Skip to main content
x
ገንዘብ ያልተደረገውን ገንዘብ ከዋጋ ንረት አኳያ በአገር ቋንቋ የተነተኑት የኢኮኖሚ ባለሙያ ያሄሳሉ
አቶ ጌታቸው ከሙያ አጋሮቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን አራተኛ መጽሐፋቸውን አስመርቀዋል

ገንዘብ ያልተደረገውን ገንዘብ ከዋጋ ንረት አኳያ በአገር ቋንቋ የተነተኑት የኢኮኖሚ ባለሙያ ያሄሳሉ

ቆፍጣና ብዕር አላቸው፡፡ ስለኢኮኖሚ ሳይንስ የሚሰጡት ትንታኔና በኢትዮጵያ ስላለው የሳይንሱ ትግበራ ዕይታቸውንና ሙግታቸውን በአማርኛ ቋንቋ ማቅረባቸውም ለተደራሲው ብቻ ሳይሆን፣ ለኢኮኖሚ ባለሙያውም አስተማሪ ሆኖ መገኘቱን አጋሮቻቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

ከሰሞኑ አራተኛውን መጽሐፋቸውን ጀባ ያሉት፣ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው አስፋው በሪፖርተር ጋዜጣ በርካታ ሙያዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ የኢኮኖሚ ህፀፆችን በመተቸትና በማሄስ፣ የኢኮኖሚ ሳይንስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ስላለው አተገባበር ተዛነፎች፣ ሙያውን ሠልጥነውበት ከሚተዳደሩበት ይልቅ ጥራዝ ነጠቆች የተቆጣጠሩት እየሆነ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው፣ በሙያቸው ጉዳይ፣ ‹‹ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዝምታን የመረጥን ቀን ሕይወታችን ያበቃል፤›› የሚለውን የመብት ተሟጋቹን የማርቲን ሉተርን መርህ እንደሚከተሉም ከመግለጽ አይቆጠቡም፡፡

ግንዛቤ ያነሰው ገንዘብ?

ቅዳሜ ታኅሳስ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ያስመረቁት መጽሐፍ ‹‹ምንዛሪ፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ገንዘብና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ›› የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የኢኮኖሚ ዘርፉን በሚመሩ ተቋማትና ኃላፊዎች፣ በሚዲያና በሌሎችም የሙያ መስኮች ስለ ገንዘብና ስለ ዋጋ ግሽበት የሚቀርቡ ትንታኔዎች ከመነሻቸው የአተረጓጎም ስህተቶች የሚታዩባቸው እንደሆኑ በማብራራት፣ የመጽሐፋቸው ጭብጥ ይንደረደራል፡፡

በኢኮኖሚ ሳይንስ ቋንቋ ገንዝብ ሦስት መሠረታዊ ተለያይቶ ፍቺዎችና አገባቦች እንዳሉት ያመላከቱት አቶ ጌታቸው፣ ገንዘብ በምንዛሪ አገባቡ ‹‹ከረንሲ›› የሚለውን የእንግሊዝኛ ፍቺ እንደሚወክል፣ ጥሬ ገንዘብ ወይም ‹‹መኒ›› የሚለውንና ገንዘብ ራሱ ግን ‹‹ፋይናንስ›› ተብለው ለየብቻ በዓውዳቸው የሚቆሙ አገባቦች እንዳሉት ያብራራሉ፡፡  በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ገንዘብ ከላይ ለተዘረዘሩት አገልግሎቶችና ጠቀሜታዎቹ እየተለየ መነገር ሲገባው፣ ሁሉንም እየደበላለቀ የመጥራትና በደፈናው ገንዘብ እየተባለ ግልጋሎት ላይ መዋሉን አቶ ጌታቸው በመቃወም ይተቻሉ፡፡ ትችታቸው ባለሙያዎችንና ቱባ ባለሥልጣናትንም ያካትታል፡፡

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት

የባለሙያው ሙግት ግን በዚህ አይገታም፡፡ በዋጋ ንረት በኩልም የሚታየውን የተምታታ ሙያዊ የሳይንሱ ቃላት አጠቃቀምና አገባብ በማሄስ ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ነጥቦች ጠቁመዋል፡፡ የዋጋ ንረት፣ ከዋጋ ግሽበትና ከዋጋ ውድነት ጋር እየተደበላለቀ ሲገለጽ መኖሩን በማመላከት፣ የእነዚህን ልዩነቶች በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡

ከዚህ ይልቅ ትኩረት የሳበውና መጽሐፉ ይፋ በተደረገበት ወቅትም፣ ከተሳታፊዎች ማብራሪያ የተጠየቀበትና ጥያቄዎችንም ያስተናገደው በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ጉዳይ ነው፡፡ የአቶ ጌታቸው መጽሐፍን በአስረጂነት ያቀረቡት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመራማሪው አቶ አሚን አብደላ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አሚን መጽሐፉን ከራሳቸው ዕይታዎች አኳያ በመንተራስ ባሰሙት ማብራሪያ፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን የዋጋ ንረት በትክክል ለመተንበይና መፍትሔዎችንም ለመጠቆም የመረጃ እጥረት፣ ሲገኝም የተምታታ መረጃ ስለሚቀርብ ድምዳሜውን አስቸጋሪና የኢኮኖሚ ባለሙያውን እጀ ሰባራ እያደረገው ነው፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተለው የዋጋ ንረት ፖሊሲ ግራ እንደሚያጋባ ሲገልጹም፣ የዋጋ ንረቱ ከአሥር በመቶ በላይ እያደገ በሚገኝበት ሁኔታ የድህነት ቅነሳ ፖሊሲው እንዴት ብሎ አብሮ እንደሚሄድ በመጥቀስ ነበር፡፡ ‹‹ሆን ተብሎ ነው ወይስ አለማወቅ ነው?›› በማለት የሚጠይቁት አቶ አሚን፣ የዋጋ ንረት እንዲህ ባለ ደረጃ እያደገ ሲሄድ የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ እንደሚባባስና የድህነት ቅነሳ አጀንዳውንም አዳጋች እንደሚያደርገው ቢታመንም፣ ኢትዮጵያ ግን ከአሥር በመቶ በላይ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገቧንና ይህም ዕድገት ከድህነት አኳያ የተጫወተው ሚና ከዋጋ ንረቱ አኳያ ተተንትኖ መታየት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ሲገልጹትም ‹‹ከደሃው ላይ በጫና እየተቀነሰ ለባለፀጋው የሚጨመርለት ሀብት መፍጠሪያ (ሰርፕለስ ኤክስትራክሽን) ነው፤›› ብለውታል፡፡ ለዚህ ዋቢ ያደረጉትም ባንኮች ለተቀማጭ ምንዛሪ የሚከፍሉት ወለድና በአገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት መጠን ልዩነትን ነው፡፡ ዓምና ወደ ሰባት በመቶ ከፍ የተደረገው የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ፣ ከዋጋ ንረቱ አኳያ ሲታይ፣ ለአስቀማጩ ኪሳራ የሚያስከትልበት ነው፡፡ ይኸውም አስቀማጭ የባንክ ደንበኛ ገንዘቡን በባንክ በማስቀመጡ ብቻ የሦስት በመቶ ኪሳራ እያስተናገደ፣ ያስቀመጠው ገንዘብ የመግዛት ዋጋው እያሽቆለቆለ፣ በአንፃሩ ተበዳሪው የዋጋ ንረት በፈጠረለት ዕድል ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ምሁራኑ አብራርተዋል፡፡

ለዋጋ ንረት መባባስ በማሳያነት ከጠቀሷቸው መካከል እንደ ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ያሉት አምራቾች አንድ ኪሎ ስኳር በአምስት ብር ወጪ ቢያመርቱም፣ በመንግሥት ማከፋፊያ ድርጅቶች በኩል ለሕዝቡ አንድ ኪሎ ስኳር በ20 ብር የሚሸጥበት አግባብ ‹‹ማንን ነው ተጠቃሚ የሚያደርገው?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በ80 ብር እየተመረተ ለተጠቃሚው በ400 ብር የሚሸጥበት አግባብ እንደ አቶ ማብራሪያ ‹‹ሰርፕለስ ኤክስትራክሽን›› ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የዋጋ ንረት እየተስፋፋ፣ ሕዝቡን ከባድ የኑሮ ፈተና ላይ የሚጥል አሠራርና ሥርዓት በመፈጠሩ፣ በርካቶች በዋጋ ንረት ሳቢያ ለቤት አልባነትና ለሥራ አጥ እየተዳረጉ የሚሰደዱት፣ ሕፃናት ለመቀንጨር፣ አብዛኛው ሕዝብም ለከፋ የኑሮ ውድነትና ድህነት የሚዳረግበት መንስዔ ይኸው የዋጋ ንረት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ለማስረዳት አቶ አሚን መነሻ ያደረጉት የአገሪቱን የወጪና ንግድ ሁኔታ ሲሆን፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ መካከል ያለው የክፍያ ሚዛን በየጊዜው እየሰፋ እንደመጣ ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጠን 18 በመቶውን የገቢ ንግድ ብቻ ለመሸፈን የሚያበቃ ስለመሆኑም አቶ አሚን ጠቅሰዋል፡፡ አስቀማጮች ከሌላቸውም ላይ ቀንሰው የሚቆጥቡትን ገንዘብ የሚበደሩት እነማን ናቸው? ያሉት አቶ አሚን፣ እንደ አይካ አዲስ ያሉት ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛ ገንዘብ በብድር ተሰጥቷቸው በኪሳራ መዘጋታቸው በጥልቅ ሊመረመር፣ እንደውም አስቀማጩ ካሳ እንደሚገባው ሁሉ በቁጭት ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፣ ከጅማ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በምትገኘው ዴዶ በተሰኘች አነስተኛ የገጠር ከተማ ውስጥ የሚታየውን የግብይት ዋጋን የማረጋጋት ልማድ፣ ከ200 ዓመታት በፊት የዘመናዊ ኢኮኖሚክስ አባት እየተባለ ከሚጠራው ፈላስፋ ከአዳም ስሚዝ ንድፈ ሐሳብ ጋር አመሳስለውታል፡፡ የዴዶ ነዋሪዎች ገበያ የሚወጡት እኩለ ቀን ከገባ በኋላ በሰባት ወይም በስምንት ሰዓት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህ የሆነበትን ምክንያትም አብራርተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ጠዋት ገበያ ቢወጡ ሁሉም ነጋዴ ወደ ገበያ ስለማይመጣ፣ ጥቂቱን ዕቃ ዋጋ በማስወደድ ሊሸጥ ስለሚችል ትክክል አይሆንም፡፡ ከሰዓት በኋላ አርፍደው ቢወጡም፣ ነጋዴው ዕቃውን ሸጦ ጨርሶ ለመሄድ ስለሚቻኮል ዋጋው ለትክክለኛው ሸቀጥ የሚገባው ስለማይሆን ትክክል አይመጣም፡፡ በመሆኑም ገበያው በሚደራበት እኩለ ቀን ላይ መውጣት የሚቀርበውን ዕቃ መጠን ከዋጋው በማስማማት የተመጠነ ግብይት ለመፈጸም ያስችላል፡፡

የተረጋጋ ገበያ በዚህ ወቅት ስለሚኖር፣ ዶዴ በሚውለው ገበያ ዋጋ አይዋዥቅም፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንደማይንፀባረቅ፣ ይልቁንም አብዛኛው ሰው የዋጋ ንረት ተጠቂ በመሆኑ ሳቢያ በሌሎች ላይ ጥገኛ ለመሆን እንደሚያስገድደው አቶ ጌታቸው ከአቶ አሚን እየተቀባበሉ አስረድተዋል፡፡

ተቀጣሪ ሠራተኞች፣ ጡረተኞችና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች በዋጋ ንረት ሳቢያ ራሳቸው መቻል እየተሳናቸው መጥቷል ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቆ ሥራ የያዘ ደመወዝተኛ፣ ከቀን ሠራተኛ ያነሰ የመደራደር አቅም እንዳለውም አብራርተዋል፡፡ ይኸውም የቀን ሠራተኛው የሸቀጥ ዋጋ ሲጨምርበት የጉልበቱን ዋጋም በዚያው ልክ ጨምሮ ቀጣሪው እንዲከፍለው ይጠይቃል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የተማረው የግልና የመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኛ ግን የዋጋ ንረቱ በመባባሱ ምክንያት፣ ምናልባት ደመወዙ እንዲጨመርለት ይጠይቅ ይሆናል እንጂ የመደራደር አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ የጎጂነቱን መጠን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

የሒሳብ ባለሙያው አቶ ይትባረክ አረጋኸኝም በባንክ የሚያስቀምጡ ደንበኞች በዋጋ ንረት ሳቢያ ገንዘባቸው ዋጋ እንደሚያጣ አምነው፣ በኢትዮጵያ የግብርናው ካፒታል ወደ ከተማ እየሸሸ የመጣው በምንዛሪ ወይም በገንዘብ ኢኮኖሚው ጫና ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የሀብት ፍሰቱ ወደ ከተማ እየፈለሰ ነው ያሉት አቶ ይትባረክ፣ እንደ ካፒታል ገበያ ያሉ አማራጭ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ቢስፋፉ ግን አስቀማጮች ገንዘባቸውን ኢንቨስት በማድረግ ከወለድ የተሻለ የገቢ አማራጭ ማግኘት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ‹‹በቆጣቢው ክስረት ተበዳሪው የሚከብርበትና የሸማቹ የመግዛት አቅም በዋጋ ንረት የሚዳከምበትን የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት መቀየር›› እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የጥሬ ገንዘብ ፍሰትንና የምንዛሪ ግብይትን በመቆጣጠርና ሚዛናቸውን በማስጠበቅ ሸማቾችን በዋጋ ንረት ከመደቆስ፣ ኑሯቸውንም ከመናጋት መታደግ እንደሚቻል በመጽሐፋቸው አብራርተዋል፡፡

እንዲህ ያሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች የተዋዙበት የአቶ ጌታቸው መጽሐፍ፣ ከሰባት ወራት በፊት ያሳተሙትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሙያዊ ዕይታዎቻቸውን ያሳፈሩባቸው አራት መጻሕፍት አሳትመዋል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታትም ሞጋች ጽሑፎቻቸውን በሪፖርተር ጋዜጣ አበርክተዋል፡፡