Skip to main content
x
ምክትል ከንቲባው ከዚህ በኋላ የሚፈናቀል አንድም አርሶ አደር እንደማይኖር ማረጋገጫ ሰጡ

ምክትል ከንቲባው ከዚህ በኋላ የሚፈናቀል አንድም አርሶ አደር እንደማይኖር ማረጋገጫ ሰጡ

ባለፉት 20 ዓመታት ቅሬታ ሲያቀርቡ የቆዩ የአዲስ አበባ ከተማ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ኑሮ እንደሚለወጥና ከዚህ በኋላ አንድም የሚፈናቀል አርሶ አደር እንደማይኖር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ማረጋገጫ ሰጡ፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ እሑድ ኅዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ተፈናቃይ አርሶ አደሮቹ በውይይቱ ላይ በርካታ ችግሮችን አንስተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በወቅቱ ከቦታቸው የተነሱበት የካሳ ገንዘብና በተለዋጭ የተሰጡዋቸው ቦታዎች ስፋት አነስተኛ መሆን፣ ቦታዎቻቸውም የሚገኙት ገደላ ገደል በሆኑ ሥፍራዎች መሆኑን፣ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆቻቸው ቤት መሥሪያ ቦታ አለመሰጠቱ፣ የግብርና ሥራ ካቆሙ በኋላ የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው ሕይወታቸውን እንዳከበደባቸው አስረድተዋል፡፡

ለችግሩ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ምክትል ከንቲባው ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የሚፈናቀል አንድም አርሶ አደር እንደማይኖር፣ የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚጎዱ ማናቸውም ሕጎች በጥናት ላይ የተመሠረተ ማስተካከያ እንደሚደረግባቸው አስታውቀዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባ የአርሶ አደሩም ናት፡፡ አርሶ አደሩን የገፋች አዲስ አበባ የትም አትደርስም፤›› ሲሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ማስፋፊያ ክፍላተ ከተማ በሚባሉት የካ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራኒዮ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ በርካታ አርሶ አደሮች በልማት ምክንያት ከቦታቸው ተነስተዋል፡፡

እነዚህ አርሶ አደሮች በአጠቃላይ ከ18 ሺሕ ሔክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የግብርና ሥራ ያካሂዱ እንደነበር፣ አርሶ አደሮቹ በተወካዮቻቸው አማካይነት ባቀረቡት ጥናት አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ቦታዎች ላይ የቤቶች ልማት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የመሳሰሉ ግንባታዎች ቢከናወኑም፣ አንዳቸውም ግንባታዎች አርሶ አደሮችን እንዳላካተቱ ተናግረዋል፡፡

በተለይ አርሶ አደሮችን ሲያስቆጣ የነበረው ቦታቸው ለልማት ተፈልጓል በሚባልበት ወቅት፣ በካሳ ክፍያ ሥሌቱ መሠረት የሚገኘው ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ ኑሯቸውን ያከበደ መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምትክ ቦታ አሰጣጡም ችግር ያለበት መሆኑ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በአርሶ አደሮቹ ተወካዮች አማካይነት በተሠራው ጥናት ይህንን ኮንነው ነበር፡፡

‹‹የምትክ ቦታ አወሳሰኑ ባለ ብዙ ጓዝ የነበረ አርሶ አደር እህል የሚወቃበትና የሚያከማችበት፣ ከብቶች የሚያሰማራበት፣ ለደስታም ሆነ ለሐዘን ዳስ የሚጥልበትን የአኗኗር ዘይቤ ከግምት ያስገባ አይደለም፤›› ሲል የተወካዮቹ ጥናት ያመላክታል፡፡

የአርሶ አደሮቹ ቅሬታ በመጨረሻ በከንቲባ ድሪባ ኩማ ጊዜ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ችግሩን የሚፈታ ‹‹የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት›› በሚል ስያሜ ተቋም ተቋቁሟል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአምስቱ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችንና ቤተሰቦቻቸውን በመመዝገብ ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡

ጽሕፈት ቤቱ አምስት ፕሮጀክቶች መርጦ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም የጀመረው እንቅስቃሴ ግን ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻለም፡፡

አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ችግር ፈትቶ አርሶ አደሮችን በፍጥነት የማቋቋም ዕቅድ መንደፉን አስታውቋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ እንዳሉት፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን የሚተካ ተቋም በቢሮ ደረጃ ይቋቋማል፡፡ ‹‹ባለፉት ሦስት ወራት የነበሩ የሕግ ክፍተቶች ተለይተዋል፡፡ አርሶ አደሮች ትክክለኛ ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ፣ ከዚህ በኋላም የሚወጡ ሕጎችና አሠራሮች ጥቅማቸውን ማስከበር የሚችሉ እንዲሆኑ ይደረጋል፤›› በማለት የአስተዳደሩን አቋም አስታውቋል፡፡

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፣ ከዚህ በኋላ የሚካሄዱ ግንባታዎችም አርሶ አደሮችን ማካተት እንጂ ማግለል የለባቸውም፡፡