይዘነን ነው የምናቅደው፡፡ በዚህ  ዕቅዳችን መሠረት በሚገባ የሚፈለገውን ነዳጅ ገዝተን አስገብተናል፡፡ ለምሳሌ አምና የነበረው የቀን ፍጆታ ከ1.4 እስከ 1.5 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ በዚህ ዓመት ከ1.7 ሚሊዮን ሊትር እስከ 1.8 ሚሊዮን ሊትር ይሆናል ብለን ነው ያቀድነው፡፡ ልክ በዚሁ መሠረት ሐምሌ 2010 ዓ.ም. 1.8 ሚሊዮን ሊትር አሠራጨን፡፡ ነሐሴ ላይ በቀን 1.7 ሚሊዮን ሌትር አሠራጨን፡፡ መስከረም ላይ 1.7 ሚሊዮን ሊትር አሠራጨን፡፡ በእነዚህ ሦስት ወራት አንድ ኮሽ የሚል ነገር አልነበረም፡፡ ጥቅምት ላይ ግን አሁን እንደሚታየው ዓይነት ችግር ተፈጠረ፡፡ በነገራችን ላይ በጥቅምት ወር ለማሠራጨት አስበን ከነበረው በላይ ወደ 1.9 ሚሊዮን ሊትር እንዲሠራጭ አድርገናል፡፡ ይህ መጠን ከሚፈለገው በላይ ነው ያሠራጨነው፡፡ ከዴፖም እያወጣን የሥርጭቱን መጠን እያሳደግን እዚህ አደረስነው፡፡ እስከ ኅዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ 1.88 ሚሊዮን ሊትር ድረስ በቀን ተሠራጭቷል፡፡ ይህን ያህል ነዳጅ እያሠራጨን ገደል እየገባ ነው፡፡ ወይም የሆነ ነገር እየሆነ ነው፡፡ ይህንን የሚሰማ ሰው የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የነዳጅ ኩባንያዎቹና ማደያዎቹ ራሳቸው ችግር አለባቸው ወደሚለው ይወስደናል?

አቶ ታደሰ፡- አዎ! ኩባንያዎቹም ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ዝም ብሎ ለወላይታ፣ ለሻሸመኔና ለእከሌ ከተማ ተጭኗል ብቻ ሳይሆን እዚያ ለመድረሱ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ተጠያቂም የሚሆኑበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ነዳጅ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚወጣበትና ስትራቴጂካዊ ምርት ስለሆነ፣ ኩባንያዎቹ ሲያከፋፍሉ በትክክል መሠራጨቱን የማረጋገጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው ናቸውና ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ሊኖር ይገባል እያሉኝ ነው?

አቶ ታደሰ፡- በትክክል! አሁን ግን ኩባንያዎቹ እጥረቱ እየተፈጠረ ያለው የነዳጅ ድርጅት ስለማይሰጠን ነው ይላሉ፡፡ ይህ ፈፅሞ አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ በዚህን ያህል መጠን የሰጠናቸው ነዳጅ የት ገባ? ከጥቅምት ወር ጀምሮ የማናውቃቸው መኪኖች ከሰማይ ዘንበዋል? ወይም መዓት መጥቷል? በተረጋጋ ሁኔታ ይሠራጭ የነበረው ነዳጅ ዛሬ እዚህ የደረሰው ምን ሆኖ ነው? ኩባንያዎቹ ለዚህ ምን ምክንያት ይሰጣሉ? ይኼ ነገር ለምን በመስከረም፣ በሐምሌና በነሐሴ አልሆነም? ሰዎች በእነዚህ ወራት በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡት ለምንድነው? እስኪ የነዳጅ ፍላጎቱ ጨምሮ ይሆናል ብለን እኮ ስንጨምር ለምንድነው ያልተረጋጋው? እንደ ሰው እንደ ዜጋ ማሰብ አያስፈልግም ወይ? በጣም ሊቆረቁረን ይገባል፡፡ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ እናወጣለን፡፡ ለስኳር ሕመምተኞች የሚሆን ዶላር የለም እየተባለ እኮ ነው፣ ለነዳጅ ቅድሚያ እየተሰጠ  ይህንን ያህል ወጪ የሚወጣው፡፡ ይኼ እኮ በጣም ያማል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከነዳጅ ሥርጭት ጋር ያለው ችግር እንዲህ ባለው ደረጃ እየተገለጸ ከሆነ፣ የግድ አንድ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ ይህም እስካሁን የነበረውን አሠራር በማየት ማስተካከል እንደሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ አንጡራ ሀብት የሚፈስበት ነዳጅ በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋሉ፣ በባለቤትነት የሚያስተዳድረውና የሚቆጣጠረው አካል ሊኖረው እንደሚገባ በግልጽ የሚያመላክትም ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ የመንግሥት ዕርምጃ ምን መሆን አለበት? እርስዎ ጉዳዩን በቅርብ እንደማወቅዎና እንደ ባለሙያ ምን መደረግ አለበት ይላሉ? የመንግሥት አካሄድ ምን ይሁን?

አቶ ታደሰ፡- አንደኛ ሥርጭቱ ጤናማ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ኩባንያዎች በኃላፊነትና በባለቤትነት መሥራት አለባቸው፡፡ በየክልሉ ያላቸውን ሥርጭት በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ መረጃዎቻችን ላይ እንደምታየው አንድ ኩባንያ ለተለያዩ ከተሞችና ማደያዎች በርካታ መጠን ያለው ነዳጅ ወስዷል፡፡ ይኼ ከሱዳን የተነሳ ነው፡፡ ይህንን የወሰደው ከአንድ ኩባንያ ነው፡፡ አሁን 26 የነዳጅ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ሁሉም በዚህ መልክ ይወስዳሉ፡፡ ነዳጅ በማንና ወዴት እንደተጫነ መረጃውን በየቀኑ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንልካለን፡፡ ቤንዚን ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ይህንን እንዴት አደረግክ? የት አደረግክ? እንዲባል ነው የምንፈልገው፡፡ ምክንያቱም ሚኒስቴሩ በአዋጅ ሥርጭቱን ይቆጣጠራል ይላል፡፡ ግን ቁጥጥሩ እየተደረገ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ንግድ ሚኒስቴር ወይም ንግድ ቢሮዎች በሕገወጥ መንገድ የተቀዳ ነዳጅ ሲይዙ የሚወስዱት ዕርምጃ የለም፡፡  ስለዚህ ዕርምጃ ለመውሰድ የሕግ ክፍተት አለ ይሉሃል፡፡ ሰሞኑን አስኮ አካባቢ ከአንድ ነዳጅ ማደያ 57 በርሜል ቤንዚን ለመጫን ወደ ማደያው የገባ አንድ ተሽከርካሪ 43 በርሜሎች እንደ ሞላ ተያዘ፡፡ ከዚያ በኋላ የተወሰደው ዕርምጃ በሕገወጥ መንገድ የተቀዳውን ቤንዚን ለማደያው መመለስ ብቻ ነው፡፡ ምንም የተወሰደ ዕርምጃ የለም፡፡ እንዲህ ማድረግ ምን ማለት ነው? አሁን ስኳር ወይም ዘይት ቢሆን ጋዜጠኞች ተጠርተው እንዲህ ሲያደርግ ተያዘ ተብሎ ይጦዛል፡፡ ይኼ ከተራው ደሃ ጀምሮ እላይ እስካለው የናጠጠ ሀብታም ድረስ የሚነካ ነው፡፡ ጠቅላላ ኢኮኖሚውን የሚነካ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን የሚያናጋ ነው፡፡ ፖለቲካውንም ያናጋል፡፡ ማኅበራዊ ሕይወት ያናጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ገንዘብ ያውም በውጭ ምንዛሪ የሚፈስበት ምርት ባለቤት አጥቶ የማንም መጫወቻ ሆነ፡፡ ንግድ ቢሮ ይህንን ካልተቆጣጠረና መስመር ካልያዘ ምንድነው የሚሠራው? ከዚህ የበለጠ ሥራው ምንድነው? ችግሩ እንዲሁ ከቀጠለ ሽንኩርት፣ ጤፍና ሌሎች ምርቶች በምን ሊመጡ ነው? አጋጣሚ ሆኖ ናፍጣ ላይ ይህ ችግር የለም፡፡ ናፍጣውም እንዲህ ቢሆን ምን ሊደረግ ነው?

ሪፖርተር፡- የነዳጅ አቅርቦት ችግር አሁን ከተጠቀሱት ጋር ብቻ የተሳሰረ ሳይሆን ሌሎች ችግሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሎጂስቲክስ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በመኪና ማጓጓዝ ወጪ አለው፡፡ ጊዜም ይወስዳልና ይህንን ክፍተት በማየት ነዳጅን በባቡር ለማጓጓዝ እንዲቻል ተወስኖ፣ ለዚህ ተብሎ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ወጥቶ የባቡር መሠረተ ልማት ተዘርግቷል፡፡ ግን የነዳጅ ማመላለሻ ባቡሮች ተገዝተው ያለሥራ ተቀምጠዋል፡፡ በአጠቃላይ ነዳጅ ከማመላለስ ጋር ያለውን የሎጂስቲክስ ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ታደሰ፡- ሎጂስቲክስን ለመቀየር መሠራት አለበት፡፡ የባቡሩ ፕሮጀክት ሲከናወን የቅንጅት ችግር ነበር፡፡ ይኼን ኮርፖሬሽኑም ሌላውም አካል ያመነበት ነው፡፡ ምክንያቱም ባቡሩ ልክ እንደ መስመር ነው የተሰመረው፡፡ ከነገድ-ሰበታ ተብሎ የተሰመረ ነው፡፡ የተሠራው ለሦስት ነገሮች ነው፡፡ ሕዝብ ለማመላለስ፣ ደረቅ ጭነት ለማጓጓዝና ለፈሳሽ ጭነት አገልግሎት ነው፡፡ የፈሳሽ ጭነት አገልግሎት ለመጀመር ጂቡቲ ላይ ካለው ሆራይዘን ኩባንያ ጋር መስመሩ መገናኘት አለበት፡፡ እኛን ማገናኘት አለበት፡፡ ይህንን ለማከናወን እኛ በቂ የሆነ ዝግጅት ማድረግ ስላለብን አዋሽ ላይ 3.6 ሚሊዮን ሊትር የሚይዝ ዴፖ ሠራን፡፡ ይህንን የሠራነው በባቡር የሚያመጣውን ነዳጅ እዚያ ለመቀበል ማለት ነው፡፡ ይህንን ዴፖ በሦስት ዓመት በመገንባት አዘጋጅተን እየጠበቅን ነው፡፡ በሆራይዘንም በኩል የሆራይዘን ባለቤቶች ያው ዳተኛ ናቸው እንጂ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም መቼና እንዴት የሚለው ነገር ፈጽሞ መስመር ሊይዝ አልቻለም፡፡ ዋገኖቹ (የነዳጅ ማመላለሻዎቹ) ከመጡ አራተኛ ዓመታቸውን ሊይዙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ያለ ሥራ አራት ዓመት መቀመጥ ነበረባቸው? እስካሁንስ ያለሥራ መቀመጣቸውስ አግባብ ነው? አይበላሹም?

አቶ ታደሰ፡- ብረት ነው፡፡ ብዙ ባይበላሽም እንኳን ገቢ አለማስገኘቱ በራሱ ውድቀት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የረፈደም ቢሆን ይህንን የአገር ሀብት የወጣበት የነዳጅ መጫኛ የባቡር አገልግሎት ወደ ሥራ ለማስገባት ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ታደሰ፡- አንድ አገራዊ ኮሚቴ አለ፡፡ ጂቡቲዎችንም ያካተተ ነው፡፡ ተነጋግረን ኮርፖሬሽኑ የአዋሽ ዴፖን በባቡር ሐዲድ ለማገናኘት የዛሬ ሦስት ወር ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ የጨረታው ውጤት አልታወቀም፡፡ በጂቡቲም በኩል ሐዲዱን ለማገናኘት እየሠሩ ነው፡፡ ግን እንደሚፈለገው አይደለም፡፡ ስለዚህ እሱ ሥራ ላይ ቢውል ብዙ ነገሮችን ሊቀርፍልን ይችላል፡፡ በተለይ ከጂቡቲ አዲስ አበባ ነዳጅ ጭኖ የሚመጣው ባቡር አሥር ሰዓት ብቻ የሚፈጅበት መሆኑ ነው፡፡ እንደገና አንዱ ጎታች (ሎኮሞቲቭ) 70 የሚሆኑ የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ይተካል፡፡ ስለዚህ በቀን ሁለቱ ባቡሮች ቢመጡ የ140 ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎችን ይተካልና እንዲህ ያሉ እሮሮዎችን ያስቀራል፡፡

ሪፖርተር፡- የነዳጅ ሥርጭት ችግር ሲነሳ ሌላም የሚጠቀሰው፣ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶችና የነዳጅ ኩባንያዎች ለነዳጅ ሥርጭት በመንግሥት የተተመነው ታሪፍ አነስተኛ ነው በማለት የሚያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ ይህ እንደ ችግር የታያል፡፡ ምናልባት ይህ ጉዳይ እናንተን ይመለከታል?

አቶ ታደሰ፡- እኛን አይመለከትም፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ይህ የታሪፍ ጉዳይ በሥርጭቱ ሒደት ላይ እንደ አንድ ችግር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የታሪፍ ማስተካከያ አለመደረጉስ ተፅዕኖ ፈጥሯል ተብሎ አይታሰብም?

አቶ ታደሰ፡- እሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ማደያዎች ህዳጉ ስላነሰ ብለው የሚያደርጉት ነገር ይኖራል፡፡ አሁን እኮ በበርሜል የሚሸጠው ለምንድነው? ወደ ሌብነት እየተገባም ነው ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በበርሜል እየተቀዳ በምሽት የሚጫነውና የት እንደሄደ የምንቸገርበት ከጎረቤት አገር ንግድ ጋር የተያያዘም ሊሆን ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን ትጠቀማለች ተብሏል፡፡ በተለይ በቅርቡ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት በፈጠሩት የሰላም ስምምነት መሠረት የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን ለመጠቀም ተዘጋጅታለች፡፡ ስለዚህ ከነዳጅ ማመላለሻና ሥርጭት ጋር ተያይዞ በአሰብና በምፅዋ ወደቦች የመጠቀም ዕድል ይኖራል፡፡ በእነዚህ ወደቦች መጠቀም ቢቻል ሊመጣ የሚችል ለውጥ አለ? በወደቦቹ ለመጠቀም እንዲቻል በእናንተ በኩል ያሰባችሁት ነገር አለ?

አቶ ታደሰ፡- አስበናል፡፡ አሁን ለምሳሌ ዘንድሮ ነዳጅ ለመግዛት ጨረታ ስናወጣ በአሰብና በምፅዋ ወደቦች ብናስገባ በምን ያህል ዋጋ ታስገባላችሁ? ብለን በጨረታው ውስጥ አካተናል፡፡ ለዚህም ዋጋ ሰጥተውናል፡፡ ግን ክፍያ በወደቦቹ አካባቢ ያለው ‹ፋሲሊቲ› በተለይ አሰብ ትንሽ ዕድሳት ይፈልጋል፡፡ ምፅዋ ከእኛ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ግን ያሉትን እንዴት መጠቀም አለብን የሚለውን እያሰብን ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜ በእነዚህ ወደቦች ለማስገባት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በአሰብና በምፅዋ ወደቦች ብንጠቀም ምን ያህል ዋጋ ልንጠየቅ እንደምንችል መረጃውን አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሰብና በምፅዋ ወደቦች በኩል አሁን ባለው ደረጃ ነዳጅ ማስገባት ቢቻል ዋጋው ሊቀንስ ይችላል? ምን አያችሁ?

አቶ ታደሰ፡- ብዙ ባንጠቀምም ለሎጂስቲክሱ ምቹ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በምፅዋ በኩል ብናስገባ ለትግራይና ለሰሜን ጎንደር ምቹ ይሆናል፡፡ ከጂቡቲ ያን ያህል ኪሎ ሜትር ከምታጓጉዝ በምፅዋ ወደ ትግራይና ሰሜን ጎንደር ብትጭን ሎጂስቲክሱን ያሳልጥልናል፡፡ ፍጥነት ይጨምራል፡፡ እንደገናም ጂቡቲ ያለውን መጨናነቅ ይቀንሳል፡፡ ቅልጥፍናው ትንሽ ይጨምራል ብለን ነው የምንታገለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ እየታየ ያለው የነዳጅ እጥረት ሕገወጥ የቤንዚን ሽያጭ መሆኑ ከታወቀ፣ ተፅዕኖው እጥረት ከመፍጠሩ አልፎ ሊፈጥራቸው የሚችሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ይኖሩ ይሆን? በአጠቃላይ የችግሩን ተፅዕኖ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ታደሰ፡- ችግሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ፖለቲካዊም ይሆናል፡፡ ታክሲዎች ነዳጅ ሠልፍ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የለም ማለት ነው፡፡ ነገሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ይነካል፡፡ ስለዚህ ሕገወጥ ተግባራትን ለመከላከል ኅብረተሰቡ መተባበር አለበት፡፡ ነዳጅ በበርሜል ሲሸጥ ዝም ማለት የለበትም፡፡ ሌላው ደግሞ በበርሜል ተጭኖ ወጥቶ እንደገና ለተጠቃሚዎች ሲቸረቸር ቤንዚኑ ከምን ጋር ተቀላቅሎ እየተሸጠ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ በበርሜል እንዲከፋፈል ፈቃድ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ታደሰ፡- ይህ ፈቃድ ራቅ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች የሌሉባቸው ቦታዎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞችን አይመለከትም፡፡ ራቅ ላሉ አካባቢዎች በበርሜል መሸጥ ቢፈቀድም ቤንዚን ግን አይፈቀድም፡፡ በነዳጅ ‹ፍላሽ ፖይንት› የሚባል ነገር አለ፡፡ የቤንዚን ፍላሽ ፖይንቱ 13 እና 14 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው፡፡ ይህ ማለት በ13 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እሳት ሊነሳ ይችላል፡፡ ናፍጣ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ፍላሽ ፖይንቱ እስከ 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ አበባ ናፍጣ እሳት ሊያስነሳ አይችልም፡፡ ቤንዚን ግን ምክንያት ካገኘ ቦግ ይላል፣ ይቀጣጠላል፡፡ ምክንያቱም ፍላሽ ፖይንቱ ዝቅተኛ ስለሆነ እሳት ያስነሳል፡፡ ስለዚህ በአንድ አካባቢ ቤንዚን በበርሜል አስቀምጦ የሚቸረችር ካለ እዚያ አካባቢ ያለ ሰው አደጋ ላይ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲህ ባለው ተግባር ላይ  የተሰማሩ ሰዎችን በመጠቆም፣ ቤንዚን በየሠፈሩ እንዳይሸጥ መከላከል ግድ ይላል፡፡  በተለይ የንግድ ቢሮዎች አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ክልልም ያሉት በጥብቅ ሊቆጣጠሩ ይገባል፡፡ ቀደም ብሎ እንደነገርኩህ የድሬዳዋ ንግድ ቢሮ እንዳደረገው በዚያ መሠረት መቆጣጠር ይገባል፡፡ መንግሥት ይህንን ያህል ገንዘብ እያፈሰሰ የሚያስመጣውን ምርትና በተገቢው ሁኔታ እየቀረበ እያለ ግብይቱን የሚያበለሻሹ አሠራሮችን መግታት ያስፈልጋል፡፡ እኛ እዚህ የተቀመጥነው አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ደመወዛችንን የሚከፍለው ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ኃላፊነት የወሰዱ የንግድ ቢሮዎች፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርም በቅንጅት መሥራት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ለነዳጅ እጥረት መፈጠር ሌላው ምክንያት እንደሆነ እየተነገረ ያለው፣ በሕገወጥ መንገድ ለጎረቤት አገሮች የሚጓጓዝና የሚሸጥ መሆኑ ነው፡፡ እውነት ነው?

አቶ ታደሰ፡- የአገራችን የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፃር ከሱዳን በስተቀር የእኛ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በኤርትራ አንድ ሊትር ቤንዚን ሁለት ዶላር አካባቢ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ በጂቡቲ አንድ ሊትር ነዳጅ ከ48 እስከ 50 ብር ይሆናል፡፡ ኬንያ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ከ36 እስከ 38 ብር ነው፡፡ ስለዚህ የእኛን ነዳጅ ወደ ውጭ ለማውጣት የሚያበረታታ ነገር አለ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በየኬላው ቁጥጥርን ማጥበቅ ያስፈልጋል፡፡ ጉምሩክና የሚመለከታቸው አካላት በቅርብ እየተከታተሉ ይህንን የአገር ሀብት እንዳይባክን፣ ኅብረተሰቡ ላይም ችግር እንዳይፈጠር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነዳጅ በኅብረተሰቡ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከመሆኑ አንፃር ሁሉም ምርቱ የእኔ ነው ብሎ መሥራት አለበት፡፡