Skip to main content
x
ከእኩዮቻቸው ወደኋላ የቀሩ ሕፃናትን የመርዳት ጅማሮ

ከእኩዮቻቸው ወደኋላ የቀሩ ሕፃናትን የመርዳት ጅማሮ

ወጣት እመቤት አይቸው የሙዚቃ ትምህርቷን የተከታተለችው በተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. የሦስት ዓመት ትምህርቷን አጠናቃ በአድቫንስድ ዲፕሎማ በኪቦርድ ከተመረቀች በኋላ ትኩረቷን ያደረገችው የትምህርት አቀባበል ችግር፣ የአዕምሮ ውስንነት ወይም ከሌሎች እኩያ ተማሪዎች ጋር በመግባባትና ትምህርት በመቀበል ቀረት የሚሉ ልጆችን ሙዚቃ ትምህርት ብናስተምራቸው ትኩረት የመስጠት ችሎታቸው ይዳብራል፣ ትምህርታቸውም ይቃናል በሚለው ላይ ነው፡፡ ከአዕምሮ ዕድገታቸው ጋር ተያይዞ የተቸገሩ ልጆችንና ወላጆቻቸውን የመርዳት ፍላጎቷ ገና ጅማሮ ላይ ቢሆንም፣ በማኅበረሰቡ በኩል ያለው አቀባበል ትንሽ ያስቸግራል ትላለች፡፡ ከእኩዮቻቸው ቀረት የሚሉ ልጆችን ለምን በሙዚቃ ለመርዳት እንደተነሳሳችና በሥራዋ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሙዚቃው ትምህርት እንዴት ገባሽ?

እመቤት፡- የምኖረው ጎንደር ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ አንጎራጉር ነበር፡፡ አሁን የመዝፈን ፍላጎቱ ባይኖረኝም ስሜቱ አለኝ፡፡ አካባቢው ጥበብ የሚወጣበት በመሆኑ ሙዚቃን እያየሁትና እየሰማሁት ነው ያደኩት፡፡ ሆኖም በሥፍራው ያለውን ተሰጥኦ በትምህርት የምታዳብሪበት የሙዚቃ ትምህርት ቤት የለም፡፡ ሚራክል የሚባል ትምህርት ቤት በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እንግዳ ተቀባይነት ተምሬያለሁ፡፡ በራሴ ደግሞ እየተጣጣርኩ ሙዚቃውን ብዙ ሞክሬ ነበር፡፡ የተወሰነ ነገር ካወቅሁ በኋላ በተሻለ አማራጭ ለመማር አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ እዛ ብዙ ተገድበው የቀሩ አሉ፡፡ ተምሬ እነሱን ባስተምር የሚልም ፍላጎት አለኝ፡፡ 2008 ዓ.ም. ላይ የአሥረኛ ክፍል ውጤቴን ይዤ በተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በቀን ክፍለ ጊዜ ገባሁ፡፡ መጀመርያ ላይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት መስተንግዶ እየሠራሁ የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ ሙዚቃውን እማር ነበር፡፡ ከስድስት ወር በኋላ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በመቀጠር ግማሽ ቀን እየሠራሁ ግማሽ ቀን ሙዚቃውን መማር ጀመርኩ፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር ወላጆች ቤት ለቤት ልጆቻቸውን እንዳስተምር መጠየቅ የጀመሩት፡፡ አንዳንድ ጽሑፍ ሳነብ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ሙዚቃ የሚያመጡት ልጆቻቸው አስቸጋሪ ሲሆኑና የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ሲኖርባቸው ነው፡፡ ሕፃናት ሲረብሹ እንዲረጋጉ ሙዚቃ እንዲማሩ ያደርጋሉ፡፡ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውንም የቀለም ትምህርት ስለማይሆንላቸው ብለው ወደ ሙዚቃ ያመጧቸዋል፡፡ ልጆቻቸው ግን ምን እንደሚፈልጉ አያውቁም፡፡ ሙዚቃ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ሕፃናት መልካም እንደሆነ ካነበብኩትና ከልምዴ መገንዘብ ችያለሁ፡፡ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ልጆች አንድ ነገር ላይ ማተኮር እንደሚፈልጉ ተረድቻለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙ ወላጆች አንዴ ስዕል፣ አንዴ ሙዚቃ ወይም የተለያዩ ነገሮችን በአንዴ እንዲፈጽሙ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ከልምዴ ያየሁት ሲሆን፣ በአንዴ ሁሉንም እንዲነካኩ ከማድረግ ይልቅ በየተራ ቢሆን ብዬ እመክራለሁ፡፡ በዚህ ዘዴ ያስተማርኳቸው ልጆች የተቀየሩ አሉ፡፡ ወላጆች ልጆች ሲያስቸግሯቸው ወይም የአዕምሮ ውስንነት ሲገጥማቸው ብቻ ሳይሆን ያስፈልጋቸዋል፣ ይጠቅማቸዋል ብለው ሙዚቃን ቢያስተምሯቸው ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምታስተምሪያቸው ልጆች ወላጆች ልጆቻቸውን ለምን ወደ ሙዚቃ ትምህርት እንደሚያመጡ ጠይቀሽ ታውቂያለሽ?

እመቤት፡- አዎ፡፡ ብዙውን ጊዜ ሲያስቸግሯቸው እንደሆነ ይነግሩኛል፡፡ ዕረፍት እንዲያገኙ የሚሉም አሉ፡፡ ወደፊት ሙዚቀኛ እንዲሆን የሚል አላጋጠመኝም፡፡ መደበኛው ትምህርት ላይ ወደኋላ የቀሩ የነበሩ ልጆች መሻሻል ማሳየታቸውን ወላጆቻቸው ነግረውኛል፡፡ በርቺ፣ ይህ ነገር በኢትዮጵያ መበረታታት አለበት የሚሉኝም አሉ፡፡ ሙዚቃ ከልጅነት ጀምሮ በደንብ መሰጠት ያለበት ትምህርትም ነው፡፡ ግን እውነታው ይህ አይደለም፡፡ ሙዚቃን ለልጆች ለማስተማር የተሟላ ግብአትም በየትምህርት ቤቱ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ይህ ነገር እንዲቀየር መሥራት እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በምን መልኩ መሥራት አስበሻል?

እመቤት፡- የሕፃናት ሙዚቃ ትምህርት ቤት መክፈት እፈልጋለሁ፡፡ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ቀረት የሚሉ ልጆችንና ሌሎችንም ማስተማር የሚችል ትምህርት ቤት መክፈትና ለልጆቹ ተጨማሪ ዕድል መፍጠር እፈልጋለሁ፡፡ ፈቃድ ለመጠየቅ በየክፍለ ከተሞች ሄጃለሁ፡፡ ነገር ግን ከ15 ዓመት በላይ ለሆኑት እንጂ ከዛ በታች አይፈቀድም ተብያለሁ፡፡ በውጭ አገሮች ሕፃናት ገና በልጅነታቸው በሙዚቃው ሲካኑ እናያለን፡፡ ይህ ዓለማዊ ነው የሚል አመለካከትም በማህበረሰቡ ውስጥ አለ፡፡ ሆኖም በመንፈሳዊ ሙዚቃዎች ልጆችን ማስተማርና አዕምሮዋቸውን መሰብሰብ ይቻላል፡፡ በአገራችን ባህላዊ በምንላቸው ክራር፣ ማሲንቆ፣ በገና፣ ከበሮና ሌሎችም ልጆችን መርዳት ይቻላል፡፡ ይህ ልጆች በሥነ ምግባር እንዲታነጹ፣ ነገሮችን በአትኩሮት እንዲመለከቱ ያስችላል፡፡ እኔም ሙዚቃን የማስተምረው መልካም ሥነ ምግባርን ለመቅረጽ፣ አገርና ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ማኅበረሰቡን እንዲያከብሩና እንዲወዱ፣ ለራሳቸው ክብር ኖሯቸው ሌሎችን እንዲረዱ ነው፡፡ የማስተምረው የልጆች መዝሙር በኖታ እየጻፍኩ ሲሆን፣ የዘፈኑ መልዕክትም መልካም መሆን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ወደ ኋላ የቀሩ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች በልጆቻቸው ሁኔታ በጣም ይጨነቃሉ፡፡ ስለሆነም መታገዝ አለባቸው፡፡ ቤት ለቤት እየሄድኩ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያላቸውን ሳስተምር ለቤተሰብም እፎይታ ነው፡፡ ጭንቀታቸውን የሚጋራቸውና የልጆቻቸውን አዕምሮ የሚሰበስብላቸው ያገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የገጠመሽ ፈተና ምንድነው?

እመቤት፡- መሥራት የሚያስችል ድባብ የለም፡፡ በሙዚቃው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ማገዝ እችላለሁ፡፡ ከተለያዩ ጽሑፎችም እንዳየሁት የሙዚቃ ቴራፒ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸውን ስሜት ለመግዛትም ያገለግላል፡፡ የሰዎችን አካላዊ፣ አዕምሮአዊና ማኅበራዊ ሁኔታቸውን ያሻሽላል፡፡ የታመሙ ሰዎችም ሕመማቸውን እንዲዘነጉ ያደርጋል፡፡ እኔ በልምድ እንዳየሁት ደግሞ ውስንነት ያለባቸው ልጆች እየተሻሻሉ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራው አድካሚ ነው፡፡ ክፍያም አይገኝበትም፡፡ ማኅበረሰቡም አይረዳሽም፡፡ በየትምህርት ቤቱ ለማስተማር ብጠይቅም እስካሁን ስላላገኘሁ ቤት ለቤት እየሄድኩ ነው የማስተምረው፡፡ በሌላ በኩል ልጆች በመደበኛው ትምህርታቸው ስህተት ሲሠሩ ወላጅ ለምን? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሙዚቃው ላይ ግን ምንም አይጠይቅም፡፡ ለሙዚቃ ትኩረት አይሰጥም፡፡ ሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ውስጥም ቢሆን አዕምሮ ችግር ላለባቸው የተለየ ትምህርት አይሰጥም፡፡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ባለው ሙዚቃን የማስተማር ክፍተት ዙሪያ ያለው ችግር ቢቀረፍ ብዬ አምናለሁ፡፡ ልጆቹ ምን እንደሚፈልጉ በመረዳት ሥዕል ከሆነ ወደ ሥዕል፣ ሙዚቃ ከሆነ ወደ ሙዚቃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ወላጆችም ደስተኛ ሆነው ልጆቻቸው ደስተኛ እንዲሆኑ ከፈለጉ ልጆቹን በፍላጎታቸው ማስተማሩ መልካም ነው፡፡ አካል ጉዳተኞችንም በሚፈልጉት መንገድ መርዳት ያስፈልጋል፡፡ ወደፊት ትምህርት ቤት ብከፍት ወይም የሚረዳን ባገኝ ትምህርት ቤት ከፍቼ መክፈል ለማይችሉት በስኮላርሽፕ መክፈል ለሚችሉ ደግሞ እያስከፈልኩ የአካል ጉዳት፣ የአዕምሮ ውስንነትና ከእኩዮቻቸው ቀረት የሚሉ ሕፃናትን መርዳት እፈልጋለሁ፡፡ ያገኘሁት ልምድም ልጆቹን ሙዚቃ በማስተማር ክህሎታቸውን ማዳበርና በትምህርታቸው የተሻሉ እንዲሆኑ እንደሚያስችል አስገንዝቦኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሙዚቃ አስተማሪ የመሆን ሐሳብ ነበረሽ? 

እመቤት፡- አስተማሪ የመሆን ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ ሆኖም ልጆቹን ሳገኝና ሳስተምር ያየሁባቸው ለውጥ ለምን አልረዳቸውም እንድል አድርጎኛል፡፡ ፍላጎቴ ኪቦርድ መጫወት ቢሆንም ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ ብዬ ተነስቻለሁ፡፡ ባንድ ውስጥ ገብቶ ለመሥራትም ቀላል አይደለም፡፡ ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ እንደሚሰጡ ግለሰቦች፣ እኔም ከልምዴ ያገኘሁትን እውቀት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡