Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር እየተጨቃጨቁ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር እየተጨቃጨቁ ነው

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]                 

 • እንዴት ዋሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ነኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሰብሰብ ብለው መጥተዋል፡፡
 • ፖሊሶች ናቸው?
 • ምነው ደነገጡ?
 • ምን ፈልገው ነው ብዬ ነዋ?
 • ኧረ ይረጋጉ፡፡
 • እኔ እኮ ተደምሬያለሁ ብያቸው ነበር?
 • ቆይ ተረጋጉ እንጂ፡፡
 • ሳልደመር ብታሰር ይሻለኝ ነበር፡፡
 • መደመር እኮ አሪፍ ነገር ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እየታሰርኩኝ የምን መደመር ነው?
 • ማነው የሚያስርዎት?
 • ፖሊሶቹ ናቸዋ፡፡
 • የምን ፖሊሶች?
 • ሰብሰብ ብለው መጥተዋል አላልሽኝም እንዴ?
 • ወቅቱን ረሱት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ወቅት ነው?
 • የበዓል ወቅት ነዋ፡፡
 • ታዲያ ምነው በዓልን እንኳን ባሳልፍ?
 • ኧረ ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ቢሮ የለም በያቸው፡፡
 • እነማንን?
 • ፖሊሶቹን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ፖሊስ እኮ የለም፡፡
 • ታዲያ ማነው ተሰብስቦ የመጣው?
 • ስጦታዎቹ ናቸዋ፡፡
 • ነው እንዴ?
 • ይኼን ያህል ይፈራሉ እንዴ?
 • ኧረ እኔ ምንም አልፈራሁም፡፡
 • እኔማ እርስዎ እንዲህ የሆኑ የተሸሸጉት ምን ይሆናሉ ብዬ አሰብኩ?
 • ኑሮ መሰለሽ የሚኖሩት?
 • እንዴት?
 • በቃ እንደተባለው ብርጭቆ ሲወድቅ አልጋ ሥር ነው መገኛቸው፡፡
 • ታዲያ ከአልጋ ሥር ሊያመልጡ ነው?
 • መስሏቸው፡፡
 • እንቅልፍ ላይወስዳቸው ያን ሁሉ ብር ለሆቴል ከሚከፍሉ አንደኛቸውን እንቅልፍ ያለበት ቦታ ቢገቡ ጥሩ ነው፡፡
 • የት ነው እሱ?
 • ቃሊቲ፡፡
 • መቼ ይቀርላቸዋል ብለሽ ነው?
 • ለማንኛውም ስጦታዎቹን ተቀብያቸዋለሁ፡፡
 • ስለዚህ ልደውል?
 • የት ነው የሚደውሉት ክቡር ሚኒስትር?
 • አይሱዙ ጋ ነዋ፡፡
 • የምን አይሱዙ ነው?
 • ስጦታዎቹን ቤት እንዲያደርስልኝ ነዋ፡፡
 • አይ ስጦታዎቹን ቤት ለመውሰድ አይሱዙ አያስፈልግም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ነካሽ? አምስት በሬ፣ አሥር በግ፣ ሰባት ፍየል፣ 30 ዶሮ በምን ይዤው ልሂድ?
 • የዘንድሮ ስጦታ የተለየ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት?
 • ዘንድሮ በሬው ሳይሆን የመጣው ቆዳው ላይ የተሳለው የእርስዎ ፎቶ ነው፡፡
 • እ…
 • በጉ ሳይሆን ቡልኮው ነው፡፡
 • ምንድነው የምታወሪው ሴትዮ?
 • እንዲሁም በርከት ያሉ ፖስት ካርዶች ናቸው፡፡
 • ፖስት ካርድ እንደ ስጦታ እንዳትቀበይ አላልኩሽም ነበር?
 • ክቡር ሚኒስትሩን የሚያነቃቃ ጽሑፍ ነው የጻፍንበት እያሉኝ ነው፡፡
 • ለማንኛውም ስጦታዎቹን አልቀበላቸውም፡፡
 • ምን ላድርጋቸው ታዲያ?
 • አከፋፍያቸው፡፡
 • ለማን?
 • ለሠራተኞቹ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ስጦታዎችን የሚሰጡ ግለሰቦችን የሚያስተባብረው ግለሰብ ጋ ደወሉ]

 • ምን እየተካሄደ ነው?
 • ሪፎርም ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እ…
 • ሪፎርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ በቀላሉ ያገኘኸው ሹመት እንዳልሆነ ታውቀዋለህ?
 • የምን ሹመት ክቡር ሚኒስትር?
 • የእኔ የስጦታ ግዢና ሰጪ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ስትሆን ዝም ብለህ እንዳላገኘኸው ታውቃለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ የተከበርኩ ነጋዴ ነኝ፡፡
 • ለዚያ አይደል እንዴ ይኼን ሹመት የሰጠሁህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ባለኝ ችሎታ አገሬን የማገለግል ነጋዴ መሆኔን ነው የማውቀው፡፡
 • ለማንኛውም የተሾምክበትን ምክንያት የዘነጋኸው መሰለኝ፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ለበዓል የምፈልገው ስጦታ ድምፅ የሚያወጣና ሳር የሚበላ እንስሳ፣ አሊያም ዘመኑ ያመጣው የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ፣ ከዚያም ከዘለለ ዘመናዊ ተሽከርካሪ መሆኑን ረሳኸው?
 • አሁን እኮ ነገሮች ስለተቀያየሩ ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • የስጦታዎች ሁሉ ስጦታ ምን እንደሆኑ አያውቁም?
 • ምንድናቸው?
 • ጋቢ፣ ጦርና ጋሻ፣ ካባ፣ ፈረስና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • እኛ እርስዎ ከሌሎቹ ባለሥልጣናት ሊያንሱ አይገባም በማለት አምስት ጋቢ፣ ጦርና ጋሻ፣ እንዲሁም ካባ ነው ያመጣንልዎት፡፡
 • እየቀለድክ ነው ሰውዬ?
 • ክቡር ሚኒስትር አዲሱ ፖለቲካችን እኮ ስጦታዎቻችን ላይ እንድንወስድ አስገድዶን ነው፡፡
 • ምን?
 • ሪፎርም!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር ጉድ ሆንኩኝ፡፡
 • ምን ሆንክ?
 • ሕይወቴ አከተመለት በቃ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው የምትለው?
 • እጅ ከፍንጅ ተያዝኩ፡፡
 • ምን ስታደርግ?
 • ሳሸሽ ነዋ፡፡
 • ምኑን?
 • ዶላሩን፡፡
 • እ…
 • አለቀልኝ በቃ ክቡር ሚኒስትር?
 • የት ነው ያለኸው?
 • ድንበር ላይ፡፡
 • እ…
 • በድንበር ነበር ላሸሸው የነበረው፡፡
 • ቦሌ ምን አለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር በየቀኑ በቦሌ የሚያዘውን የዶላር መዓት ስመለከት በድንበር ይሻላል ብዬ ነዋ፡፡
 • ለነገሩ የኤርፖርት ጠባቂዎች በሙሉ ተቀይረው ሰው በምን ያሳልፍ?
 • እሱን ፈርቼ ነበር እኮ የድንበሩን መላ ያመጣሁት?
 • ታዲያ ምን ተሻለ?
 • ክቡር ሚኒስትር መላ ይፈልጉልኝ፡፡
 • ምን ዓይነት መላ?
 • እንደ አኳኋናቸው የሚለቁኝ አይመስልም፡፡
 • ይለቁኛል ብለህ አስበህ ነበር?
 • እኔማ የተወሰነ አቅሜያቸው አመልጣለሁ ብዬ ነበር፡፡
 • አሁን እኮ እንደ ድሮው አይደለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም እያስፈራሩኝ ነው፡፡
 • ምን እያሉ?
 • የተያዘብኝ ዶላር በርካታ ስለሆነ ሕገወጥ የውጭ ባንክ ነህ እያሉኝ ነው፡፡
 • በቃ በሰበስክ ማለት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በአፋጣኝ ያስፈቱኝ፡፡
 • እሱን ማድረግ አልችልም፡፡
 • ይኼ አካሄድ አያዋጣዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • እኔ ቅርንጫፍ ባንኩ ነኝ ብዬ ዋናውን ማጋለጤ አይቀርም፡፡
 • ማነው ዋናው ባንክ?
 • እርስዎ፡፡
 • እ…
 • በቃ ደዋውለው ያስፈቱኝ፡፡
 • እሱ እኮ ድሮ ቀረ፡፡
 • የፈለጉትን ጉዳይ በአንድ ስልክ አልነበር እንዴ የሚጨርሱት?
 • አልሰማህም እንዴ?
 • ምኑን?
 • One call ተቀየረ እኮ?
 • ወደ ምን?
 • ወደ Missed call!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር እየተጨቃጨቁ ነው]

 • ለምንድነው የእኛ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ዜና ያልተሠራው?
 • ክቡር ሚኒስትር የምንሠራውና የማንሠራውን ዜና እርስዎ ሊነግሩን አይችሉም እኮ?
 • ከዚህ በላይ ምን ዜና አለ?
 • ማለት?
 • ያን ሁሉ ሰው ጠርተን፣ ያን ሁሉ ድግስ ደግሰን እንዴት ዜናው አልተሠራም?
 • ድግስ ሁሉ እኮ ዜና አይሆንም፡፡
 • እ…
 • በዚያ ላይ በትንሹም ቢሆን የራሳችን ነፃነት አለን እኮ?
 • ዲስኩርህን ትተህ ለምን እንዳልተዘገበ ንገረኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር ያው ለሕዝቡ ዜና ይሆናል የምንለውን መዝነን እኮ ነው ዜና የምንሠራው፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅዎታል?
 • ደግሞ እናንተ ዜና ትመርጣላችሁ እንዴ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • በየቀኑ በገቡ ዜና ትቀልዱብናላችሁ አይደል እንዴ?
 • ምንድነው የገቡ ዜና?
 • ስማ አንድ የግጥም መድብል አሳትሞ የማያውቅ ሰው ሳይቀር ከውጭ ገባ ብላችሁ አይደል እንዴ ዜና የምትሠሩት?
 • እ…
 • አንድ ነጠላ ዜማ ያለው ሰው አገሩ ገባ ብላችሁ እኮ በቀጥታ ታስተላልፋላችሁ?
 • እሱን አላውቅም፡፡
 • ታዲያ በምን መሥፈርት ነው የእኛን ዜና ሳታስተላልፉ የቀራችሁት?
 • እኔ እንጃ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹንስ ቢሆን በየጊዜው አይደል እንዴ ገቡ እያላችሁ የምታስተላልፉት?
 • እሱ እኮ ያው መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ ፓርቲዎቹ እየተመለሱ ስለሆነ ነው፡፡
 • ቢሆንስ የአንድ ፓርቲ አመራሮች ስንቴ ነው ገቡ ተብሎ የሚዘገብላቸው?
 • አንዴ ነዋ፡፡
 • እናንተ ግን እንደ ተከታታይ ድራማ በየጊዜው ገቡ እያላችሁ ነው የምትዘግቡት፡፡
 • ምን እናድርግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት?
 • እናንተ ራሳችሁ ምርጥ የፖለቲካ ድራማ ነው የምትሠሩት፡፡
 • እ…
 • የፓርቲ አመራሮቹን እንደ ተከታታይ ድራማ በፓርት በፓርት ስታስገቧቸው እኛም ክፍል አንድ፣ ክፍል ሁለት እያልን እንዘግባቸዋለን፡፡
 • ለማንኛውም እናንተ ትኩረት የምትሰጡት ዜና ገብቶኛል፡፡
 • ምንድነው?
 • ገቡ የሚለው ዜና ነዋ፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ አንድ ዜና ልንገርህ፡፡
 • ምን ዓይነት ዜና?
 • እኔም ከረጅም ጊዜ በኋላ ጂም ጀምሬያለሁ፡፡
 • ጥሩ ነው፡፡
 • ታዲያ ሚኒስትሩ ገቡ ብለህ ዜናው ለምን አትሠራውም?
 • የት?
 • ጂም ነዋ፡፡
 • ይኼ ዜና አይደለም፡፡
 • የገቡ ዜና ነው የምትሠሩት ብዬ ነው እኮ?
 • በቅርቡ ሲገቡ ዜናውን እንሠራዋለን፡፡
 • የት ስገባ?
 • እስር ቤት!