Skip to main content
x
‹‹ቻይና ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን መተው አትፈልግም›› አቶ ጌዲዮን ገሞራ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪ

‹‹ቻይና ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን መተው አትፈልግም›› አቶ ጌዲዮን ገሞራ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪ

አቶ ጌዲዮን ገሞራ ጃለታ በፖለቲካና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በተመራማሪነት ለስምንት ዓመታት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አገልግለዋል፡፡ በዚያ ቆይታቸው ወቅትም ከ80 ያላነሱ ጥናታዊ ጽሑፎችን በመሥራት በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ጭምር አሳትመዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎቻቸው ውስጥም በቻይናና በአፍሪካ ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ምርምሮቻቸው ይገኙበታል፡፡ በኦክስፋም ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት በኩልም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመምራት ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የራሳቸው ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ ኢንተርናሽናል ኮንሰልት የተሰኘ ኩባንያ በመመሥረት እየሠሩ የሚገኙት አቶ ጌዲዮን እንደ አፍሪካ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትና ሌሎችም የጥናትና የምርምር ሥራዎችን እንዲያከናወኑ ስምምነት ካደረጉባቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አቶ ጌዲዮን በኢትዮጵያና በቻይና ወቅታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ በመመሥረት ከሪፖርተር ጋር ያደረጉትን ቆይታ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡  

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያለዎት ምልከታ ምንድነው?

አቶ ጌዲዮን፡- እንደማስበው ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ለረዥም ዓመታት የተዘረጋ ፍላጎት አላት፡፡ ኢትዮጵያን ለአፍሪካና ለተቀረው ዓለም እንደ ማሳያ ሞዴል መጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም በርካታ ፕሮጀክቶችና ሌሎች ሥራዎችንም ሲተገብሩ የቆዩት ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዲፕሎማሲያቸው እንደ መግቢያ በር ስለሚመለከቱ፣ ኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን ጥለው ቆይተዋል፡፡ ከ108 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ለቻይና ትልቅ የገበያ መዳረሻ መሆኗም ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡ ቻይና በኢትዮጵያ ቀዳሚ የሆነችበትን የውጭ ኢንቨስትመንት ድርሻ ይዛለች፡፡ 60 በመቶ የቻይና ኢንቨስትመንትም በማኑፋቸክሪንግ ዘርፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2011 ያለውን ጊዜ ካየን፣ የቻይና ኩባንያዎች የ11.5 ቢሊዮን ዶላር የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በኢትዮጵያ መረከብ ችለው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ብቻ የ3.3 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶችን ተረክበዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሳያሳው ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ ፍላጎት እንዳላት ሲሆን፣ በቻይና እየቀነሰ የመጣው የግንባታ ገበያ በኢትዮጵያ ግን ትልቅ እንቅስቃሴ አለው፡፡

በቻይና የግንባታ ሥራዎችና ሌሎችም መስኮች እየተዳከሙ በመምጣታቸው፣ የቻይና መንግሥት ኩባንያዎቹ ወደ ሌሎች አገሮች በመሄድ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማድረግ የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበትን፣ ነገር ግን በበርካታ ቅድመ ሁኔታዎች የተሞላ ብድር በማቅረብ ጭምር ፕሮጅቶችን እየወሰዱ በግንባታው መስክ ሰፊ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የዜድቲኢ መምጣትና የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን መቆጣጠር በዚህ አግባብ ሊታይ ይችላል፡፡ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተውን ብድር ይዞ በመግባት ለዓመታት በሞኖፖል የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን በኢትዮጵያ መቆጣጠር የሚችልበትን ዕድል አግኝቷል፡፡ እኛም በኩባንያው የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎች ላይ ጥገኛ ሆነን የምንቆይባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ ቢታይም ቻይና ግን በአገሮች ውስጥ ጉዳይ እንደማትገባ ትናገራለች፡፡

እኔ እንደምረዳው ግን ቻይና በተለይም በፖለቲካው መስክ የርዕዮተ ዓለማዊ ጫና ታደርጋለች፡፡ መረዳት የሚገባን እ.ኤ.አ. ከ1949 ወዲህ ቻይና እየተመራች ያለችው በአንድ ፓርቲ ሥር ነው፡፡ እርግጥ ነው በዚህ ጊዜ ውስጥ 700 ሚሊዮን ቻይናውያንን ከድህነት ተላቀዋል፡፡ ኢኮኖሚያቸውንም በፈጣን ዕድገት ውስጥ እንዲጓዝ በማድረግ መዋቅራዊ ለውጥ አስመዝግበዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮም ከአፍሪካ አገሮች የፓርቲ ግንኙነት መሥርተዋል፡፡ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ከኢሕአዴግ እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) እና ከሌሎችም ጋር ግንኙነት መሥርቷል፡፡ ለአፍሪካ ተምሳሌት ሆነው መታየት ይፈልጋሉ፡፡ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ በኢሕአዴግ ላይ የርዕዮተ ዓለማዊ ተፅዕኖ ሳያሳድር አልቀረም፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቻይናን መከተል እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ማለት አንድ ፓርቲ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እስከቻለ ድረስ፣ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለውን መተማመኛ እንዳገኘ ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የአገሮቹ በፓርቲ ደረጃ የሚደረግ ግንኙነት በመንግሥታዊ ግንኙነታቸውም ውስጥ ዘልቆ ገብቷል እያሉ ነው?

አቶ ጌዲዮን፡- አዎን! ሁለቱ አገሮች ለረዥም ጊዜ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የቃኙት በዚህ መሠረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአዲሱ የኢሕአዴግ ትውልድ እየተመራች ነው፡፡ ይሁንና ኢሕአዴግ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ጠንካራ አጋር ነው ካለ በአሁኑ መንግሥት ውስጥ ይህ ግንኙነታቸው እንዴት ይታያል?

አቶ ጌዲዮን፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት አማካይነት በርካታ ለውጦች በተለይም የዴሞክራሲያዊ ለውጦች በአገሪቱ እየታዩ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ በሮች መከፈታቸው ትልቅ ቦታ እየተሰጠው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከቀድሞው የኢሕአዴግ አካሄድ አኳያ ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ፖሊሲ እያራመዱ ስለመሆናቸው የሚጠቁም ነው፡፡ እርግጥ እንዲህ ያለውን ለውጥ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅትም ታዝበን ነበር፡፡ ከምርጫው በኋላ የዴሞክራሲያዊ ጅምሩ ተገለበጠ እንጂ ነገሮች መታየት ጀምረው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዴሞክራሲ ክፍት የተደረጉ ጅምሮችን እያየን ነው፡፡ ከመጪው ምርጫ በኋላ ምን ሊኖር እንደሚችል እንጠብቃለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ ታዲያ አዲሱ የኢትዮጵያ አስተዳደር ግንኙነቱን ከቻይና ይልቅ ወደ ምዕራቡ ዓለም ያደላ እንዲሆን እያደረገ ነው ማለት ነው?

አቶ ጌዲዮን፡- በጥቅሉ ለመናገር ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ በቻይና ላይ ጥገኛ ሆና ቆይታለች፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ቻይና ለኢትዮጵያ ትልቅ ፖለቲካዊ ድጋፍ ሰጥታለች፡፡ ይህ ድጋፍም በፋይናንስ ዕገዛ ጭምር የሚገለጽ ነው፡፡ ከፍተኛ ብድር አቅርባለች፡፡ የባቡር ፕሮጀክቶች፣ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉና ሌሎችም በቻይና ሰፊ የፋይናንስ ድጋፍ የተገነቡ ናቸው፡፡ አንዳንድ ምሁራን ኢትዮጵያ የቻይና ሞዴል ናት ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ የነበረችውን ቻይና ትመስላለች ይላሉ፡፡ እኔ እንደምገምተው አዲሱ አመራር ኢትዮጵያ በቻይና ላይ የነበራትን ጥገኝነት መቀነስ ፈልጓል፡፡ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ጅምር ለውጦች ዙሪያ ከፍተኛ ፍላጎት አድሮበታል፡፡ የዓለም ባንክን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ መንግሥታት የፋይናንስ ድጋፍ ለመስጠት ቃል እየገቡ ነው፡፡ እንደማስበው አዲሱ አመራር ከምዕራቡ ዓለም ማግኘት የሚችለውን ድጋፍ ሁሉ ለማግኘት እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምዕራብ አገሮች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በገንዘብ ለማገዝ ዳተኞች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ቀንደኛ አጋር ብትሆንም ብዙም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት አልነበራትም፡፡ በአዲሱ አመራር ወቅት ከምዕራቡ ዓለም ምን የተለየ የኢኮኖሚ ድጋፍ ሊታሰብ ይችላል?

አቶ ጌዲዮን፡- ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት እንዳከተመ የምዕራቡ ዓለም አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ ዘንግቷት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ቻይና ዕድሉን በማግኘቷ ከአፍሪካ ጋር ግንኙነት ለመመሥረት የቻለችው፡፡ አፍሪካ ለምዕራባውያን ሸክም ነበረች፡፡ ይሁንና የቻይና መምጣት ምን ያህል እንደተሳሳቱ አሳይቷቸዋል፡፡ ወደ አፍሪካ መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1993 የጃፓን አፍሪካ ግንኙነት የተመሠረተበት የቲካድ ጉባዔን ተከትሎ፣ ቻይናም እ.ኤ.አ. በ2000 ፎካክ እየተባለ የሚጠራውን የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ማካሄድ ጀመረች፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ተመሳሳይ ስብሰባዎችን ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ በአፍሪካ ሊናቁ የማይችሉ ዕድሎች አሉ፡፡ የገበያ መዳረሻነቷና ያላት ሕዝብ ብዛት ማንም በቀላሉ አፍሪካን እንዲገምታት አያደርገውም፡፡ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴ አኳያ የምዕራብ መንግሥታት ለመምጣት ከዚህ የተሻለ ዕድል የላቸውም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሚመጡት ከፋይናንሳቸው ጭምር ነው ማለት እንችላለን?

አቶ ጌዲዮን፡- አዎን! ምዕራባውያን ብቻም ሳይሆኑ የዓረቡ ዓለምም እየመጣ ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲና ኳታር በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዳለመታደል ሆኖ የትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ለውጥ በአፍሪካ ቢታይም፣ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ግን በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት የላቸውም፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ከሁለት የማበልጡ ፕሮጀክቶችን ብቻ ነው በአፍሪካ ፋይናንስ ያደረገችው፡፡ ከዚህ አኳያ የምዕራቡ ዓለም በምን አግባብ የቻይናን የአፍሪካ የበላይነት ሊያስቀር ይችላል?

አቶ ጌዲዮን፡- ቻይናን ሊቀድሙም ሊቋቋሙም አይችሉም፡፡ በጣም ከባድ ነው፡፡ ቻይናን በምን አግባብ መቋቋም እንደሚችሉ ስለማያውቁ ሥጋት ውስጥ ናቸው፡፡ የቻይና የገንዘብ አቅም ከሚያስቡት በላይ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ቻይና ለአፍሪካ ልማት የሚውል የ60 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር፡፡ በ2017ም በተመሳሳይ የ60 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡ ለአፍሪካ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፣ ቻይና በራሷ ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ ፈርጣማ ሆናለች፡፡ ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› የተሰኘው የመሠረተ ልማት ውጥኗ ዓለምን ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ለማገናኘት ያሰበ ነው፡፡ ድሮ ‹‹መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያቀናሉ›› ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን መንገዶች ሁሉ ወደ ‹‹ቤጂንግ ያቀናሉ›› በሚለው ሳይተካ አይቀርም፡፡ የቻይና ኃያልነት ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር በአብዛኛው ጎኑ ወደ ምዕራቡ ዓለም ያደላና ለምዕራቡ አስተሳሰብ የተመቸ ይመስላል፡፡ በርካቶች ከዚህ በመነሳት የአመራሩ አካሄድ ቻይናን አላስደሰተም ይላሉ፡፡ የእርስዎ ሐሳብ ምንድነው?

አቶ ጌዲዮን፡- በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ስናየው ቻይና የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አቀንቃኝ አይደለችም፡፡ አንድ ዓይነት መንግሥት ነው በቻይና አገዛዝ ውስጥ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው፡፡ በቻይና ለታዩት አስገራሚ ለውጦች መንስዔው የቻይና ኮሙዩኒስት ሥርዓትና አገዛዙ ነው የሚጠቀሰው፡፡ የቻይና መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ግንዛቤ ከምዕራብ መንግሥታት ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ምዕራባውያን ለሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ቅድሚያ መሰጠት አለበት ይላሉ፡፡ ቻይና በበኩሏ ከኮንፊሺየስ አስትምህሮዎች ጀምሮ በምታምንበት ለኢኮኖሚ መብት ነው ቅድሚያ የምትሰጠው፡፡ የኢኮኖሚ መብቶች ከምርጫ ነፃነት በፊት ይቀመጣሉ፡፡ በመሆኑም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ቻይና ከምታራምደው አኳያ የርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነቶች ይታዩበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ወደፊት በሁለቱ አገሮች መካከል ሊፈጠር የሚችል የሳሳ አጋርነት ሊኖር እንደሚችል አስባለሁ፡፡ ይሁንና ቻይና ከየትኛውም ዓይነት መንግሥታዊ ሥሪት ጋር አብሮ የመሥራት ችግር የለባትም፡፡ በኢትዮጵያ ካላት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት አኳያ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው አካል የትኛውም ዓይነት ቢሆን አብራ ትጓዛለች፡፡  የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለሚያስፈልጋት ልማት በቻይና ላይ ጥገኛ ሆና መቆየቷ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ግን ኢትዮጵያን በፖለቲካ ገበያ ውስጥ ባለው አካሄድ መሠረት በቻይና የተፅዕኖና የፖሊሲ ጫና ውስጥ ተጋላጭ ሊያደርጋት የሚችል ሁኔታ ይፈጠር ይሆን?

አቶ ጌዲዮን፡- ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያው ተፅዕኖ ተጠቂ ልትሆን የምትችልበት አግባብ ቢኖርም፣ ይህ ግን ግልጽ በሆነ መንገድ ሊመጣባት የሚችል አይመስለኝም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቻይና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የተጀመሩት ለውጦች ብዙም አላስደሰቷትም ማለት ይቻላል?

አቶ ጌዲዮን፡- የቻይናን የፖለቲካ ሥሪት ማጤን ይኖርብናል፡፡ በአንድ ፓርቲ አማካይነት ለዓመታት ስትተዳደር የኖረች አገር ነች፡፡ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ነው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አገሪቱን የመራው፡፡ እርግጥ ጥቂት ፓርቲዎች በቻይና አሉ፡፡ ገዥውን ፓርቲ ለመገዳደር የሚያበቃ አቅም ግን የላቸውም፡፡ ለበርካታ ጊዜያት ቻይናን ጎብኝቻለሁ፡፡ ሕዝቡ መንግሥትን የሚቃረን ነገር መናገር ያስፈራዋል፡፡ አብዛኛው ሰው ፖለቲካ ከመናገር ይቆጠባል፡፡ የቻይና ባለሥልጣናት እነሱ የሚተዳደሩበትን ዓይነት ሥርዓት አጋር በሚሏቸው መንግሥታትም ቢተገበር የሚመርጡ ናቸው፡፡ የቻይና መንግሥት በአፍሪካ ተመሳሳይ አቋምና ፖሊሲ የሚያራምዱ አገሮችን ማየት ይፈልጋል፡፡ የምዕራብ መንግሥታት ለዓመታት ቻይና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድታራምድ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ ይሁንና አልተሳካላቸውም፡፡ እንደማስበው ቻይናውያን በኢትዮጵያ እየሆነ ባለው ነገር ብዙም ደስተኞች አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ አካሄድ እነሱ ከሚከተሉት መንግሥታዊ ሥርዓት ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ቢጤያቸውን ቢያገኙ ግን አይጠሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ጎብኝተዋል፡፡ በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝትም የቻይና ትኩረት በሁለቱ አገሮች መካከል ‹‹የጋራ ፖለቲካዊ መተማመን›› እንዲፈጠር ማድረግ የሚለው አንደኛው አጀንዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ምንን ያመለክታል?

አቶ ጌዲዮን፡- በኢትዮጵያ የሚታየው ሪፎርም ከቻይና ጋር የነበረው ፖለቲካዊ ግንኙነት ላይ መለያየትን የሚያመላክት ቢሆንም፣ ቻይና ኢትዮጵያን ለምዕራባውያን መተው አትፈልግም፡፡ ከአዲሱ አስተዳደር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማደስ እንደሚፈልጉና በአጋርነት ለመቀጠል እንደሚያስቡ ለማረጋገጥ ያለመ ጉብኝት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ስላላቸው ያንን በቀላሉ ማጣት አይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቻይና አፍሪካ ፎረም አስተናግዳ ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያ ቻይና ሦስተኛውን ፎረም በቤጂንግ ስታዘጋጅ 48 የአፍሪካ መሪዎች ታድመው ነበር፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ምን ያህል ለቻይና ወሳኝ አገር መሆኗን ያስመሰከረ ውጤት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በሌላውም አካባቢ ያላት ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቅም ሌላው ቻይና አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንዳታቋርጥ የሚያስገድዳት ጉዳይ ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነት ውስጥ አሁንም ፍላጎቷን እንደምታጠናክር የሚያረጋግጥ፣ ብሎም የአዲሱ አመራር ፍላጎቶችን ለማወቅ ታስቦም ሊሆን ይችላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በቻይናና በአሜሪካ መካከል ባሉ አለመግባባቶች በተለይም በንግድ ጦርነት ሳቢያ ተጎጂ ሆናለች ማለት ይቻላል? በምሥራቅ አፍሪካ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር በመሆኗ ቻይና ይህንን አጋጣሚ እንደ ምክንያት በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር የምትችልበት ዕድል ይኖራታል?

አቶ ጌዲዮን፡- በእኔ ምልከታ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በጥቅሉ ከንግድ ጦርነቱ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አጋጣሚው ለእነዚህ አገሮች የግብርና ምርቶች የበለጠ የገበያ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ ይቀርቡ የነበሩ እንዲህ ያሉ ሸቀጦች በታሪፍ ምክንያት ስለተቋረጡና ሁለቱ አገሮች አንዱ የአንዱን ምርት ከመግዛት እየታቀቡ በመሆኑ፣ ታዳጊ አገሮች የገበያ አጋጣሚውን ያገኛሉ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያም ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ችግሩ ግን ኢትዮጵያም ሆነች የተቀረው አፍሪካ ከወጪ ንግድ ይልቅ ገቢ ንግድ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ አገሮቹ ወደ ውጭ የሚልኩት ብዙ ምርት የላቸውም፡፡ አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚያስችል የምርት ሒደትና የእሴት ጭማሪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ያላትን 13.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዕዳ ለማስመለስ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ አትራፊ ኩባንያዎችን ልትወርስ የምትችልበት ሥጋት ይታይዎታል?

አቶ ጌዲዮን፡- ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡ ቻይና ‹አንጎላ ሞድ› እየተባለ የሚጠራ አካሄድ አላት፡፡ አንጎላ ሞድ የተሰኘው አሠራር ዕውቅና ያጋገኘው የአንጎላ መንግሥት ከቻይና ለተበደረው ገንዘብ የነዳጅ ሀብቱን ማስያዣ ይሆነው ዘንድ በማዋሉና ብድሩን በወቅቱ መክፈል ባለመቻሉ ምክንያት፣ የቻይና መንግሥት ብድሩ እስኪከፈለው የነዳጅ ኩባንያዎችን መውረሱ አንጎላ ሞድ የሚባለውን ስያሜ አስገኝቷል፡፡ በቅርቡ በዛምቢያም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ የዛምቢያ ኢነርጂ አምራች ኩባንያ በቻይና ተወርሷል፡፡ ቻይናውያን አትራፊ የመሰላቸውን ዘርፍ ወይም ተቋም ለዕዳ ማስያዣነት በማዋል ገንዘባቸውን ያስመልሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የቻይናን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ኩባንያ ነው፡፡ ባለዕዳ እስከሆንክ ድረስ የምትባለውን ለመፈጸም ትገደዳለህ፡፡ 

ሪፖርተር፡- መንግሥት በከፍተኛ ወለድ የሚገኙ ብድሮችን ለማቆም ተገዷል፡፡ አቅሙ ስለሌለው ብቻም ሳይሆን፣ እንደ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅትም ባቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ ጫና ነው መንግሥት በአብዛኛው ከቻይና ይገኙ የነበሩትን የአጭር ጊዜ ከፍተኛ ወለድ ብድሮችን ለማቆም የተገደደው፡፡ ይህ ለቻይና በኢትዮጵያ ሁኔታ መከፋት ሌላው ምክንያት ነው ሊባል ይችላል?

አቶ ጌዲዮን፡- ቻይናውያን በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት እንዳለ ይገነዘባሉ፡፡ ቢሮክራሲው በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ይህም እምነት እንዲጥሉበት ያደርጋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለበትን ዕዳ መክፈል እንደሚችል ያውቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ የወጪ ንግዱ በየጊዜው እየወረደ በመጣበት ወቅት፣ በየሦስት ወራት ዕዳውን መክፈል ለዚህ መንግሥት ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆንበት መገንዘብ አለብን፡፡ ይህ ለሁለቱም መንግሥታት አሳሳቢ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በኩል በቻይና ላይ የመጣው ተቀናቃኝነት ለአዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ስትራቴጂካዊ ነው፡፡ እነሱ ለመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወደ ምዕራቡም ወደ ምሥራቁም እንዲያተኩር ተደርጎ የተቀረፀ ነው፡፡ ለዓመታት ወደ ቻይና እንዲያይ ያስገደደው ከምዕራብ አገሮች የሚያገኘው ድጋፍ በጤና፣ በትምህርት፣ በፀረ ሽብርና በመሳሰለው ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኖ በመቆየቱ ነው፡፡ በአንፃሩ ከቻይና እንደ መንገድ፣ ባቡርና ሌሎችም ትልልቅ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ በማግኘቱ ነው ወደ ቻይና ያደላ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሲተገበር የቆየው፡፡ ከጃፓንና ከህንድ ጋር የዲፕሎማሲው ግንኙነት እንዲጠናከር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ እንደማስበው በአዲሱ አስተዳደር ወደ አንድ ወገን ያዘነበለውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሚዛን ወደ ማስተካከሉ ሥራ የተገባ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በምዕራቡ መንግሥታት ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ፖለቲካዊ ለውጦች ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ከቻይና በኩል ብዙም ይፋ የሆነ መግለጫ ሲሰጥበት አልሰማንም፡፡ ይህ ምን ሊያስከትል ይችላል?

አቶ ጌዲዮን፡- እንዳልኩት ከቻይና መንግሥታዊ ባህሪይ ውጪ የሆነ መንግሥት በኢትዮጵያ እየመጣ በመሆኑ፣ ለዚህ መንግሥት በይፋ ዕውቅና እንዲሰጡት አይጠበቅም፡፡ ቻይናን ሞዴል ያደረገ የልማት አካሄድ ነበር በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየው፡፡ የአፍሪካ መንግሥታት የቻይናን የልማት ሞዴል ለመከተል የፈለጉት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥታዊ ባህሪ የቱም ዓይነት ቢሆን የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት ስለማይቸግር ነው፡፡ አምባገነን መንግሥታት ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ አሳይተዋል፡፡ ደቡብ ኮሪያ ለዚህ ተጠቃሽ ነች፡፡ ነገር ግን በዓረብ አብዮት ወቅት ያየነውና በእኛም አገር የታዘብነው፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችም እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ አስፈላጊ መሆናቸውን ነው፡፡ ፍትሐዊነትና የሰብዓዊ መብቶች መከበር የግድ አስፈላጊዎች ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሹማምንት በቻይና ሕገወጥ ሀብት አካብተዋል እየተባሉ ይታማሉ፡፡ ቻይና በዚህ ተግባር እጇ አለበት በሚለው ይስማማሉ?

አቶ ጌዲዮን፡- ቻይና ብቻ አይደለችም ከአፍሪካ የሚሸሸውን ገንዘብ የምታስተናግደው፡፡ በርካታ የምዕራብ አገሮችም በሕገወጥ መንገድ ለሚጎርፈው ገንዘብ መዳረሻዎች ናቸው፡፡ ቻይናም ሆነች የምዕራብ አገሮች እንዲህ ያለው ጉዳይ ላይ ዝምታን ይመርጣሉ፡፡ ወደ አገሮቹ የሚጋዘው ገንዘብ አቅማቸውን ስለሚያፈረጥመው ከመቀበል አይቦዝኑም፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ የገንዘብ ሀብታቸውን ከሚያጡ አገሮች ተርታ መመደቧ የታወቀ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ ሰፊ የሙስና ወንጀል በኢትዮጵያ ተስፋፍቶ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በሕገወጥ መንገድ የሚሸሸው ገንዘብ ብዙም አያስገርምም፡፡  

ሪፖርተር፡- የቻይና በአፍሪካ ቆይታ ወደ ወታደራዊ ፍላጎት ተሸጋግሮ በምሥራቅ አፍሪካ የባህር ኃይል መሥርታለች፡፡ አንዳንዶች አፍሪካን በፖለቲካ የመቀራመት አካል ሲያደርጉት፣ ቻይና ግን ለኢኮኖሚ ፍላጎቶቿ ጥበቃና ከለላ ለመስጠት ያደረገችው እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ እውነታው የቱ ነው?

አቶ ጌዲዮን፡- ቻይና ወደ አፍሪካ የመጣችው ዘግይታ ነው፡፡ ከቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም በኋላ በቻይናና በአፍሪካ መካከል ሁሉን አቀፍ የአጋርነት ግንኙነቱ እያደገ መጥቷል፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና የንግድ ግንኙነት ላይ ተመሥርቶ የተዘረጋው ግንኙነት በርካታ ቻይናውያንንና ኩባንያዎቻቸውን ወደ አፍሪካ በገፍ እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡ በአፍሪካ ካላቸው መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ፍላጎትና አቅም አኳያ በአፍሪካ በሚታየው የሰላም ሁኔታ ሥጋት ቢገባቸው ምክንያታዊ ነው፡፡ እየተስፋፋ በመጣው የንግድና የኢኮኖሚ አቅማቸው ሳቢያ እንደማስበው ወታደራዊ ኃይላቸውንም ማምጣታቸው ሊያስማማ የሚችል ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቻይናውያን በሌሎች አገር ውስጣዊ ጉዳይ አንገባም ይሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ እየተለወጠ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ የምዕራብ አገሮች በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ በተለይም እንደ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ኤርትራ ባሉት አገሮች ውስጥ ሰፊ ወታደራዊ ይዞታዎችን አደራጅተዋል፡፡

አቶ ጌዲዮን፡- ቀይ ባህር በዓለም በጣም ሥራ የሚበዛበት የመርከቦች መተላለፊያ ክፍል ነው፡፡ የንግድ መስመሮቹ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መርከቦቹም ጥበቃ ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ወታደራዊ ይዞታዎቹ ለደኅንነት ከለላ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በየቀኑ ወደ ቻይና የሚደረጉ ጉዞዎች በርካታ ናቸው፡፡ እንደማስበው ይህ የኢኮኖሚ አቅሟ ነው ቻይናን በአፍሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች እንዲኖሯት ያስገደዳት፡፡