Skip to main content
x
የአገር ተስፋ በእኩያን አይጨናገፍ!

የአገር ተስፋ በእኩያን አይጨናገፍ!

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአራቱም ማዕዘናት ከዳር እስከ ዳር ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ለማገዝ በአንድነት መነሳቱን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ይህንን ጉዞ ለማጨናገፍ የሚርመሰመሱ እኩያን ደግሞ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እያደቡ ጥቃት ፈጽመውበታል፡፡ በወቅቱ አሠላለፍ መሠረት ለለውጥ የተነሳው ሕዝብና የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለመጫን ያሰፈሰፉ ኃይሎች ተፋጠዋል፡፡ ሕዝብ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደውን መንገድ ለመያዝ ሲንቀሳቀስ፣ ይህንን ጉዞ ለማደናቀፍ እንቅስቃሴ የጀመሩ በየቦታው ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለመግለጽ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚቀረፉትና ሕዝብ ነፃነቱን የሚያጣጥምበት ሥርዓት መገንባት የሚቻለው፣ የሰላማዊ ፖለቲካ የጨዋታ ሕግ ሲከበርና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል ጥብቅ ዲሲፕሊን ሲኖር ነው፡፡ በአንድ በኩል ሥልጣናችንና ጥቅማችን ለምን ተነካብን የሚሉ ወገኖች፣ በሌላ በኩል መያዣና መጨበጫ የሌለው አቋም ይዘው ትርምስ የሚፈጥሩ ኃይሎች እርስ በርስ እየተመጋገቡ የአገር ተስፋን ለማጨለም እየጣሩ ነው፡፡ እነዚህ ከታሪክ የማይማሩ ለሕዝብና ለአገር ደንታ የሌላቸው ኃይሎች በተባበረ ጥረት በሕግ አደብ እንዲገዙ መደረግ አለበት፡፡ የአገር ተስፋ መጨለም ስለሌለበት፡፡

በዚህ ዘመን አገራቸውን የሚያፈቅሩ ኢትዮጵያውያን ከሚፈለጉባቸው ግዴታዎች መካከል ዋነኛው፣ የሕዝብን የዘመናት አንድነትና አብሮ የመኖር የጋራ እሴቶች የሚንዱ ድርጊቶችን በፅናት መታገል ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ ተደብቀው እርስ በርሱ ለማባላት ያሰፈሰፉ ኃይሎች፣ ያገኙትን አጋጣሚ በሙሉ በመጠቀም የጥላቻ መርዝ እየረጩ ነው፡፡ በተለይ ወጣቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ስሜታቸውን በመኮርኮር የብሔር፣ የሃይማኖት፣ ወዘተ. ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ሴራዎችን ይሸርባሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎችን እርስ በርስ በማጋጨት የጦርነት አውድማ እንዲፈጠር ይቀሰቅሳሉ፡፡ የግለሰቦችን ዕለታዊ ጠብ ወደ ብሔር ወይም ሃይማኖት ግጭት በመለወጥ ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎችን በመፈብረክ በሕዝብ ውስጥ አለመተማመን ለመፍጠር ይራወጣሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለመታዘብ እንደተቻለው በደካማ ጎን በመግባት ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሚሆኑ ዘመቻዎችን ይከፍታሉ፡፡ የእነሱን ሴራ የማይገነዘቡ የዋሆች ደግሞ ያለ ምንም ማመዛዘን የማይፈለግ ድርጊት እየፈጸሙ ጥፋት ያደርሳሉ፡፡ በእነዚህ እኩያን ምክንያት የአገር ሰላም እየተቃወሰ ሕዝብ ግራ እየተጋባ ነው፡፡ ይህንን በመገንዘብ አገር ወዳድ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረው በመሥራት ሴራቸውን ማክሸፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአገር ተስፋ በእነዚህ እኩያን መጨለም ስለሌለበት፡፡

‹‹በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች አሉባልታ ይፈጥራሉ፣ ሞኞች ደግሞ እየተቀባበሉ ያሠራጫሉ፣ ነፈዞች ደግሞ አሉባልታውን የራሳቸው ያደርጉታል፤›› ይባላል፡፡ በዚህ ዘመን በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች የሕዝብ ደም የሚያፈሱት በማር የተለወሰ የአሉባልታ መርዝ በመንዛት ነው፡፡ ይህንን መርዝ የሚያስተጋቡ ደግሞ ሳያውቁ መሣሪያ እየሆኑ ነው፡፡ ሕዝብ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ ጠንክሮ በመሥራት ራሱንና አገሩን ለመለወጥ የሚያደርገውን ጥረት በአሉባልታ ማደናቀፍ፣ በተጨማሪም ለውጡን የሚመሩ ወገኖችን እንዲጠራጠር ማድረግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለዚህ ዋነኛ መንገዱ ደግሞ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚታገሉ ኃይሎችን በማጥላላት የብሔርተኞች ጠላት አድርጎ ማቅረብ ሲሆን፣ ይህን ሴራ ማክሸፍ የሚገባቸው ተባባሪ ይሆናሉ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ልዩነትን ይዞ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሐሳብ የበላይነት መፎካከር ሲቻል፣ ሁሉንም ነገር የግጭት መነሻና መድረሻ ማድረግ የተለመደው ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት በማየሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ የማይረዳ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ስብስብ፣ እንደ ዘመነ መሳፍንት ሁሉንም ጉዳይ ለግጭት መቆስቆሻ የሚጠቀም ከሆነ የሕዝብና የአገር ጠላት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ሥፍራ ሊሰጠውም አይገባም፡፡ ካሁን በኋላ በቀበሮ ባህታውያን መታለል መብቃት አለበት፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንነቱ የመኩራት፣ ማንነቱን የማስተዋወቅና በገዛ አገሩ በእኩልነት የመኖር መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ በሕጉ መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ መጠቀም፣ በራሱ የመዳኘትና ባህሉን የመጠቀም መብቱም መከበር አለበት፡፡ ይህ እየሰፋና እያደገ አንድ የጋራ አገር ለመገንባትና ዴሞክራሲን ሥርዓት ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ የግለሰብና የቡድን መብቶች በአግባቡ ተከብረው በገዛ አገር ባይተዋር ሳይሆኑ መኖር ሲቻል ደግሞ፣ የአገር አንድነት እየተጠናከረ የዴሞክራሲና የብልፅግና ጉዞ ይጀመራል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሕግ የበላይነት የሚመራ ሥርዓት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ከቻሉ፣ አገርን ወደ ባርነትና አዘቅት ለመክተት የሚንደፋደፉ አይሳካላቸውም፡፡ የድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ በብሔርና በእምነት እየተከፋፈሉ ከመወዛገብ ይልቅ፣ በሠለጠነ መንገድ በመነጋገር ለማኅበራዊ ፍትሕና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን እጅ ለእጅ መያያዝ ይበጃል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከሥልጣንና ከጥቅም በላይ ምንም የማይታያቸው ራስ ወዳዶችና በስሜት የሚነዱ አገር እየበጠበጡ ነው፡፡ እነዚህ ዕድሜና ጊዜ የማያስተምራቸውን እኩያንና ተላሎች በሕግ አደብ አስገዝቶ፣ ሕዝብን ከጨለማው ወደ ብርሃን ማሸጋገር አገራቸውን የሚወዱ ወገኖች ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ይገባል፡፡ አገር ከሌለ ምንም የለም፡፡

በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች በሙሉ ከእነ ልዩነቶቻቸውም ቢሆን በጋራ ለመሥራት መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ ‹መጀመርያ የመቀመጫዬን› እንዳለችው እንስሳ፣ የአገርን ጉዳይ ከምንም ነገር በፊት ማስቀደም ይገባል፡፡ በተለይ በሕዝብ መስዋዕትነት በተገኘው ለውጥ ምክንያት፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ስብስቦች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወደ አገር ቤት ከገቡ በኋላ አገርን በመረበሽ ላይ ያሉ ዘመን የማያስተምራቸው ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች፣ የጀመሩት አደገኛ ጉዞ እንደማያዋጣቸው ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ የሰላም ምልክት የሆነውን ነጭ ጨርቅ እያውለበለቡ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲገቡ በዓይኑ በብረቱ ያያቸው ሕዝብ ብዙ ነገር እየታዘበ ነውና ቢጠነቀቁ መልካም ነው፡፡ ካለፈው ስህተት ባለመማር ያንኑ ስህተት መደጋገም የሚያስከፍለው ዋጋ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክር አቅምና ዝግጅት የሌላቸው ደግሞ መድረኩን ለሌሎች ቢለቁ ተመራጭ ነው፡፡ ወቅቱ የሐሳብ ልዕልና ያላቸው የሚፎካከሩበት እንጂ ‹እርስዎም ይሞክሩት› እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሰንቆ ተነስቷል፡፡ ይህ ተስፋ ደግሞ በማንም እንዳይጨናገፍ ይፈልጋል፡፡ የአገር ተስፋ በእኩያን አይጨናገፍም እያለ ነው!