Skip to main content
x
‹‹ዛሬ ነገ እየተባለ የጠፋው ጊዜ ከባድ ጉዳት አድርሷል›› የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

‹‹ዛሬ ነገ እየተባለ የጠፋው ጊዜ ከባድ ጉዳት አድርሷል›› የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

በተደረገለት የሰላም ጥሪ መሠረት አገር ቤት ገብቶ በሰላም ለመንቀሳቀስ ከኤርትራ የተመለሰው በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ‹‹ሸኔ›› የተባለው የኦነግ ቡድን፣ ከኤርትራ ይዞት ከመጣው ውጪ ሠራዊቱን ካምፕ ባለማስገባቱና ዛሬ ነገ እየተባለ በባከነው ጊዜ ምክንያት ከባድ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡ ዓርብ ጥር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና የዘመቻ መምርያ ኃላፊ ብርሃኑ ጁላ፣ በዚህ ቡድን ምክንያት በሕዝብ ላይ ጭምር ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

በሕግ መሠረት መታጠቅ ያለባቸው መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስና ሚሊሻ መሆናቸውን ያመለከቱት ጄኔራሉ ሌላ ኃይል ታጥቆ እንዲንቀሳቀስ እንደማይፈቀድ አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ከመንግሥት ጋር የገባውን ቃል አጥፎ ‹‹ዛሬ ነገ ሠራዊቴን ካምፕ አስገባለሁ›› እያለ ጊዜ በማጥፋት፣ አዳዲስ አባላትን በመመልመልና በማሠልጠን በሕዝቡ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንና ፀረ ሕዝብ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሸኔ›› የተባለው ቡድን የያዘው ተግባር ‹‹መንግሥትን ማታለል ይመስላል›› በማለት የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ ቡድኑ መንገድ እየዘጋ፣ የከባድ ተሽከርካሪዎችን ቁልፍ እየቀማ፣ መንገዶችን በተሽከርካሪ በመዝጋት፣ ኮት በማንጠፍ ገንዘብ በመሰብሰብ የእሱን አስተሳሰብ የማይቀበሉትን ደግሞ እያሰረና በመሬት ውስጥ እንደሚያሰቃይ ተናግረዋል፡፡

ከተያዙበት አምልጠው አዲስ አበባ የመጡ ሰዎች ሰውነት ላይ ጠባሳና የገመድ ክርክር እንዳለባቸውም ጭምር የገለጹት ጄኔራሉ፣ የክልሉን የዞንና የወረዳ መዋቅሮችን አፍርሷል ብለዋል፡፡ የጦር መሣሪያዎች ከግምጃ ቤትና ከሚሊሻዎች በመዝረፍ ቀደም ሲል የነበረውን የሕዝብ ስሜትና ተስፋ ያጨለመ እንደሆነም አክለዋል፡፡

ይሁንና አሁን መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከ15 ቀናት በፊት በተጀመረ ሥራ ሕግ መከላከያ እያስከበረ መሆኑን የገለጹት ጄኔራሉ ትጥቅ ማስፈታት መጀመሩን፣ መንገዶች መከፈታቸውንና የተዘጉ አካባቢዎችን ነፃ ማውጣት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

‹‹እሱ ያፈረሰውን መዋቅር እየገነባን፣ እሱ የገነባውን እያፈረስንና የዘረፈውን ትጥቅ እየመለስን አሁን ምዕራብ ኦሮሚያ ቀጣና ወደ ተሻለ ሰላም ተመልሷል፡፡ ሕዝቡም የንግድ እንቅስቃሴ ጀምሯል፤›› ሲሉም የተወሰደውን ዕርምጃ ገልጸዋል፡፡

የተወሰደው ዕርምጃ ሕዝቡ ድረሱልን በማለት ለመንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረት እንደሆነ፣ አሁን የታጠቁ ኃይሎች ከከተማ ወደ ጫካ መግባታቸውን፣ ብሎም ሠራዊቱ እየተከታተለ ትጥቅ የማስፈታትና ሕግ የማስከበር ሥራ እያከናወነ እንደሆነ አክለዋል፡፡

እንደ ጄኔራሉ ገለጻ ‹‹አባ ቶርቤ›› በሚባል መጠሪያ የሚንቀሳቀስ ኃይልም በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ከአሁን ቀደም ሕዝቡ ለሸኔ ቀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ እየገደለና እያስፈራራ ሕዝቡን ያሸብር እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ ዕርምጃ ሳይወስድ መቆየቱን የተናገሩት ጄኔራሉ፣ መዘግየቱ ምንም እንኳን ኪሳራ ቢኖረውም ውጤት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ሕዝብ መሀል ያለ ኃይልን በመደበኛ ውጊያ ማሸነፍ ስለማይቻልና ሕዝብን ማሳተፍ ስለሚያስፈልግ፣ ሕዝቡም የታጠቀው ኃይል ይሆነኛል አይሆነኝም የሚለውን መዝኖ የማይረባና ነፃነትን ሊያመጣለት የማይችል እንደሆነ አውቋል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ሆሮ ጉድሩ ውስጥ ዲንጎሮ የተባለ ወረዳ ከመንግሥት የተዘረፈን 130 መሣሪያዎችን ሕዝቡ ራሱ ማስመለስ እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሕዝቡ ከመከላከያ ጋር የተባበረው በደንብ ካያቸው፣ ከገመገማቸው፣ ምን ዓይነት ተፈጥሮ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑና ምን እንደሚፈልጉ ካወቀ በኋላ ነው፡፡ ፀረ ሰላም የሆነ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉና ሕዝብ እንደሚበድሉ፣ እነዚህ በኋላ ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከአሁኑ አሳይተዋል ብሎ ተፍቷቸዋል፤›› ሲሉም የሕዝቡን ተሳትፎ አመክንዮ አስረስተዋል፡፡  

ጄኔራሉ በመግለጫቸው በጎንደር የዘጠኝ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ክስተት በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የተለያዩ የተምታቱ መግለጫዎች በተለያዩ መንገዶች እየወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ በደንብ መጣራት አለበት ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ሁሉም ሳያጣራ ነው እየተናገረ ያለው የሚል አመለካከት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

በተለይ ጉዳዩን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና ለውጡን የሚያደናቅፉ ናቸው ብለው፣ ‹‹እኛ ይጣራ ብለን ወስነናል፡፡ የሚጣራው ከክልል፣ ከመከላከያም ከሌላ የሚመለከተው አካል ተጨምሮ ነው፡፡ እኔ ያለኝ መረጃ መከላከያ ሰው አልገደለም የሚል ነው፡፡ ሕዝብ ገደለ ነው እየተባለ ያለው፡፡ መከላከያ ሕዝብ አይገድልም፡፡ ገድሎም አያውቅም፤›› በማለት፣ በተለይ ከለውጡ በኋላ በከፍተኛ ጥንቃቄ በላቀ መንገድ ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ እየሠራ እንዳለ አክለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ዛላምበሳና ሽሬ ሕዝብ ሠራዊቱን መንገድ ላይ አስቁሞ አትሄዱም ሲል በውይይት መፈታቱን ገልጸው፣ የአካባቢው ወጣቶች አጥፍተናል በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል ያሉት ጄኔራሉ፣ በጎንደር ግን ለየት ያለ ሁኔታ እንደገጠማቸው አብራርተዋል፡፡

‹‹ሙሉ ጎንደር ሳይሆን ምዕራብ ጎንደር ቅማንት የሚባለው መተማና ጭልጋ ያለው ቀጣና ለብዙ ጊዜ የፀጥታ ችግር አለበት፡፡ ከቅማንት ማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ችግር ያለበት ነው፤›› ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ‹‹እዚያ አካባቢ ያለ ኅብረተሰብ የታጠቀ ነው፡፡ በዚያ ቀጣና የጎበዝ አለቆችም አሉ፡፡ የጎበዝ አለቆች አንዳንዴ ወደ ሚዲያ እየመጡ የሚፎክሩ፣ የየራሳቸው ተከታይ ያላቸው ናቸው፡፡ ሽፍቶችም አሉ፡፡ በርካታ ሽፍቶች አሉ ይታወቃል፡፡ አርማጨሆ በሽፍታ ይታወቃል፤›› በማለት የአካባቢውን ባህሪ ከገለጹ በኋላ፣ ግጭት የተከሰተው መከላከያ አጅቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ በርካታ ተሽከርካሪዎች ቆመው ሳለ በተቃጣበት ጥቃት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መከላከያ የአጀባ ግዳጅ ተሰጥቶት 30 የሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሽከርካሪዎችን በማጀብ ሲንቀሳቀስ ሸዲ የተባለ ቦታ ላይ በሕዝቡ ጥርጣሬ ተፈትሾ ካለፈ በኋላ፣ ቦቴ ይዘው ውኃ ለመቅዳት የሚሄዱ ወታደሮች ጥቃት ተፈጽሞባቸው ሁለቱ ሲቆስሉ በወሰዱት ራስን የመከላከል ዕርምጃ ምክንያት መከላከያ ሰው ገደለ ተብሎ በሌላ ቦታ በአጀብ ሊንቀሳቀስ የነበረው ኮንቮይ እንዲቆም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ተሽከርካሪዎቹ ሲቆሙ ዙሪያውን ገዥ መሬት ይዘው የነበሩ ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸውንና ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡

‹‹ሌላው ግን ጋራና ተራራ ይዞ ሕዝብና ሠራዊት ሳይለይ ተኩስ ከፈተ፡፡ በዚህ መሀል የተጎዱ ሰላማዊ ዜጎች አሉ፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ እኛም እናወግዛለን፡፡ ሕይወታቸው ባለፈ ሲቪል የኅብረተሰብ ክፍል በጣም ነው የሚሰማን፡፡ ምንም ያልታጠቀ ሰው መሞት የለበትም፤›› ሲሉም ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የመከላከያ ጥይት አንድም ሰው አልመታም ብለው መናገር እንደማይችሉ፣ አድፍጦ ያለውን ትቶ አጠገቡ ወዳለው ሲቪል ኅብረተሰብ የተኮሰ ወታደር ካለ ተጣርቶ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ እስከ ዛሬ የተወራው ወሬም አደገኛ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ መጠቀሚያም ጭምር እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡ እገሌ ገደለ፣ እገሌ አልገደለም የሚያስብል ምርመራ አልተደረገም ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጦር ሕግ እንደሚከተሉና በጎንደር በተለየ ሁኔታ ብሎ ደፍሮ መግለጫ ማውጣት ትክክል አይደለም በማለት፣ በአካባቢው በርካታ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውንና ለክልሉም ለወደፊት አደገኛ የሆነ ሁኔታ መኖሩን፣ በተጨማሪም ማን እንደሚያዝ እንደማይታወቅና የክልሉ ትዕዛዝ ተግባራዊ የሚሆንበት ቦታ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ይሁንና መከላከያ ተሳስቶ አድርጎ ከሆነ ይቅርታ ይጠይቃል፣ ካሳ ይከፍላል፤›› ሲሉም፣ ውጤቱ በመከላከያ ከግዳጅ ውጪ የተደረገ ጥፋት የሚሳይ ከሆነ ከላይ ያሉትን ደግመው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ብዙ ተኳሽ ስላለ መጣራት አለበት ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ዛላምበሳና ሽሬ አካባቢ የነበረን ጦር ለማንቀሳቀስ ሲጀመር የአካባቢው ኅብረተሰብ የጦርነት ሥጋት አለብን፣ ጎረቤት አገር ሊያጠቃን ይችላል፣ በማለት እንዳይወጣ መለመኑን የተናገሩት ጄኔራሉ፣ ሕፃናት ጭምር ከትምህርት ቤት ወጥተው መንገድ ላይ የጦርነት ሥጋት አለብን ማለታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ሕፃናት ይኼንን አስበው ያደርጋሉ ብለው እንደማያምኑና ከኋላ ሆነው የሚገፉ አካላት መኖራቸውን ገልጸው፣ ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ሲወሰን ምክንያቱ ምንድነው ብሎ የሚጠይቀው የፌዴራል መንግሥት ብቻ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ‹‹የትግራይ ሕዝብም ለምንድነው ሠራዊት የምታንቀሳቅሰው አይልም፤›› በማለት፣ ‹‹ሪፖርት እንዲደረግለት የሚፈልግ አካል አለ፡፡ ሪፖርት ግን አናደርግለትም፤›› ሲሉም አበክረው ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን  ሠራዊቱ ከሰሜን ግንባር የተንቀሳቀሰበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ አሁን ጦርነት የለም ብለዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር ጦርነት አይኖረንም የሚል መተማመን በመንግሥት በመፈጠሩ፣ እንዲሁም ሠራዊቱን ለቀጣይ ሥጋት ለማዘጋጀት ሪፎርም ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሪፖርት የሚፈልገው አካል ግን ብዙ ችግር እያስከተለ ነው፤›› ብለዋል፡፡