Skip to main content
x
ንብ ባንክ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ በማድረግ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር አሳደገ
የንብ ባንክ የቦርድ አመራር አባላት የባንኩን የካፒታል ማሳደጊያ ሐሳብ ለባለአክሲዮኖች በማቅረብ አጸድቀዋል

ንብ ባንክ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ በማድረግ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር አሳደገ

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች የባንኩን ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ፡፡ ባለአክሲዮኖቹ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፉት ቅዳሜ፣ ኅዳር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡

የባንኩ ዳሬክተሮች ቦርድ የባንኩ ካፒታል ማደግ እንዳለበት የሚጠይቅ ሐሳብ ማቅረቡን ተከትሎ፣ ቀደም ሲል 2.2 ቢሊዮን ብር የነበረውን ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወስኗል፡፡ የባንኩ የተመዘገበ (የተፈረመ) ካፒታል 2.2 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከባንኩ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ እስከ 2010 ዓ.ም. ማጠናቀቂያ ድረስ 2.1 ቢሊዮን ብር የነበረውን ካፒታል፣ ሒሳብ ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ባንኩ ሙሉ ለሙሉ ከፍሎ አጠናቋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው በተስማማበት መሠረት፣ ካፒታሉን ለማሳደግ የአክሲዮን ሽያጭ ለባለአክሲዮኖች ብቻ እንዲካሄድ ስለመወሰኑም ታውቋል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንዣ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባንኩን ካፒታል ከዕጥፍ በላይ ማሳደጉ የባንኩን የወደፊት እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማሳደግ ያስችላል፡፡ እንደ አቶ ክብሩ ገለጻ፣ ባንኩ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ግንባታዎችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ባሻገር የባንኩን የ2010 ዓ.ም. የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያትተው፣ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ሒሳብ መጠን 21.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከ2009 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ5.1 ቢሊዮን ብር ወይም የ30.6 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ የተቀማጭ ገንዘቡ ዕድገት ባንኩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ እንደሆነ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወልደ ትንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ገልጸዋል፡፡ ዕድገቱ የተመዘገበው በሁሉም የሒሳብ ዓይነቶች እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የባንኩ አስቀማጮች ቁጥርም ባለፈው ዓመት ከነበረው 520,791፣ በ156,387 ወይም 30.4 በመቶ ጨምሮ ወደ 679,178 እንዳደገ ታውቋል፡፡ ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን ወደ 13.5 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ይህም አኃዝ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ2.8 ቢሊዮን ብር ወይም የ26.5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የተበዳሪዎች ቁጥርም ከ11,085 ወደ 11,626 ከፍ ብሏል፡፡ የብድር ስብጥሩ ሲታይም ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ ለማምረቻዎች 23.4 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድ 17.6 በመቶ፣ ለሕንፃ ግንባታ 13.3 በመቶ፣ ለወጪ ንግድ 15.2 በመቶ፣ ለገቢ ንግድ 14 በመቶ ዋና ዋናዎች ናቸው፡፡ ለሆቴልና ቱሪዝም 9.8 በመቶ ሲሰጥ፣ የቀረው ብድር ለትራንስፖርት፣ ለግብርና፣ ለማዕድን ኃይልና ለውኃ ዘርፎች፣ እንዲሁም ለሠራተኞችና ለግል ፍጆታዎች የዋሉ ብድሮች ተሰጥተዋል፡፡

በተሸኘው ዓመት 154.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው ንብ ባንክ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከ2009 ዓ.ም. አኳያ በ12.3 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. የተገኘው 166.9 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢው የቀነሰው የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አንፃር በ15 በመቶ እንዲቀንስ በመደረጉ፣ እንዲሁም ባንኮች ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ 30 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ በገዙበት ዋጋ እንዲሸጡ የሚያስገድድ መመርያ በመውጣቱ ነው ተብሏል፡፡ ይህም በባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ ቅናሽ መመዝቡን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

 የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 26.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ብር 21.1 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ26.4 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡

የባንኩ የሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ ገቢ 2.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 585.8 ሚሊዮን ብር ወይም የ30.9 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

የባንኩ ትርፍ ከገቢ ግብር በፊት 658.75 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ተመዝግቦ ከነበረው ብር 644.78 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር በ13.97 ሚሊዮን ብር ወይም 2.2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አቶ ወልደ ትንሳይ ጠቁመዋል፡፡ ከግብር ተቀናሽ በኋላ ባንኩ ያስመዘገበው የትርፍ መጠን 514.85 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ ካለፈው ዓመቱ የ493.74 ሚሊዮን ብር ትርፍ አኳያ የ21.11 ሚሊዮን ብር ወይም የ4.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳይፈታ መቆየቱና ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር መበራከቱ፣ ከሚሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 30 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ በመግዥያ ዋጋ እንዲሸጥ የሚያስገድድ አዲስ መመርያ መውጣቱ በባንኩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አሉታዊ ተፅዕኖ የነበራቸው ችግሮች ናቸው፡፡ የባንኩ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች መጨመራቸው፣ እንዲሁም ባንኩ በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን የተከፈለ ካፒታል ለሕንፃ ግንባታ እያዋለ መሆኑ በትርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረም ሪፖርቱ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

የባንኩ ቋሚ ንብረት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቅሶ፣ ይህ መጠን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 495.6 ሚሊዮን ብር ወደ 1.9 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል በመደረጉ በዘንድሮው ትርፍ ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም፣ ባንኩ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝለትን ሥራ እየሠራ ስለመሆኑ እንደሚያሳይ የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳድጋል የተባለውና በውጭ ኩባንያ ሲጠና የቆየው አዲሱ ስትራቴጂክ ፕላን ከአንድ ወር በኋላ ሥራ ላይ እንደሚውል አቶ ክብሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ክዋኔዎች የተካተቱበት ዕቅድ ባንኩን መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሳድገው እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡