Skip to main content
x
ኢትዮጵያዊው የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመረጡ
አቶ ተፈራ መኰንን

ኢትዮጵያዊው የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመረጡ

ኢትዮጵያዊው የአቪዬሽን ባለሙያ አቶ ተፈራ መኮንን የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና  ጸሐፊ ሆነው ተመረጡ፡፡

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን የአዲሱን ዋና ጸሐፊ ምርጫ ያካሄደው ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በሊቪንግስተን ዛምቢያ ነበር፡፡ አቶ ተፈራ ከቻድ፣ ከቡርኪና ፋሶና ከዛምቢያ ዕጩዎች ብርቱ ፉክክር የገጠማቸው ቢሆንም፣ በሊቪንግስተን በተካሄደው ጉባዔ ማብራሪያ ካቀረቡ በኋላ በተካሄደው ምርጫ ተፎካካሪዎቻቸውን በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት ማሸነፍ እንደቻሉ ታውቋል፡፡

አቶ ተፈራ መኮንን በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የ37 ዓመታት ልምድ እንዳላቸው ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ለረዥም ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2002 እስከ 2005 የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡

ሞንትሪያል ካናዳ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሆነው እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2014 ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ተቀጥረው ናይሮቢ በሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ፣ የሶማሊያን የአየር ክልል ለአንድ ዓመት ያህል በኃላፊነት አስተዳድረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 2015 ጀምሮ የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን በትራንስፖርት ዳይሬክተርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

አቶ ተፈራ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ ዲግሪ የተቀበሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋም በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪነት ሠልጥነዋል፡፡ በትራንስፖርት ኢኮኖሚክስና በአየር ትራፊክ ቁጥጥር አገልግሎት ዲፕሎማ እንዳላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ዳካር ሴኔጋል የሚገኘው የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅትና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ.ኤ.አ. 1964 የተመሠረተ ሲሆን፣ ዋና ኃላፊነቱም የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ሥራዎች ማስተባበር ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከአፍሪካ ኅብረት በተሰጠው ውክልና የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ምሥረታን በዋነኛነት ሲያስተባብር ነበር፡፡ አቶ ተፈራም ይህንኑ ሥራ በኃላፊነት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽንን በዋና ጸሐፊነት እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ሲመሩ የቆዩት ናይጄሪያዊቷ ኢያቦ ሶስና በጡረታ ከተገለሉ በኋላ፣ ኮሚሽኑ ባወጣው ማስታወቂያ የተለያዩ አገሮች ዜግነት ያላቸው 15 አመልካቾች ሲወዳደሩ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ በተደረገው ማጣራት አቶ ተፈራ የቅርብ ተፎካካሪያቸው የነበሩትን የቻዱን ተወካይ ሚስተር ጉልፒና ሴባህን በድምፅ ብልጫ እንዳሸነፉ ታውቋል፡፡

የቅጥር ሒደቱ አንድ ዓመት ተኩል ያህል የፈጀ ሲሆን፣ አቶ ተፈራ የምርጫ ቅስቀሳ ባካሄዱት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ተፈራ እንዲመረጡ የማሳመን ሥራ ከማከናወኑም በላይ፣ በሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የሚመራ ልዑክ ምርጫው ወደ ተካሄደበት ሊቪንግስተን ዛምቢያ በመላክ ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አቶ ተፈራ መኮንን እንዲመረጡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለተለያዩ አገሮች የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት ደብዳቤ የጻፈ መሆኑን፣ ዋና ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ከልዑኩ ጋር ወደ ሊቪንግስተን አብረው እንዳቀኑም ታውቋል፡፡