Skip to main content
x

ሕገ መንግሥት ሲፈልጉ የሚያጌጡበት የክት ቀሚስ ሳይሆን በአዘቦት ጭምር የሚያጠልቁት የዘወትር መጎናፀፊያ ነው

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር በሰደደባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ ሕገ መንግሥት ፈርጀ ብዙ አገልግሎት ያለው ቁልፍና መተኪያ የሌለው የሕግና የፖለቲካ ሰነድ ነው፡፡ ከዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች ሥርዓት ጋር ተያይዞ የታየ እንደሆነ ሕገ መንግሥት በምድራችን የሚገኝ አንድ አገር በየብስ፣ በባህርና በአየር ረገድ ያለው ወሰን በውል ተለይቶ ይታወጅበታል፡፡ ውስጣዊ ገጽታውን ስንመለከት ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሒደት የተረቀቀና በብዙኃኑ ነፃ ውሳኔ ወይም በወኪሎቻቸው አማካይነት ተመክሮበት የፀደቀ ሕገ መንግሥት፣ የምልዓተ ሕዝቡ ሉዓላዊነት ተረጋግጦ መንግሥቱ ይደራጅበታል፡፡ የሕግ አውጪ፣ የሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካላቱ ዝርዝር ሥልጣንና ኃላፊነት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተከፋፍሎ ይደላደልበታል፣ የሥራ መደራረብ እንዳይፈጠር ዳር ድንበር ተበጅቶላቸው አንደኛው ሌላውን እንዳይሻማ እርስ በርስ ተናበው የሚሠሩበት ማዕቀፍ ይበጅበታል፡፡

ከሁሉም ይልቅ ዜጎች በተፈጥሮ የተቀዳጇቸው ሰብዓዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች በአግባቡ ተዘርዝረው የሚሰፍሩትና ተገቢውን ጥበቃ የሚያገኙትም፣ በዚሁ አውራ ልዕለ ሕግ አማካይነት እንደሆነ እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡ በታሪክ የኋሊት ብንጓዝ እንኳ እ.ኤ.አ. በ1215 ከወጣው ከታላቁ የእንግሊዝ ማግና ካርታ፣ ይልቁንም እ.ኤ.አ. ከ1889 የፓሪስ የሰውና የዜጋ መብቶች መግለጫ (ቻርተር) ወዲህ እየወጡ የምናያቸው አያሌ አገሮች ሕግጋተ መንግሥታት ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ዓይነተኛ ዓላማቸው የየመንግሥታቱን ሥልጣን በመገደብ፣ የዜጎቻቸውን ልዕልና ከፍ ማድረግ መሆኑን በቀላሉ ለመረዳት አያዳግተንም፡፡

በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ቢሆን በወፍ በረር ዕይታ ሲዳሰስ ይህንን ማዕከላዊ እሴት አስመልክቶ የጎላ እንከን ይታይበታል ለማለት እምብዛም አያስደፍርም፡፡ እንዲያውም ለቁጥር የሚያታክቱ አያሌ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችንና ዴሞክራሲያዊ ነፃነቶችን መዘርዘሩ ሳያንሰው፣ አገሪቱ በየጊዜው ከምትፈርማቸውና ያለ ገደብ እየተቀበለች ከምታፀድቃቸው አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ውሎች ጋር ሳይቀር ራሱን ገና ከጅምሩ በጥብቅ አቆራኝቶ እናገኘዋለን፡፡ ይህንን ለመረዳት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 9 (4) እና አንቀጽ 13 (2) ድንጋጌዎች በዋቢነት ይመለከቷል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀርን ለመጀመርያ ጊዜ የሚያስተዋውቀው የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ቋንቋንና የሕዝቦችን ማንነት መሠረት በማድረግ አገሪቱን በክልሎች ከማዋቀሩም በላይ፣ የግዛት ወሰኗም በእነዚሁ ክልሎች አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ልክ የሚገለጽና አስቀድሞ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተወሰነ ስለመሆኑ በደምሳሳው ይነግረናል፡፡ የሰነዱን አንቀጽ 1 እና 2 ድንጋጌዎች ይመለከቷል፡፡

እዚህ ላይ ‹‹ዓለም አቀፍ ስምምነቶች›› የሚላቸው በዙሪያዋ የሚገኙት አጎራባች አገሮች ነፃ ከመውጣታቸው በፊት፣ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት በተለያዩ ጊዜያት ከእነዚሁ አገሮች ቅኝ ገዥዎች ጋር ያደረጓቸውን ውሎች ሳይሆን እንደማይቀር ለመገመት ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ ተጨማሪ አስተያየት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የዚህ ጽሑፍ ዓይነተኛ ዓላማ ባለመሆኑ ለጊዜው ብዙ ልገፋበት አልወደድኩም፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በተለይ ከአንቀጽ 8 እስከ 12 ባሉት አንኳር ድንጋጌዎቹ ሥር ይበልጥ ተጨንቆና ተጠቦ ያካተታቸው ዋና ዋና መርሆች፣ የየትኛውንም ተደራሲ ትኩረት የሚስቡና አብዝተው የሚያማልሉ መሆናቸው አንድና ሁለት የለውም፡፡ የ‹‹ሕዝብ ሉዓላዊነት››፣ የ‹‹ሕገ መንግሥት የበላይነት››፣ የ‹‹ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ አይጣሴ፣ አይገረሰሴነት››፣ የ‹‹መንግሥትና የሃይማኖት መለያየት››ም ሆነ የ‹‹መንግሥታዊ አሠራር ግልጽነትና የባለሥልጣናት ተጠያቂነት›› ሕገ መንግሥቱ ገና ከመነሻው ሲዋቀር የተደገፈባቸው ፅኑ ምሰሶዎች ናቸው ቢባል ፈፅሞ ማጋነን ሊሆን አይችልም፡፡

በእርግጥ የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ፋይዳ መመዘን የሚገባው ከገቢራዊነታቸው ይልቅ፣ እዚህም እዚያም እየተለቃቀመ ተሰባስቦ በታጨቀባቸው አሸብራቂ መርሆች አንፀባራቂነትና በውስጡ ባሰፈራቸው የሰብዓዊ መብት መዘርዝሮች ብዛት ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡ ሰነዱ የላቀውን ክብርና ሞገስ የሚያገኘው በገቢር ሲተረጎም ብቻ ይሆናል፡፡

ማኅተምን በአንገት ማጥለቅ ብቻውን የትኛውንም ሰው ክርስቲያን፣ ፊትን በሂጃብ መሸፈን ብቻውን እንዲሁ የትኛውንም ሰው እስላም ሊያሰኝ እንጂ ሊያደርግ እንደማይችል ሁሉ፡፡

እንበልና በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶች በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 15፣ 16 እና 17 ሥር የክብር ቦታ ተሰጥቷቸው በፊታውራሪነት ተደንግገዋል፡፡ ለምሳሌ ማንም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ ምክንያት በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ የተደነገገ ከባድ የወንጀል ድርጊት በመፈጸሙ ተከስሶ በመደበኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ካልተባለና የሞት ቅጣት ካልተወሰነበት በስተቀር፣ ውድ ሕይወቱን በዘፈቀደ ዕርምጃ እንደማያጣ በአንቀጽ 15 ሥር ሠፍሯል፡፡ በፍርድ ተወስኖ ቢገኝ እንኳ እንዲህ ያለው የሞት ቅጣት ራሱ ተፈጻሚነት የሚኖረው፣ በመጨረሻ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀርቦ ከታየና እንዲፀና ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 117 ንዑስ (1 እና 2) ድንጋጌዎችን ይመለከቷል፡፡

የአካል ደኅንነት መብትማ በማናቸውም ሁኔታ የማይሸራረፍና ከናካቴው አይነኬ እንደሆነ ከወዲሁ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ የተነሳ ይመስላል፣ ለየትኛውም ዓላማ በማንኛውም ሰው የአካል ደኅንነት መብት ላይ መንግሥት ተብዬውም እንኳ በልዩ ሁኔታም ቢሆን ማናቸውንም ዓይነት ጉዳት እንዳያደርስ፣ ሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 16 ሥር መጠነ ሰፊ ክልከላ ጥሎበት የምናገኘው፡፡

የነፃነት መብትን በተመለከተ ደግሞ ማንም ሰው በሕግ ከተደነገገው ባፈነገጠ አካሄድ ሊያዝ ወይም ሊታሰር እንደማይችል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 ንዑስ (2) በማያሻማ ቋንቋ ይደነግጋል፡፡ ከባድ ወንጀል ሊፈጸም ሲል፣ በመፈጸም ላይ ሳለ ወይም ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር በወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው በመርማሪ ፖሊስ ሊጠራ፣ ወይም ይህንኑ ተቃዋሚ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም ሊያዝ የሚችልበት ዝርዝር አሠራር ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 19 ሥር ካካተታቸው ድንጋጌዎች በተጨማሪ፣ በአገሪቱ ነባር የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 19 ንዑስ (1)፣ አንቀጽ 25፣ አንቀጽ 26 ንዑስ (1) እና አንቀጽ 51 ንዑስ (1) ሥር አስቀድሞ መሥፈሩን እናውቃለን፡፡

ከዚሁ ጋር በተዛመደ ኢሰብዓዊ አያያዝን አምርሮ የሚቃወመው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18 ንዑስ (1) በበኩሉ ጭካኔ የተመላበት፣ አረመኔያዊ የሆነና ሰብዓዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ወይም የሚያዋርድ አያያዝን ወይም ቅጣትን በፅኑ  ይኮንናል፡፡ በእርግጥ ይህ ዓይነቱ የሰቆቃ ድርጊት በማንኛውም ሰው ላይ ተፈጽሞ ቢገኝ በየትኛውም ደረጃ በወንጀሉ የተሳተፉትን አካላት ሁሉ በሰብዕና ላይ ከመነጣጠሩ የተነሳ ቀድሞ ነገር አንዳች ይቅርታ ሊያሰጥ ወይም በይርጋ ቀሪ ሊደረግ በማይችል ከባድ ወንጀል እንደሚያስከስስና በፅኑ እንደሚያስቀጣ ሕገ መንግሥቱ በሌላ ሥፍራ፣ ማለትም በአንቀጽ 28 ንዑስ (1) ሥር ይደነግጋል፡፡

እነሆ ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው ሁሉ በየትኛውም ደረጃ ቢሆን በዘፈቀደ ሊጣሱና ሊገሰሱ የማይገባቸው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች መሆናቸውን እንደገና በአንክሮ ለማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ የእነዚህና እነዚህን የመሳሰሉት ወርቃማ ድንጋጌዎች ገቢራዊነት ምን ይመስላል የሚለውን ማዕከላዊ ነጥብ ግን፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከምንመለከታቸው አሰቃቂና አንገት አስደፊ እውነታዎች ጋር ካልተመሳከረ በስተቀር አስተማማኝ ብያኔ ሊሰጥበት አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አሠርተ ዓመታት ለፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተሃድሶ በትጋት ስትሠራ እንደቆየች አሌ አይባልም፡፡ ከሁሉም በላይ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በንፁህ የመጠጥ ውኃና በመሳሰሉት የመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታና ሥርጭት ረገድ የራሷን አቅምና የተባባሪ አገሮችንም ሆነ የዓለም አቀፍ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ድጋፍ አቀናጅታ በመጠቀም ያደረገችው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያሳየችው ትጋትና ያስመዘገበችው አፈጻጸም በውስጥም ሆነ በውጭ ብዙ፣ በጣም ብዙ እንደተባለለት መካድ አይቻልም፡፡

ይሁን እንጂ በማደግ ላይ ያለችው አገር ከዚህ አዎንታዊ ዕርምጃዋ ጋር በተያያዘ የልማት አጋሮቿን ትኩረት አብዝታ የሰበችውን ያህል እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በሲቪልና በፖለቲካ መብቶችና ነፃነቶች አከባበርና ጥበቃ በኩል ስሟ በበጎ ሲነሳ የተሰማበትን ጊዜ ማስታወስ ያዳግታል፡፡ በተቃራኒው ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በየጊዜው በሚያወጧቸው ዘገባዎች ሁሉ ያለ ማቋረጥ እንደተወቀሰችና ጠዋት ማታ እንደተብጠለጠለች ነበር፡፡ መንግሥቷ ራሱ ያለ ዕረፍት ለሚወርድበት ለዚያ ከፍተኛ የወቀሳና የትችት ናዳ ይሰጥ የነበረው የማላገጫ ምላሽ መልሶ ራሱን ክፉኛ የሚያስጠቃው መስሎ የሚታይባቸውን ብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል፡፡

አንድ አብነት ብቻ መዝዞ ለመጥቀስ ያህል ለምሳሌ ከወራት በፊት የምናውቃት ኢትዮጵያ ጥቃቅንና መናኛ ምክንያቶችን ፈልጋ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን እያደነች በመያዝና ዘብጥያ በማውረድ፣ ከዓለም አገሮች ውስጥ ለአንደኛው የቀረበች እንደነበረች ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ ሆኖም ይህ ዕርምጃቸው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29 ድንጋጌዎች ይፃረር ወይም አይረር እንደሆን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ጥያቄ በቀረበላቸው ቁጥር፣ ቀደምት ጠቅላይ ሚኒስትሮቿን ጨምሮ አንዳች አንዳች የሚያህሉ የየደረጃው ባለሥልጣናቷ ሁሉ የተለማመዱት አንድ ዓይነት የደቦ መልስ ነበር፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በሌላ ወንጀል ካልሆነ በስተቀር በጋዜጠኝነቱም ሆነ በጦማሪነቱ ምክንያት የታሰረ ሰው የለንም!›› የሚል፡፡

እነ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ርዕዮት ዓለሙና ዮናታን ተስፋዬ ያለ አበሳቸው የተያዙትና ተፈርዶባቸው ወህኒ የወረዱት በስርቆት፣ በድብደባ ወይም በነፍስ ግድያና በመሳሰሉት ደረቅ ወንጀሎች ይመስል፡፡

ጥልቅና ውስብስብ ለሆነው የሰው ልጅ የመማርና አካባቢን የመገንዘብ ችሎታ ሳይቀር አነስተኛ ግምት የሚሰጠው ይህ ዓይነቱ አሰልቺ የምንተዳዬ ምላሽ፣ በተለይ ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የክፉ ደዌ ያህል ተጣብቷቸው ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ሰውየው የጋዜጠኝነትም ሆነ የጦማሪነት ሥራ ምን እንደሆነ ዓለማችን ጨርሶ እንደማይገባት ቆጥረው ማንም ሰው ሐሳቡን በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ ወዘተ ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጽ በመሰንዘሩ ወይም ድምፁን በብዙኃን የመገናኛ ዘዴዎች በማሰማቱ ምክንያት አልታሰረም ወይም አልተከሰሰም እያሉ ደጋግመው ሲለፍፉ፣ ከራሳቸው ጋር የሚጣሉ መስለው አለመታየታቸውን ዛሬም ቢሆን ሳስበው ያስደነግጠኛል፡፡

አስቀድሞ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ስምምነቶችን ወዳና ፈቅዳ በይፋ የተቀበለች አገር ናት፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ራሱ በአገሪቱ ውስጥ በስፋት ሲፈጸም የቆየውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በራሷ የማጣራትና ጥፋተኞችን ለይታ በአፋጣኝ ለፍርድ የማቅረብ አቅም ቢያንሳት እንኳ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የመጠየቅ ዕድል ይሰጣታል፡፡ ሆኖም ይህንን አማራጭ ለመጠቀም ይፈቅዱ እንደሆን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዛይድ ራአድ አል ሁሴን ቀዳሚ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር አያይዞ ቢቢሲ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 18 ቀን 2017 ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኃይለ ማርያም የሰጡት አሳዛኝ አይሉት አስቂኝ መልስ፣ ‹‹እስከ ታች ድረስ ወርዶ ምሬት የሚቀርብባቸውን ከባባድ ጥሰቶች የማጣራት ችሎታና ተቋማዊ ብቃት ያለው የራሳችን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እያለን፣ የውጭ መርማሪዎችን በመጋበዝ ሉዓላዊነታችንን አናስደፍርም፤›› በሚል ተራ ምፀት የታጀበ ነበር፡፡

ሰውየው ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ እስከተባለበት ቀን ድረስ ሳይለወጥ ለረዥም ጊዜ የቀጠለው መስሎ የማደር ቁርጠኝነታቸው ከፍተኛ አግራሞት የጫረበት ይህ ጸሐፊ ራሱ፣ አዲስ ስታንዳርድ በተሰኘውና በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየታተመ በሚሠራጨው የአገር ውስጥ ‹ኦንላይን› መጽሔት ላይ እ.ኤ.አ. May 9 ቀን 2017 (ከ19 ወራት በፊት መሆኑ ነው)፣ “Ethiopia: The Chief Commissioner’s Visit and its Fallout” በሚል ርዕስ ባቀረበው አነስተኛ መጣጥፍ፣ ተከታዩን ትችት አዘል አስተያየት እስከ መሰንዘር ደርሶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

“I fail to comprehended what Prime Minister Hailemariam Desalegn had to tell the world when he told the BBC on April 18, 2017 what the country’s sovereignty would be jeopardized should he allow an outside mechanism to conduct the alternative investigation of the human rights’ complaints.”

ከየትኛውም የሕግ ዓይነት በላቀ ሁኔታ ሕገ መንግሥት እንዳስፈላጊነቱ የምናከብረው ወይም በአማራጭ የምንሽረው ሰነድ አይደለም፡፡ ከመሠረታዊ ልዕልናው የተነሳ ይህንን እንድናደርግ ፈጽሞ አይፈቅድልንም፡፡ ያለን ብቸኛ ምርጫ ለእርሱ መቆም ወይም በእሱ ላይ መቆም ይሆናል፡፡

አደረጃጀቱን በሚመለከት ሕገ መንግሥት እንደማናቸውም የሕግ ሰነድ ተከፋፍሎ ይዘጋጅ እንጂ፣ በተከባሪነትና በተፈጻሚነት ረገድ የሚበላለጡና የዘፈቀደ አድልዎን የሚያስተናግዱ አናቅጽ የሉትም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሚተገበርበት ምድር ዛሬ ተከብረው ነገ የሚጣሱ ወይም በተገላቢጦሹ ዛሬ ተጥሰው ነገ የሚከበሩ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ማሰብ አይቻልም፡፡ ስለሆነም የአንድ አገር ዜጎች በወኪሎቻቸው አማካይነት መክረው የተስማሙበት ወይም ቢያንስ ተስማምተው እንዳወጡት የሚዘመርለት ሕገ መንግሥት፣ በዚያች አገር ውስጥ በሁሉም ሥፍራ ወጥ በሆነና ልዩነት በሌለው መንገድ መከበርና መፈጸም ይኖርበታል፡፡

በእርግጥ አስቀድመው በጥናት የተለዩና ራሱ ሕገ መንግሥቱ የተቀበላቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲከሰቱ፣ የአንዳንድ ድንጋጌዎቹ ሙሉ ተፈጻሚነት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው ያልተፈለገ ወይም ያልተጠበቀ አጋጣሚ በሕግ ለተወሰነ ጊዜና አልፎ አልፎም በተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚሠራበት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

የትኛውም ሕገ መንግሥት ለራሱ ቀናዒ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በተለይ ለሕግ ጠቢባን ይህ እንግዳ ነገር ሊሆንባቸው አይችልም፡፡ አገርና ሕዝብ የሚተዳደሩበት የበላይ ሕግ ለተደጋጋሚ ጊዜ ሲጣስ ምላሽ የሚሰጥበትና ልዕልናውን የሚከላከልበት ጠንካራ ማሽነሪና ግልጽ ሥነ ሥርዓት ከሌለው፣ ራሱን በዜሮ የሚያባዛ ባዶ ሰነድ ይሆናል፡፡ በእማ ዘውዴ ቋንቋ ‹‹የወረቀት ላይ ነብር›› ሆኖ ይቀራል ማለት ነው፡፡

በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ይህ አስከፊ ዕጣ ፈንታ ሳይገጥመው አልቀረም፡፡ በተለይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና ነፃነቶችን የያዘው የሕገ መንግሥቱ ሦስተኛ ምዕራፍ ከሁሉም ለባሰ አደጋ ተጋልጦ ቆይቷል፡፡ ንፁኃን ዜጎች ለምን ተፈጠራችሁ ተብለው በወንጀል ምርመራ፣ በሕግ ማስከበርና አንዳንዴም በዳኝነት ስም በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶቻቸውን ያላግባብ ተነጥቀዋል፡፡ ሀብትና ንብረታቸውን ተዘርፈው ኑሯቸው እጅግ ተመሰቃቅሏል፡፡ ይህ ገቢራዊ ሲደረግ የቆየው ሕገ መንግሥቱ ባደራጃቸው የፖሊስ፣ የደኅንነትና የፍትሕ ተቋማት ጭምር መሆኑ ሲታይ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ የከበደና የመረረ ያደርገዋል፡፡

እንግዲህ ከደርግ ውድቀት ማግሥት የመጀመርያዎቹን አራት ዓመታት ከመለማመጃነታቸው የተነሳ ናቅ አድርገን ብንደግፋቸው እንኳ ሕገ መንግሥቱ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ወንድና ሴት ወገኖቻችን ላይ የወረደው ግፍና መከራ ያስከተለውን ከባድ ኪሳራ ማካካስ ባይሞከርም፣ በጥቂቱ መቀነስ የሚቻለው መረን በለቀቀው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ቁልፍና ቀንደኛ ተጠርጣሪዎች ሆነው የተገኙትን ግለሰቦች ከየተደበቁበት ዋሻ አድኖ በመያዝ፣ አፋጥኖ በመመርመርና ለተገቢው የፍርድ አካል አቅርቦ በማስቀጣት ብቻ ይሆናል፡፡

እንደ አገራችን "ኖሜንክሌቸር" (Nomenclature) ከሆነ ሕገ መንግሥቱን በዝርዝር መክረው ያፀደቁት የሕዝብ እንደራሴዎች እንዳልሆኑ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ቀድሞ ነገር ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔውን የመሠረቱት በጊዜው መንግሥታዊ በትረ ሥልጣኑን በኃይል አሸንፎ በተቆጣጠረው አማፂ ድርጅት ረዥም እጆች ዘዋሪነት፣ ከየአካባቢው የተመለመሉና የአንድ ርዕዮት ካድሬዎች የሚበዙባቸው የብሔር ብሔረሰቦች ተጠሪዎች ናቸው ተብለው የተሰባሰቡ ሰዎች ነበሩ፡፡

እንዲያ መሆኑን እያወቅን እንኳ ሕገ መንግሥት እንዲኖረን ስለተደረገበት ኢሕገ መንግሥታዊ አካሄድ ያን ያህል ያማረርንበት አንድም ቀን አልነበረም፡፡ ቅሬታችን በስፋት የመነጨውና ቀስ በቀስ ወደ ዛሬው የለውጥ ፍላጎት እየተሸጋገረ የመጣው ‹‹ነገሩ ስለ ራሱ ይናገራል›› እንደሚለው የቀድሞ የላቲን ፈሊጣዊ አነጋገር፣ ሕገ መንግሥቱ በቃል ያለውን በገቢር ሆኖ መገኘት ባለመቻሉ ብቻ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ ሕገ መንግሥቱን የምንፈልገው ኅዳር 29 በመጣ ቁጥር እንደ ክት ቀሚስ ከተደበቀበት ቁም ሳጥን እያወጣን ልንለብሰውና በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ልናጌጥበት አይደለም፡፡ በአዘቦት ጭምር ልናጣፋውና መላ ሰውነታችንን ከቁርም ሆነ ከሃሩር ልንከላከልበት እንጂ፡፡

እነሆ ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡ ዛሬም ቢሆን ዛሬነቱን ክዶ የኋሊት ወደ ትናንት ሊያፈገፍግ የሚችልበት አንዳች ተፈጥሯዊ ምትኃት የለም፡፡ ስለሆነም ከልባችን ከተነሳሳን ትናንት ያለፍንበትን አስፀያፊ ኩነት በከንቱ ማስተባበሉን አቁመን አኩሪ የሕገ መንግሥት ታሪክ ባይኖረን እንኳ፣ ሕገ መንግሥቷን በዘፈቀደ የማትጥስና የማትገስስ አዲስ አገር መፍጠርና እንደ ወትሮው በጉያዋ ተሰባስቦ በአብሮነት መቀጠል አያቅተንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡