Skip to main content
x
በሕዝብ ስም መነገድ ነውር ነው!

በሕዝብ ስም መነገድ ነውር ነው!

የአንድ አገርን ሕዝብ በብሔር ወይም በተለያዩ ማንነቶች በመከፋፈል በስሙ መነገድ የዘመናችን ልሂቃን መለያ ከሆነ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከልዩነቶቹ ይልቅ የጋራ እሴቶቹና መስተጋብሮቹ የሚያመዝኑት ይህ ሕዝብ፣ በተለያዩ መልክዓ ምድሮችና የአየር ፀባዮች ውስጥ ቢኖርም ዕጣ ፈንታው ግን አንድ ነው፡፡ ለዘመናት የተለያዩ ገዥዎች ቢፈራረቁበትም፣ የተለያዩ ባዕዳን ወራሪዎች ቢዘምቱበትም፣ ለማመን በሚያዳግት ሰቅጣጭ ድህነትና ኋላቀርነት መከራውን ቢያይም፣ የግፍና የበደል ዓይነቶች ቢፈራረቁበትም በእናት አገሩ ጉዳይ ሲደራደር አይታወቅም፡፡ ይህ ለአገር ያለው የማይበርድ ፍቅርና የጋለ ስሜት ከዘመን ወደ ዘመን፣ እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እዚህ ደረጃ ተደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ ሲተዛዘን፣ ሲደጋገፍና ያገኘውን እየተጎራረሰ መኖሩ መቼም ቢሆን አይታበልም፡፡ ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሕዝብን ለማቃቃር፣ ለማጋጨትና ደም ለማፋሰስ የሚጥሩት ግን የአገር ህልውናን ከራሳቸው ርካሽ ጥቅም በታች የሚያዩ ከንቱዎች ናቸው፡፡ አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ መታገል ያለበት እነዚህን በአፍቅሮተ ንዋይና በጭካኔ የሰከሩ እኩዮችን ነው፡፡

እነዚህ ወገኖች የራሳቸውን ጥቅምና ሥልጣን ለማደላደል ሲፈልጉ የሕዝብን ስም በከንቱ ያነሳሉ፡፡ የሕግ ተጠያቂነት ሲመጣባቸውና ራሳቸውን ለመከላከል ሲፈልጉ በሕዝብ ስም ይነግዳሉ፡፡ እነሱ ጠግበው ሲያገሡ ሕዝብ ከድህነት ተላቆ በዕድገት ግስጋሴ ላይ እንደሆነ ይደሰኩራሉ፡፡ ሕዝብ ከሰውነት ተራ ወርዶ በድህነትና በጭቆና ሥር እየማቀቀ፣ ያለ ምንም ይሉታ ስለብልፅግና ያወራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ያለፉት 27 ዓመታት ትርክት ይኼ ነበር፡፡ ሕዝብ ምሬቱ ተባብሶ ፈንቅሎ ሲወጣና በቃኝ ሲል ምላሹ ምን እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ አሁን በተቃራኒው ሕዝብ ሕግ ይከበር ብሎ ዕርምጃዎች መወሰድ ሲጀምሩ፣ ብሔር ውስጥ መወሸቅና በሕዝብ ስም መነገድ የወቅቱ ፋሽን ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በሕዝብ ስም የመነገድ አባዜ የተፀናወታቸው ደግሞ ለውጡ ሰላምና ዴሞክራሲን እንዲያጎናፅፍ ማገዝ ሲገባቸው፣ የተለመደው የተዛባ የታሪክ ትርክት ውስጥ ሆነው በሕዝብ መካከል አለመተማመን እየፈጠሩ ግጭት ይቀሰቅሳሉ፡፡ የረባ ሕዝባዊ አጀንዳ ሳይኖራቸው አገር ለማመስ ሲቅበዘበዙ ይታያሉ፡፡ ከትናንቱ የሌሎች ስህተት ከመማር ይልቅ፣ በትዕቢት ተወጥረው አንዱን ባለቤት ሌላውን ባዕድ ለማድረግ ይውተረተራሉ፡፡ አስተዋዩ ሕዝብ እነዚህንም መታገል አለበት፡፡

ሁሌም እንደምንለው የአገር ህልውና ከቡድኖችና ከግለሰቦች በላይ ነው፡፡ ትውልድ አልፎ ሌላ ትውልድ ይተካል፡፡ መንግሥት በሌላ መንግሥት ይለወጣል፡፡ አንድ መሪ ሄዶ ሌላ መሪ ይመጣል፡፡ አገር ግን ዘለዓለማዊ ናት፡፡ ዋናው ቁም ነገር አገር እንዴት በዘለቄታዊነት ለትውልድ ትተላለፋለች የሚለው ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን የሚገኘው ከምርጫ ሳጥን ውስጥ ብቻ እንደሆነ ለማሰብም ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት የሌለው ኃይል፣ አገርን የዘረፋና የጭካኔ አውድማ በማድረግ የበላይነቱን የማስቀጠል ተስፋ እንደሌለው ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ጊዜ ለአገር የሚያስቡ ዴሞክራቲክ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል፣ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ አምባገነንነት እንዳትመለስ መጠንከር አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሕዝብ ስም እየነገዱ አገር ለማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎችን በተጨባጭ ማጋለጥ፣ ግጭት እየቀሰቀሱ ደም የሚያፋስሱትን ሕግ ፊት ማቅረብ፣ ለውዥንብር የሚዳርጉ ማናቸውም ድርጊቶችን ከመፈጸም መታቀብና ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ጠበቃ መሆን የግድ ይላል፡፡ የአድርባይነትና የአስመሳይነት አባዜዎች ተቀባይነት ማጣት አለባቸው፡፡ ይህንንም ሕዝብ በንቃት መከታተል አለበት፡፡

በሕዝብ ስም የመነገድ ሱስ ያለባቸው ከጥፋታቸው እንዲታረሙ ቢፈለግም፣ የተፀናወታቸው ክፉ ልማድ በቀላሉ የሚለቅ አይደለም፡፡ ሕዝብ በቃኝ አንገሸገሻችሁኝ ብሎ አንቅሮ ሲተፋቸው፣ ግጭት እየቀሰቀሱ ቁም ስቅሉን ያሳዩታል፡፡ አገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትግባ ተብሎ የሕዝብ ይሁንታ ሲቸር፣ እነሱ ደግሞ ረግጦ የመግዛት አባዜያቸው ስለማይለቃቸው ‹ሰይጣን ለአመሉ ከመጽሐፍ ይጠቅሳል› እንዲሉ፣ ስለሕግ የበላይነት መከበር ይደሰኩራሉ፡፡ በገዛ እጃቸው ሲንዱት የነበረውን ሕግ ለሕገወጥነት መጠቀሚያ ይፈልጉታል፡፡ ሕዝብ በእንዲህ ዓይነቱ ከንቱነት መጭበርበር የለበትም፡፡ ማንኛውም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል እንደሆነ የሚያስረዳውን መሠረታዊ የሕግ መርሆ በመቀልበስ፣ የዜጎች አለኝታና መከታ መሆን የሚገባውን ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ በማድረግ፣ በዜጎች መካከል መኖር የነበረበትን ፍትሐዊነትና እኩል ተጠቃሚነት በመናድ፣ በሕግ ከለላ ሥር ያሉ ወገኖችን በማሰቃየትና በመሳሰሉት ጥሰቶች መጠየቅ ያለባቸው ኃይሎች እንዴት ሆኖ ነው ስለሕግ የበላይነት ደፍረው የሚናገሩት? በሕዝብ ስምስ እስከ መቼ ይቀልዳሉ? ሕዝብ ይህንን ጉዳይ በአንክሮ መረዳት አለበት፡፡ ማንም በስሙ እንዲነግድበት ሊፈቅድ አይገባም፡፡

ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ መሆን አለበት፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አቋምም ሆነ በሌሎች ልዩነቶች በመከፋፈል ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ኃይሎችን ሊጋፈጣቸው ይገባል፡፡ በሴራና በአሻጥር ልክፍት ውስጥ ያሉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት የተፀናወታቸው ጀብደኞች በተደሰቱና በተከፉ ቁጥር የሒሳብ ማወራረጃ እንዳያደርጉት ራሱን መከላከል አለበት፡፡ በስሙ እየነገዱ ከገዛ ወገኑ ጋር ጠላትነት እንዲሰማው የሚያደርጉ እኩዮችን ይበቃችኋል ከማለት አልፎ ማጋለጥ አለበት፡፡ ‹ለሕዝብ ጥቅም› እየተባለ ራስንና ቢጤን ከማበልፀግና አገርን ከማደህየት የዘለለ ፋይዳ የሌላቸው ኃይሎች ሲዋሹ አብሮ መንጎድ አይገባም፡፡ አሁን የሚያዋጣው ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር እጅ ለእጅ ተያይዘው በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚኖሩባት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር መፍጠር ነው፡፡ ለዚህ ፍላጎት ዕውን መሆን ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሥራ ለማከናወን ቆርጦ መነሳት ተገቢ ነው፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ፀረ ሕዝብ ሆኖ መገኘት ግን ውርደት እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ ለዚህም ነው በሕዝብ ስም መነገድ ነውር ነው የሚባለው!