Skip to main content
x
ዳሸን ባንክ 1.14 ቢሊዮን ብር አተረፈ
የዳሸን ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ

ዳሸን ባንክ 1.14 ቢሊዮን ብር አተረፈ

በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ በ2010 የሒሳብ ዓመት 1.14 ቢሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ፡፡

ባንኩ የ2010 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን የተመለከተውን ሪፖርቱን ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ንዋይ በየነ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ትርፍ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ያመለክታል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱን ከታክስ በፊት ያገኘው የ1.14 ቢሊዮን ብር ትርፍ በአገሪቱ የግል ባንክ በ2010 ሒሳብ ዓመት ሁለተኛው ከፍተኛ ትርፍም ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ እንደ ባንኩ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ14 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በኃላ የተመዘገበው የትርፍ መጠኑ 928.9 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በቀደመው የሒሳብ ዓመት ደግሞ ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍ 814.8 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡  

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የትርፍ መጠን ዕድገት ማሳየቱ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠኑን ያሳደገለት መሆኑን አሳይቷል፡፡ ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን 430 ብር ያስገኘለት ሲሆን፣ በ2009 ሒሳብ ዓመት አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ መጠን 425 ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

  ከዚህ ባሻገር ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት ባንኩ 8.1 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሎ አጠቃላይ የተቀማጭ 36 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 29 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በዚህን ያህል ማሳደግ በመቻሉም የባንኩን የማበደር አቅም ማሳደግ ችሏል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመትም የባንኩ የብድር ክምችት መጠን 23 ቢሊዮን ብር መድረስ መቻሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የብድር ክምችት ከቀዳሚ ዓመት ጋር ሲነፃፀር 29 በመቶ ዕድገት ያለው ብድር ሊሰጥ መቻሉን ያሳያል፡፡ ባንኩ በቀደመው ዓመት የብድር ክምችቱ 17.8 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከባንኩ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ከፍተኛ ብድር የሰጠው ለአገር ውስጥ ንግድ፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለወጪና ገቢ ንግድ ነው፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ እንቅስቃሴ እመርታ የታየበት ስለመሆኑ የሚያሳዩ የተለያዩ አኃዛዊ መረጃዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ የባንኩን ጠቅላላ ሀብት በተመለከተ የቀረበው መረጃ ይህንኑ ያመለክታል፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት በ2010 መጨረሻ ላይ የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠን በ31 በመቶ ጨምሮ 45.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ባንኩ በተለይ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ውጤት ቢያስመዘግብም የተለያዩ ተግዳሮቶችን በማለፍ የተገኘ ነው ተብሏል፡፡

አቶ ንዋይ እንደጠቀሱትም ባለፈው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ምክንያት ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ተከስቷል፡፡ በፀጥታው ችግሮች በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ ባንኮችን ጨምሮ በአንዳንድ የንግድ ተቋማት ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ አንዳንድ የባንክ ቅርንጫፎች ተዘግተው ነበር፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም ባንኮች የሚያዘዋውሩት ጥሬ ገንዘብ ችግር ደርሶበት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ የመጣ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ውሳኔ ለተቋማቱ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በካፒታል መልክ በማስገባት አገሪቱ የገጠማትን አሳሳቢ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተወሰነ ደረጃ እንደሚያቃልል ይታመናል፡፡

በባንክ የሥራ ዘርፍም መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በዚህ መሠረት አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመራር በአገሪቱ ካሉ ባንኮች ጋር የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይት መደረጉን አውስቷል፡፡

ውይይቶቹንም ተከትሎ የተለያዩ መመርያዎች እንዲሻሻሉ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ፈጣን ምላሽ ዳሸን ባንክ ለአዲሱ የብሔራዊ ባንክ አመራር ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

ሆኖም መሻሻሎቹ እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ በአስገዳጅነት በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠው የ27 በመቶ የቦንድ ግዥና ካከማቹት የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ላይ የሚጠየቁት 30 በመቶ በአገር ጠቃሚ መሆኑ ቢታመንም፣ በባንኮች ገቢና የሥራ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ እየቀጠለ ነው ብለዋል፡፡