Skip to main content
x
‹‹የተማሪዎች ምገባ በመንግሥት በጀት መካተቱ ትልቅ ስኬት ነው›› ወይዘሪት ሜቲ ታምራት፣ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሕፃናት ጤናና ምግብ ባለሙያ

‹‹የተማሪዎች ምገባ በመንግሥት በጀት መካተቱ ትልቅ ስኬት ነው›› ወይዘሪት ሜቲ ታምራት፣ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሕፃናት ጤናና ምግብ ባለሙያ

በአስከፊ ድህነት ውስጥ ከሚገኙ የዓለም አገሮች ተርታ በግንባር ቀደምነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ብዙ አሰቃቂ የድህነት ታሪኮችም የሚሰማባት ምድር ነች፡፡ የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት አሁንም ድረስ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የማይታሰብ ሆኖ 40 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የቀነጨረ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ማኅበራዊ ችግር ሕፃናት ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡ ጾማቸውን ክፍል የሚገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እስኪያቅታቸው ይራባሉ፡፡ ራሳቸውን ስተው የሚዘረሩ፣ በዚህ ምክንያት ከክፍል የሚቀሩ ከነአካቴው ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ይህንን ሥር የሰደደ ችግር በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀርፍ ተስፋ የተጣለበት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የተጀመረው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ታስቦ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች በመተግበር ላይ የሚገኘውን የምገባ ፕሮግራም መንግሥት ወጥ በሆነ መንገድ ሊያስኬደው ኃላፊነቱን ወስዶ መሥራትም ጀምሯል፡፡ አጠቃላይ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሕፃናት ጤናና ምገባ ባለሙያዋን ወይዘሪት ሜቲ ታምራትን ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ጅምሩ ምን ይመስላል?

ወይዘሪት ሜቲ፡- የትምህርት ቤት ምግባ ሰፊ ፕሮግራም ነው፡፡ ችግረኛ ተማሪዎችን ለመርዳት በትምህርት ቤት ማኅበረሰቡና በተለያዩ ተቋማት ለዓመታት ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በባለሀብቶች፣ በመንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በሃይማኖት ድርጅቶች አማካይነት ፕሮግራሙ ይተገበር ነበር፡፡ ነገር ግን የሚደረገው ድጋፍ ፕሮግራሙ ወጥ በሆነ ሁኔታና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲከናወን የሚያደርገው አልነበረም፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ ሥራ ጎልቶ የወጣው ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ በ2007 ዓ.ም. የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበርን አቋቁመው መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ነው፡፡ በወቅቱ አሥሩም ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ነበር መሥራት የጀመሩት፡፡ ከተለያዩ አገር በቀል ድርጅቶችና ግለሰቦች ገንዘብ በማሰባሰብም ለተማሪዎች ምግብ የማቅረብ ሥራውን ያከናውናሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና ሴቶችና ሕፃናት ቢሮው በዋናነት አብረው ይሠሩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ፕሮግራሙ በቀጥታ እነሱን የሚመለከት ነው፡፡ መንግሥት ድጋፍ የሚሹ ሕፃናትን የማገዝ ኃላፊነትም አለበት፡፡ በተለይ በእኛ ቢሮ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በጋራ ሲሠራ ነበር፡፡ ውስን ኮታ ስለነበር ተማሪዎችን በመመልመል፣ ሴቶችና ሕፃናት ደግሞ ምግብ የሚያበስሉ እናቶችን በጋራ የመለየት ሥራ ሠርተናል፡፡ ወ/ሮ ሮማን የትምህርት ምገባ ፕሮግራም ጎልቶ እንዲወጣ፣ በመንግሥትና በሌሎች አጋዥ አካላት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ትልቁን ሥራ ሠርተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮራምን በተመለከተ ዘንድሮ ምን የተለየ ነገር አለ?

ወይዘሪት ሜቲ፡- በዘንድሮ ዓመት የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራሙ የተለየ መርሐ ግብር ተጀምሯ፡፡ መንግሥት 51,000 ለሚሆኑ ተማሪዎች በጀት ይዞ የምገባ ፕሮግራሙ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ እንዲህ ሲደረግ የመጀመርያው ስለሆነ ፕሮግራሙ በመንግሥት በጀት እንዲገባ፣ ለአወጣጥና ለአሠራር የተመቸ እንዲሆን ማድረጉ ጊዜ ወስዶብን ስለነበር መጀመር ከነበረብን ጊዜ ዘግየት ብለን ነው የጀመርነው፡፡ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ለመጀመርያ ዙር የለቀቀልን 66.9 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ለአንድ ዓመት የጠየቅነው ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ የመጀመርያው ዙር በጀት የተለቀቀልን ዘንድሮ ታኅሣሥር ወር ላይ ነው፡፡ ይህ ለኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ቢዘገይም ፕሮግራሙ በመንግሥት በጀት ውስጥ መካተቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አንደኛ ለጉዳዩ መንግሥት ትኩረት እንደሰጠ ያሳያል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ፕሮግራሙ ቀጣይነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ብዙም የሚያስተማምን አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የእናት ወግን ማንሳት እንችላለን፡፡ የእናት ወግ 2010 ዓ.ም. ላይ 22 ሺሕ ተማሪዎችን ሲመግብ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በአንድ ጊዜ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ቀንሶ 9,000 ተማሪዎችን ብቻ ነው እየመገበ የሚገኘው፡፡ ቋሚ የበጀት ምንጭ የለውም፡፡ ከተለያዩ አገር በቀል ድጋፍ ሰጪ አካላትና ከቻይና ፋውንዴሽን ነበር ገንዘቡን የሚሰበስበው፡፡ እንደ ንግድ ባንክ፣ ቴሌ፣ ሚድሮክና አየር መንገድ ያሉ አገር በቀል ድርጅቶች ናቸው ፕሮግራሙ የሚተገብርበትን ገንዘብ የሚሰጡት፡፡ በዚህ ዓመት ግን የሚጠበቀውን ያህል ገንዘብ ስላላገኙ 9,000 ተማሪዎችን ብቻ ነው እየመገቡ የሚገኙት፡፡

ሪፖርተር፡- ሚድሮክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ ማድረጋቸውን አቁመዋል፡፡ የሁለቱ ድርጅቶች ድጋፍ ምን ያህል ቢሆን ነው የተመጋቢዎች ቁጥር በዚህ መጠን ሊቀንስ የቻለው?

ወይዘሪት ሜቲ፡- 10,000 ተማሪዎችን ይመግብ የነበረው ሚድሮክ ነበር፡፡ ድርጅቱ ቃል የገባውን ገንዘብ መስጠት ሲያቆም ነው በአንዴ የተመጋቢዎች ቁጥር በዚህ መጠን የቀነሰው፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ አንዳንድ ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የሚስብ ኃይል ነው፡፡ ፕሮግራሙን ስቆጣጠር ያየሁትም ይህንኑ ነው፡፡ ምግቡን ብለው ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች አሉ፡፡ ብምግብ ዕጦት ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ልጆች አሉ፡፡ እነዚህ ልጆች እጅግ ደሃ ከሆኑ ቤተሰቦች የወጡ፣ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁና በልመና ከሚተዳደሩ የማኅበረሰቡ ክፍሎች የተገኙ ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን በአግባቡ መመገብ ያቃታቸው የጉልበት ሥራዎችን ሠርተው የሚተዳደሩ ወላጆች አሉ፡፡ ወላጅ የሌላቸው ደግሞ በጣም በችግር ነው የሚኖሩት፡፡ ይህ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ለእኔ ወጪ አይደለም፡፡ እንደ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ምክንያቱም የነገውን ትውልድ ለመቅረፅ ዛሬ መደረግ ያለበት ነገር ነው፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት መዋል አለባቸው፡፡ ትምህርት ቤት ሲውሉ ደግሞ ቢያንስ ቁርስና ምሣ ማግኘት አለባቸው፡፡ ምግብ ሳይመገብ እንዴት ነው ተማሪን ተማር ውጤታማ ሁን ማለት የሚቻለው? የዓለም ባንክም እንደሚለው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ወጪ ሳይሆን ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ያ ልጅ አድጎ በትምህርት ራሱን ችሎ መልሶ አገሪቱን ነው የሚያገለግለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምግብ ማግኘት የሕፃናት መብት ነው፡፡ አብዛኞቹ በዚህ ፕሮግራም የታቀፉ ታዳጊዎች የዕለት ምግብ የማያገኙ ናቸው፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በብዙ አቅጣጫ ታዳጊዎችን ሲያልፍ ደግሞ አገሪቷን የሚጠቅም ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በስንት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው የምትሠሩት?

ወይዘሪት ሜቲ፡- አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም አላቸው፡፡ በየክፍለ ከተማው በሚገኙ 234 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የትምህርት ቤት ምገባ አለ፡፡ የምንሠራው ከእናት ወግ ጋር ተከፋፍለን ነው፡፡ የእናት ወግን እንደ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ሳይሆን እንደ አጋር ነው የምንወስደው፡፡ ሥራውም አጥጋቢና እኔም በግሌ የምኮራበት መመሥገን ያለበት ድርጅት ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ ደፍረው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ባይጀምሩ ዛሬ የደረሰበት አይደርስም ነበር፡፡ የእናት ወግ ጉለሌ፣ አራዳና ቂርቆስ አካባቢ በሚገኙ ብዙ ትምህርት ቤቶች ላይ እየሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ ልደታ በሚገኘው መተባበር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ 500 ተማሪዎችን የሚመግበው የእናት ወግ ነው፡፡ እኛ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ ብንሠራ ደስ ይለናል፡፡ ነገር ግን ካሉት 234 ትምህርት ቤቶች መካከል በ221 ትምህርት ቤቶች ላይ ነው መንግሥትና የእናት ወግ እየሠሩ የሚገኙት፡፡ ብዙ የችግረኛ ተማሪዎች ቁጥር ያለባቸውን ትምህርት ቤቶች የሚመለምሉልን ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡ ክፍለ ከተሞች የትኞቹ ትምህርት ቤት ጋር የከፋ ችግር እንዳለ፣ የትኞቹ ምን ያህል ኮታ ማግኘት እንዳለባቸው፣ የትኞቹ ከተቋማት ድጋፍ እንደሚያገኙ ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ በቀደም ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት  በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 9,000 ተማሪዎችን የሚረዳ ሌላ ተቋም እንዳለ ተረድተናል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ቀጥታ ድጋፍ የሚያደርገው የባሰ ችግር ባለባቸው 221 ትምህርት ቤቶች ላይ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙት መካከል የከፋ ችግር ያለባቸው ተለይተው ነው በፕሮግራሙ የሚካተቱት፡፡ ነገር ግን አቅም ቢኖር ሁሉም ሳይለዩ በአንድነት ቢመገቡ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ልጆች ከፍ ካሉ በኋላ ከሌሎቹ ተለይተው የዕርዳታ ምግብ መብላታቸው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ነው፡፡ ይህ ካለባቸው ችግር ባይብስም የምናስተውለው ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- 51,000 ተማሪዎች በመንግሥት በምገባ ፕሮግራሙ እንዲካተቱ ስታደርጉ ምግቡን የሚያበስሉ ምን ያህል እናቶችስ መልምላችኋል?

ወይዘሪት ሜቲ፡- እናቶችን የመመልመል ሥልጣኑ የተሰጠው ለሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮግራም የሚመለመሉ እናቶች በየወረዳቸው እንዲሠሩ ታስቦ ነው፡፡ በሚኖሩበት ወረዳ ላይ ሲሠሩ የራሳቸው ልጅ ከተመጋቢው መካከል ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ እናትየውም ልጇም ይረዳሉ፡፡ የምግቡ ጥራት ላይም የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የራስሽ ልጅ የሚበላውን ጥሩ አድርገሽ ትሠሪያለሽ፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው እናቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ እናቶች እኮ ራሳቸው ምገባ የሚያስፈልጋቸው የሚመስሉ ናቸው፡፡ በጣም ችግረኛ ናቸው፡፡ የእናት ባህሪ ያላቸው፣ ንግድን የማያስቡ ስለሆኑ ፕሮግራሙ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ዓምና የእናት ወግ በ12 ብር ነበር ቁርስና ምሣ ሲያቀርብ የነበረው፡፡ ይህንን ሥራ ለሌላ አካል ብትሰጪው በ12 ብር አያቀርብልሽም፡፡ የምግቡ ጣዕምም ከሞላ ጎደል ጥሩ የሚባል ነው፡፡ እኛም የምንጠቀመው የእናት ወግ የሚከተለውን አሠራር ነው፡፡ ዘንድሮ ሴቶችና ሕፃናት ካደራጀና ሥራ ካስጀመራቸው በኋላ የመንግሥት የአከፋፈል ሥርዓት በሚፈቅደው መንገድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሆነው መደራጀት አለባቸው ተብሏል፡፡ ያለዚያ ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ገንዘብ አይወጣም የሚል ነገር አለ፡፡ ስለዚህ በጥቃቅንና አነስተኛ መልክ እያደራጇቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸውን በትክክል መግለጽ አልችልም፡፡ የእናት ወግ 22 ሺሕ ሕፃናትን በሚመግብበት ወቅት እንኳ 900 እናቶች ይሠሩ ስለነበር እንዲሁ መገመት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚቀርቡት ምግቦች ሥርዓተ ምግብን መሠረት አድርገው ነው?

ወይዘሪት ሜቲ፡- ሕፃናቱ የተመለመሉት በጣም የችግረኛ ልጆች መሆናቸው ታይቶ ነው፡፡ አንዳንዶቹን ጠጋ ብለሽ ምን በልተህ መጣህ/ሺ? ብለሽ ብትጠይቂ ዛሬ የእኔ ተራ አይደለም የወንድሜ ተራ ነበር አልበላሁም ይላሉ፡፡ ቀርበሽ ከልጆቹ ስትጠይቂ በጣም የሚረብሽሽን ታሪክ ነው የሚነግሩሽ፡፡ አንዳንዶቹም ከጓደኞቻቸው አንሰው ላለመታየት ባዶ ምሣ ዕቃ ይዘው የሚሄዱ ናቸው፡፡ በምሣ ዕቃቸው ቆሎ ይዘው የሚሄዱም አሉ፡፡ በዓይኔ ያየሁትን ልንገርሽ፡፡ አንድ ልጅ አንድ እንጀራ ላይ ወጥ የተደረገበት ምግብ ይዛለች ጓደኞቿ መብላት ጀምረዋል፡፡ እሷ ግን ቢርባትም አትበላም፡፡ ዞር ዞር እያለች ታያለች፣ ትቁነጠነጣለች በኋላ ላይ አስተማሪዋን ስጠይቃት ከሁለት ወንድሞቿ ጋር ቤት ወስዳ እንደምትበላው ነገረችኝ፡፡ ይህንን ያህል የከፋ ችግር ላለባቸው ነው አሁን ድጋፍ የሚሰጠው፡፡ የሥነ ምግብ ጉዳይ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሠራው ተደራሽነት ላይ ነው፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሕፃናት በሙሉ ተደራሽ ሆነዋል ወይ? የሚለው ነገር ነው፡፡ እነዚህ ልጆች በሙሉ ተደራሽ ከሆኑ ሥነ ምግብን በተመለከተ እንሠራለን፡፡ በምግብ ዕጦት ምክንያት ትምህርት የሚያቋርጡ፣ መቅረት የሚያበዙ ተማሪዎችን ለመታደግ በትንሽ ገንዘብ በርካታ ሕፃናቶችን መድረስ ላይ ነው ትኩረታችን፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የሚቀርበው ምግብ የተለመደው እኛ የምንበላው ነው፡፡ እንጀራ በሽሮ፣ በምስርና ሩዝ ይበላል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በተለየ ሁኔታ እንቁላል ተጨምሯል፡፡ እንቁላል የተጨመረው በብዙ ትግል ነው፡፡ በየሳምንቱ ሐሙስ እንጀራ በሽሮ ወጥ ከጎኑ የተቀለለ እንቁላል እየተደረገ ነው የሚቀርብላቸው፡፡ እንቁላል ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ሕፃናቱ ላይ የሚፈጥረው ደስታ ገራሚ ነው፡፡ በሥነ ምግብ ይዘቱ ጥሩ አይደለም አልልሽም፡፡ እኛ የምንበላውን ነው የሚሉበት፡፡ ለዚያውም ዘንድሮ ተሻሽሏል፡፡ ድጋፍ የሚፈልጉ ሕፃናት በሙሉ በዚህ መልኩ እንዲካተቱ ጥረት አድርገናል፡፡ 51,000 በመንግሥት፣ 9,000 በእናት ወግ፣ 9,600 ደግሞ መንግሥታዊ ባልሆነ በአንድ ተቋም በአጠቃላይ 69 ሺሕ ተማሪዎች በከተማው የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማዋ የሚገኙ የችግረኛ ተማሪዎች 69 ሺሕ ብቻ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ባለው የገንዘብ መጠን ልክ ተረጂዎችን የመለየት ሥራው ምን ያህል ከባድ ነበር? ወይም አንዱን ከአንዱ መለየቱ እንዴት አለፈ?

ወይዘሪት ሜቲ፡- አንዱን ከአንዱ መለየት በጣም አስቸጋሪና አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ በተለይ የእናት ወግ ብቻውን በሚሠራበት ወቅት አንዱን ከአንዱ መለየቱ በጣም ከባድ ነው ይሉን ነበር፡፡ አሁን ግን ሌላ 51,000 መጨመር ትልቅ ነገር ነው፡፡ ያለው ችግር በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይደለም፡፡ ሌሎች ድጋፍ የሚፈልጉ አሉ፡፡ ቢያንስ ግን በተቻለ መጠን በጣም የከፋ ችግር ያለባቸውን ለማካተት ተሞክሯል፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ በጣም ውድ ነው፡፡ ራሱን የቻለ የአሠራር ሥርዓት የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ ሌሎች አገሮች የተለያዩ አሠራሮችን ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ህንድ ያሉ አገሮች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን ለመደገፍ የተለያዩ አካሄዶችን ይጠቀማሉ፡፡ ከግብር የሚገኘውን የተወሰነ መጠን ለትምህርት ቤት ምገባ ያደርጋሉ፡፡ ባለሀብቶች እንዲህ ላሉ ተግባራት ሲረዱ ከሚከፍሉት ግብር ላይ የተወሰነ ተቀናሽ ይደረግላቸዋል፡፡ እኛም እንዲህ ያሉ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ ከመንግሥት በሚገኝ ድጋፍ ብቻ መወሰን አይገባም፡፡ አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ለሌላቸው ማካፈል አለባቸው፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራምም ሊዘጋጅ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሙ ሥር የሰደደ ችግር ያለበት ክፍለ ከተማ የትኛው ሆኖ አገኛችሁት?

ወይዘሪት ሜቲ፡- እውነት ለመናገር ሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ ችግር አለ፡፡ በተለይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ላይ ትልቅ ችግር አለ፡፡ በክፍለ ከተማው ፈለገ ዮርዳኖስ የሚባል ትምህርት ቤት አለ፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆችን ስታያቸው ራሱ በችግር የሚኖሩ መሆናቸውን ትረጃለሽ፡፡ በማይመች የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ፣ ኑሮን ለማሸነፍ እናቶቻቸው ሴተኛ አዳሪ መሆንን የመረጡ ናቸው፡፡ ወደ ጉለሌ ስትመጪ ደግሞ ድል በትግል የሚባል ትምህርት ቤት አለ፡፡ እዚያም ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው፡፡ ከዚያ ክፍለ ከተማ ሳትወጪም እንደዚሁ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናት የሚማሩበት ትምህርት ቤት አለ፡፡ በልመና የሚተዳደሩና ፀበልተኞች በብዛት የሚኖሩበት አካባቢ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ከነዚህ ወላጆች የተገኙ ናቸው፡፡ ወደ ንፋስ ስልክም ብትሄጂ እንዲህ ነው፡፡ የተሻሉ የሚባሉት እንደ አራዳ ክፍለ ከተማ ያሉት ናቸው፡፡ ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ ያለው የትምህርት ቤት ቁጥርም የተለያየ ነው፡፡ በፕሮራማችን የሚሰጣቸውም ኮቴ በዚሁ መጠን ሰፊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ረገድ ፈር ቀዳጅ የሚባሉት እነ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው የሚከተሉት የትምህርት ቤቶችን አቅም በመገንባት የምገባ ፕሮግራሙን በባለቤትነት እንዲመሩት የማድረግ ተሞክሮ አለ፡፡ አሠራሩን ለመከተል  አላሰባችሁም?

ወይዘሪት ሜቲ፡- አይቀርም፡፡ ለሁሉም ነገር መንግሥት ላይ ብቻ መወሰን ልክ አይደለም፡፡ የተለያዩ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ ለምሳሌ የእነ ወይዘሮ ፍሬዓለም አሠራር በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የእነሱን አሠራር ከተማ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይከብዳል፡፡ ለትምህርት ቤቶቹ ከብት ሰጥቶ ሕፃናት ወተት እንዲጠጡ የማድረግ አካሄድ እኔ በግሌ በጣም እስማማበታለሁ፡፡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት የሚከታተሉ ትንንሽ ልጆች እንጀራ ከሚበሉ አንድ ኩባያ ወተት በዳቦ ቢሰጣቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ በገጠር ሲሆን ሰፊ የግጦሽ ቦታ ስለሚኖር የተመቸ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ግን ይለያል፡፡ ሌላ ቦታም እንዲሁ ከዳቦ ቤት በሚገኘው ገንዘብ የተማሪዎች የምግብ ወጪ የሚሸፈንበት ተሞክሮም አለ፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን ላይ መሰል ፕሮግራሞችን ማን ይምራው? ከሚል ጉዳይ አንፃር ትምህርት ቤቶችና ድጋፍ አቅራቢ ተቋማት እየተጋጩ ነው፡፡ አንዳንዴም ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራ ውጪ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ተጠምደው ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡