Skip to main content
x
እንደ ፖለቲካው በተስፋ የሚጠበቀው ኢኮኖሚ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

እንደ ፖለቲካው በተስፋ የሚጠበቀው ኢኮኖሚ

ላለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ፖለቲካዊ ክንውኖች ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካ ጭምር ተስፋ የሚሰጡ ስለመሆናቸው የውጭ መገናኛ ብዙኃን በስፋት ሲዘግቡበት ሰንብተዋል፡፡

ከሰሞኑም የ120 ዓመታት ባለዕድሜው ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣም የኢትዮጵያን ጉዳይ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሪፎርም ዕርምጃዎች አኳያ አስነብቧል፡፡ በአዲሱ የ2019 ዓመት አገሮች፣ ኩባንያዎች፣ መሪዎችና ሌሎችም ጉዳዮች በምን ሁኔታ በኢኮኖሚና በፖሊቲካው መስክ ዓመቱን ሊጓዙ እንደሚችሉ ጋዜጣው ትንበያውን ሲያሰፍር፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድንም አካቷል፡፡ በርካቶችም የፋይናንሺያል ታይምስ ትንታኔን በትዊተር ገጻቸው ተቀባብለውታል፡፡

የጋዜጣው ከየአቅጣጫው ‹‹ዓለምን በዚህ ዓመት ስንተነብያት›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ዓብይ ትንታኔ መሠረት፣ ኢትዮጵያ በዓለም ከታዩና ከሚጠበቁ በርካታ ክስተቶች ውስጥ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፖለቲካዊ ሪፎርም እንደጅማሮው የመቀጠሉ ጉዳይ ዋናው ጭብጥ እንደሆነ ጋዜጣው አመላክቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮና ከዚያም በፊት መወሰድ ከጀመሩት ዕርምጃዎች መካከል በርካታ እስረኞችን በገፍ የመፍታት፣ ተቋማትን መልሶ የማደራጀት፣ ግማሽ ካቢኔያቸውን በሴቶች ባለሥልጣናት የማዋቀር ሚናቸው ጎልተው ተጠቅሰዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት እንዲሳተፉ የማድረግና የተሰደዱ ፖለቲከኞችና ምሁራንም ጭምር ወደ አገር ቤት ተመልሰው በተለያዩ ኃላፊነቶች እንዲመደቡ ተደርገዋል፡፡ እንዲህ ባሉት ወጣ ያሉ ዕርምጃዎቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለምን ትኩረት ማግኘታቸውና ኢትዮጵያንም በዴሞክራሲያዊ ጉዞዋ በአፍሪካ ቦታ የሚሰጣት አገር እንድትሆን ሊያስፈርጁ የሚችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ ስለመጀመራቸው አያጠያይቅም፡፡ በፖለቲካው መስክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመሩት ፓርቲ ጀምሮ በየአካባቢው የሚታዩትን አለመግባባቶች፣ እዚህም እዚያም ሄድ መለስ የሚሉትን ደም አፋሳሽ ግጭቶች በምን አግባብ አስቁመውና አገሪቱን አረጋግተው ሌሎች አንገብጋቢ በሆኑ የአገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ የሚለው በበርካቶች በጉጉት የሚጠበቅ ዕርምጃ መሆኑ አልቀረም፡፡

ጅምር ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎች

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት በእጅጉ ይሻሉ ከሚባሉት ጉዳዮች ዋነኛው የኢኮኖሚው ዘርፍ ነው፡፡ እርግጥ ተስፋ የሚሰጡ ዕርምጃዎች በተመረጡ ማግሥት በፓርቲያቸው ማዕከላዊ ኮሚቴ በኩል የተወሰነውና ተግባራዊነቱ የሚጠበቀው ፕራይቬታይዜሽን በዓለም ጉልህ ተደማጭነት እንዲያገኙ የረዳቸው ይመስላል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሙሉና በከፊል ወደ ግል የማዛወሩ ዕርምጃ የሚያከራክሩ ነጥቦች ቢኖሩትም፣ በአብላጫው በአዎንታዊ ጎኑ ሲነሳ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በፕራይቬታይዜሽኑ ዕርምጃ ላይ በሁለት ጎራ ቆመው እየተከራከሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉት በከፊል አክሲዮኖችን በመሸጥ ወደ ግል ይዛወራሉ መባሉ አንደኛው መከራከሪያ ሆኖ ከርሟል፡፡

 ከዚህ በተጓዳኝ የአገሪቱን አሳሳቢ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው ያከማቹ ግለሰቦች ያለምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው እንዲያስተናግዱ ያስተላለፉት መመርያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት መንግሥት ከአቡዳቢ ልማት ፈንድ ለልማት ዕርዳታ ቃል የገባው ሦስት ቢሊዮን ዶላር (11 ቢሊዮን ድርሃም) በትልቁ የሚወሳ ነው፡፡ ቃል ከተገባው ከዚህ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለቀቀው የአንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጊዜያዊ ፋታ ከሚሰጡ ዕርምጃዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ ይህንኑ ጉዳይ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤም) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት አካቶታል፡፡ የገንዘብ ድርጅቱ መንግሥት እንዲህ ያለውን ድጋፍ ማግኘቱ ያለበትን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ችግር እንደሚያቃልልለት ቢጠቅስም፣ መንግሥት ያለበትን የዕዳ ጫና ለማቃለል በማሰብ (አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ባቀረቡበት ጠንካራ ግፊት ጭምር) የአጭር ጊዜ ብድሮችን ማቆሙና እየተዳካመ ከመጣው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ጋር ተዳምሮ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ይበልጥ ሊያጠናክሩበት የሚችሉ ክስተቶችን ኢኮኖሚው በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ አይኤምኤፍ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

ለአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት ለቻይና መንግሥት መከፈል ያለበት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድርም፣ መክፈያ ጊዜው ከአሥር ዓመታት ወደ 30 ዓመታት እንዲራዘም ከቻይና መንግሥት ጋር መደራደራቸውም በዓብይነት ከሚጠቀሱት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔዎች መካከል የማይታለፈው ነው፡፡

ምንም እንኳ ረጅም ዓመታት የፈጀ ሒደት ውጤት መሆኑ የታወቀ ሆኖ፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የተሰኘ ተቋም በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩም የውጭ ኩባንያዎች በጨረታና በድርድር ፕሮጀክቶችን እንዲገነቡ የሚያስችላቸውና መንግሥትም ከከፍተኛ የብድር ጫና መጠነኛ እፎይታ የሚያገኝበትን አካሄድ መከተል መጀመሩም፣ ከብዙ በጥቂቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በኩል ከተወሰዱ ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃዎች መካከል ሊወሳ ይችላል፡፡

ዓብይኖሚክስ በምሁራን ዕይታ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ ይህ ነው የሚባል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳላስተዋወቁ የሚያመላክቱ ትችቶች ይቀርቡባቸዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶላንድ ትራምፕ ‹‹ትራምፕኖሚክስ›› እየተባሉ የሚጠቀሱላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አሏቸው፡፡ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤም ‹‹አቤኖሚክስ›› የሚል ቅጽል ያገኙበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግብረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹ዓብይኖሚክስ›› ምን ይሆን? 

የአገሪቱን አሳሳቢ የኢኮኖሚ ችግሮች በተለይም በውጭ ምንዛሪ መስክ የሚታየውን ዕጥረት ለመፍታት ካደረጓቸው ጥረቶች መካከል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የጠየቁበትና ለዚህም ሲባል፣ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የተሰኘ ተቋም መመሥረቱም በኢኮኖሚ ምሁራን ዘንድ ቸል የሚባል ዕርምጃ አይደለም፡፡ ይሁንና ዘለቄታዊ መፍትሔ ወይም በማክሮ ኢኮኖሚ ስሌት ሚዛን የሚደፋ አካሄድ ሆኖ አልተገኘም፡፡

በአገር ውስጥና ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስብስብ በምክር ቤት ደረጃ የተቋቋመው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ፣ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውልና በበጎ ፈቃድ ላይ በመመሥረት ‹‹በቀን አንድ ዶላር›› በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር  ዓብይ አነሳሽ ንግግር ላይ ተመሥርቶ የተጀመረ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ተቋም ነው፡፡ ይሁንና ለሰባት ወራት ገደማ አንድ ዶላር በቀን ለሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ምላሹ ደካማ ሆኖ ቆይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጓቸው ንግግሮችም የዳያስፖራውን ማኅበረሰብ ሸንቆጥ አድርገው ነበር፡፡ ቃል የተገባው በተግባር እንዲገለጥ ባሰሙት ግሳጼ መሠረትም፣ ቃል የተገባውን ጨምሮ እስከ ዓርብ፣ ታኅሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የተሰባሰበው ገንዘብ ከ1.7 ሚሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ አላለም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እሳቤ መሠረት ግን በውጭ እንደሚኖር የሚገመተው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮኑ በቀን አንድ ዶላር እንኳ ቢያዋጣ፣ በሰባት ወራት ውስጥ ከ210 ሚሊዮን ዶላር በላይ በተገኘ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል በምሁራኑ ዕይታ መሠረት መንግሥት በእንዲህ ያሉ የልገሳ ፕሮግራሞች ላይ የሚመሠረት የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ላይ ጥገኛ መሆን የለበትም  የሚሉት፡፡ እንደሚጠበቀው መዋጮው ቢመጣ ግን ለመንግሥት ትልቅ እፎይታ የሚሰጠው ስለመሆኑ ግን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በመደበኛ ባንኮች የሚላከው የውጭ ሐዋላ ገቢ እንዲስፋፋ ቢደርግና በዚያም ላይ ትኩረት ቢሰጥበትና ዳያስፖራውም አስተዋጽኦውን በዚህ በኩል ቢያደርግም፣ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሻሻል ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም የሚጠቅሱ አሉ፡፡

አቶ ጌታቸው አስፋው የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ዘወትር በጋዜጦች ሐሳባቸውን በማጋራትና መጻሕፍት በማሳተም ጭምር የታወቁ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዘጠኝ ወራት ቆይታቸው በኢኮኖሚው ረገድ ምን ለውጥ አመጡ? ለሚለው ጥያቄ ምላሻቸው ይህ ነው የሚባል የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ እንዳላዩ የሚጠቁም ነው፡፡ ከበፊቱ የተለየ አዲስ አካሄድ ወይም ብዙም አልታየም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ እንደ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ያሉት ጉዳዮችም ቢሆኑ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች ሊባሉ እንደማይችሉ አብራርተዋል፡፡ በሥራ አጥ ቅነሳ፣ በዋጋ ግሽበት፣ በወጪ ንግድ አፈጻጸም፣ በበጀትና በሌላው መስክ አዲሱ አስተዳደር ያስቀመጣቸው ግልጽና ተጨባጭ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን እንዳልተመለከቱ የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ይልቁንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት እነዚህን ጨምሮ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባዋል ያሉት በአገሪቱ ምርታማነትና ለሰው ኃይል በሚከፈለው ደመወዝና ጥቅማጥቅም ላይ የሚታየውን ክፍተት ነው፡፡

አብዛኛው በሥራ መስክ የተሰማራው የአገሪቱ የሰው ኃይል ሠርቶ ከሚያስገኘው ውጤት በላይ ገቢ የሚያገኝ በመሆኑ አገሪቱ ኪሳራ እያጋጠማት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በገቢና በሥራ ውጤት ወይም በምርታማነት መካከል ተገቢው መመጣጠን እንዲኖር የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹አትዮጵያ አብዛኛው ሰው ከሠራው በላይ ገቢ የሚያገኝባት አገር መሆኗ ሊስተካከል ይገባዋል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች ላይ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር ያሳየው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሌለ ይጠቅሳሉ፡፡ እንደውም ‹‹ኢኮኖሚው ተረስቷል፤ ፖለቲካው በዝቷል›› ከሚሉ ምሁራን ሐሳብ ጋር እንደሚስማሙ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው እምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሁነኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ስብስብ ወይም አማካሪ የላቸውም፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሱት እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክና ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ያሉት ተቋማት ውስጥ ይህ ነው የሚባል የማክሮ ኢኮኖሚ ተንታኝ ቡድን መኖሩ እስኪያጠራጥር ድረስ ኢኮኖሚው ቸል እንደተባለ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ፡፡

በአዲሱ አስተዳደር ውስጥ ከቀደመው የተለየ አካሄድና ለውጥ አይታይም ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በተቃዋሚው ጎራም ሲሰነዘሩ የሚደመጡ ኢኮኖሚያዊ ዕሳቤ ያላቸው የፖለቲካ ሥርዓተ መንግሥት አስተሳሰቦችም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያልተዛመዱ ሆነው እንዳገኟቸው ያብራራሉ፡፡ ተቃዋሚዎች የሊበራል አሊያም የሶሻል ዴሞክራሲ መንግሥት በኢትዮጵያ መመሥረት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን በመጠቅስ አቶ ጌታቸው እንደሚያብራሩት፣ በተለይ የሶሻል ዴሞክራሲ ዕሳቤያቸው፣ በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ከሚተዳደረው 80 ሚሊዮን ሕዝብ አኳያ የማያስኬድ አማራጭ ነው በማለት ውድቅ ያደርጉታል፡፡

እንደ ስዊድን ያሉ አገሮች በሶሻል ዴሞክራሲ መርኅ፣ ሳይሠሩ ገቢ እንዲያገኙ ድጋፍ የሚደረግበት (ዌልፌር ስቴት ወይም ትራንስፈር ፔይመንት) አሠራርን የሚከተሉ ከመሆናቸው አኳያ፣ በኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን አካሄድ ለመከተል የሚያስችል የሀብት አቅም ያልተገነባ ከመሆኑም ባሻገር፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ሥሪት አንፃር ውኃ የማያነሳ ሙግት እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡

ከአቶ ጌታቸው ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ያንጸባረቁት ሌላው የኢኮኖሚ ምሁር ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ሁሉ በርካታ መጻሕፍትን በማሳተምና ሙያዊ ትንታኔዎችን ለመገናኛ ብዙኃን በመስጠት የሚታወቁት ደምስ (ዶ/ር)፣ በአዲሱ አስተዳደር ኢኮኖሚው ‹‹ሙሉ በሙሉ ተረስቷል፤›› ሊባል በሚችል ደረጃ መዘንጋቱን ገልጸዋል፡፡ 

እንደውም በአዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር እየጎላ የመጣው አካሄድ ከአገር በቀል ፖሊሲያዊ ጉዳዮችና ምክረ ሐሳቦች ይልቅ በውጮች ላይ የመንጠልጠል አባዜ በመሆኑ፣ ውሎ ሲያድር ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ደምስ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡ ‹‹ወደ ራሳችን መመልከት አለብን፡፡ የውጭ አማካሪዎች የሚያቀርቡት የፖሊሲ ሐሳብ ከሳራቸው ጥቅም አኳያ የሚቃኝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አደገኛ ነው፤›› ያሉት ምሁሩ፣ መንግሥት በፖለቲካው ላይ ክፉኛ መጠመዱም ለኢኮኖሚው ሥጋት እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡

ምሁራኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የወራት ቆይታ ወቅት እንደ ሌሎች አገሮች ‹‹ዓብይኖሚክስ›› ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሥልትና ፖሊሲ እንዳልመጣ እየገለጹ ነው፡፡ ድምዳሜያቸውም ፖለቲካው ኢኮኖሚውን ተጭኖታል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እሳት የማብረድ ዘመቻ ላይ እንጂ የተወጠነ የኢኮኖሚ ግብ መከተል አለመጀራቸው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

በአንፃሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽንና በኢትዮጵያ የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ትብብር የተዘጋጀ ከፍተኛ የፓናል ውይይት ላይ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያዎች ለማድረግ ጥናቶች መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የ100 ቢሊዮን ዶላር አቅም እንደሚኖረውም ተጠቅሶ ነበር፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው በጥቅሉ ከፋይናንስ ዘርፉ፣ ከወጪ ንግዱ፣ ከዓመታዊው የኢኮኖሚ ዕድገት እስከ ውጭ ብድርና ዕዳና መሰል ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥን ተገልጿል፡፡ መንግሥት አሻሽለዋለሁ ለሚለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መነሻ ይሆናሉ ያላቸውን ሐሳቦች ባስደመጠበት መድረክ፣ በርካታ ሙግት አዘል ሐሳቦችም ተስተናግደው ነበር፡፡ መንግሥት አሁን ባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢቀጥል፣ አለያም ማሻሻያዎችን በማድግ ማለትም የግሉና የመንግሥት አጋርነትን በማክሮ ኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ እንዲታቀፍ በማድረግ የሚመጡ ለውጦች ምን እንደሚመስሉ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የኢኮኖሚ ባለሙያው ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ዮሐንስ እንዳቀረቡት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዓመታት እያደገ ቢመጣም፣ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል እየሰፋ የመጣ ልዩነት ለማስተናገድ መገደዱን ጠቅሰው ነበር፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የገጠመው የተወዳዳሪነት ችግር ዕድገቱን እየጎተተው መምጣቱንም አንሰተዋል፡፡