Skip to main content
x

የህዳሴ ግድቡን ተርባይኖች ለመግጠም የ78 ሚሊዮን ዶላር አዲስ ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የተጓተተውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራ በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ገጠማና ሙከራ፣ እንዲሁም የብረታ ብረት ሥራዎችን እንደተፈራረመ ታወቀ፡፡ ሐሙስ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በጀርመን ከሚገኘውና ቮይት ኃይድሮ ሻንጋይ ከተሰኘው የቻይና ኩባንያ ጋር የ77.9 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል፡፡

ለህዳሴ ግድቡ ስድስት የተርባይን ጀኔሬተሮች ግንባታና የተጓደሉ ዕቃዎችን ለማቅረብ፣ የተከላ፣ የፍተሻናሙከራራዎችን ቮይት ለማከናወን ተስማምቷል፡፡ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና የቮይትይድሮ ሻንጋይ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ታንግ ሹ በአዲስ አበባ እንደተፈራረሙ ከመሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉት፣ የተጓተተውን የግድቡን ግንባታ ወደ ቀድሞው ፍጥነት ለመመለስ ከኩባንያው ጋር የተደረገው ስምምነት ወሳኝነት አለው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሆሮ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ቮይት ኃይድሮ ሻንጋይ ከዚህ ቀደምም ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር ስምምነት በማድረግ የጄነሬተር ተርባይን ዕቃዎች አቅርቦት ላይ ተሳትፏል፡፡ ሜቴክ ሲያከናውናቸው የነበሩ ሥራዎች ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲዛወሩ በተወሰነው መሠረት፣ ውሉን በማሻሻል ስምምነት እንደተካሄደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በወዲያኛው ሳምንት ፓወር ቻይና ከተሰኘው ኩባንያ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ግንባታ ለማከናወን፣ የ125.6 ሚሊዮን ዶላር የግንባታ ስምምነት መፈራረሙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኮንትራት ስምምነቱ የተከናወነው የውኃ መቀበያ አሸንዳዎችንና የመቆጣጠሪያ በሮችን፣ እንዲሁም 11 ኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን የዲዛይን፣ የአቅርቦት፣ የገጠማ፣ የፍተሻና የሙከራ ሥራዎች ለማከናወን ከኩባንያው ጋር ስምምነት እንደተደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡

መሥሪያ ቤቱ በማኅበራዊ ትስስርና በድረ ገጹ ይፋ እንዳደረገው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የፓወር ቻይና ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቲያን ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡ ወሳኝ የተባሉት የግድቡ የኃይደሮሊክ የብረታ ብረት መዋቅር ሥራዎች እ.ኤ.አ. በጁን 2020 ይጠናቅቃሉ የተባለ ሲሆንአጠቃላይ የግድቡ ግንባታም እ.ኤ.አ. በ2022 ተጠናቆ መንግሥት እንደሚረከበው ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ጄኔራል ኤሌክትሪክና በፈረንሣይ አልስቶም አጋርነት (ጂኢ አልስቶም) ለአምስት የተርባይን ጄነሬተሮች ግንባታና ገጠማ ሥራዎችን ለማከናወን የ53.9 ሚሊዮን ዩሮ መፈራረሙን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከጂኢ አልስቶም ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ከአምስቱ ሁለቱ ተርባዮኖች እ.ኤ.አ. በ2020 እንደሚጠናቀቁና ለሚጠበቀው የቅደመ ኃይል ማመንጨት ሥራ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ በመንግሥት ዕቅድ መሠረት በቅድመ ማመንጨት የመጀመርያው ምዕራፍ የግንባታ ሥራ እስከ 750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ይመነጫል፡፡ ይሁንና እያንዳንዳቸው የሚተከሉት የኃይል ማመንጫ ተርባዮች 400 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖራቸዋል፡፡

በቅርቡ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በመሩት የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ ከአራት ዓመታት በፊት መጠናቀቅ የነበረበት የህዳሴው ግድብ ግንባታ አንድ ኪሎ ዋት በአምስት የአሜሪካ ሳንቲም ታስቦ ቢሰላ፣ ኢትዮጵያ ከኃይል ንግድ ታገኝ የነበረውን የ800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አሳጥቷታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እስካሁን ለግንባታው ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎም ግንባታው ከ35 በመቶ ያላነሱ ሥራዎችን በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ማጠናቀቅና ሥራ ማስጀመር ይጠበቅበታል፡፡

ለዚህ ሥራ ምን ያህል ተጨማሪ ገንዘብ ይጠይቃል የሚለው እየተጠና እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ እስካሁን ከተከናወነው የ65 በመቶ አጠቃላይ የግንባታ ሥራ ውስጥ በሜቴክ አማካይነት ሲከናወኑ የቆዩት የብረታ ብረትና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች በ25 በመቶ አፈጻጸም ላይ ሲገኙ፣ በሳኒሊ ኩባንያ የሚከናወነው የሲቪል ግንባታ ሥራ ግን ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁ መገለጹ ይታሳቃል፡፡