Skip to main content
x
‹‹ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈልጉ የኤሌክትሪክ ኃይልና የትራንስፖርት ፕሮጀክቶችን በመንግሥትና በግል አጋርነት ለማከናወን የጨረታ ሒደት እየተጠበቀ ነው››

‹‹ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈልጉ የኤሌክትሪክ ኃይልና የትራንስፖርት ፕሮጀክቶችን በመንግሥትና በግል አጋርነት ለማከናወን የጨረታ ሒደት እየተጠበቀ ነው››

ተሾመ ታፈሰ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ

ተሾመ ታፈሰ (ዶ/ር) ዋና ዳይሬክተር በመሆን በቅርቡ በአዋጅ የተቋቋመውን የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የተሰኘውንና በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘውን መሥሪያ ቤት በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተመድበው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው መሾማቸው ቢታወቅም፣ ይኼንን ቃለ ምልልስ የሰጡት ግን ከአዲሱ ሹመታቸው ቀደም ብሎ ነበር፡፡ መንግሥት በግልና በመንግሥት አጋርነት አማካይነት ቢያንስ ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ የሚጠይቁ 17 ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መወሰኑን በማስመልከት መግለጫ ከሰጡ በኃላ ዝርዝር ጉዳዮቹ ምን እንደሚመስሉ አንባብያን ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይኼንኑ ጥያቄ ሊያስተናግድ ይችላል በማለት ከተሾመ (ዶ/ር) ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡-  የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት በሕግ ማዕቀፍ ቦርድ ተቋቁሞለትና ጽሕፈት ቤት ተከፍቶለት ሥራ ጀምሯል፡፡ ለረዥም ጊዜ ጥያቄ ሲቀርብበት የቆየ ጉዳይ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የዚህ ተቋም መመሥረት ምን ለማምጣት ነው ዓላማውስ ምንድነው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት እንደ ጽንሰ ሐሳብ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በተለይም በሕዝብ አገልግሎት ሰጪ መስኮችና በልማት ሥራዎች ላይ በጋራ በመሥራት ውጤታማና ለገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ ለማምጣት ብሎም የሕዝብን ፍላጎት ለማርካት እንዲያስችል በግሉ ዘርፍ ውስጥ ያለውን ዕውቀትና ገንዝብ ወደ ሕዝብ አገልግሎት ሥራዎች በማምጣት በአጋርነት የሚሠሩበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ አሠራር በዓለም ተተግብሮ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ውጤታማነቱም በተለይ ለዚህ ሥራ አግባብነት ያለው ሕግ፣ አግባብነት ያለው ተቋምና ተገቢው ሥርዓት ከተዘረጋለት ውጤታማነቱ አያጠያይቅም፡፡ እንዲሁ በዘልማድና ያለበቂ ዝግጅት ቢገባበት ግን ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ በግልና በመንግሥት መካከል በተለያዩ መስኮች ላይ አብሮ የመሥራት ልምድ ቢኖርም፣ በተሻለና ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲሁም በተገቢው የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ኖሯቸው የተተገበሩ ፕሮጀክቶች ግን አልነበሩም፡፡ ከብዙ የምርምር ውጤቶችና ምክረ ሐሳቦች በኋላ እንዲሁም በመንግሥትም ጥናቶች ተደርገው፣ በመጨረሻም የመንግሥትና የግል አጋርነትን ለመተግበር የሚያስችል ፖሊሲ ፀድቋል፡፡ ከዚያም ባሻገር የአገሮችን ልምድ በመቀመርና የኢትዮጵያን ልዩ ሁኔታ በመመልከት፣ ከፍተኛ የልማት ሥራዎችን ለመሥራትና ለኢትዮጵያ ራዕይ መሳካት አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ለመንግሥትና ለግል አጋርነት ማስፈጸሚያዎች የሕግ ማዕቀፎችም ወጥተዋል፡፡ አዋጅና ደንብ ወጥቷል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕግ መመርያም በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ እንግዲህ ፖሊሲና ሕግ መኖሩ ብቻ ትግበራውን ዕውን አያደርገውም፡፡ ተቋም ያስፈልገዋል፡፡ ፕሮጀክቶችን ከመለየት ጀምሮ ወደ ጨረታ እስከሚገባበት ሒደት ድረስ ያለውን ሥራ የሚከታተልና የሚያፀድቅ አሥር አባላት ያሉት ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ መንግሥትን በመወከል ሚኒስትሮች የተወከሉበት፣ ከግሉ ዘርፍም ልምድ ያላቸው ሁለት አባላት የሚሳተፉበት እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነት አስተዳደር ቦርድ ሥር የቴክኒክ ሥራዎችን፣ የማስተባበርና የማደራጀት ተግባራትን የሚያወጣ በጠቅላላው በአጋርነቱ ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን እየለየና ከመንግሥት አካላት ጋር እየተባበረ በመሥራት ለቦርዱ የሚያቀርብ ጽሕፈት ቤት ተቋቁማል፡፡ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ጽሕፈት ቤቱ ራሱን በማደራጀት ላይ ይገኛል፡፡ ሥራው ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ በመጀመሪያው ዙር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት አማካይነት የሚታገዙ ይሆናሉ፡፡ ባለሙያዎቹም በዚህ መንገድ የተመደቡ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አማካሪዎችም እያገዙን ነው፡፡ በመሆኑም ለመጀመሪያው ዙር በኤሌክትሪክ ኃይልና በትራንስፖርት መስክ ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ጥናት ተካሂዶ፣ ጥናቱም ለቦርዱ ቀርቧል፡፡ ለቦርድ ከቀረቡት ፕሮጀክቶች ውስጥ 14 የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች፣ ሦስት የትራንስፖርት፣ በጠቅላላው ከ6.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈልጉ 17 ፕሮጀክቶች በመንግሥትና የግል አጋርነት እንዲከናወኑ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም በኃይድሮ ኤሌክትሪክ አምስት፣ በሶላር ኃይል ስምንት፣ እንዲሁም የተመረተውን የኤልክትሪክ ኃይል ወደ ተጠቃሚው የሚያስተላልፉ የሰብስቴሽን ፕሮጀክቶችም እንዲተገበሩ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ጨረታ ሒደት እንገባለን ብለን እናስባለን፡፡ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ኩባንያዎችን በማስተባበር ወደ ግንባታ እንደምንገባ ተስፋ እንደርጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በኃይድሮና በሶላር የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ እንዲሁም የመነጨውን ኃይል የሚያሰራጩ በጥቅሉ 14 ፕሮጀክቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ሦስቱ የትራንስፖርት ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- በትራንስፖርት መስክ ያሉት ሦስት ፕሮጀክቶች በአንድ መስመር ያሉ ናቸው፡፡ ከአዳማ ጀምሮ እስከ ድሬዳዋ ባለው መስመር በሦስት ፕሮጀክቶች ተከፋፍለው የሚተገበሩ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከአዳማ አዋሽ፣ ከአዋሽ ሚኤሶ፣ ከሚኤሶ ድሬዳዋ ባለው መስመር ለሚገነቡት የፍጥነት መንገዶች ግንባታ እስከ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚገነቡ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም በጉዳዩ ላይ የአዋጭነት ጥናት ሠርቶ እንዲያቀርብ መልዕክቱ ተላልፎታል፡፡ የአዋጭነት ጥናቱ ከቀረበ በኋላ በሕጉ መሠረት ተገቢውን ባለሙያና ባለሀብት በመለየት ወደ ጨረታ ሒደት እንገባለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የግሉ አጋርነት አሥር የቦርድ አባላት አሉት ብለዋል፡፡ የትኞቹ ሚኒስትሮችና የግል ዘርፍ ተወካዮች እንደተወከሉ ብናውቃቸው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- በአዋጁ መሠረት የአጋርነት ሥራው ከፖሊሲውም መረዳት እንደሚቻለው በመጀመርያው የፕሮጀክቶች ምዕራፍ መንግሥት ትኩረቱ በመሠረተ ልማትና በኃይል ዘርፍ ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት ነው፡፡ መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማስገባት እየሠራ ነው፡፡ እንዲሁም የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት የተቀመጡ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የኃይልና የትራንስፖርት ዘርፎችን የሚመለከቱት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መንግሥት ከግሉ ጋር ተባብሮ ሊሠራባቸው የሚችላቸው 17 ፕሮጀክቶች ተለይተዋል፡፡ በመሆኑም ሕጉን ያወጣው አካል ወሳኝ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ናቸው የተካተቱት፡፡ ለምሳሌ የገንዘብ ሚኒስትር ሰብሳቢ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር አባል፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አባል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አባል፣ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር አባል፣ ከግሉም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሕግ የግሉን ዘርፍ የሚወክል እንደመሆኑ መጠን ተጠይቆ የግሉን ዘርፍ ይወክላሉ ብሎ ያቀረባቸው ሁለት ተወካዮች ተካተዋል፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዳይሬክተር እንደ ጸሐፊ በቦርዱ ውስጥ ይሳተፋሉ፡፡ በአጋነት የሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ፍትሐዊነታቸው ምን እንደሚመስል ለመከታተል የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የነበረው (የሰላም ሚኒስቴር) በአባልነት ይሳተፋል፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ፕሮጀክቶች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊተገበሩ ይችላሉ? ጨረታውስ የሚወጣው መቼ ነው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- ጨረታውን ለማውጣት የሚያስፈልጉ ሒደቶች አሉ፡፡ የተመከረባቸውና የተጠኑ፣ አስፈላጊነታቸውና የቴክኒክ ይዘታቸው በሚገባ የተተነተኑና የተለዩ ፕሮጀጀክቶች ለቦርድ ይቀርቡና ቦርዱም አስፈላጊነታቸውን ከመንግሥት ዓላማና ግብ ጋር መዛመዳቸውን በመለየት ብሎም በመንግሥት አቅም ብቻ የማይተገበሩ መሆናቸውን ሲገነዘብ፣ የመንግሥት ድርሻና የግሉ ዘርፍ ድርሻ በድርድር ተለይቶ ለጨረታ እንዲበቁ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል፡፡ ሁሉም አዋጭ ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በግል አጋርነት ይያዛሉ ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ቦርድ ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም አያካትትም፡፡ በቦርዱ የተለዩት ፕሮጀክቶች ከታወቁ በኋላ የዳይሬክቶሬት ጄኔራሉ ጽሕፈት ቤት ፕሮጀክቶቹ ከሚተገበርባቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች (ኮንትራክቲንግ አውቶሪቲስ) በመገናኘት በተለዩት ፕሮጀክቶች ላይ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናት እንዲዘጋጅ እናደርጋለን፡፡ ጥናቱ ከተዘጋጀ በኋላ ለቦርዱ ቀርቦ አዋጭነታቸውን በመመልከት ውሳኔ ይሰጥባቸዋል፡፡ ውሳኔ የተሰጠባቸው ፕሮጀክቶች እንዲተገበሩ ጨረታ ይወጣባቸዋል፡፡ ሆኖም የሚሳተፈው የግል ኩባንያ ማንነትና አቅም፣ ብቃትና ችሎታቸው ታይቶ ፍላጎት ላላቸው የጨረታ ሰነዱ ይላክላቸዋል፡፡ የጨረታ ሰነዱ የተላከላቸው ኩባንያዎች ለጨረታ ያቀረቡት የግንባታ ዝርዝር ሐሳብና ዋጋ ታይቶና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ጋር የውል ስምምነት የሚፈረምበት አሠራር ይኖራል፡፡ የውል ስምምነት ከተደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ቢያንስ ለ20 ወይም ለ25 ዓመታት ፕሮጀክቱን የሚያስተዳድር አንድ ኩባንያ ይቋቋማል፡፡ ይህ ኩባንያ የተፈረመውን ውል እያስተዳደረ ፕሮጀክቶችን መምራት ይጀምራል ማለት ነው፡፡ እንደ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋንርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ጽሕፈት ቤት፣ ለፕሮጀክቱ መተግበር የሚኖረን ሚና እዚህ ላይ ያበቃል፡፡ ነገር ግን በተገባው ውል መሠረት እየተተገበረ ስለመሆኑ የሚከታተል አንድ የፕሮጀክት አስተዳደር ቡድን ይቋቋማል፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ ከእኛ ተቋም የሚወከል ባለሙያ ይመደባል፡፡ በዚህ አግባብ ፕሮጀክቶችን እንከታተላለን፡፡ ዋናው የፕሮጀክት አስተዳደር፣ የቁጥጥር ብሎም የክትትል ሥራ ግን ፕሮጀክቶቹን የሚያስተገብረው ተዋዋይ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ሒደቱን ማገዝ፣ የጨረታ ሒደቶችን መምራትና መከታተል እንዲሁም ሒደቱን አጠናቆ ውል ማፈራረም የእኛ ተቋም ሥራ ይሆናል፡፡ መቼ የሚለው ጥያቄ እንደ ፕሮጀክቱ ዓይነትና ባህርይ፣ እንደ ተዋዋዮቹ አካላት ድርድርና ስምምነት የሚወሰን ነው፡፡ እርግጥ በጨረታ ሰነዱ የሚመለከቱ ጉዳዮችና የጊዜ ሰሌዳዎች መኖራቸው የማይቀር ቢሆንም፣ በአብዛኛው በተዋዋዮቹ በሚገቡት ስምምነት የሚፈጸም ነው፡፡ በነገራችን ላይ የመንግሥትና የግል አጋርነት የሕግ ማዕቀፍ የመንግሥትና የግሉን ተዋዋይ አካላት በድርድር እንዲጨርሱ የሚያስችልና ፍላጎታቸውን እንዲያስተናግድ ታስቦ ገዳቢነት ያላቸው ጉዳዮች ክፍት እንዲደረጉ ታስቦበት የተዘጋጀ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መስክ መሳተፍ የሚፈልጉ የውጭ ኩባንያዎች ከዘህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያነሱ የነበረው የኤሌከትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ይደረግ የሚል እንደነበር ይታወቃል፡፡ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ ሲጠበቅ ነበር፣ ማሻሻያ ተደርጓል ማለት ነው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- በታሪፍ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት እኔ ተገቢው ኃላፊ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን እየሠሩበት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ዝርዝር ነገሩን ለማወቅ ካስፈለገ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎችን ወይም የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርን ማነጋገሩ ይበጃል፡፡ ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ አኳያ በጥቅሉ ሲታይ ግን ይህ የታሪፍ ጉዳይ የድርድራቸው አካል ነው፡፡ የአገሪቱ ስታንዳርዶች አሉ፡፡ የግል ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አምርተው ለመንግሥት ለመሸጥ በሚፈልጉበት ወቅት ሒደቱና አሠራሩን የሚመለከቱ ስታንዳርዶች አሉ፡፡ ይሁንና በርካታ አብሮ ለመሥራት የሚቀርቡ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡ በቶሎ ሥራው እንዲጀመር እየወተወቱ ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ዋስትና የሚሰጥ የመንግሥት የሕግ ማዕቀፍና ተቋም መፈጠሩ የውጭ የግል ኩባንያዎች እንዲጎርፉ አስችሏል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የተለዩት ፕሮጀክቶች እንዲለሙ ከተለዩና ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው ኩባንያም ከተሰየመ በኋላ ፕሮጀክቱን የሚመራ አንድ ራሱን የቻለ ኩባንያ ይቋቋማል ብለዋል፡፡ የዚህ ኩባንያ ልዩ ባህሪያት ምንድን ናቸው? ምን ዓይነት የተለየ ገጽታ ይኖረዋል?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- ኩባንያው የግል ኩባንያ ነው የሚሆነው፡፡ የግል ኩባንያ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕግ ማለትም በመንግሥትና በግል ዘርፍ ሕግ መሠረት እንዲለማ የተወሰነውን ፕሮጀክት ለማስተዳደር የሚያስችል አቅምና ብቃት ያለው የግል ተቋም ነው የሚሆነው፡፡ እንደየ ፕሮጀክቱ ሁኔታም የኩባንያዎቹ ማንነትና አቅም፣ ብቃትና ችሎታቸው እንደሚሰማሩበት የሥራ መስክም ይለያያል፡፡ አብዛኛውን ሥራቸውን የሚወስነው የፕሮጀክት ስምምነቱ ሰነድ ነው፡፡ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው፣ ተጠያቂነት ያለባቸው፣ መብትና ግዴታቸው በሕግ የተደነገጉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የግል አጋርነት የሚያመጣቸው ፕሮጀክቶች በታችኛው ተጠቃሚው ሕዝብ ላይ ጫና ያሳድራሉ፣ ዋጋ ይጨምሩበታል የሚሉ ሥጋቶች ይነሳሉ፡፡ ለምሳሌ የግል ኩባንያዎች በዚህ ማዕቀፍ የሚሳተፉት ትርፍ ለማግኘት ነው፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚሳተፉት የግል ኩባንያዎች ካላቸው የኢንቨስትመንት ድርሻ አኳያ ትርፍ ማግኘት ስለሚፈልጉ ሕዝቡ የሚባለውን ያህል ተጠቃሚ አይሆንም የሚሉ ሥጋቶች ይነሳሉ፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ሥጋቶች ያያቸው ነገሮች አሉ?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- እንዲህ ያሉ ሥጋቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በፖሊሲው ተካተዋል፡፡ የፖሊሲው ትኩረት አንደኛውና ዋናው ጉዳይ የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ ነው፡፡ እርግጥ ነው የግሉ ዘርፍ ለትርፍ እንጂ ለፅድቅ አይመጣም፡፡ ሆኖም በዚህ ሒደት ውስጥ ሕዝብስ ምን ይጠቀማል የሚለው ታይቷል፡፡ ለምሳሌ የፍጥነት መንገድን እንውሰድ፡፡ የፍጥነት መንገድ የገነባው ኩባንያ በ20 ዓመታት ውስጥ የአገልግሎት ክፍያ በማስከፈል ያሰበውን ትርፍ ያገኛል ማለት ነው፡፡ በየጊዜው በሚታይ የዋጋ መለዋወጥ ምክንያት በየጊዜው ሒሳብ ልጨምር ቢል ግን ልክ አይመጣም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለመከላከል መንግሥት በድርድር ሒደት ወቅት በአግባቡ አቋሙን ያስታውቃል፡፡ ለምሳሌ ይኼንን ትርፍ ልታገኝ የምትችለው ከዚህ እስከዚህ ባለው ታሪፍ ስታስከፍል ነው፣ ከዚህ በላይ ግን ማስከፈል አይቻልም ወዘተ. የሚሉ አንቀጾች በድርድር ሒደቱ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ፡፡ ኩባንያው ይህ አያዋጣኝም ካለና በመንግሥት ሐሳብ ካልተስማማ ፕሮጀክቱ ሊቀርም ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ መገንባት አለበት ብሎ ካመነ፣ ኩባንያው ማስከፈል እስከሚፈቀድለት ታሪፍ ድረስ ይፈቀድለትና ከዚያ በላይ የሚመጣውን ግን መንግሥት እንዲሸፍን ሊስማማ ይችላል፡፡ መንግሥት እከፍላለሁ ብሎ በውል ይስማማል፡፡ ስለዚህ የግል ኩባንያው የሚያገኘው ትርፍ ሕዝብን ጫና ውስጥ እንዳይከት፣ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲህ ያሉ መንገዶችና አካሄዶች ይኖራሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሚተገብራቸው ፕሮጀክቶችና አካሄዶቹ በአብዛኛው የሊበራል አካሄድ የሚከተሉ ይመስላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በገባቸው ስምምነት መሠረት የሚጠበቅባትን ባትወጣ፣ የውጭ ኩባንያዎች ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የፍትሕ ተቋማት በመውሰድ ዳኝነት መጠየቃቸው አይቀሬ የሚሆኑባቸው አጉዳዮች እየመጡ ነው፡፡ ስለዚህስ ጉዳይ ምን ዝግጅት ተደርጓል?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- እኔ የሕግ ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን እስከማውቀው ድረስ በሌሎች ሕጎች ያላየሁትና በመንግሥትና የግል አጋርነት ሕግ ውስጥ የተቀመጠው ነገር በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ በስምምነትና በውይይት ጉዳዩን መፍታት እንደሚችሉ፣ ይህ ባይሆን ግን ወደ ግልግል ዳኝነት መሄድ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በኮንትራት ስምምነታቸው መሠረት በኢትዮጵያ ሕግ የሚዳኙ ይሆናሉ፡፡ ይህ በጠቅላላው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን የሚገዛ ማዕቀፍ ነው፡፡ መንግሥታዊውም የግሉ ዘርፍም ተዋናዮች በአገሪቱ ሕግ መሠረት ይዳኛሉ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ፕሮጀክቶቹና ድርድሮቹ ሁኔታ መሀል ላይ አለመግባባት ቢከሰት ሁለቱም ወገኖች በሚስማሙበት የሕግ ማዕቀፍ ለመዳኘት ስምምነት ሊያስሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በስምምነት ለመዳኘት እንደሚችሉ የሕግ አንቀጽ መቀመጡ በርካቶች ተመራጭ ያደረጉት ነው፡፡ በስምምነት የሚወሰን በመሆኑም ይህን ያህል ለኢትዮጵያ የሚያሠጋት ነገር አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ወይም የሚከናወኑ ሥራዎች ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሔ አያመጣም በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡

ተሾመ (ዶ/ር)፡- በላይኛው ጥያቄ ውስጥ ከተንፀባረቀው አንድ ሐሳብ ልጀምር፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አካሄድ ሊበራል ነው የሚለው ሐሳብ የተሳሳተ ነው፡፡ ከተፈጥሮው ስንነሳ በአብዛኛው የግል ኩባንያዎች ወይም የገበያ ኃይሎች የሚቆጣጠሩት፣ የመንግሥት ሚና የተገታበት አሠራር ነው ሊበራል የሚባለው፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ግን ሁለቱንም አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ እንዲያውም በርዕዮተ ዓለም ክርክር ውስጥ ካየነው የእኛ የመንግሥትና የግል አጋርነት ሥርዓት መሀል ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ መንግሥት ለሕዝቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች መሟላት አገልግሎት የመስጠት ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህን ኃላፊነቱን ለግሉ ዘርፍ አሳልፎ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ሊበራል መንግሥታት ሙሉ በሙሉ ለግሉ ዘርፍ ወግነው የሚሠሩ በመሆናቸውና የግሉን ዘርፍ ፍላጎቶች የሚያስጠብቁ በመሆናቸው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚታየው ልዩነት እምብዛም ነው፡፡ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ በተለይም ደግሞ ልማታዊ ወይም ሶሻሊስታዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ መንግሥት የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንቅስቃሴዎቹን በዚህ መነሻነት ይቃኛል ማለት ነው፡፡ እንደ እኛ አገር ልማታዊ መንግሥት ሲኖር አንደኛው ቁልፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን የሚተገበርበት ምክንያት የሕዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው፡፡ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት የመንግሥት ፈቃድ የተሰጠባቸውን ፕሮጀክቶች ይዞ በድርድር የሚተገብር አካል ነው፡፡ በዚህ ሒደት ኮንትራቱን የማስተዳደር፣ ሕጋዊ ማዕቀፉን፣ ተቋማዊ ማዕቀፉን የሚከታተለው መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህም ምንጊዜም የሕዝብ ጥቅም መረጋገጡን፣ የአገር የልማት ዕቅድ መተግበሩንና ፕሮጀክቶቹ እንደታሰቡት መፈጸማቸውን ሁሉ ይቆጣጠራል፡፡ ስለዚህ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሊበራል ነው ከማለት ይልቅ ‹ሚስቶ› የሆነ የጋራ ተግባር ነው ማለት ነው፡፡ እንዲያውም በአግባቡ በሕግና በሥርዓት ከተመራ የግሉን ዘርፍ ሀብት ወደ መንግሥት በማምጣት ሰፊ ሥራ ሊሠራበት እንደሚችል ከደቡብ ኮሪያና ከቻይና ታይቷል፡፡ የእነዚህ አገሮች የልማት ሚስጥር ይኼው ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ ሀብት መንግሥት ወደሚፈልገው የልማት ሥራ ማምጣት በመቻላቸው በከፍተኛ ደረጃ ያደጉ አገሮች ለመሆን በቅተዋል፡፡  የአገራችን የግል ዘርፍ እንዲያድግ መንግሥት ድጋፍ መስጠት እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የውጭ ኩባንያ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሲወዳደር፣ ከአገር ውስጥ የግል ባለሀብት ጋር በመሆን የሚሳተፍ ከሆነ ማበረታቻ ይታሰብለታል፡፡ በኩባንያው ማኔጅመንት ውስጥ እስከ 40 በመቶ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ካሳተፈ፣ ከሚቀጥራቸው ሠራተኞች ውስጥ እስከ 60 በመቶ ኢትዮጵያውያንን ካሳተፈ ማበረታቻ ይደረግለታል፡፡ ይህ ቀላል ማበረታቻ አይደለም፡፡ የውጭ ባለሀብቶች አሸንፈው ፕሮጀክቶችን መረከብ ይፈልጋሉ፡፡ ለማሸነፍ ደግሞ ነጥቦች ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነጥብ ለማግኘት ደግሞ ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት መግባታቸው የማይታለፍ ይሆንባቸዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥትና በግል አጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ይደራደራሉ፡፡ የኢትዮጵያ የድርድር አቅም ምን ያህል ነው? የመደራደር ችሎታችንስ እንዴት ነው የታየው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- የድርድር አቅምን በተመለከተ በተግባር ያለውን ጉዳይ እንመልከት፡፡ አንድ የመንግሥት ተቋም እንበልና ካሉት 20 ፕሮጀክቶች ውስጥ አሥሩን ራሴ እሠራለሁ ብሎ በራሱ ፋይናንስና አቅም ሊገባ ይችላል፡፡ የተቀሩትን ግን ከዕውቀቱም ከልምዱም አኳያ የተሻለው የግሉ ዘርፍ ነው ብሎ ሊወስን ይችላል፡፡ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎችም ይመጣሉ፡፡ ሥራውን በሚመለከት የሚደረገው ድርድር ኩባንያዎቹ እንዲሠሩት የሚፈለገው ሥራ የሕዝብ ጥቅም ማስጠበቁን፣ የጥራት ደረጃው ምን እንደሚሆን፣ ፕሮጀክቱ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅና ወዘተ. አቋሙን ያስታውቃል፡፡ ያዋጣኛል በተባለው ጥራትና በሚፈለገው ጊዜ ውስጥ አቀርባለሁ የሚል ኩባንያ ሥራውን ይረከባል፡፡ የመንግሥት አቋም ግልጽ ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅምን የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ተቋማት ቢሆንም የግል ኩባንያውም ይኼንኑ ተረድቶና ለዚሁ ተገዥ ሆኖ እንዲገባበት ነው የሚደረገው፡፡ መንግሥት የሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቀው ፕሮጀክት በሦስት ብር መገንባት አለበት ብሎ ሊነሳ ይችላል፡፡ ኩባንያው አያዋጣኝም አምስት ብር ነው ዋጋዬ ቢል መልሱ አጭርና ግልጽ ነው፡፡ አይሆንም አንደኛው ምላሽ ሲሆን፣ አማራጭ ካለ የለም በሦስት ብር ገንባና ትርፍ ካላገኘህ ቀሪውን ገንዘብ በ20 ዓመታት ውስጥ እንዴት እንደምታገኘው እንደራደር ሊለው ይችላል፡፡ በዚህ የማይስማማ ኩባንያ ሌላ ሥራ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ሁለቱም እኩል የመደራደር አቅም አላቸው፡፡ እንግዲህ ድርድሩ እንዲህ ባለው ግልጽና መሠረታዊ ጉዳይ ግንዛቤ ሊያዝበት ይችላል፡፡ አንድ የማይካድ ነገር አለ፡፡ ከውጭ የሚመጡ ኩባንያዎች በሚሆኑበት ጊዜ ከዚህ አገር ያገኙትን ጥቅም ሙሉ በሙሉ ወደ ውጭ ገንዘብ ቀይረው ወደ አገራቸው የመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸው ድርድር ላይ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ መንግሥት በእጅጉ የሚፈልገው ፕሮጀክት ቢሆንና የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ቢቸግረው፣ በተለያዩ ዘዴዎች የውጭ ተደራዳሪውን ኩባንያ ለማሳመን ጥረት ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን ገንዘቡ የሚመጣው በብድር አይደለም፡፡ ኩባንያዎቹ በቀጥታ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ነው፡፡ የዚህ ጥቅሙ የብድር ዕዳ ጫና ለመቀነስ ማስቻሉ ነው፡፡ ከዓመታት በኋላ ገንዘቡ ወደ ውጭ እንዲወጣ በሚጠየቅበት ወቅት፣ እንዴት ይወጣል የሚለው ላይ የመደራደሪያ ዘዴን ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተር፡-  ከተለዩት 17 ፕሮጀክቶች በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ የትኛው ተግባራዊ ሆኖ ሊታይ ይቻላል?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ የትኞቹ ከሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ መጠናቀቅ በፊት ዕውን ይሆናሉ የሚለውን በተመለከተ፣ በዘርፉ ያለው ዕቅድ ውስጥ የተቀመጠው የሚመልሰው ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይልን በተመለከተ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ለየትኛው ፕሮጀክት ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መገንባት እንዳለበትና አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ዝርዝር ጉዳዩን እነሱ ናቸው የሚመልሱት፡፡ የእኔ ተቋም ሚና መሥሪያ ቤቶቹ ለመንግሥትና ለግል አጋርነት የመረጧቸው ፕሮጀክቶች በተገቢው መንገድ እንዲሳኩ ድጋፍ መስጠት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶቹ ከዚህ ቀደምም በዕቅድ የነበሩ ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎቹም ሆኑ የፍጥነት መንገዶቹ ከዚህ ቀደም በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ናቸው፡፡ በመንግሥትና በግል ማዕቀፍ እንዲገነቡ ያስፈለገበት የስትራቴጂ ለውጥ ምንድነው?

ተሾመ (ዶ/ር)፡- የስትራቴጂ ለውጥ የለም፡፡ አዋጁ በመሀል ነው የመጣው፡፡ አዋጁ ከወጣ በኋላ እንዲተገበሩ የሚታሰቡ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በግል አጋርነት አማካይነት እንዲገነቡ በመወሰኑ ሳይገነቡ ቆይተው የነበሩና እንዲገነቡ የሚታሰቡት በዚህ አኳኋን ይገነባሉ፡፡ ቀድሞም ኮንትራታቸውና ግንባታቸው ተጀምሮ የነበሩ ሥራዎች በዚያው እንዲቀጥሉ ተደገዋል፡፡