Skip to main content
x
የቀድሞ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ወደ ግል ተቋማት በማቅናት ባልደረቦቻቸውን ተቀላቅለዋል

የቀድሞ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ወደ ግል ተቋማት በማቅናት ባልደረቦቻቸውን ተቀላቅለዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓይብ አህመድ (ዶ/ር) በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ላይ ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች መካከል፣ ባንኮችን ይመሩ የነበሩ የሥራ ኃላፊዎችን በአዲስ የመተካትና የማሸጋሸግ ሥራ አንዱ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥንና ምክትላቸውን በሌሎች እንዲተኩ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንቶችም በአዳዲስ አመራሮች መተካታቸውም ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ባንክ፣ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ አዳዲስ አመራሮች እንዲመደቡላቸው ከማድረግ ባሻገር፣ ለሦስቱም ባንኮች አዳዲስ የቦርድ ሰብሳቢዎችም ተሹመውላቸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹምሽርና ምደባ መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ በቃሉ ከንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው ተነስተው በብሔራዊ ባንክ ቁልፍ የሆነውን የምክትል ገዥነትና የማክሮ ኢኮኖሚ ኃላፊነት ቦታ እንዲረከቡ ተሹመው ነበር፡፡

ይሁንና አቶ በቃሉ አዲሱን ኃላፊነት ለመቀበል ሲያንገራግሩ መቆየታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ግን አቶ በቃሉ የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ቢሮ ተረክበው በአዲሱ ሹመታቸው መሠረት ሥራ ቢጀምሩም፣ በባንኩ የነበራቸው ቆይታ ግን ብዙም አልዘለቀም፡፡ አራት ወራት ሳይሞላቸው በምክትል ገዥነት የተሾሙበትን ኃላፊነት በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃም አቶ በቃሉ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማስታወቂያ በባንኩ የማስታወቂያ ሰሌዳ ተነበበ፡፡ አቶ በቃሉ ወትሮም እያንገራገሩ የተቀበሉትን ኃላፊነት ‹‹ልቀቁኝ›› ማለታቸው ለምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጨረ ሲሆን፣ የወደፊት ማረፊያቸውን በመገመት ሲሰነዘሩ የቆዩ መላ ምቶች እውነታውን በማረጋገጥ የግል ባንክ ለመምራት ማቅናታቸውን አመላክተዋል፡፡

አቶ በቃሉ ከንግድ ባንክ ከለቀቁ በኋላ ከአቢሲኒያ ባንክ የቦርድ አመራሮች ጋር በመነጋገር አቢሲኒያ ባንክን እንዲቀላቀሉ በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት፣ ሲደራደሩ እንደቆዩና ለብሔራዊ ባንክ መሾማቸውም ዱብ ዕዳ ሆኖባቸው ኃላፊነቱን ለመቀበል አንገራግረዋል የሚል አስተያየትም ተደምጧል፡፡

እንደተባለውም አቶ በቃሉ ከብሔራዊ ባንክ ከለቀቁ ሁለት ወራት በኋላ፣ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል፡፡ ከቀድሞው የንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት ቢሯቸው በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአቢሲኒያ ዋና መሥሪያ ቤት ከማክሰኞ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲሱ ቢሯቸው ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ አቶ በቃሉ አዲሱን ቢሯቸው እስከተረከቡበት ዕለት ድረስ ግን ላለፉት ሦስት ወራት በነበሩበት የብሔራዊ ባንክ የምክትል ገዥነት ቦታቸው የተተካ ተሿሚ የለም፡፡

በአገሪቱን ትልቁንና መንግሥታዊውን ባንክ በፕሬዚዳንትነትና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ለ20 ዓመታት የመሩት አቶ በቃሉ፣ ከባንኩ ባሻገር ሁሉንም የአገሪቱ ባንኮች በአባልነት ያካተተውን የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ የግል ባንኮች ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ሲጀምሩ፣ ንግድ ባንክን በመልቀቅ ወደ ግል ባንኮች ካቀኑት ውስጥ አቶ በቃሉ የመጀመርያው ባይሆኑም ለእሳቸው መሾም፣ ተሰናባቹ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት እንዳደረጉት የተነገረው ድጋፍ ግን የተለየ ሆኖ ይገኛል፡፡ በአቶ በቃሉ የተተኩት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ሲለቁ፣ ተከታያቸው እሳቸው እንደሆኑና ይህንንም ለቦርዱ ጭምር በማሳወቅ ተፈጻሚ እንዲሆን ማስቻላቸው ያልተለመደ ነበር፡፡

አቶ ሙሉጌታ አቶ በቃሉን የባንኩ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ለማድረግ ሲያግባቡ መቆየታቸው የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይህንን ለማድረግ የተገፋበትና እሳቸው የፕሬዚዳንትነት ቦታውን ለመልቀቅ የሻቱበትን ምክንያት ግን ግልጽ አላደረጉም፡፡ ነገር ግን አቶ በቃሉ ኃላፊነቱን በመረከባቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸውን ለአቶ በቃሉ አስረክበዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ እስካለፈው ሳምንት መጀመርያ ድረስ በአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ለአራት ዓመት ተኩል ሲያገልግሉ ቆይተዋል፡፡ በጠቅላላው በአቢሲኒያ ባንክ የዘጠኝ ዓመታት ቆይታ እንደነበራቸውና፣ ባንኩን የተቀላቀሉትም የብድር አስተዳደር ዳይሬክተር በመሆን ነበር፡፡ በኋላም ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ከአራት ዓመት ተኩል በፊት ሲሆን፣ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት የሆኑትም የባንኩን የቀድሞ ፕሬዚዳንት የአቶ አዲሱ ሀባን በመተካት ነበር፡፡ አቶ አዲሱ አቢሲኒያን ከለቀቁ በኋላ የደቡብ ግሎባል ባንክን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ተሰናባቹ አቶ ሙሉጌታ በባንክ ኢንዱስትሪ ከ26 ዓመታት በላይ የሠሩ ሲሆን፣ የአቢሲኒያ ባንክን ከመቀላቀላቸው በፊት በንግድ ባንክ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው እስከ ብድር አስተዳደር ዳይሬክተርነት ደርሰው ነበር፡፡

 በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ልማት ባንክና ብሔራዊ ባንክ የመጡ ስለመሆናቸው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለአብነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ለይኩን ብርሃኑ ከገዥነታቸው ከለቀቁ በኋላ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከአቶ በቃሉ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አቢ ንግድ ባንክን ሲለቁ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱም የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት መሆናቸው በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ 20ኛ ዓመቱን የተሻገረ ሲሆን፣ በዚህ ዕድሜ ውስጥ ስድስት ፕሬዚዳንቶች ሲያፈራርቅ፣ አቶ በቃሉ ሰባተኛው ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አቢ ሳኖ በአቶ በቃሉ ሲተኩ፣ የአቶ አቢ ሳኖ ማረፊያ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አቶ አቢ አሁንም ድረስ የባንኩ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡