Skip to main content
x
የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ
ከግራ ወደ ቀኝ ጽሑፍ አቅራቢዎች አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስና ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ ሲሆኑ መድረኩን የሚመሩት የፍሬዴሪክ ኤበርት ስቲፍተንግ ባልደረባ አቶ ሰለሞን ጎሹ (መሀል) ናቸው

የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ

በብሩክ አብዱ

የፍሬዴሪክ ኤበርት ስቲፍተንግ (ኤፍኢኤስ) በሚያዘጋጃቸው መድረኮች በዋናነት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሳት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ውይይቶች እንዲደረጉ ዕድል ያመቻቻሉ፡፡ ተቋሙ ማክሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ያዘጋጀው ውይይትም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖሯቸው የሚችሉ ሚናዎችን በማንሳት አሁን ያሏቸውን ዕድሎች፣ ሥጋቶችና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ምን ይጠበቃል የሚሉት ነጥቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የውይይቱም መሪ ሐሳብ፣ ‹‹አዲሱ መርህ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› የሚል ነበር፡፡

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ነበሩ፡፡ እሳቸውም፣ ‹‹በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት ያሉበት ተግዳሮቶችና የወደፊት ዕጣ ፈንታ›› በሚል ርዕስ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ይሁንና በእሳቸው መቅረት ምክንያት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

አቶ ሌንጮ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ  ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉባቸውን ችግሮች ከውጭና ከውስጥ ተፅዕኖዎች አንፃር አንስተው የገመገሙ ሲሆን፣ በዋናነትም የፖለቲካ ቡድኖች በከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ብዙኃኑ ኅብረተሰብ የሚኖርበትን የገጠሩን ክፍል መዘንጋታቸውን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡድኖች እምብዛም አገራዊ ጉዳዮች እንዳሉ የማይቀበሉ መሆናቸውን፣ አብዛኞቹ በሐሜት ላይ በመንጠላጠል ከዋናው የፖለቲካ ተልዕኮ በላይ የአንዱን መልካም ስምና ተቀባይነት ለማጥፋት የሚያደርጉት ፍትጊያ እንደሚበዛ አውስተዋል፡፡

አቶ ሌንጮ አክለውም፣ ‹‹አሁን በኢትዮጵያ አሥጊ የሆነው ወደ ጠንካራ አምባገነናዊ ሥርዓት እንገባለን ወይስ ወደ ዴሞክራሲ እንሸጋገራለን የሚለው ምርጫ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት ሒደት ውጤታማ እንሆናለን ወይስ አንሆንም›› የሚል ነው፣ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም እያደገ የመጣው ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ቁጥርና የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሥጋት እንደሆነ፣ ታጋሽ መሆን እንደሚጠይቅና በተለይም በሕዝብ ቁጥር መጨመር ላይ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

መድረኩ የተለያዩ ምልከታዎች ያሏቸውን ሰዎች በአንድ ላይ ያመጣ ሲሆን፣ ይኼንን ውይይት ሐሳብ ለመስጠትና ቅርፅ ለማስያዝ አራት አወያዮች መድረኩን ይዘዋል፡፡ በሐሳብ አቅራቢነት የተሰየሙት የቀድሞ የኢዴፓ ሊቀመንበርና የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሕግ ማሻሻያ ቡድን አስተባባሪ ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ቡድን መሥራቾች አንዷ ወ/ሪት ሶልያና ሽመልስና በምሥረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኢብን) የሴቶችና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉባቸው የሚሏቸውን ፈተናዎች፣ ዕድሎችና ከተለያዩ ባለድርሻዎች የሚጠበቁ ተግባራትን አስረድተዋል፡፡

የመጀመርያውን ንግግር ያደረጉት አቶ ሙሼ ወሳኙ የውይይቱ አካል ዴሞክራሲን ማስፋት የሚለው እንደሆነ አውስተው፣ በተለይ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ምንም የተደረገ ነገር የለም ከሚለውና ቢያንስ የምርጫ ቦርድ በተቋም ደረጃ ተቋቁሟልና ጅምር አለ ከሚሉት መሀል ላይ ያለ ሐሳብ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ከተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ብለው በ1950ዎቹና በ60ዎቹ ከተመሠረቱ ፓርቲዎች ሕጋዊ መሠረትን የያዙ በመሆናቸውና ቢያንስ የፓርቲ ማቋቋሚያ አዋጅን ተከትለው በመቋቋማቸው፣ የተለያዩ እንደሚያደርጋቸው ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሥርዓቶቹ ብቁ እንዳልነበሩ፣ የተጀመሩትም መጨናገፋቸውን በማውሳት ፖለቲካ ውስጥ የገቡ ሰዎች ለስደት፣ ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ባለፉት 27 ዓመታት የተመሠረቱ ፓርቲዎች በብዛት ራሳቸውን የሚሸጡበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ የኮሙዩኒስት አደረጃጀት ስላለን ለምንፈልገው ሶሻል ዴሞክራሲም ሆነ ሊበራል ዴሞክራሲ የሚያመች አደረጃጀት የለንም፣›› ብለዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ስለሚደርሱባቸው ብቁ ተፎካካሪ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

በተጨማሪም አቶ ሙሼ እንደሚሉት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙያና በርዕዮተ ዓለም አንድ ላይ ከሚሰበስቧቸው ሰዎች ይልቅ በቤተሰብና በዝምድና ወይም ባላቸው የተለየ ቀረቤታ የተሰባሰቡ በመሆናቸው፣ ጠንካራ አደረጃጀትና አመራር ሊመሠርቱ እንዳልቻሉ፣ ይህም በቡድን የተደራጁ የተወሰኑ አካላት በፓርቲዎቹ ውስጥ እየተደጋገፉ መቆየትን እንጂ ጠንካራ ፓርቲን የመመሥረት ሕልሙ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹በተለያዩ ጊዜያዊ ችግሮችና መገፋቶች ምክንያት ፓርቲዎቹን በአባልነት የሚቀላቀሉ ግለሰቦች ስለሚበዙና የሚሰውለት የፖለቲካ ዓላማ ስለማይኖራቸው ሥራ ሲያገኙ ይንጠባጠባሉ፤›› ሲሉም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ አባላት ሊኖሯቸው እንዳልቻለ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ሙሼ ፓርቲዎች በከተማ ላይ የተንጠላጠለ የፖለቲካ አሠራር ስላላቸው ጥርት ያለ የመደብ ድጋፍ እንዳይኖራቸው ሆነዋል ሲሉ፣ የአቶ ሌንጮ ለታን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች እንዳሉ የሚቀበሉት ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ አለመቻልን እንደ ሌላ ችግር ያወሳሉ፡፡

‹‹ለምሳሌ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን መብት ከአገራዊ አንድነት አንፃር እንዴት ነው ማየት የምንችለው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በተጨማሪም ቡድናዊ መብቶች ላይ በማጠንጠን የተጠመዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገራዊ ጉዳዮችን መዘንጋት እንደሚታይባቸው፣ ይህ በተለይ በብሔር በተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በስፋት እንደሚስተዋል አስረድተዋል፡፡

እሳቸው ያነሱት ሌላው ጉዳይ ራዕይ ላይ መግባባት መፍጠር አለመቻሉን ነው፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ኢትዮጵያ ነው ልናይ የምንፈልገው?›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለሚታዩ ለውጦች የመንግሥት አካላት ቁርጠኝነት እንደማይታይባቸው፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን፣ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች (ለምሳሌ የክልልነትና የማንነት ጥያቄዎች) ብሎም የዴሞክራሲ ተቋማት ያለባቸው የብቃትና የገለልተኝነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፈተና ይሆናል ይላሉ፡፡

‹‹እነዚህን ተቋማት የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ትልቁ ፈተና ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ግንባታን ዕውን ለማድረግ የፓርቲና የመንግሥት መቀላቀል አንዱ ፈተና ሆኖ መቆየቱን ወ/ሪት ሶልያና ሽመልስ ያስረዳሉ፡፡ በፓርቲ ውስጥ በተከሰቱ ችግሮችም የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ችግር ላይ ይወድቃል የሚሉ ሥጋቶች እንደነበሩ፣ ያንን ፓርቲ ለማዳን ሩጫ እንደነበርና ተቃዋሚዎችም ተመሳሳይ አስተሳሰቦችን ሲያንፀባርቁ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

እሳቸውም የአቶ ሙሼን ሐሳብ በመጋራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠራ የርዕዮተ ዓለምና የመርህ ችግሮች እንዳሉባቸውና ግልጽ የሆነ አገራዊ አጀንዳ ማንፀባረቅ እንደሚሳናቸው ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ ሲያነሱም፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ስለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምን ያስባሉ የሚለው በግልጽ እንደማይታወቅና ተመሳሳይ ግልጽነቶች እንደሚጎሉ በበርካታ ዘርፎች እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በላይም የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአዴግን ጨምሮ ለሚከሰቱ ጉዳዮች ራስን ማዘጋጀት ከባድ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል፡፡

ወ/ሪት ሶልያና ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ግብባታ ሌላው ፈተና የሚሉት እየከረረ የመጣው ብሔርተኝነት ሲሆን፣ በዚህ ሳይወሰዱ መቆየት ለፓርቲዎች ከባድ ይሆንባቸዋል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ሕገ መንግሥቱ ፀረ ዴሞክራሲ ሆኖ በመቀረፁ፣ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ለብሔር ያደላ ስለሆነ ሌላው ፈተና እንደሚሆን ያስረዱት ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ  ናቸው፡፡

‹‹የእኛ ሕገ መንግሥት በውይይትና በክርክር ለመቀየር ለማይቻሉ ጉዳዮች ዕድል የሰጠ ነው፣ ለምሳሌ በጎሳ መደራጀት፡፡ ይህ ደግሞ ለዴሞክራሲ ግንባታ ፈተና ነው፤›› ይላሉ፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተሳሰቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ ከተነሱት መካከል አናሳ የሴቶች ተሳትፎ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ሚና፣ የትምህርት ሥርዓት ውጤታማነት፣ ደካማና እኩል ዕድል የሚሰጥ ሚዲያ አለመኖሩና የተለያዩ ጉዳዮች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንደ ፈተና ቀርበዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የመሥራት ችግር፣ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ አለማድረግ፣ ሁሉም ነገር በሕግና በሕግ ብቻ መደረግ እንዳለበት መግባባት ላይ አለመድረስ፣ በአመፅና በተቃውሞ ሁሉን ነገር የማስፈጸም አስተሳሰብ መኖርና ይኼንንም ወደ ትክክለኛው የፖለቲካ አስተሳሰብ ለማምጣት አለመቻሉ እንደ ፈተና ተነስተዋል፡፡

የሴቶችን ተሳትፎ በሚመለከት አስገዳጅ የማመጣጠን ሕግ አስቀምጦ መተግበር እንደሚቻል ያስታወቁት አቶ ሙሼ ሰሙ፣ በኬንያና በተለያዩ አገሮች ያሉ ልምዶችን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ሴቶች አጠቃላይ የፖለቲካ ተሳትፎ ፍላጎት እንዲኖራቸው፣ በሥልጠናም ሆነ በትምህርት ማብቃት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ ፈተናም ዕድልም ይዞ እንደመጣ በውይይቱ ላይ የተነገረ ሲሆን፣ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸውን ፕሮግራሞች ለወጣቱ በቀላሉ ለማድረስ መጠቀም እንደሚያስችላቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና ፓርቲዎች ግለሰቦች በሚጥሩበት ደረጃ ሲጥሩ እንደማይታይ ተወስቷል፡፡ ይህም ካላቸው ውስን የሰው ኃይልና የሀብት ማነስ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡ ስለዚህም ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ሲገኙ ግልጽ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

በቀጣይ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻዎች የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደሚጠበቁ የተነገረ ሲሆን፣ መንግሥት ሰላምን ማረጋገጥና ነፃና ገለልተኛ ምርጫን ማስጠበቅ እንደሚኖርበት ተወስቷል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ሁሉንም እኩል እንዲያገለግሉና መንግሥት በሚሰጠው አጀንዳ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸውንም አጀንዳ ይዘው እንዲቀርቡ የሚያስችሉ አሠራሮች እንዲፈጠሩ መደረግ እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ፓርቲዎች ውስጠ ዴሞክራሲያቸውን ማጠንከርና የሚፈለግ ርዕዮተ ዓለም ይዘው መምጣት እንደሚኖርባቸው ተወስቷዋል፡፡ ማኅበረሰብን የማንቃት ሥራ ማከናወን የሁሉም ኃላፊነት መሆኑም የተነገረ ሲሆን፣ ያገባኛል የሚል ኅብረተሰብ መፍጠርም አስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡

ጌታቸው (ዶ/ር) አሁን ፓርቲዎች ወደ ሥራ መግባት አለባቸው በማለት፣ ከደጋፊዎቻቸው ጋር መሥራትና እርስ በርስ ያላቸውን ቀረቤታና ግንኙነት ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው መስተጋብርም ግልጽ መሆን እንደሚኖርባቸውና ለምሳሌ በሪፎርሙ ምን ሚና መጫወት እንዳለባቸው መለየት አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ መንግሥትም የተጀመሩ ማሻሻያዎችን ከግብ የማድረስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትነትን ኃላፊነት ለመያዝ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ፣ በሕግ መሠረት የማስተዳደር ሥራ መከናወን አለበት፣›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡

‹‹በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶች በመብዛታቸው ጥሩ ዕድል ነው፤›› የሚሉት ወ/ሪት ሶልያና፣ ‹‹ፓርቲዎች ከሕዝቡ እምነት ለማግኘት እነዚህን ሪፎርሞች መጠቀም አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥትና ፓርቲ እንዲለዩ፣ አሁን እየተሻለ የመጣው የፖለቲካ ምኅዳር እንዳይንሸራተት መሥራት፣ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት፣ ሰላምና ደኅንነትን ማስጠበቅ፣ ስትራቴጂካዊ ትኩረት በማድረግ ወደ ፖሊሲ አማራጮች መሄድ፣ ከጽንፈኛ ብሔርተኝነትና ይኼንን ለመጠቀም ከሚደረግ እሽቅድድም ራስን መቆጠብ ብሎም በዴሞክራሲ ተቋማ አቅም ላይ ትኩረት ማድረግ የሚሉትን በምክረ ሐሳብነት ቀርበዋል፡፡

በተጨማሪም በውይይት የመግባባት ባህልን ማሳደግና የእኔን ካልተቀበልክ ከሚል አመለካከት መውጣት፣ በትምህርት ቤት የሚሰጡ እንደ ሥነ ምግባርና ሲቪክ ያሉ ትምህርቶችን ውጤታማነት መገምገም አስፈላጊ እንደሆነም ተወስቷል፡፡