Skip to main content
x
የትምህርቱን ዘርፍ የፈተነው የሰላም ዕጦት

የትምህርቱን ዘርፍ የፈተነው የሰላም ዕጦት

በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት የዩኒቨርሰቲ ፕሮግራም አራት ዓመት እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይህም ተቀባይነትን ካገኘ የመጀመርያ ዓመት ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ሙያቸው የሚገቡ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያዊነትን ሊላበሱ የሚችሉባቸውን ኮርሶች እንዲማሩ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

ከሁሉም ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡና ከ1,200 በላይ የሚሆኑ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ተሳታፊ የሆኑበት የሰላም መድረክ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከሚከታተሉትም ኮርሶች መካከል የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ተማሪዎቹ አገራቸውን በደንብ እንዲያውቁ፣ ግንኙነትንና ማንነትን እንዲቀበሉ፣ የባህል ብዝኃነት በሚገባ እንዲረዱ፣ ኀብረ ብሔራዊ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ብዙ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ሕዝቦችና ይህ ሲዋሃድ ውበት መሆኑን እንዲገነዘቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን እየተሠራበት ያለው የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርት ውስጥ ስለሰላም የሚገልጽ ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለው፣ አሁን ግን እየተዘጋጀ ያለው የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርት የአገሪቱን ዜጎች ሰብዕና የመገንባት ተልዕኮ እንዳለው ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለየዕድሜያቸው በሚመጥን መልኩ፣ እንዴት ማስተማር እንደሚቻልና እንዴትስ ሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ መካተት እንዳለበት የሚጠቁም ጥናት እንደተጠናቀቀና ስትራቴጂ ሰነድም እንደተዘጋጀ ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የታሪክ መምህራን ስለዴሞክራሲ ሲያስተምሩ እንደ ማጣቀሻ የሚጠቀሙት የግሪኳን አቴንስ ነው፡፡ ነገር ግን በአገራችን የዴሞክራሲ ግንባታን ለማስተማር የሚያስችል እሴትና ባህል፣ እንዲሁም የዳበረ አገር በቀል ዕውቀት አለ፡፡ በተለይም ምርምር ተደርጎበት በሰነድ አለመያዙ ካልሆነ በስተቀር የገዳ ሥርዓት ለዴሞክራሲ ግንባታ ዋነኛው መንገድ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡  በመሆኑም እየተከለሰ ባለው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ይህ እንዲካተት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ሰላም በመታጣቱ የተነሳ በሕዝቡ፣ በተለይ ችግሮቹ በተከሰቱባቸው አካባቢዎችና እየተቀነቀነ ባለው የትምህርት ፍኖተ ካርታና በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ ላይ እግጅ ከፍተኛ የሆነ ኡሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል፡፡

ሕዝብ እያለቀና እየተፈናቀለ፣ የመንግሥት ሀብትና ንብረት እየወደመ፣ ከሁሉም በላይ በጣም ውድ የሆኑ የሕፃናትና የሴቶች ሕይወት እየጠፋ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ትዕግሥት ለምን አስፈለገ? ብለው የሚጠይቁ ወገኖች እንዳሉ ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ ወገኖች ይህንን ጥያቄ የሚያነሱት ከመቆርቆር አንፃር ቢሆንም፣ ሰላምን መምራት በትዕግሥትና በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት መገንዘብ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በነፍጥና በኃይል መምራት ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስህተት እንዳይደገም መጠንቀቅ እንደሚገባ፣ ይህም ለዴሞክራሲ ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት መሆኑ በደንብ መታወቅ እንደሚኖርበት ነው ሚኒስትሩ ያመለከቱት፡፡

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ‹‹የዘላቂ ልማት ግንባታ በትውልድ ቅብብል የሚከናወን ወይም እንደየትውልዱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት አዳዲስ መንገዶች እየተቀየሱ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብ እንዲቀጥል ከተፈለገ መግባባት፣ መደማመጥ፣ መቻቻልና ማኅበራዊ እሴቶችን በየትውልዱ ውስጥ ማስረፅ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

አገር ግንባታና አገራዊ ትስስር ሲታሰብ ትምህርት፣ የሥነ ምግባር ውጤት፣ እንዲሁም የተስተካከለ የዜጎች ሰብዕና ወሳኝና በተለይም የሰላም ትምህርት ከታችኛው ዕርከን ጀምሮ መስጠት እግጅ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ትምህርት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ከጥቅሞችም መካከል ተፈጥሮን የመመርመር፣ የመለየትና የማወቅ፣ እንዲሁም በኅብረተስብ ሥሪት እሳቤ አወቃቀርና መስተጋብር ላይ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉ እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡

‹‹በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ መደማመጥና መቻቻል እንዲኖር ትምህርት ትልቁ መሣሪያ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ ትምህርት ቤቶች በማኅበረሰብ ሥነ ምግባር የዳበረ ሰብዕና ማበልፀጊያ ማዕከል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹በአገር ግንባታ ሒደት ሥነ ምግባር የተላበሰ ትውልድ መቅረፅ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶች እንደ መንግሥት እየተቆጣጠርናቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹን በተሟላ ሁኔታ ለመቆጣጠርም ሆነ ሰላምን በዘላቂነት የመገንባቱ ሒደት ገና ረዥም መንገድ መጓዝ የሚጠይቅ መሆኑን መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ትምህርት ቤቶች ለሁከት የሚጋብዙና የሚጋበዙ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ለመቋቋምና ለማስቀረት ያሳያችሁትን ትጋት፣ እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት ተግዳሮት ተቋቁማችሁ ያለፋባችሁበትን መንገድ ማድነቅ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ወቅታዊ ችግሮችን ከማቃለል ባሻገር ዘላቂ ለሆነው የሰላምና የአገር ግንባታ የሚመጥን ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ረገድ በአዲስ ቅኝትና መንገድ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን በሚጠይቅ ወቅት ላይ እንደምንገኝ አመልክተው በዚህ ዓይነቱ ሒደት ላይ መምህራን በጠንካራ አገራዊ ስሜትና ፍቅር እንደሚንቀሳቀሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ በንቲ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛው የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ የትምህርቱ ጥራት ምንም እንኳን አሳሳቢ ቢሆንም የተጠቀሱትን ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ ማድረግ በቀላሉ የሚገምት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ይኼም ሆኖ ግን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የትምህርት ተቋማት እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎሉ፣ እንዲሁም የመማር ማስተማሩም ሥራ እንዲታወክ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የትምህርት ማኅበረሰቡ የመማር ማስተማሩን በተረጋጋ ሁኔታ ማስኬድ ብቻ ሳይሆን በግልጽ ለጥቃት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡  

ይህንንም የተገነዘበው ማኅበሩ በተጠቀሱት ችግሮች ዙሪያ ሲወያይበት፣ ሐሳቦችንና አቋሞችን ሲይዝና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲገናኝ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ ድንበሮች ለተፈናቀሉ መምህራንና ወገኖች ከ150,000 ብር በላይ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ማኅበሩ ከለገሰው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በሚያጋጥሙ መድረኮች ሁሉ ስለሰላም ሲናገርና፣ ሲያስተምር አባሎቹም ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ በወላይታ ሶዶ ከተማ ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ባካሄደው 31ኛው መደበኛው ዓመታዊ የምክር ቤት ስብሰባ በአገሪቱ የሰላም ጉዳይ አጀንዳ ይዞ በመምከርና አሳሳቢ መሆኑን አፅንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡ አገር አቀፍ ጉባዔም እንዲዘጋጅ ወስኗል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ውሳኔውን ማስፈጸም ስላለበት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይህንኑ አገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ችሏል፡፡ በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር መጀመርያ ላይ ለሚካሄደው የሕዝብ ቆጠራ ለመምህራን ኃላፊነት ተሰጥቷል፡፡ በማንኛውም መልኩ የሚሰጠውን ኃላፊነት እንደምንወጣ ለአፍታም ቢሆን አልጠራጠርም፤›› ብለዋል፡፡

ከተመሠረተ ሰባ ዓመት የሆነው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የምሥራቅ አፍሪካ (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሌያ፣ ኤርትራ) አገሮችን በመወከል በአፍሪካ ደረጃ የሥራ አስፈጻሚ አባል ከመሆኑም በላይ የትምህርት ዓለም አቀፍ (ኢዱኬሽን ኢንተርናሽናል) አባል መሆኑንም ከፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው በዚሁ መድረክ፣ ‹‹በሰላም ግንባታ የመምህራን ሚና›› በሚል ዙሪያ ያጠነጠነ ጽሑፍ ቀርቦ በታዳሚዎቹ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ግልጽነት በጎደላቸው ነጥቦች ዙሪያም ማብራሪያ የሚጠቁሙ የተለያዩ ጥያቄዎች፣ ሐሳብና አስተያየቶች ተንቀፀባርቀዋል፡፡

ከቀረበውም ጽሑፍ ለመረዳት እንደተቻለው አገሪቱ በልማት የበለፀገች፣ ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ በዓለም መድረክ ውስጥ ተገቢውን ቦታ የያዘች፣ የሌሎችን ችግሮች መፍታት የምትችል እንድትሆን የሁሉም ምኞት መሆኑን፣ ይህ ምኞት ተስፋ ወይም ተግባራዊ የሚሆነው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ግን ምኞት ብቻ እንደሚሆንና ከዚህ አንፃር ሰላም ትልቅ ዋጋ እንዳለው አመልክቷል፡፡

ከተንፀባረቁትም አስተያየቶች መካከል ሰላማችን የደፈረሰበት ምክንያት የተፈጥሮ ሀብታችንን የመዘበረና፣ ብሔራዊ ነፃነታችንን የደፈረ የውጭ ጠላት መጥቶባት ሳይሆን፣ ፍላጎትና አልጠግብ ባይነት፣ ከራስ በላይ አገርንና ሕዝብን አለማስቀደምና ራስ ወዳድነት በመስፈኑ ነው የሚሉ ይገኙበታል፡፡

ይህን እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ የጥፋት ኃይሎች በፈጠሯቸው ዕረፍት የለሽ ደባዎች ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ አገሪቷ ሰላም እንዳጣች፣ መሪዎቻችን ሕዝቡን ለልማት ማነሳሳታቸውን ትተው የቤት ሥራቸው እሳት ማጥፋት ብቻ ሆኖ እንደቀረ፣ መምህራንም ለተማሪዎች ዕውቀት ማስጨበጥና ተማሪዎችም ያለ ሥጋት በየትምህርት ቤታቸው ዕውቀት ሊገበዩ እንዳልቻሉ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የጠቆሙት፡፡

ይህን የመቆጣጠር ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው አለመሆኑን፣ በየአካባቢያቸው የሚታዩ አንዳንድ የማይመች ሥጋቶች ሲኖር ወይም ሲከሰት ወዲያውኑ መቆጣጠር፣ ይህም ካልተቻለ ደግሞ ለመቆጣጠር ለሚችል አካል መረጃ መስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ከታዳሚዎች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡