Skip to main content
x

ንግድ ባንክ በሦስት ወራት ውስጥ ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ

የተበላሸ ብድሩ ወደ 3.4 በመቶ አድጓል

ባለፈው ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የቀነሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2011 ሩብ ዓመት ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡ በሩብ ዓመቱ የተገኘው የትርፍ መጠን በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ900 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ባንኩ የ2011 ሩብ ዓመት እንቅስቃሴውን በተመለከተ ይፋ እንዳደረገው፣ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ ወደ 457 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ በሩብ ዓመቱ ብቻ ስምንት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ አሰባስቧል፡፡ በዚህ ዓመት ሦስት ወራት የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በ2010 የመጀመርያው ሩብ ዓመት የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 17.3 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

በሌላ በኩል የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን እያደገ በመምጣት ወደ 3.4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የተበላሸ የብድር መጠኑ በየጊዜው እየጨመረ እንደመጣም የባንኩ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የንግድ ባንክ የተበላሸ ብድር መጠን 2.5 በመቶ ነበር፡፡ በ2009 ወደ 2.8 በመቶ ከፍ ሲል፣ ዓምና ግን ወደ 3.4 በመቶ አሻቅቧል፡፡ ባንኩ ከሚያበድረው ከፍተኛ ገንዘብ አንፃር አጠራጣሪው ወይም የተበላሻው ብድር ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ባንኩ የተበላሸ የብድር መጠኑ እየጨመረ መምጣቱ የአጠራጣሪ ብድሩ መጠን መጨመሩን እያመላከተ ሲሆን፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ትርፍ መጠን ዕድገት መውረድ ከዚሁ ጋር የተያዘ ስለመሆኑ የሚገልጹ አሉ፡፡

እንደ ባንኩ መረጃ ባንኩ በ2010 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከ2009 ዓ.ም. አኳያ ከአራት ቢሊዮን ብር ያላነሰ ቅናሽ በማሳየት 10.32 ቢሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ በ2009 ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 14.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2010 የተመዘገበው ትርፍ በ2009 ከተገኘው ብቻም ሳይሆን፣ በ2008 ዓ.ም. ከተገኘውም ትርፍ አኳያ ያነሰ ነበር፡፡ በ2008 ከታክስ በፊት የተመዘገበው ትርፍ 13.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በተመሳሳይም በ2007 ዓ.ም. የተገኘው ትርፍም ቢሆን 11.7 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ ዓመት ከቀዳሚዎቹ ሦስት ዓመታትም ያነሰ ሆኖ መገኘቱ የባንኩ የተበላሸ ብድር ከፍ ማለቱ ጋር የተያዘ ነው፡፡

ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ ያሽቆለቆለበት ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ ባያስቀምጥም፣ ከብድር አመላለስ አኳያ የገጠመው ችግር ዋናው ምክንያት እንደሆነ ሲገለጽ ይመደጣል፡፡ ለዚህም ሰበብ የሚደረገው ለአብዛኞቹ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በገፍ ሲያበድር የነበረ ከመሆኑ ጋር በመያያዝ ነው፡፡ በዚህ ዓመት መጀመርያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ፣ ባንኩ ከደምበኞቹ ያስመለሰው ብድር መጠን 13.6 ቢሊዮን ብር ነው፡  በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ያስመለሰው ብድር 14.7 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት የነበረው አፈጻጸም የተሻለ እንደነበር ያመለክታል፡፡

በ2011 የመጀመርያው ሩብ ዓመት የሰጠው የብድር መጠንም በ2010 የመጀመርያው ሩብ ዓመት ከሰጠው ያነሰ ሆኗል፡፡ በዘንድሮው ሩብ ዓመት የሰጠው ብድር 14.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት 14.6 ቢሊዮን ብር አበድሮ ነበር፡፡

በአንፃሩ በ2007 ዓ.ም. 91.9 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ሰጥቷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. እንዲሁ የሰጠው አዲስ ብድር 94.5 ቢሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ የዓምና የብድር መጠንም 100.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር ከባንኩ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከባንኩ አኃዛዊ መረጃ አኳያ፣ የ2010 ዓ.ም. የባንኩ ትርፍ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ሊያንስ የቻለው፣ ከብድር አመላለሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ የ2010 ዓ.ም. ወጪው ከቀደሙት ዓመታት ይልቅ በከፍተኛ መጠን ከመጨመሩ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ይገለጻል፡፡ በ2008 ዓ.ም. አጠቃላይ ገቢው 27.2 ቢሊዮን ብር በነበረበት ወቅት ጠቅላላው ወጪው 13.4 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ነገር ግን ከታክስ በፊት 13.7 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ አስችሎት ነበር፡፡

በተመሳሳይ በ2009 ዓ.ም. የባንኩ ዓመታዊ ገቢ 31.9 ቢሊዮን ብር ሊደርስ በመቻሉና ዓመታዊ ጠቅላላ ወጪውም 17.3 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ ከታክስ በፊት 14.6 ቢሊዮን ብር ማትረፍ አስችሎታል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የባንኩ ዓመታዊ የገቢ መጠን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ውጤት የታየበት ሆኖለታል፡፡ በ2010 መጨረሻ ባንኩ ያገኘው ገቢ 37.24 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በአንፃሩ ወጪውም በዚያኑ ያህል ከፍተኛ የሚባል ሆኗል፡፡ በዚሁ ዓመት ባንኩ ዓመታዊ ጠቅላላ ወጪ 26.32 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የወጪው ዕድገት ለ2010 ዓመት የባንኩ የትርፍ መጠን ማዘቅዘቅ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡

በጥቅሉ በ2010 የሒሳብ ዓመት የባንኩ አፈጻጸም ከቀደመው ጊዜ በተለየ ያነሰ ቢሆንም በተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ግን አሁንም ዕድገት የታየበት ሆኗል፡፡ ባንኩ በ2010 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 451.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2009 መጨረሻ ላይ ባንኩ የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ 364.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2007 ደግሞ 288 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት በአዲስ ቦርድ አባላትና የሥራ ኃላፊዎች እየሠራ ሲሆን፣ የ2011 የመጀመርያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 578 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ሀብት መጠን 565 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. ግን 485.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. 384.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡  ባንኩ የተቀማጭና የሀብት መጠንም ሰፊ ዕድገት የተመዘገበበት እንደነበር ያመለክታል፡፡ ይሁንና የትርፍ ምጣኔውን ማሽቆልቆልና የተበላሸ የብድር መጠኑ ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመምጣቱ፣ ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ግድ የሚለው ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡

ከተመላሸ ብድር አኳያ አብዛኞቹ ባንኮች ያስመዘገቡት ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ጣርያ በታች ነው፡፡ ይሁንና ከባንኮቹ ሁሉ ከፍተኛ የተበላሸ ብድር ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም. የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን 40 በመቶ ደርሷል፡፡