Skip to main content
x
የወርቅ ገቢ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ወረደ

የወርቅ ገቢ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ወረደ

ከኢትዮጵያ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች አንዱና ዋነኛው በመሆን ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገኘው የነበረው የወርቅ ማዕድን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሽቆልቆሉ በ2010 ዓ.ም. ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር በመውረዱ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ክንውን ያመላከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2010 ዓ.ም. ሪፖርት፣ የወርቅ ማዕድን አፈጻጸም ከየትኛውም ጊዜ በባሰ ደረጃ እያሽቆለቆለ በመምጣት ዝቅተኛውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዳስመዘገበ አሳይቷል፡፡ በዓመቱ ከፍተኛ የገቢ ቅናሽ የታየበት የወጪ ንግድ ምርት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እንደ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ከወርቅ የተገኘው 100.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህ መጠንም ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ የወርቅ ማዕድን ያስመዘገበው ዝቅተኛው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ዓምና ከወርቅ የተገኘው ገቢ ከካቻምናው በ52 በመቶ ያነሰም ሆኗል፡፡ የገቢ ቅናሹ በየትኛውም የወጪ ንግድ ምርት ላይ ያልታየ ዝቅተኛው ገቢ ስለመሆኑም ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከወርቅ የወጪ ንግድ በ2009 ዓ.ም. 208.8 ሚሊዮን ዶላር ተመዝግቦ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. 290 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቶም ነበር፡፡ ይሁንና ባለፉት አሥር ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ከዘርፉ እየተገኘ ያለው ገቢ እጅጉን እየቀነሰ ከመምጣቱ ባሻገር፣ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ አኳያ የነበረው የወርቅ ድርሻም ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡

ባለፉት አሥር ተከታታይ ዓመታት ውስጥ የነበረውን የወርቅ የወጪ ንግድ የሚያሳዩ መረጃዎች የተሻለ የገቢ መጠን ሲመዘገብባቸው ከነበሩት ውስጥ በተለይም በ2004 ዓ.ም. 602.4 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቶ እንደነበር ያጣቅሳሉ፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከጠቅላላ የወጪ ንግዷ የ3.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስመዝግባ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ከወርቅ የተገኘው ገቢ የ19.1 በመቶ ድርሻ እንደነበረው የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ይህም ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ሊባል የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወርቅ ማስገኘት እንደቻለ ይጠቁማል፡፡ በ2004 ዓ.ም. ከቡና የተገኘው 833 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ የነበረው ድርሻም 24 በመቶ ነበር፡፡

በ2005 በጀት ዓመትም ቢሆንም የወርቅ የወጪ ንግድ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገኘው ምርት ነበር፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ገቢ 18.1 በመቶ ድርሻ በመያዝ 578.8 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡ ነገር ግን ይህ የወርቅ የወጪ ንግድ ከ2004 ዓ.ም. በኋላ ቅናሽ በማሳየት በ2006 ዓ.ም. ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ወደ 456.2 በመቶ በመውረድ የወርቅ የወጪ ንግድ ቁልቁል ጉዞውን በመቀጠል በ2010 መጨረሻ ላይ 100.5 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ከሁሉም የወጪ ንግድ ምርቶች 2.86 ቢሊዮን ዶላር ሲመገዘብ፣ የወርቅ ድርሻ 10.1 በመቶ ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ውስጥ የወርቅ ድርሻ ወደ 7.2 በመቶ ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ የወርቅ የገቢ ድርሻ ከየዓመቱ እየቀነሰ በመምጣት በ2010 ዓ.ም. ብሶበት ወደ 3.5 በመቶ በመውረዱ የወርቅ የወጪ ንግድ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ አመላክቷል፡፡ የወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ በእጅጉ ከመቀነሱም በላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የምርት መጠንም እንደ ገቢው ሁሉ እየቀነሰ ከመምጣቱ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም በ2008 ዓ.ም. ለውጭ ገበያ ቀርቦ የነበረው የወርቅ መጠን 8.6 ሚሊዮን ግራም ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ወደ ስድስት ሚሊዮን ግራም ዝቅ ሲል፣ በ2010 ዓ.ም. ይብሱን ወደ 2.8 ሚሊዮን ግራም መውረዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከወርቅ የወጪ ንግድ 602.4 ሚሊዮን ዶላር በተገበኘት በ2004 ዓ.ም.  ወደ ውጭ የተላከው የወርቅ መጠን 112.2 ሚሊዮን ግራም ነበር፡፡

በ2010 ዓ.ም. ከወርቅ ባሻገር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ቅናሽ ከተመዘገበባቸው ምርቶች ውስጥ ቡና አንዱ ነበር፡፡ በብሔራዊ ባንክ ሪፖርት መሠረት፣ የዓምናው የቡና የወጪ ንግድ ገቢ በአምስት በመቶ ቀንሷል፡፡ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢም 839 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከቡና የተገኘው ገቢ 883.2 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከወርቅና ከቡና በተጨማሪ የሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ቅናሽ ካሳዩ ምርቶች ውስጥ የቁም ከብትና የጫት የወጪ ንግድ እንዲሁም የጥራጥሬ ምርቶች ይካተታሉ፡፡

በመረጃው መሠረት የጥራ ጥሬ የወጪ ንግድ በ3.7 በመቶ፣ የቁም እንስሳት 9.6 በመቶና ጫት 3.6 በመቶ ቅናሽ አስተናግደዋል፡፡ የምርቶቹ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መቀነስም በጠቅላላ የወጪ ንግድ ገቢ ላይ ተፅዕኖ በማሳረፍ ከካቻምናውም ያነሰ አፈጻጸም እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡

በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በ2.8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ የወጪ ንግድን ጨምሮ በ2010 ዓ.ም. የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 2.75 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህም በ2009 ዓ.ም. ከተገኘው 2.83 ቢሊዮን ዶላር አኳያ ያነሰ ነው፡፡

በወጪ ንግድ ነባር ከሆኑ ምርቶች አንፃር ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ  መሆን የጀመረው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያደገ መምጣቱም ታይቷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ይፋ እንዳደረገው፣ በ2008 ዓ.ም. 31.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከኤሌክትሪክ ኃይል ወጪ ንግድ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ገቢ እያደገ በመምጣት በ2010 ዓ.ም. ወደ 84.3 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከዘርፉ የተገኘው ገቢ 73.4 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ ምንዛሪ ገቢ በ15 በመቶ ማደጉን ያሳያል፡፡ ከጠቅላላው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢም ኤሌክትሪክ የሦስት በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡