Skip to main content
x

ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት የኢትዮጵያ ልማታዊ ካፒታሊዝም

በኒዮሊበራል ካፒታሊዝም ያደገና የለማ ደሃ አገር የለም

በአንዳርጋቸው አሰግድ

ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን እንደያዘ ያወጀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ “ነፃ ገበያ” የሚባለውን የሊበራል ካፒታሊዝም ፖሊሲ ነበር፡፡ 223 የመንግሥት የማምረቻና የአገልግሎት ድርጅቶች ከ1987 እስከ 1994 ዓ.ም. ባለው ዘመን ለግል ባለሀብቶች በ3,463 ሚሊዮን ብር ተሸጡ፡፡ በ2,338 ሚሊዮን ብር (70 ከመቶውን) የገዙት የሼክ መሐመድ አላሙዲን ሚድሮክና ሳዑዲዎች ነበሩ (ወርቁ ገበየሁ፣ Has Privitization Promoted Efficency in Ethiopia? 2005፣ 6 እስከ 9)፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም የበኩላቸውን ገዝተው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ልማታዊ ካፒታሊዝም በሚል የሚታወቀውን የዕድገት ፖሊሲ እንደሚከተል አሳወቀ፡፡ በሥራ ማዋል ጀመረ፡፡ ራሱን “ልማታዊ መንግሥት” እያለ ገለጸ፡፡

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በ2010 ዓ.ም. ሥልጣን ከጨበጡ ወዲህ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ምንነት በግልጽ አላሳውቁም፡፡ ይሁንና አንዳንድ ዕርምጃዎቻቸው የኢትዮጵያን የዕድገት ጎዳና በኒዮሊበራል ሥሪት (Model) ወደ መቃኘት እንዳቀኑ ያመለክታሉ፡፡ በዚህም ለማለት ይቻላል ኢትዮጵያ በ27 ዓመታት ውስጥ ሦሰት ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን፣ ወይም በየዘጠኝ ዓመቱ አንድ ሌላ የአኮኖሚ ሥሪት ያየች አገር ሆናለች፡፡ የመስኩ ባለሙያዎች አሉታዊ ጫናውን እንደሚያብራሩት ተስፋ ይደርጋል፡፡ በኒዮሊበራሊዝም ሥሪት ያደገና የለማ ደሃ አገር አለ ብሎ የሚዘከር የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያ ይኖራል ብዬ ግን አልገምትም፡፡ ያም ተባለ ያ ለነገሩማ ሁሉም የካፒታሊስት ዓይነቶች (ዝርያዎች) ናቸው፡፡ ሁሉም የርዕዮተ ዓለማዊ ወይም የማኅበራዊ ፖለቲካ አመለካከቶች ናቸው፡፡ በመሠረቱና ዞሮ ዞሮ የሚለያዩትም፣ በመንግሥት ሥፍራና ሚና ጉዳይ ረገድ በሚይዙት ርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከት (አቋም) ነው፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የአስተዳደሩ ፖሊሲዎችና ተግባራዊ አፈጻጸም ለየትኛው ማኅበራዊ ክፍል (መደብ) በይበልጥ ያደላል/ይወግናል ለሚለው ጥያቄ እንደሚገኘው መልስ ነው፡፡

ሊበራል ካፒታሊዝም በአጠቃላይ የቀድሞ (ክላሲካል)፣ ዘመናዊና ኒዮሊበራል በሚል ይለይ እንጂ ወደ ዝርዝር ሲገባ በርካታ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ የጀርመንና የፈረንሣይ፣ የአሜሪካና የስዊድን፣ የጣሊያንና የስዊዘርላንድ. . . ካፒታሊዝም በብዙ ይለያያሉ፡፡ ዘመናዊ ሊበራሊዝም ለግል ንብረትና ጥረት መአከላዊ ሥፍራ የሚሰጥ ቢሆንም እንደ ቀድሞውና እንደ ኒዮሊበራሊዝም ‘ሁሉም ነገር በገበያ ይወሰን፡፡ ሁሉንም ነገር ለግል ባለሀብቶች’ የሚል አመለካከት የለውም፡፡ እንደዚሁም ‘የመንግሥት ሥፍራና ሚና ይሽመድመድ’ አይልም፡፡ በመንግሥት ሥፍራና ሚና እንደውም ዘመናዊ ሊበራልና ልማታዊ ካፒታሊዝም በብዙ ይመሳሰላሉ፡፡ ልማታዊ ካፒታሊዝምም እንደዚሁ አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ቻይና፣ ማሌዥያ፣ ታይላንድ፣ ቬትናም፣ ሲንጋፖርና ደቡብ ኮሪያ ይለያያል፡፡  

ዘመናዊ ሊበራል ካፒታሊዝምን የሚያራምዱ መንግሥታት የዝቅተኛዎቹን ማኅበራዊ ክፍሎችና የድኩማንን ደኅንነት የመንከባከብ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው በጽኑ ያምናሉ፡፡ ስለዚህም ለግል ባለሀብቶች ዕድገት ሁኔታዎችን የሚያመቻቹና መብቶቻቸውን አጠንክረው የሚጠብቁትን ያህል ሕጋዊ ገደቦችንም ያፀኑባቸዋል፡፡ በዚያውም ልክ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈንና መደርጀት አጠንክረው ይቆማሉ፡፡ የዝቅተኛ ማኅበራዊ ክፍሎችንና የድኩማንን ማኅበራዊ ተቋዳሽነት ለመንከባከብ ይተጋሉ፡፡ ለዚህም ዋናው መሣሪያቸው በግል ባለሀብቶች ትርፍና ዓመታዊ ገቢ ላይ የሚጥሉት ከፍተኛ የቀረጥና የግብር ክፍያ ነው፡፡ እንደዚሁም ጠንካራ የማኅበራዊ እንክብካቤ ሕጎቻቸውና ደንቦቻቸው ናቸው፡፡ ከቀረጥ በሚገኘው ገንዘብ ጠንካራ የማኅበራዊ አገልግሎት አቅራቢ ተቋሞችን ያደራጃሉ፡፡ ከዚህም አኳያ የሠራተኛ  የሶሻል ዴሞክራሲና የሶሻሊስት ፓርቲ ከሚባሉት በሚመሳሰል ለመንግሥታዊ ደሃ ተኮር ፖሊሲ ይሞግታሉ፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ነፃ ገበያም ያለ ልጓም እንዳይፈነጭ በመንግሥታዊ ፖሊሲዎችና በነፃ ገበያ ክንዋኔ መካከል የተስተካከለ (የማያዳላ) ሚዛን (Fine Balance) እንዲኖር ይጥራሉ፡፡

ኒዮሊበራሊዝም የሚባለው ክላሲካል ከሚባለው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ጀምሮ ረዥም የጀርባ ታሪክ ቢኖረውም በዘመናችን ጎልቶ የተከሰተውና የተንሰራፋው ባለፈው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሬገንንና በእንግሊዛዊቷ ማዳም ታቸር ገዥነት ዘመን ነው፡፡ በይዘቱ ከ20ኛው ክፍለ ዘመኖቹ ዘመናዊ ሊበራል ካፒታሊዝም ሆነ ከልማታዊ ካፒታሊዝም በጣም ይለያል፡፡ በእጅጉ የሚዛመደው ይልቁኑ ከቀድሞው የ19ኛው ክፍለ ዘመን (ክላሲካል) ሊበራሊዝም ጋር ነው፡፡ “ኒዮ” ከግሪክ ቋንቋ የተወረሰ ቃል ሲሆን፣ እንደ “አዲስ” ተመልሶ የመጣን (ነፍስ የዘራን) ክስተት ለመግለጽ ይውላል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ ሊበራሊዝም ላይ “ኒዮ” የሚለው ቃል የታከለው ተመልሶ የመጣ የቀድሞ (ክላሲካል) ሊበራሊዝም ዝርያ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ በሌላም በኩል ከዘመናዊው ሊበራል ካፒታሊዝም የሚለይ መሆኑን ለማስረገጥ ነው፡፡

እንግሊዛዊው ተመራማሪ ዴቪድ ሃርቬ የኒዮሊበራሊዝምን ምንነት በአጭሩና በጥሩ እንደገለጸው “ኒዮሊበራሊዝም በመጀመርያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አመለካከትን (ርዕዮተ ዓለምን) ወደ ተግባር የመተርጎሚያ ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ የመነሻ ሐሳቡም የግለሰብ ሰብዓዊ ደኅንነት ተሟልቶ ሊረካ የሚችለው የግለሰብ መዋዕለ ንዋይና ክህሎት ሙሉ ነፃነትን ሲጎናፀፉ ነው፡፡ የመንግሥት ሚና ይህ ግብ ያለገደብ እንዲሳካ አሰፈላጊዎቹን ተቃውሞች ማቋቋምና መጠበቅ ነው፡፡ የሠራዊት፣ የመከላከያ፣ የፖሊስና የሕግ ተቋሞች ኃላፊነት ሚናና ተግባርም የግል ንብረትን ደኅንነት የመጠበቅና የነፃ ገበያን ያልተገደበ እንቅስቃሴ የመንከባከብና የማረጋገጥ መሆን አለበት፤” የሚል ነው (David Harvey A Brief History of Neoliberalism 2005)፡፡

ልማታዊ ካፒታሊዝም ስሙ ጭምር እንደሚገልጸው ዕድገትንና ልማትን ለሚያስቀድም ግብ በመንግሥታዊ አስተዳደር መሪነት ወደ ተግባር የሚተረጎም ካፒታሊዝም ነው፡፡ መንግሥቱ ስለዚህም ልማታዊ መንግሥት (Developmental State) ይባላል፡፡ ልማታዊ ካፒታሊዝም ከዘመናዊ ሊበራልና በተለይም ከኒዮሊበራል ካፒታሊዝም በእጅግ ይለያል፡፡ የልማታዊ ካፒታሊዝምን ምንነት ለመጀመርያ ጊዜ በጥሩ ያብራሩት የጽንሰ ሐሳቡ መሥራች ተብለው የሚታወቁት አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ካልመርስ ጆንሰን ናቸው፡፡ ካልመርስ በአጭሩ እንደገለጹትም፣ ‘ልማታዊ  ካፒታሊዝም በእንዱስትሪ ምርትና በውጭ ንግድ ወደ ኋላ በቀሩና የአገሬው ባለሀብቶች አቅምና የሠለጠነ የሰው ኃይል (ሰብዓዊ ካፒታል) ደካማ በሆኑባቸው አገሮች ውስጥ፣ አስተዳደሩ በዕድገትና በልማት ሥራዎች ላይ አተኩሮ ከድህነት አረንቋ የሚያላቅቁ መንግሥታዊ ዕርምጃዎችን የሚወስድበት ካፒታሊዝም ነው፡፡ ለዚህም፣ መንግሥት ራሱ በአንድ በኩል ግብርናን በማዘመን፣ እንዱስትሪዎችን በማሳደግና የውጭ ንግድን በማበረታታት ሥራዎች ላይ ይሰማራል፡፡ በሌላ በኩል ትምህርትንና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና አስፈላጊ ተቋሞችን በመገንበትና በማደርጀት በከፍተኛ ይንቀሳቀሳል፡፡ የግል ባለሀብቶችን ዕድገትና የገበያ ትስስርን ለማጎልበትና ለማደርጀት ይሠራል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዝቅተኞቹን የማኅበራዊ ክፍሎች በማይጎዳ መንገድ እንዲዳብር በተለያዩ ፖሊሲዎች ያግዛል’ (Chalmers Johnson MITI and the Japanese Miracle 1982)፡፡

ልማታዊ ካፒታሊዝም አሁን አሁን በተለይ የደሃ አገሮች የዕድገትና የልማት ጎዳና እየተባለ ይነገር እንጂ በአንዱ ወይም በሌላው ወቅትና በአንዱ ወይም በሌላው መንገድ በሥራ ሳያውለው ያደገ አንድም የሊበራል ወይም የኒዮሊበራል አገር የለም፡፡ ለዚህም የአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት አሜሪካን ከ1930ዎቹ ቀውስ እንድታገግም በሥራ ያዋሉትን አዲስ ውል (New Deal) ለማስታወስ ይቻላል፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጦስ ያደቀቃቸው የአውሮፓ አገሮች ያገገሙትም፣ አስተዳደሮቻቸው ለረዥም ዓመታት በያዙት የኢኮኖሚ መሪነት ሥፍራና ሚና ነበር፡፡

“ሁሉም ነገር በገበያ ጡንቻ ይወሰን” የሚሉት የኒዮሊበራል መንግሥታት አስተዳደሮችም ቢሆኑ ታሪፍና ድጎማ (Subsidy) በሚል የሚታወቁትን የኢኮኖሚ አመራር መሣሪያዎች በሥራ ያውላሉ፡፡ የአሜሪካን መንግሥት ግብርናን፣ ነዳጅንና የወጭ ንግድን በየዓመቱ በ15 ቢሊዮን ዶላር ይደጉማል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት አባል መንግሥታትና ኅብረቱ በ2017 ነዳጅን ብቻ እስከ 112 ቢሊዮን ዩሮ ድረስ ደጉመው ነበር፡፡

የጋራ ግብርና ኅብረት (CAP) በሚባለው ፕሮግራም መሠረት ኅብረቱ ብቻ ከ50 ቢሊዮን ዩሮ ያላነሰ ለገበሬዎቹ በየዓመቱ ይደጉማል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ የአሜሪካንን የ2007/8 (1999/2000) ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ለመጠገን ለባንኮች ያደረጉት የ700 ቢሊዮን ዶላር፣ ለመኪና ኢንዱስትሪዎች ያደረጉት የ80 ቢልዮን ዶላርና ለኢኮኖሚ ማንቀሳቀሻ በሚል ያደረጉት የ800 ቢሊዮን ዶላር ድጎማዎች ሌሎቹ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከ2016 (2008) ጀምሮ በቻይናና የአሜሪካን አጋር በሚባሉት አገሮች ላይ ጭምር በየዕለቱ የሚያውጁት የታሪፍ ጥሎሽም ጊዜያዊ ምሳሌ ነው፡፡ የዘመናዊ ሊበራልና የኒዮሊበራል መንግሥታት አስተዳደሮችና ባንኮች ሕዝባቸው የአገሩን ምርት እንዲመርጥና እንዲሸምት የሚደርጉት ከፍተኛ ቅስቀሳና በድጎማ ጭምር የሚፈጽሙት ማበረታችም ሁሉ የዚሁ አካል ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ ድጎማ ያደጉት ካፒታሊስት አገሮች መንግሥታት ለራሳቸው ሲሆን መብታቸው መሆኑን አስረግጠው በጡንቻ ጭምር በተግባር የሚያውሉት የየአገራቸው የዕድገትና የልማት ፖሊሲና ከካፒታሊስት ሥርዓት የቀውስ እሽክርክሪት የመውጫ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው፡፡ በልማታዊ ካፒታሊዝም ሥሪት ከድህነት አረንቋ ለመላቀቅና ለማደግ የሚጥሩት አገሮች በሥራ ሲያውሉት ግን፣ የደቡብ ኮሪያው የኢኮኖሚ ተመራማሪ ቻንግ በትክክል እንዳለው፣ ‘የግል ባለሀብቶችን ሰብዓዊ ነፃነትና የግል ካፒታሊዝምን ዕድገት የሚጋፋ አፋኝና ለዕድገትና ለልማት የማይበጅ ፖሊሲ’ እያሉ ያወግዙታል፡፡ ባላቸው ጉልበት ሁሉ ለማክሽፍ ይታገሉታል’ (Ha-Joon Chang፣ Kicking Away the Ladder 2002)፡፡ ስትራቴጂያቸውን በግልጽ ለመገንዘብ በቻይና፣ ኢራንና አጋር አገሮች በሚሏቸው ላይ ሳይቀር የተከፈተው የትራምፕ ዘመቻ ጥሩ ወቅታዊ ምሳሌ ነው፡፡ በህንድ፣ በቬትናምና ወዘተ. እያለ መቀጠሉም የማይቀር ሊሆን ይችላል፡፡

የተመለከተው የኒዮሊበራሎች ጨቋኝ ስትራቴጂ በአንድ ወገን ለማደግ የሚጥሩትን ደሃ አገሮች የሰውና የተፈጥሮ ሀብት ገባሪ አድርጎ ለማስቀረት ካላቸው ግብ ይመነጫል፡፡ በሌላውም በኩል ለማደግ የሚጥሩትን ደሃ አገሮች ከነሱ ምርቶች ፍጆታ ጋር የተቆራኙና የነሱ ተመፅዋች አድርገው ለማስቀረት ካላቸው ስትራቴጂያዊ ግብ ይመነጫል፡፡ እሳቤያቸው ድብቅ አይደለም፡፡

ደሃ አገሮች በልማታዊ ካፒታሊዝም ጎዳና ወደ ዕድገትና ልማት ካቀኑ የሰውና የተፈጥሮ ሀብታቸውን እያፈሱ ለነሱ ከመገበር ለራሳቸው ያውላሉ፡፡ ካደጉት አገሮች አረንቋ ወጥተው ራሳቸውን የቻሉ ነፃ አገሮችና ሕዝቦች ይሆናሉ፡፡ የሰው ካፒታላቸውንና ምርታቸውን አሳድገው ተወዳዳሪ ለመሆን ጭምር ይበቃሉ፡፡ ከተመጽዋችነት ወጥመድ (ፍዳቸው) ተላቀው ቀና ብለው የሚሄዱ ይሆናሉ፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንዳለው “የምግብ ሰሌዳውን እያዩ ከመቋመጥ ተላቀው፣ ከገበታው ላይ ይቀመጣሉ”፡፡

ለሪፖርተር ዕትም ባቀረብኩት አንድ ጽሑፍ በአጭሩ ለማመልከት እንደሞከርኩት፣ የኒዮሊበራሎች ሥሪት በደሃ አገሮች ላይ እየተጫነ በተግባር ሲተረጎም “መንግሥት ከኢኮኖሚ ተሳትፎ ይውጣ፡፡ የማምረቻ፣ የማከፋፈያ፣ የአገልግሎት ሰጪና የገንዘብ ድርጅቶች ሁሉ ከመንግሥት ይዞታ ወደ ግል ንብረት ይዛወሩ፡፡ አገሮች ለውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋይ ፍሰትና ለውጭ ሸቀጦች ዝርገፋ ያለገደብ ይከፈቱ፡፡ የብሔራዊ ገንዘብ ዋጋ ይቀነስ፡፡ ሕጎችና ደንቦች ለግል ባለንብረቶች ትርፍ መጨመር በሚጠቅሙ መንገዶች ይደንገጉ፡፡ ባለሀብቶች አነስተኛ ቀረጥ ይክፈሉ፡፡ መንግሥት ለምግብ፣ ለሕክምና፣ ለቤት፣ ለውኃ፣ ለመብራት፣ ለማመላለሻ፣ ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ወዘተ. የሚያደርገው ድጎማ ይሰረዝ፡፡ የኢኮኖሚው ዕጣ በገበያ ጡንቻ ብቻ ይወሰን፡፡ የሠራተኛ ደመወዝ ይቀነስ (በገበያ ይወስን)፡፡ ሠራተኞች በማኅበር ለመደራጀት ያላቸው መብት ይገደብ፡፡ የሥራ መቆም መብት ይሰረዝ የሚለውን ጭብጥ ይይዛል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የካፒታሊዝም ሥሪት እያሽቆለቆለ የሄደ እንጂ ያደገና የተመነደገ አንድም የአፍሪካ፣ የእስያና የደቡብ አሜሪካ ደሃ አገር የለም” (የዴሞክራሲያዊ ምኅዳር መስፋትና ምርጫ 2012፣ ሪፖርተር፣ መስከረም 2፣ 2011)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ መንግሥታዊ/ልማታዊ ካፒታሊዝም ሥሪት እንዳልተቀየረ አልፎ አልፎ ይገልጻሉ፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ግን፣ አንዳንድ ዕርምጃዎቻቸው ወደ ኒዮሊበራል መንገዶች እያዘመሙ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት የሆኑትን የአየር መንገድ፣ የቴሌን፣ የመብራት ኃይልንና የሎጂስቲክ መስክ ንብረቶችን በከፊል ለውጭ ባለንብረቶች እንደሚሸጡ አስታውቀው ነበር፡፡ የእንዱስትሪ ፓርኮች በሚባሉት ሕንፃዎች ውስጥ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች እየገቡ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በጥቅምት 2011 ዓ.ም. ደግሞ አንድ ኤግል ሂልስ የተባለ የዱባይ ኩባንያ በአዲስ አበባ ውስጥ የ50 ቢሊዮን ብር ግንባታ እንደሚያካሂድና 27 በመቶው (13 ቢሊዮን አምስት መቶ ሺሕ ብር) በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ተነግሯል (Ezegaኅዳር 2፣2011)፡፡  በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የብዙ ሚሊዮን ዶላር፣ ዩሮና ፓውንድ ብድርና ድጋፍ ተቀባይ ሆናለች፡፡ አንዳንዶቹ ሦስት ቢሊዮን ከተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች፣ 1.2 ቢሊዮን ከዓለም ባንክ፣ 231 ሚሊዮን ዩሮ ከፈረንሣይ፣ ከጀርመን፣ ከኖርዌይና ከአውሮፓ መዋዕለ ንዋይ ባንክ፣176 ሚሊዮን ፓውንድ ከእንግሊዝ ናቸው፡፡ ቻይናም በአሥር ዓመት ውስጥ ይከፈላት የነበረውን የ30 ሚሊዮን ብድር በሰላሳ ዓመታት እንዲከፈል ተስማምታለች፡፡

አበዳሪዎቹና “ለጋሾቹ” የተዘረዘረውን ያህል ገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልቀቃቸው ጥያቄዎችን ቢጭር አያስደንቅም፡፡ ይሁንና፣ ኢሕአዴግ በአቶ መለስና በአቶ ኃይለ ማርያም ዘመኖችም ቢሆን የውጭ እጅ ያጠረበት ገዥ አልነበረም፡፡ ብዙዎች በትክክል እንደሚሉት በእርግጥም፣ አበዳሪዎቹና “ለጋሾቹ” ኢትዮጵያን በሚመለከት የራሳቸው ጉዳይና ግብ ያላቸው ቢሆን ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በመጡበት ወቅት የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ከፍተኛ ነበር፡፡ ከፍተኛ የውጭ ገንዘብ መገኘቱ ለጊዜውም ቢሆን አስተነፍሷል፡፡ ይሁንና ከእነ ወለዱ ሲከፈል የአገሪቱን የዕዳ መሸከም አቅም በከባድ እንደሚጫነውና ዕቅዶቿን እንደሚፈታተን ግልጽ ነው፡፡

የሚያስገርመው ማለቱ ሲያንስ ነው ማለቱ ሲያንስ ነው፡፡ አንዳንድ ከውጮቹ ጋራ የተቆራኙ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ከናካቴው “መንግሥት የውጭ ብድር መፍራት የለበትም” እያሉ በይፋ እስከ ማወጅ የደፈሩበትም ዘመን ሆኗል (ሪፖርተር ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ዓ.ም.)፡፡ አብዝቶ የሚያስገርመው፣ የኛዎቹ እስከዚህ ሲዳፍሩ የዓለም አቀፍ አበዳሪዎቹ የዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም እንኳን የአንድ አገር ብድር ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ 50 ከመቶ ከደረሰ ቀይ መብራት ያበራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንኩ የዓለም ዕድገት አመልካች ሪፖርት መሠረት፣ በ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የብድር ሸክም ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ 57 ከመቶ ደርሶ ነበር (IMF Ethiopia Debt Sustainability Analysis December 12 2017)፡፡ ስለዚህም፣ ቀደም ሲል “መካከለኝ” በሚል ይገመገም የነበረው የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና (Debt Distress)፣ በ2009 እና በ2010“በከፍተኛ አሳሳቢ” (high risk)በሚል ተገምግሞ ነበር (IMFEthiopia: Recent DevelopmentsJanuary 24 2018)፡፡ ለዚህም ዋናዎቹ ምክንያቶች በአንድ ወገን የውጭ ንግድ ማሽቆልቆልና በሌላውም ወገን የተቋቋሙት የማምረቻ ድርጅቶችና የግብርና ምርታማነት በእጅጉ ከግብ በታች የወረደ መሆኑ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከግል የፋይናንስ ገበያዎች የምትበደር አገር ብትሆን ኑሮ ደግሞ ከብድር የታገደች አገር ትሆን ነበር፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ የተረጋጋውንና ሰላም የሰፈነውን ያህል በንፅፅር የተሻለ ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ተቃራኒው ከባድ አሉታዊ ተፅዕኖውን ማሳረፉ አይቀርም፡፡ የአሁኑ ብድርና “ልገሳ” ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካለባት ዕዳ ጋር ሲደመር በእጅጉ ያሳስባል፡፡ አቶ ጌታቸው ዓለሙ ለአዲስ ስታንዳርድ ባቀረቡት ጽሑፍ ኢትዮጵያ የ49 ቢልዮን ዶላር (27 ከውጭ፣ 22 ከአገር ውስጥ) ባለዕዳ መሆኗን አመልክተው ነበር (አዲስ ስታንዳርድ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡፡

በርካታ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ዶ/ር ዓብይ የኢትዮጵያን ስትራቴጂያዊ መንግሥታዊ ድርጅቶችና ተቋሞች ወደ ግል ይዞታ እንዳያዘዛውሩ በመጠየቅ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል፡፡ የአየር መንገዱን ወደ ግል ይዞታ የማዞር ዕቅድ በሚመለከተው በኩልም ድርጅቱን ለሰባት ዓመታት የመሩትና የድርጅቱ የ2025 ራዕይ አባት በሚል የሚታወቁት አቶ ግርማ ዋቄ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ “የአጭር ጊዜ ፍላጎት የረዥም ጊዜ ተስፋችንን እንደማያጨልም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ዕርምጃ ከወሰዱ እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች ተሞክሮ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የኬንያ አየር መንገድ በከፊል ወደ ግል እንዲዛወር መደረጉ ብዙም አልጠቀመውም፡፡ እንደሚታወቀው የኬንያ አየር መንገድ አሁንም ኪሳራ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፋማ ነው፡፡ ከአየር መንገዱ ትርፍ የተወሰነውን መንግሥት ለሌሎች ፕሮጀክቶች መደገፊያ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የግል ንብረት አድርጉ ብለው አያውቁም በንግድ መርሆች እስከተዳደረ ድረስ፤” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል (ሪፖርተር፣ ኅዳር 9፣ 2011 ዓ.ም.)፡፡

ዶ/ር ዓብይ ለግልጽ ደብዳቤዎቹ የሰጡትን ይፋ መልስ አልሰማሁም፡፡ ይሁንና የባዕድ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ድርጅቶችን የፈቃድ አወጣጥና አሰጣጥ ለማቃለል እየተሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዓለም ባንኩ ማቲው ቬርጊስም በዶ/ር ዓብይ አስተዳደር “የሦስት ዓመታት የሪፎርም ፍኖተ ካርታ መሠረት፣ አስተዳደራቸው ቀስ በቀስ ከልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሥሪት እየወጣ መምጣቱን የሚያመላክት ነው፤” በማለት ገልጸዋል (ሪፖርተር፣ ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት መንገዷን እየቀየረች ስለመሆኗ የዓለም ባንክ ገለጸ ኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡፡   በሌላ በኩል አንዳንድ የኢኮኖሚ “ሊቅ” (ኤክስፐርት) የሚባሉ ኢትዮጵያውያን የቴሌቪዥን መስኮቶችን እያጨናነቁ እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ አንዳንዴም ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት የኢትዮጵያ ባንኮች፣ የገንዘብ ተቋሞች፣ የመሬት ይዞታና ሌሎች የሕዝብ ሀብቶች ሁሉ ወደ ግል እንዲዛወሩ ያስፈልጋል እያሉ ሲገፉ ይደመጣሉ፡፡ ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት የቴሌቪዥን መስኮቶችን ያጨናነቁበት መጠን ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ በመሆኑ ነው እንጂ ጣቢያዎቹ አንዳንድ ጊዜ ማበራችሁንና መስኮታችሁን ሁሉ ለባዕድ ካፒታል ደለላ “ሊቃናት” ከፍታችሁ አስተናግዱ የተባሉ ነው የሚመስለው፡፡

ተጋባዦቹ ደለላ “ሊቃናትም” በቀጥታ ስለሚፈሰው የመዋዕለ ንዋይ መጠን፣ ስለሚያስተዋውቁት ቴክኖሎጂና የአመራር ክህሎት ሲያወረዱት በእጅግ ያስጎመጃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና፣ መዝናኛና የንግድ መረጃ መረብ “ኢትዮጵያ በ2010 156 ትልልቅ ኩባንያዎችን ሳበች፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የፈሰሰው የባዕድ መዋዕለ ንዋይ 4.1 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ” ብሎ የዘገበውም በእጅጉ ያስቋምጣል፡፡ (Ezega August22፣ 2018)፡፡ ተጋባዦቹ “ሊቃናት” ከተናገሩት ይልቅ ያልተናገሩት እንደሚበልጥ የሚያስተውል አድማጭ የቋመጠውን ያህል ተመልሶ ቢደመም አያስገርምም፡፡ የድለላ “ሊቃውንቱን” ልበ ሙሉነት በአንክሮ ያጤነ፣ ኢስተርሊ “የሊቆች አምባገነንት” ያለውን ቢያስታውስ አይፈረድበትም (William Easterly፣ Tyranny of Experts፣ 2013)፡፡

በግልጽ የማይነገረው የተገቡት ውሎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደምን እንዳስጠበቁ ነው፡፡ ወይም ከራሱ ከኢትዮጵያና ከሌሎች አገሮች አሉታዊ ተሞክሮዎች መወሰድ ስለሚገባው ትምህርትና ጥንቃቄ ነው፡፡ ስለሠራተኞች ጤንነትና መብት ነው፡፡ ስለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ነው፡፡ በግዥና በሽያጭ ደረሰኞች ስለሚጭበረበረው ወጭና ገቢ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚሆነው አገራዊ ግብዓት እጅግ በጣም ትንሽ ወይም ምንም እንደሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ግብዓቱ ሁሉ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክፍያ ከውጭ እንደሚመጣ ነው፡፡ ወይም ኢትዮጵያ ከፈረሱ ጋሪው በቀደመበት ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ አገር መሆኗን ነው፡፡ የማይነገረው ሌላም ከትርፋቸው ውስጥ ስንት ከመቶውን መልሰው በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚያውሉ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባንኮች እየተበደሩ “ስለጠፉት” “የባዕድ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ” ሌቦች ነው፡፡ ያስተዋውቃሉ ስለሚባለው የቴክኖሎጂ ዓይነትና ደረጃ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባለሀብቶች ጋራ ስላላቸው ወይም ስለሌላቸው የካፒታል ሽርክናና የአመራር ትብብር ነው፡፡ በነሱና በየኤምባሲዎቻቸው ጭምር እየታገዘ በተለያዩ ሕገወጥ መንገዶች ወደ ውጭ ስለሚወጣው  ካፒታል ነው፡፡ . . .በዋሽንግተን የሚገኘው ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንትገሪቲ ድርጅት እንደዘገበው ለምሳሌ በ2000 እና በ2009 (ከ1993 እስከ 2002) መካከል $11.7 ቢለዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል (Global Financial Integrity December 5 2011)፡፡ አዲስ ስታንዳርድ ቀጥሎ እንደዘገበውም፣ በ2004 እና በ2013 (ከ1997 እሰከ 2006) መካከል 26 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ወጥቷል (Addis Standard May 9 2016)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በሕገወጥ መንገዶች የወጡትን ቢሊዮኖች ለማስመለስ እየሠሩ እንደሆኑ ደጋግመው ገልጸዋል፡፡ መልካም ይሆናል፡፡ ለኢትዮጵያ ከዚህ ባላነሰ የሚያስፈልጉት ደግሞ ግን የባዕድና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንና የደላሎቻቸውን የካፒታል እንቅስቀቃሴ የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ጠንካራ የመንግሥት ተቋሞችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የውሎችና የመረጃዎች ግልጽነትና የአደባባይ ንብረት መሆን ነው፡፡ ከትርፋቸው ውስጥ የተወሰነ መቶውን መልሰው በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያውሉ የሚያስገድድ ሕግ ነው፡፡ ግብዓቶችን በኢትዮጵያ ለማምረትና ለማቅረብ የሚደረግ ከፍተኛ ጥረት ነው፡፡ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል የሚገኙትን ሥራ አስፈጻሚዎች የሚጠይቁ፣ የሚቆጣጠሩና ምክር ቤቶች መኖር ነው፡፡

በእኔ ዕይታ የኢትዮጵያን ሕዝብ ንብረቶች በተልካሻ ምክንያቶች ለውጭ ባለሀብቶች ከመሸጥ ይልቅ፣ ያስከፈለውን ከፍሎ የአስተዳደር አመራሮቹን ማሻሻል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ሺሕ ጊዜ አስበልጦ ይጠብቃል፡፡ ያስከፈለውን ከፍሎ የኢትዮጵያን ልጆች ቴክኒካል ዕውቀት ማሳደግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ሺሕ ጊዜ አስበልጦ ይጠብቃል፡፡ ቴክኖሎጂው ዞሮ ዞሮ በአንጡራ ገንዘብ የሚገዛ ነው፡፡ አለፍ ሲልም የሚኮረጅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ ልጆች ከደረሰበት ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌ፣ የመብራት ኃይልና ወዘተ፣ በኢትዮጵያ ልጆች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋራ የማይስተካከሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ከሁሉም ከሁሉም በላይ ግን የመገናኛውን፣ የአየር መንገዱን፣ የፋይንስና የኃይል ምንጩን ለባዕዳን ያሰረከበ አገር ብሔራዊ ነፃነቱን ካስረከበ አገር በምንም እንደማይለይ መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ አኳይ የፈረንሣይ የቀድሞ ቅኝ ግዛት የነበሩትን የምዕራብ አፍሪካ አገሮች አሳዛኝ ሁኔታ ማጤኑ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንደሚለግስ ቢታወስ መልካም ነው፡፡

የኢሕአዴግ ልማታዊ ካፒታሊዝም

የኢሕአዴግ ልማታዊ ካፒታሊዝም ሥሪት አመንጪ ሕወሓት በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ አቶ መለስ የዕድገት ሥሪት ምርጫቸውን ያደረጉት ስለልማታዊ ካፒታሊዝም አጥንተውና ከባለሙያዎች ጋር ተወያይተውበት እንደነበር በሰፊው ተነግሯል፡፡ ለድኅረ ምረቃቸው የጀመሩት ጥናታዊ ጽሑፍም የአደባባይ ንብረት ነው፡፡ አሌክስ ደ ዋል የተባለው ተመራማሪ በቅርቡ ያቀረበው ጽሑፍ የግንዛቤያቸውን ከፍታ በአጭሩ ይገልጻል (Alex de Waal The Future of Ethiopia August 2018)፡፡ ሆኖም የሚያሳዝነው ቢባል ይሻላል፡፡ አቶ መለስ የነኩትን ነገር መልሶ የመግዣና የሥልጣን መጠበቂያ መሣሪያ ያደርጉታል፡፡ ስለሆነም አጠኑት የሚባለውን ልማታዊ ካፒታሊዝም እንኳን በአግባቡና በጥሩ በሥራ ሳያውሉት ቀሩ፡፡ ይባስ ብለው የኢትዮጵያን ልማታዊ (መንግሥታዊ) ካፒታሊዝም ለገዥ ፓርቲያቸው ካፒታሊዝም አሳልፈው ሰጡት፡፡ ኤፈርት፣ ጥረት፣ ቱምሳ/ዲንሾና ወንዶ የተባሉት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ኩባንያዎችና የኢሕአዴግ አገዛዝ የፈለፈላቸው በሥልጣን ባላጊዎች፣ ጥገኞች፣ ደላሎች፣ ኮንትሮባንዲስቶች፣ የሕንፃዎችና የመሠረተ ልማት ኮንትራክተሮችና ወዘተ. ፈነጩበት፡፡

የአቶ መለስ ስል አዕምሮ ይህንን እውነታ የሳተ አልነበረም፡፡ እንደሚታወሰው አንድ ጊዜ “ወይ ልማታዊ ካፒታሊዝም ያሸንፋል፡፡ ወይ ኪራይ ሰብሳቢነት ያሸንፋል” ብለው ነበር፡፡ ከመሬት አይነሳ እንጂ ፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ዘመቻም ከፍተው ነበር፡፡ ገለጻቸውን አንዳንዶች በወቅቱ ‘የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ካፒታሊዝም የሚባለውም ሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት የራሱ የኢሕአዴግ ናቸው፡፡ ይዋል ይደር እንጂ ሁለቱም ተሸናፊዎች ይሆናሉ’ በማለት አጢነውት ነበር፡፡ ትንተናቸው ‘አንዱ ካሌላኛው ውጭ ህልውና የለውም’ ከሚል እሳቤ የሚነሳ ነበር፡፡ ፍሬ ይዘቱም፣ ‘ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲቀፈቀፍ ሁኔታዎችን ከድሮውም ያመቻቸው ከድሮውም የአንድ የገዥ ፓርቲ ካፒታሊዝም መስፈን ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ከተሸነፈ የገዥው ፓርቲ ካፒታሊዝም የግዱን ይሸነፋል፡፡ አቶ መለስ ገዥ ፓርቲያቸው በፈለፈላቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ይጨክናሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም’ የሚል ነበር፡፡

በርካታ የኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የፀረ ሙስናና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች ሪፖርቶች ለምክር ቤቱ የቀረቡ ቢሆንም ቅሉ የአቶ መለስና የአቶ ኃይለ ማርያም ፀረ ኪራይ ሰብሳቢ ዘመቻ ከመግለጫዎች ያላለፈ እንደነበር ማስታወሱ የሚታወቀውን መድገም ይሆናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጠንካራ የፀረ ሙስና እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል፡፡ ለጥልቀቱና ስፋቱ “ትልቅ የእስር ቤት ከተማ ካልገነባን በስተቀር የአገሪቱ እስር ቤቶች አይበቁንም” እስኪሉም አድርሷቸዋል፡፡ ዕርምጃዎቹ “በሕግ እስካልተፈረደበት ድረስ ማንም ሰው ነፃ ነው” በሚለው መርህ መሠረት እስከተጠናቀቁ ድረስ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የዜና አሠራጪዎች የሕግን ለሕግ መተው እንዳለባቸውም ጠንክሮ መነገር አለበት፡፡ ሥራቸው ዜናዎችን በሂሳዊ መነጽር እየበጠሩ ማቅረብ እንጂ ለገዥዎች ዕርምጃዎች ከገዥዎቹ በላይ መጮህ አይደለም፡፡ ሙያዊ ኃላፊነታቸውና ተግባራቸው የፍርድ ቤት ውሎዎችን ለማንም ሳይወግኑ ማሰማት ነው፡፡ በምርምርና በተጨባጭ መረጃ የተደገፉ ዘገባዎችን ማቅረብ ነው፡፡ ተጋባዦቻቸውም ለፍርድ ቤት መስጠት የሚገባቸውን ቃል ለዜና ፍጆታ ማዋል የለባቸውም፡፡ ነገር ግን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የመጨረሻ መጨረሻ የሚሠፈሩት እስከዚህም በቀድሞዎቹ በሥልጣን ባላጊዎች ላይ በሚወስዱት ዕርምጃዎች እንዳልሆነም ግልጽ ነው፡፡ ከራሳቸው ባለሥልጣኖች መካከል በሥልጣን በሚባልጉ ላይ ከሥር በሥር በሚወስዱት ወይም በማይወስዱት ዕርምጃ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የሚበጀው እውነተኛ የኢትዮጵያ ልማታዊ ካፒታሊዝም ነው  

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እንዳሉት የኢሕአዴግ ካፒታሊዝም ዘመን ባለሥልጣኖች የብልግና መጠን “አንድ ከተማን የሚያክል እስር ቤት” የሚጠይቅ መሆኑ፣ በአንድ በኩል በኢሕአዴግ የ27 ዓመታት የገዥነት ዘመን ለተገነቡት በርካታ መሠረቶች ዕውቅናን ከመስጠት ማቀብ የለበትም፡፡ በሌላውም በኩል “የልማታዊ ካፒታሊዝምና የልማታዊ መንግሥት ነገር ከንግዲህ በኢትዮጵያ ያክትም፡፡ ሁራ ኒዮሊበራሊዝም ለዘላለም ይኑር” ከሚያሰኝ መደምደሚያ ላይ አያስደርስም፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነት አረንቋ ተላቃና በቀጣናዋና በዓለም መድረኮች ላይ ኮርታ ለመታየት የምትበቃው አሁንም በልማታዊ ካፒታሊዝም ሥሪት ነው፡፡ በልማታዊ መንግሥት ነው፡፡

ወደፊት መራመድ የሚቻለው ከ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ “ልማታዊ መንግሥት” አያያዝ ተገቢው ትምህርት ሲቀሰምና በተገኙት አዎንታዊ መሠረቶች ላይ ቆሞ ሲቀጠል ነው፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት ደግሞ የኢትዮጵያን ልማታዊ ካፒታሊዝም ከኢሕአዴግ የምርትና የንግድ ድርጅቶች መንጋጋ ውስጥ ፈልቅቆ በማውጣት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሆነ እውነተኛ (Genuine) ልማታዊ ካፒታሊዝም ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ የመገንባት ጎዳና በመያዝ ነው፡፡ ከወቅቱ የዓለም አቀፍና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳትና በታቀደ መርሐ ግብር መሠረት ደረጃ በደረጃ በሥራ ላይ በማዋል ነው፡፡ ይሁንና እንግዲህ የኢትዮጵያ የሆነን መንግሥታዊ ካፒታሊዝም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ላይ የመገንባት ስትራቴጂ ምን ምን ጉዳዮችን ሊያጤን ይገባዋል?

በሚከተለው ዋና ዋና የሚመስሉኝን እንዳንድ ጉዳዮች የኤዢያ ነብሮች የነበሩበትን ሁኔታና ዓብይ አካሄዳቸውን እያስታወስኩ ከኢትዮጵያ አካሄድ ጋራ በአጭር በአጭሩ ለማስተያየት እሞክራለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን ኢትዮጵያ አቶ መለስን የቀደሙ የኢትዮጵያ ልማታዊ ካፒታሊዝም አራማጆች እንደነበሯትም እንዲታወስ ያስፈልጋል፡፡ አድማጭ አጥተው ማለፋቸው በእጅጉ ያስቆጫል፡፡ አንዳንዶቹ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ብላታ ድሬሳ አማንቴና አቶ ከበደ ሚካኤል ነበሩ (ባህሩ ዘወዴ፣ Pioneers of Change in Ethiopia፣2002)፡፡

የኤሺያ ነብሮች (ሆንግ ኮንግ፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን) የመንግሥት ካፒታሊዝምን (ልማታዊ መንግሥትን) የገነቡት፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባት በአንድ በኩል ከፍተኛ የማምረትና የምርት ልውውጥ በሚፈለግበትና በሚደረግበት ዘመን ነበር፡፡ ስለነበርም ጥራት ከፍተኛው መመዘኛ ነበር፡፡ በዓለም ገበያ ላይ ዛሬ ለመወዳደር የሚቻለው በጥራት ነው፡፡ እነሱ መንግሥታዊ ካፒታሊዝምን ወደ መገንባት ያቀኑበት ዘመን በሌላው በኩል የዓለም ካፒታሊስትና ሶሺያሊሰት ፊናዎች ፉክክርና ትንቅንቅ በፎመበት የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ነበር፡፡ ሉዓላዊነታቸው ሳይቀር (እስከ ዛሬም ድረስ ቢሆን) በአንድ ኃያል መንግሥት የሚጠበቅላቸው አገሮች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በራሷ አቅምና ልጆች መጠበቅና ማስከበር ያለባት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የመንግሥት ካፒታሊዝሟን ወደ መገንባት ያቀናችው የኒዮሊበራሎች ሉላዊነት በሚፈነጭበት የፋይናንስ ካፒታል የበላይነትን በያዘበትና አገሮች ብሔራዊ ገበያቸውን ለኒዮሊበራሎች በርግደው እንደዲከፍቱ ባዕድ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ከባድ ተፅዕኖ በሚጭኑበት ዘመን ነው፡፡ የቀረጥ ገነት በሚባሉ ደሴቶች አስተናጋጅነት፣ ከደሃ አገሮችና ከአደንዛዥ ዕፅዋት ሽያጭ የሚያፍሱትን ቢልዮን ዶላሮችን በኦንላይን እያጠቆሩ (እያነጡ) አገሮችንና መንግሥታትን በሚያውኩበትና በሚያፈራርሱበት ዘመን ነው፡፡ የጠቆሩ ዶላሮችን “የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ” በሚል ስያሜ ወደ ደሃ አገሮች እየገቡ በሚያጥቡበት ዘመን ነው፡፡ ግብይት ኦንላይን በሚባለው መረብ ውስጥ እየገባ፣ ባንድ በኩል ቅፅበታዊ እየሆነና በሌላውም ወገን ያላደጉ አገሮችን አምራችና ነጋዴ ከውድድር እያወጣ በሄደበት ዘመን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ ልትቋቋም የምትችለው፣ ሕዝቦቿ ከክልለ አጥሮች ከፍ ሲሉና በብሔራዊ/አገራዊና በቀጣናዊ ደረጃ ሲያስቡ ነው፡፡

የኤዢያ ነብሮቹ የበርካታ አኅጉራዊ ወደቦችና የሌሎች በርካታ ወደቦች ባለቤቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌም ጃፓን አምስት፣ ደቡብ ኮሪያም ሦስት ትላልቅ ወደቦች አሏቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ወይም የወደቦች ተኮናታሪ አገር ናት፡፡ ተኮናታሪዋ ኢትዮጵያ በተሻለ የወደቦቹ ተጠቃሚ ሆና የምትቆየው ግን የሕዝቦቿን ውስጣዊ ሰላምና አንድነት አጠንክራና በአፍሪካ ቀንድ ማንም የማይደፍራት አገር ሆና ስታቆም ነው፡፡ እነሱ እስከ 95 እና 99 ከመቶ ድረስ የአንድ ብሔር ሕዝብ አገሮች ነበሩ፡፡ ናቸው፡፡ የአንድ ብሔር ሕዝብ አገራቸው ብሔርተኛ ነበሩ፡፡ ስለነበሩም እንደ ኢትዮጵያ የመንግሥት ካፒታሊዝም ግንባታቸውን ከፌዴራል አስተዳደር ሥርዓት ግንባት ጋራ እዚያው በዚያው ለማሰኬድ መድከም ያስፈለጋቸው አገሮች አልነበሩም፡፡

በአንድ ደሃና የብዝኃ ብሔር አገር የፌዴራል አስተዳደርንና የመንግሥት ካፒታሊዝምን መገንባት በራሱ ከባድ ዕቅድና ሸክም መሆኑ ሳያንስ “የኢትዮጵያ ዓብይ ቅራኔ በብሔሮቿ መካከል ያለው ቅራኔ ነው” የሚለው የቅራኔዎች አፈረጃጀት ተደርበበት፡፡ የብሔሮች መብት ከብሔሮቿ ብሔራዊ/አገራዊ ግዴታዎች ጋራ ሳይተዋወቅ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ አገራዊ/ብሔራዊ አዎንታዊ ብሔረተኝነት ውሎ አድሮ ተሸረሸረ፡፡ ሄዶ ሄዶ፣ ክልሎች “የነሱና የእኛ” የሚባሉ አሃዶች ወደ መሆን አዘመሙ፡፡

የካፒታልና የሠራተኛ ነፃ እንቅስቃሴዎች ተገደቡ፡፡ የመንግሥትና የግል የምርትና የአገልግሎት ተቋሞችና ድርጅቶች “የኛና የነዚያ” በሚል አተያይ እየተለዩ ጋዩ ወደሙ፡፡ ኢትዮጵያዊው ዜጋ፣ በተወላጅና በመጤ እየተለየ ተመደበ፡፡ የዜግነት መብቱን ተገፈፈ፡፡ ውሎ አድሮ ከክልል ማባረርና ማስወጣት ተከተለ፡፡ ውሎ አድሮ አንዳንድ ክልሎች በራሳቸው ሉዓላዊ አገር የሆኑ ይመስል ሕዝቦችን በሚልዮን ከሚያፈናቅሉበትና ለስደት ከሚዳርጉበት ሁኔታ ላይ ተደረሰ፡፡ የዚያኑም ያህል የልማታዊ ካፒታሊዝም መሐንዲሶች ሊሆኑ ይገባቸው የነበሩት ያገሪቱ ልሂቃን፣ ተማሪዎችና ባለሀብቶች ተሰነጣጠቁ፡፡ አገራዊ/ብሔራዊ አዎንታዊ ብሔረተኝነት ላሸቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ካፒታሊዝም (ልማታዊ መንግሥት) ግንባታ በቅራኔዎችና በግጭቶች ተተበተበ፡፡ ለአገሪቱ አንድነት እስኪያሠጋ ተደረሰ፡፡

እነሱ በአዎንታዊ ብሔርተኝነት ታንፀውና ተሞልተው ለጋራ ወደፊታቸው በጋራ ወደፊት የሚራመዱ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ እያዩ ወደፊት ለመራመድ በሚግተረተሩ የፖለቲካና የብሔር ድርጅቶች ተትረፈረፈች፡፡ በሰማኒያ ብሔሮቿ ሳይሆን በሰማኒያ ለየራሳቸው እንጂ ለብሔራዊ/አገራዊ ግዴታቸውና ኃላፊነታቸው በማይጨነቁ የብሔር፣ የሊበራል፣ የሶሻል ዴሞክራት፣ የሠራተኛ ፖርቲዎቿ የፖለቲካ ጎጠኝነት ተቸገረች፡፡ ሁለትና ሦስት ፓርቲዎችን ለማስተናገድ የማይሰንፈውን ዴሞክራሲን ራሱን ለሰማኒያ ተረባርበው አፈኑት፡፡ እነሱ በበርካታ ውስጣዊ ግጭቶችና ጦርነቶችና በበርካታ የአፄያዊና የአምባገነኖች አገዛዞች ውስጥ የማቀቁ ቢሆኑም ታሪክን በተገቢው መንገድ ለሚመረምሩት የታሪክ ባለሙያዎች ትተው የጋራ ወደፊታቸውን በጋራ ለመገንባትና ወደ 20ኛው ክፍለዘመን ለመሻገር የሚጣደፉ ነበሩ፡፡ ወደ ኋላ መቅረታቸው ባሳደረባቸው የብሔራዊ ቁጭት ሲቃ የተብሰለሰሉና ለወደፊት የጋራ ታሪክ የሚተርፍን የራሳቸውን ታሪክ ለመሥራት የሚሟሟቱ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃንና ምሁራን ግን በታሪክ ትረካና በታሪክ ጠባሳዎች ቆጠራ ከመናቆርና ከመናጨት መሻገር ተሳናቸው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን “የአባት ዕዳ ለልጅ” በሚለው የኦሪት ሕግ በመተናነቁ በረቱ፡፡

የኤዢያ ነብሮች የመንግሥት ካፒታሊዝምን በሚገነቡበት በ50ዎቹ እና በ60ዎቹ ዘመን ከጃፓን በስተቀር የተቀሩት የኤዥያ ነብር አገሮች የሕዝብ ብዛት ከ15 እና 20 ሚልዮን የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ከመቶ ሚልዮን በላይ ለሆነ ደሃ ሕዝብ ማስላት ያለባት አገር ናት፡፡ የነሱ ዘመን እንደዚሁም እንደ ዛሬው ጊዜ የአየር ንብረት የተዛባበት ዘመን አልነበረም፡፡ ተፈጥሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምታመርባት ኢትዮጵያ ከአሥር ሚልዮን የማያንስ ሕዝቧ በየዓመቱ ለረሃብና ለችጋር የሚጋለጥባት አገር ናት፡፡ ሚልዮን ሕፃናቶቿና ጎልማሶቿ ሆዳቸውን እያከኩ የሚያነጉባት አገር ናት፡፡

እነሱ በተፈጥሮ ሀብት ያልትደሉ ቢሆኑም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከድህነት ተላቀቁ፡፡ መጽዋች ለመሆን በቁ፡፡ በተፈጥሮ ሀብቷና  በሕዘቦቿ ታታሪነት የታደለችው ኢትዮጵያ የምግብ ደኅንነቷን እንኳን ከዓመት ዓመት ለማረጋግጥ አልበቃችም፡፡ እነሱ ለተፈጥሮ ሀብታቸው የሚቋምጥ አገር የለባቸውም፡፡ በዓባይ ባለቤቷና በአፍሪካ ቀንድ የውኃ ቋቷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ግን ያላተኮረ የቅርብና የሩቅ መንግሥት የለም፡፡ ስለዚህም ስቲቨን ሰሎሞን “የሦስተኛው ዓለም ጦርነት በውኃ ምክንያት ይሆናል” ያለው ጉዳይ ኢትዮጵያን በቅርብ ይመለከታታል (Steven Solomon Water: The Epic Struggle for Wealth, Power and Civilization 2010)፡፡ አቶ ዳደ ደስታ በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም “እኛ የውኃን ጉዳይ የምናየው ከጥቅሙ እንጂ ከስትራቴጂክነቱ አንፃር አይደለም” ያሉትም በእጅግ እውነት ነው (የትግራይ ተሌቪዥን፣ ኅዳር 18 ቀን  2011 ዓ.ም.)፡፡ በዕውነታነቱ ጥንካሬ ልክ ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ስትራቴጂያዊ ትብብርን ለማድረግ ሲዳዱ አይታዩም፡፡ አለመተባበራቸው ለግብፅና ለአጋሮቿ የሚልኩት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት መሆኑንም እንኳን ልብ የሚሉት አይመስልም፡፡

እነሱ የአገር በቀል ባለሀብቶቻቸውን የኪሳራ ሥጋት መጋራት በሚል እሳቤ ባለሀብቶቻቸውን በመደጎም ጭምር በተለያዩ መንገዶች የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡ የአገራቸው ልጆች የአገራቸውን ምርቶች እንዲሸምቱ የሚቀሰቅሱ፣ የሚያስተምሩና የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡ በቅንጦት ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ቀረጦችን በመጣል የሚገድቡ ነበሩ፡፡ በዚያው ልክ የቀረጥና የግብር ግዴታቸውን በማይወጡና ገንዘብ በሚያሸሹ ያገሬው ባለሀብቶች ላይ ከፍተኛ ዕርምጃዎችን የሚወስዱ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ካፒታሊዝም ግን የአገሪቱን በሕግ ተዳዳሪ ባለሀብቶች በማላሸቁ ተጋ፡፡ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚላቸውን ፍጡሮቹን በቅንጦት ሸቀጦች ፍጆትና ድሎት አቀናጣ፡፡ ማስታወቂያዎቹ “ከውጭ ያሰመጣናቸው” በሚሉ የወጭ አምልኮ ቅስቀሳዎች ተሞሉ፡፡ እነሱ የእንዱስትሪ ግብዓቶችና የመለዋወጫ ዕቃዎች ከአገሬው በአገሬው እንዲመረቱ የሚተጉ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ጋሪው ከፈረሱ ቀድሞ ሁሉንም ግብዓት ከውጭ የሚያስመጡ እንዱስትሪዎች “ደረጁ”፡፡  እነሱ ለትምህርት ጥራትና ለክህሎት የሚጨነቁና የሚተጉ ነበሩ፡፡ ለመምህር፣ ለሙያና ለክህሎት ከፍተኛ ክብር ነበራቸው፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ የትምህርት ተቋሞች ቢገነቡም ትምህርትንና ክህሎትን ማቃለሉና ማኮሰሱ ሥራዬ ተብሎ የተያዘሆነ፡፡ የነሱ ቢሮክራሲ ለተገልጋዩ ሕዝብ የሕግ፣ የደንቦች፣ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓቶቸና የተገልጋይ መብትና ግዴታዎች አስተማሪና መሪ ሆኖ ጭምር የሚያገለግል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በካድሬ እብሪተኞችና በሥልጣን ባላጊዎች የተጠቀጠቀ ዋሻ ተደረገ፡፡ የዛሬ ኪሳቸውን እንጂ የልጅ ልጆቻቸውን የነገ ዕጣ ፈንታ አርቀው በማያዩ ባለሥልጣኖችና ካድሬዎች ተሞላ፡፡ የሥልጣን ወንበሮች ለጉቦ ማጋበሻ የሚታደሉ መቀመጫዎች ተደረጉ፡፡ በጄኔራል ዓብይ አበበ አገላላጽ “ለበልቶ ሟቾች” የሚታደሉ መቀመጫዎች ሆኑ (አውቀን እንታረም፣ 1955)፡

በነዚህ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ውስጥ እየተከናወነ ያለው የኢትዮጵያ የመንግሥት ካፒታሊዝም ግንባታ ሊሳካ የሚችለው፣ ኢትዮጵያ የተመለከቱትንና ተመሳሳይ ጉዳዮችን ጭምር በብሔራዊ ደረጃ ከሒሳብ ውስጥ አሰገብታ የራሷ የመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ብሔራዊ ስትራቴጂ ባለቤት ስትሆን ነው፡፡ ዜጎቿና ብሔሮቿም ይልቁኑ ከረዥም ዘመን የጋራ ብሔራዊ ስትራቴጂያዊ ጥቅሞቻቸው ጥበቃ አመለካከት ውስጥ ገብተው ለቆንጆ የጋራ ወደፊታቸው የሚበጃቸውንና ለጋራ ታሪክ የሚተርፋቸውን የጋራ ታሪክ ለመሥራት በአንድነት ሲነሳሱ ነው፡፡ የራሳቸው የፌዴራል አስተዳደርና የመንግሥት ካፒታሊዝም ግንባታ ጎዳና ባለቤት ሲሆኑ ነው፡፡ የዛሬውና መጪው ትውልድም በጋራ ስትራቴጂው አምኖና ተማመኖ ወደፊት የሚገልጸውን ብሩህ የጋራ ዓለም በጋራ ለማየትና ለማለም ሲችል ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የፖለቲካ መሪዎቿ፣ ልሂቃንና ምሁራን ሲቪክ ባህል የሚባለውን ተጎናጽፈው ብሔራዊ/አገራዊ የጋራ ወደፊትን በእኩልነትና በዴሞክራሲ ዕውን ለመድረግ ሲደራደሩና ሲስማሙ ነው፡፡ ወይም Elite Bargain የሚባለውን ሲካኑ ነው፡፡ ተደራድረው ለተስማሙበት ሲቆሙና የአስተማሪ መሪ ሲሆኑ ነው፡፡ የጀርመኑ ገጣሚና ድራማቶግ ቤርቶልት ብሬሽት “ወዝ አደሩ የተማረ አስተማሪ ያስፈልገዋል“ ይል ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ የጋራ ወደፊት ግንባታ የተማሩ አስተማሪ ብሔራዊና ሰትራቴጂያዊ የሆኑ የፖለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃንና ምሁራን ያስፈልጋሉ በሚል ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ ቢመለስ የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃንና ምሁራን ከዚህ ከፍታ ላይ ሲቆሙ ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት በኢትዮጵያ ያብባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ልማታዊ ካፒታሊዝም (ልማታዊ መንግሥት) ግንባታ መልካም ፈር ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ የኒዮሊበራሎችን የግብፅንና የአጋሮቿን ጫና በተሻለ ለመቋቋም የሚያስችል ትከሻ ይኖራታል፡፡

የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃንና ምሁራን የጋራ ወደፊትን የሚያፀና ብሔራዊ ውል መሐንዲስ መሆን/አለመሆናቸው የሕዝቦቿን መፃዒ ዕድል ይወስናል፡፡ ከሆኑ የዛሬውን የታሪክ ጥሪ የተቀበሉ መሐንዲሶች ይሆናሉ፡፡ የአዲሲቷና ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ መሥራች አባቶች እየተባሉ ከሚወደሱበት ከነገ ታሪካቸው ጋራ ቀጠሮ የያዙ ይሆናሉ፡፡ ካልሆኑ ለነገው ቄሮዎችና ፋናዎች የግብዣ ደበዳቤያቸውን ዛሬ ልከው ያበቁ የታሪክ ተወቃሾች ሆነው ያበቃሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡