Skip to main content
x
የየመንና ሶሪያ ዜጎች በሸገር ጎዳና

የየመንና ሶሪያ ዜጎች በሸገር ጎዳና

ከአብዛኞቹ የዓረብ አገሮች መካከል በድህነት የምትታወቀው የመን የሺሕ ዓመታት ታሪክ ባለቤት፣ በቀደምት ሥልጣኔ ከሚታወቁት ውስጥ እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ከ40,000 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳላቸው የሚነገርላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የመቃብር ሥፍራዎቿ፣ ከ2,000 ዓመታት በፊት እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ጥንታዊዋ ሰንዓ የየመንን ቀደምትነት የሚመሰክሩ የሥልጣኔ አሻራዎች ነበሩ፡፡ የአልሳላህን መስጊድ ለመጎብኘት፣ በኤደን ባህረሰላጤ ለመዝናናት፣ ለሰኮትራ ደሴት ምትሀታዊ ውበት የሆነውን የአሸዋ ቁልል በፎቶ ለማስቀረት ወደ የመን የሚሄዱ ጎብኚዎች በርካታ ነበሩ፡፡ ደሃዋ ምድር የመን ኑሮ ለገፋቸው አፍሪካውያንም መዳረሻ እንደነበረችም አይዘነጋም፡፡

የመን ባለታሪክም፣ የበረሀ ገነትም፣ ደሃም ብቻ ብዙ ነገር ማለት ነበረች፡፡ የአሁኗ የመን ግን የውድመት፣ የእልቂት፣ የሰቆቃ ተምሳሌት ሆናለች፡፡ በጉግል መፈለጊያ ላይ የመን የሚለውን ቃል ሲከትቡ በመፈለጊያ ዝርዝሩ ከሚመጡት አማራጮች መካከል የየመን ቀውስ፣ የየመን የእርስ በርስ ጦርነት፣ የየመን ረሃብ የሚሉት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ ከ2011 በኋላ እየተባባሰ የመጣው የየመን ቀውስ የሰላምን ዋጋ የሚያዋድዱበት፣ የጦርነትን አስከፊነት የሚታዘቡበት ህያው ማሳያ ነው፡፡ የሺሕ ዓመታት ታሪክ ባለቤት የመን ነበረች እንጂ አለች ለማለት አያስደፍርም፡፡ በየጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ የመናውያን እንደ ጤዛ ሲረግፉ፣ በጥይት ሲደበደቡ፣ በፍንዳታ ሲናወጡ እስካሁን ኖረዋል፡፡ በቅርቡ ከተፈፀሙ ጥቃቶች መካከል አንዱን በምሳሌነት አንስተናል፡፡

አልጀዚራ እንደዘገበው፣ እ.አ.አ ማርች 26 ቀን 2018 በተፈፀመው ጥቃት ቢያንስ አሥር ሺሕ የመናውያን ተገድለዋል፡፡ 40 ሺሕ ያህሉ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እ.አ.አ በ2017 በትንሹ 50 ሺሕ ሕፃናት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የሕፃናት አድኑ ድርጅት በአማካይ በየቀኑ 130 ሕፃናት በጦርነቱ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ አስታውቋል፡፡ እስካሁን ከሞት የተረፉ ሦስት ሚሊዮን የመናውያን መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው በየአቅጣጫው እግሬ አውጪኝ ብለዋል፡፡

     አንፃራዊ ሰለም አለባቸው ተብሎ ተፈናቃዮቹ የሠፈሩባቸው አካባቢዎችም ተፈናቃዮችን ማስተናገድ የሚችል በቂ መጠለያ የሌላቸው፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያለባቸው፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ያልተዳረሰባቸው እንደሆኑ የሚያሳዩ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በ100 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ረሃብ የመንን እንደሚያሳቀይ ተነግሯል፡፡ እስከ 14 ሚሊዮን የሚደርሱ የመናውያን ለከባድ ረሃብ እንደሚዳረጉም ይገመታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት በከባድ ረሃብ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በምግብ እጦት በአጥንታቸው የቀሩ ሕፃናት ምስል እዚህም እዚያ እየታየ ይገኛል፡፡ 280 ሺሕ የሚሆኑ ወደ ተለያዩ አገሮች ገብተው የፓለቲካ ጥገኝነት ጠይቀዋል፡፡ የፖለቲካ ጥገኝነት ከተጠየቁ አገሮች መካከል ጂቡቲና ሶማሌ ላንድ ይገኛሉ፡፡ 

ሩቅ ምሥራቋ ሶሪያም የሰቆቃ ምድር ከሆነች ቆይታለች፡፡ እ.አ.አ ከ2011 የጀመረው የሶሪያ ቀውስ እስካሁን ከ500 ሺሕ በላይ የሚሆኑን ለእልቂት ዳርጓል፡፡ ከ200 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሟቾች በጦርነቱ ውስጥ ምንም ድርሻ የሌላቸው ንፁሐን ናቸው፡፡ እ.አ.አ እስከ 2016 ድረስ 11.2 ሚሊዮን ወይም የጠቅላላው ሕዝብ እኩሌታ የሚሆኑ ሶርያውያን በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች የፖለቲካ ቀውስ ጦሱ ለሌሎችም የዓለም አገሮች በተለይም ለምዕራባውያኑ ጭምር ተርፏል፡፡

ሕይወታቸውን ለማትረፍ እግሬ አውጪኝ የሚሉ በረሃውን አቆራርጠው ባህር ቀዝፈው ይታደጉናል ወደሚሏቸው ምዕራባውያን ሄደዋል እየሄዱም ይገኛሉ፡፡ አጋጣሚው ከባድ የስደተኞች ቀውስ የፈጠረባቸው አንዲት ነፍስ እንዳትጠፋ ዘብ የሚቆሙ አገሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ባህር ሲበላቸው ጆሮ ዳባ ልበስ እንዲሉ፣ ዕድሜያቸውን ሙሉ ከቆሙለት ዓላማ አፈንግጠው የራሳችሁ ጉዳይ እንዲሏቸውም ያስገደደ ጭምር ነው፡፡

አጋጣሚው ከመሞት መሰንበት ያሉ የሁለቱ አገሮች ዜጎች በቅርብ የሚገኙ ጎረቤት አገሮችን እንደ አማራጫቸው እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው ይመስላሉ፡፡ ጂቡቲና ሶማሌላንድን ጥገኝነት እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ የገቡም በየመንገዱ እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ በተለይም የሶሪያ ዜጎች በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ የዕርዳታ ወረቀቶችን ይዘው በየመንገዱና ካፌው ሲለምኑ እየታዩ ነው፡፡ ነጣ ያለ ቆዳ ያላቸው ሲለምኗቸው የደነገጡም ለሲሪያና ለየመን እንደ አዲስ አልቅሰዋል፡፡ በየካፊቴሪያው እየገቡ ሲለምኑ፣ በየመንገዱ ከመኪኖች ጋር ተቀዳድመው ለዕርዳታ እጃቸውን ሲዘረጉ ለአገሩ ሰላም ያልተጨነቀ የለም፡፡ አብዛኞቹ የየመንና የሶሪያ ስደተኞች ቋንቋ ባይችሉም ሁኔታቸው ብዙ ነገር ይላል፡፡

ትላንት የነበራቸው ማንነት ዛሬ ዋስ ሆኖ የሰው እጅ ከማየት አላወጣቸውም፡፡ ማን ያውቃል ዳቦ መግዣ ስጠኝ ብሎ እጁን የሚዘረጋው አባት የተሳካ ሕይወት የነበረው ዶክተር ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ሲሪያ›› እያለች ወጪና ወራጁ እንዳያልፋት የምትለማመጥ እናት ልጇን ጥይት በልቶት እንደሆነስ? ወዲያና ወዲህ እየተሯሯጡ እርዱን የሚሉ ታዳጊዎች ወላጆቻቸውን መንገድ ላይ ቀብረውስ ቢሆን? ሁሉም ትላንት የነበራቸው ማንነት ከአገራቸው ጋር ታሪክ ሆኖ የቀረ ይመስላል፡፡ ኑሮን አንድ ብለው እንደ አዲስ ለመጀመር አማራጫቸው ልመና ሆኗል፡፡ ለልመና እጃቸውን በዘረጉ መጠን የሰው ሁሉ ዓይን የሚከተላቸው እነዚህ ስደተኞች ሕፃን ተሸክመው ሲንከራተቱ ታይተዋል፡፡

ወቅታዊ ክስተት በሆነው በዚህ አጋጣሚ ጥቂት የማይባሉ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ያጋጠማቸውን አስተዛዝነው በመጻፍ ለብዙዎች ስሜታቸውን አጋርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሰላም ሲባል መልክ ካልያዘ እንደ የመንና ሶሪያ የመሆን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን በማግባባትና በማስጠንቀቂያ ያቀረቡም ነበሩ፡፡ ስደተኞቹ በብዛት ቦሌ አካባቢ የሚታዩ ሲሆን፣ አትላስ፣ ቦሌ መድኃኔዓያለም፣ ወሎ ሠፈር በተደጋጋሚ ጊዜ የሚታዩባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡

በሁለቱ አገሮች የተፈጠረው እልቂት ቢያሳዝናቸውም የስደተኞች ካምፕ በመግባት ፋንታ ጎዳና ላይ በልመና መሰማራታቸው እንዴት ይታያል ሲሉ የሚጠይቁም አልታጡም፡፡  ‹‹አገራቸው ላይ ችግሮ ኖሮ የሚመጡ እዚህ ጥገኝነት ጠይቀው መኖር ይችላሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ማንኛውም የውጭ ዜጋ በገባበት ቪዛ ነው መንቀሳቀስ የሚችለው፡፡ በሥራ ቪዛ የገባ ይሠራል፡፡ በቱሪስት ቪዛ የገባም እንዲሁ ከመጎብኘት ባለፈ ምንም ማድረግ አይችልም፤›› የሚሉት የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ዓለማየሁ ዜጎቹ በልመና የተሰማሩበትን ሁኔታ በቀጣይ እንደሚጣራ ገልጸዋል፡፡ 

በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ እንደማይኖሩ በእርግጠኛነት መናገር ባይቻልም በሺዎች የሚቆጠሩ የገቡት ግን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ ይዘው ነው፡፡ እንደ አቶ መንግሥቱ ገለፃ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 431 የሶሪያ ዜጎች በቱሪስት ቪዛ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 365ቱ ተመልሰው ወጥተዋል፡፡

እ.አ.አ ከኖቨምበር 2017 እስከ ኖቨምበር 2018 ድረስ 9,292 የመናውያን እንዲሁ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ፣ ከዚህ ውስጥ 8,965ቱ ተመልሰው መውጣታቸውን የሚናገሩት፣ በቦሌ ኤርፖርት የአየር ኬላዎች ማስተባበሪያ ኃላፊው አቶ አይከፋው ጎሳዬ ናቸው፡፡ ዜጎቹ የአንድ ወር የቱሪስት ቪዛ ተሰጥቷቸው የገቡ ሲሆን፣ ‹‹ምን ያህል እንደገቡ አሁን ላይ መረጃው ባይኖረንም በድንበር በኩል የሚገቡም ይኖራሉ፤›› ብለዋል፡፡