Skip to main content
x
የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆን ኡንግ የቻይና ጉብኝት
ፕሬዚዳንት ኪምና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂፒንግ እ.ኤ.አ. በ2018 ለሦስት ጊዜያት ተገናኝተዋል

የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆን ኡንግ የቻይና ጉብኝት

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡንግ ለአራት ቀናት ጉብኝት ቻይና ገብተዋል፡፡ ከአሜሪካ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ለመገናኘት ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት ፕሬዚዳንት ኪም ቻይና የገቡት፣ በቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ግብዣ እንደሆነ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ ደግሞ ፕሬዚዳንት ኪም ከባለቤታቸው ሪ ሶል ጁ እና ከከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን በግል ባቡራቸው ወደ ቻይና መግባታቸውን አስፍሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ኪም ለአራት ቀናት በቻይና በሚኖራቸው ቆይታ፣ ከአገሪቱ ቁልፍ የዲፕሎማሲ፣ የንግድና የዕርዳታ አጋር ከሆነችው ቻይና ጋር አራተኛውን ጉባዔ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ መካከል ሰፍኖ የነበረው ውጥረት፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው ኪም ከተገናኙ በኋላ የረገበ ቢመስልም፣ ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ኪም ለአሜሪካ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡

የ2019 መግባትን አስመልክተው ፕሬዚዳንት ኪም በሰጡት መግለጫ፣ የኑክሌር ጦር ማበልፀጋቸውን ለማክሰም ቃል የገቡትን እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ በአሜሪካ በኩል ተመጣጣኝ ዕርምጃ ካልተወሰደና ሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣሉ ገደቦች ባሉበት ከቀጠሉ ሰሜን ኮሪያ ሌላ አማራጭ ልትከተል ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

በአገሪቱ ቴሌለቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ዋሽንግተን ተመሳሳይ ዕርምጃ ከወሰደች የኑክሌር ጦር መሣሪያ የማውደሙ ሒደት እንደሚፈጥንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ሰሜን ኮሪያ የሕዝቦቿንና የአገሪቷን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ አዲስ መንገድ ትከተላለች፡፡ አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ሕዝብ ትዕግሥት ባልሆነ መንገድ በመረዳት ማዕቀብ እንዲጣል ጫና ብትፈጥርና በዓለም ፊት የገባችውን ቃል ባትፈጽም ሰሜን ኮሪያ አዲስ መንገድ ትከተላለች፤›› ብለው በተናገሩ ሳምንት ወደ ቻይና ያቀኑት ፕሬዚዳንት ኪም፣ ከዚህ ቀደም ለሦስት ጊዜ ቻይና የሄዱት ከፕሬዚዳንት ትራምፕና ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃኤ ኢን ጋር ከመገናኘታቸው በፊትና በኋላ እንደነበር አልጀዚራ አስታውሷል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩ የፕሬዚዳንት ኪም የቻይና ጉብኝቶች፣ ዋና የተባሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን አስቀድሞ ወይም አስከትሎ ሲሆን፣ የአሁኑ ጉብኝትም ኪምና ትራምፕ የገቡዋቸውን ቃሎች በማክበሩ ሒደት ቻይና ከፊት ሆና አብራ እንድትሠራ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡ አሜሪካና ሰሜን ኮሪያም በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ቀደምም በአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ መካከል የነበሩ ውዝግቦችን በማዘለብና ሁለቱ አገሮች ተቀራርበው እንዲነጋገሩ በማመቻቸት ቻይና ግንባር ቀደም ነበረች፡፡

የአሜሪካና ቻይና የንግድ ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ባለበት ወቅት ፕሬዚዳንት ኪም ከአሜሪካ ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነት ቻይናን ጣልቃ ማስገባት መፈለጋቸው አጋጣሚውን ለመጠቀም ነው አስብሏቸዋል፡፡ ‹‹ቻይናን በአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ጣልቃ ማስገባት ቁልፍ ስትራቴጂያዊ አካሄድ›› መሆኑም ተገልጿል፡፡

35ኛ ዓመታቸውን ትናንት ያከበሩት ኪም፣ የቻይና ጉብኝት የአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ቀጣይ ውይይት አመላካች መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆን ኡንግ የቻይና ጉብኝት
ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆን ኡንግ በሲንጋፖር ካፒላ ሪዞርት ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. የኑክሌር ስምምነት ሲፈራረሙ

 

የቻይና ሚና

የፕሬዚዳንት ኪም የአሁኑ የቻይና ጉብኝት በቀጣይ የአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንቶች የሚገናኙበትን ቦታ ለመወሰን የአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት በቬትናም መገናኘታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ቀጣዩ የአሜሪከና ሰሜን ኮሪያ ውይይትም በተለይ ሰሜን ኮሪያን ከኑክሌር ጦር መሣሪያ ትጥቅ ነፃ ማድረግ ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡

ትራምፕና ኪም በሲንጋፖር በተገናኙበት ወቅት የኑክሌር ጦር መሣሪያን በመፍታት ላይ የገቡት ቃል በዋሽንግተንና ፒዮንግያንግ መካከል የአተረጓጎም ልዩነት ፈጥሯል፡፡

ሁለቱ አገሮች ከኑክሌር ጋር የተያያዘ ውዝግባቸውን አለመፍታት ደግሞ ለቻይና ራስ ምታት ነው፡፡ ከሰሜን ኮሪያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ቻይና ብሎም በቅርቡ ሰላም ያወረዱት ደቡብ ኮሪያና ሰሜን ኮሪያ የኮሪያ ልሳነ ምድር የጦር አውድማ እንዲሆን አይፈልጉም፡፡ ሰሜን ኮሪያም ከቻይና የምትመክረው ቀጣናው እንዲረጋጋ ከአሜሪካ ጋር የገባቻቸውን ቃል በማክበሩ ረገድ ቻይና እንድታግዛት ነው፡፡

የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆን ኡንግ የመጀመርያ ውይይት

ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆን ኡንግ በሲንጋፖር ካፔላ ሪዞርት ፊት ለፊት የተገናኙት ሰኔ 5 ቀን 2010 .. ነበር፡፡  ከውይይታቸው በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰጡት መግለጫም፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ለማውደም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ እስኪወድሙም ማዕቀቡ ይቀጥላል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

‹‹ሰሜን ኮሪያ ዋነኛውን የኑክሌር ሙከራ ጣቢያዋን አውድማለች፡፡ ነገር ግን ከዚህ የበለጠ በማድረግ ከተቀረው ዓለም በንግድ ግንኙነቷን ለማስቀጠል ገደብ አይደረግባትም፤›› ብለውም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ትጥቋን መፍታቷ ከተረጋገጠና ሥጋት መሆኗ ካቆመ ማዕቀቡ አይቀጥልም ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡ የሰሜን ኮሪያውን ኪምም፣ ‹‹ባለተሰጥኦ አዕምሮና አገሩን የሚያፈቅር፤›› ብለው አሞግሰዋልም፡፡ ወደፊት ኋይት ሐውስ እንደሚጋብዟቸውም ተናግረው ነበር፡፡

ኪም ጆንም፣ ሁለቱም ያለፈውን ለመርሳት መስማማታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ዓለም ትልቅ ለውጥ ያያል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህ ውይይት እንዲካሄድ በማድረጋቸው ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፤›› በማለት ከትራምፕ ጋር ያደረጉትን ስምምነት አሞካሽተዋል፡፡ በቃላት ጦርነት ሲናቆሩ ቆይተው ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አዲስ ክስተት የነበረ ቢሆንም የደረሱት ስምምነት ዛሬ ላይ የግንዛቤ ልዩነት አለበት ሲባል ተሰምቷል፡፡

ለዶናልድ ትራምፕውይይቱ ግብ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሣሪያዋን ሙሉ በሙሉ እንድታስወግድ ሲሆን፣ ኪም ጆን ኡንግ የኢኮኖሚ ልማትን ይሻሉ፡፡ ሁለቱ መሪዎች ዳግም ተገናኝተው የመረዳት ልዩነት አስከትሏል ለተባለው የቀደመው ስምምነታቸው መፍትሔ የሚያስቀምጡ ከሆነ፣ ለኮሪያ ልሳነ ምድርም ሆነ ለዓለም ሥጋት ሆኖ የቆየውን የጦርነት ንፋስ ያረግበዋል ተብሏል፡፡