Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ

ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከባለሀብት ጋር እያወሩ ነው]

 • እንኳን ደስ አለዎት፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • አልሰማሁም እንዳይሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን?
 • ዕግዱ ተነሳ፡፡
 • ከአገር እንዳትወጣ የተባልከው?
 • እሱን እንኳን ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡
 • እንዴት?
 • የሦስት ሺሕ ሰዎች የጉዞ ዕግድ መነሳቱን ሰምቻለሁ፡፡
 • ዋናው የአንተ ተነስቷል ወይ?
 • አላወቅኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምኑ ነው ደስ ያለህ?
 • እኔ ስለሌላ ዕገዳ ነው የማወራው፡፡
 • የምን ዕገዳ?
 • የሪል ስቴት፡፡
 • አትለኝም?
 • ይኸው ከስብሰባ ወጥቼ ነው የማናግርዎት፡፡
 • እንዴት ተነሳ?
 • በቃ ተነሳ፡፡
 • ስማ እኔ እኮ እንቅልፍ ካጣሁ ሰነባበትኩ፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር እኔ ራሴ መቼ ተኝቼ አውቃለሁ?
 • ይጣራል ከተባለ ጀምሮ ጤናዬ ጥሩ አይደለም፡፡
 • የስንት ሰው ጤና መታወኩን እኔም አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ዕግዱ እንዴት ተነሳ?
 • እኔም ግራ ገብቶኛል፡፡
 • ሊያዘናጉን እንዳይሆን?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ማለቴ ነፃ ነን ብለን ስንዘናጋ ጎል እንዳይከቱን፡፡
 • መጠርጠሩ አይከፋም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ?
 • የምን አገልግሎት?
 • ለሪል ስቴቶቹ የስም ማዘዋወር ምናምኑን ነዋ፡፡
 • ይጀመራል ተብሏል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ እኔ በአፋጣኝ በስሜ ያሉትን ቤቶች ማስተላለፍ አለብኝ፡፡
 • ለማን ነው የሚያስተላልፉት?
 • ለወዳጅ ዘመዶቼ ነዋ፡፡
 • እሱን አሁን ማድረግ አደጋ አለው፡፡
 • የምን አደጋ?
 • ዕግዱ የመጣው እኮ ከፍተኛ የሆነ የቤትና የንብረት ዝውውር ስለነበረ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በስምዎ ያሉትን ንብረቶች ለሌሎች ቢያስተላልፉ በድጋሚ መንግሥትን ሊያነቁት ይችላሉ፡፡
 • እንዴት?
 • ብቻዎን እኮ ያሉዎት ቤቶች ክፍለ ከተማ ያስመሠርቱዎታል፡፡
 • እ. . .
 • ሐሳባችንንማ አክሽፎብናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ነው ያከሸፈው?
 • ለውጡ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እስኪ ተወው፡፡
 • የእኔ እኮ ሐሳብ በስምዎ ከተማ መመሥረት ነበር፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ሥርዓቱ ባይቀየር እኮ እርስዎ ብቻዎን መሆን ይችሉ ነበር፡፡
 • ምን?
 • ክልል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያለ ኃላፊ ዘንድ ይደውላሉ]

 • ዛሬ ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዲያው እንዳትረሱኝ ለማለት ነው፡፡
 • ምነው አምባሳደር መሆን ፈለጉ?
 • ምነው? ምን አደረግኩህ?
 • እንዴት በፊት አምባሳደር መሆን እንደሚፈልጉ ነግረውኝ ነበር እኮ?
 • ድሮ ነዋ፡፡
 • አሁን ምን ተገኘ?
 • ስማ ድሮ እኮ አምባሳደርነት መጦሪያ፣ ከዚያም በላይ የሽምግልና ቢዝነስ መሥሪያ ነበር፡፡
 • አሁንማ እሱ ቀርቷል፡፡
 • ስለዚህ ምን በወጣኝ ብዬ ነው በስተርጅና የምሰቃየው?
 • ለነገሩ አሁን የሚሠራ ብቻ ነው አምባሳደር መሆን የሚቻለው፡፡
 • ሁሉን ነገር መዘጋጋት ግን ያዋጣል?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ቢያንስ አምባሳደርነት ዕድሜያችንን ሙሉ ያገለገልን ሰዎች መጦሪያ ነበራ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ማንን ነው ያገለገሉት?
 • ሕዝቡን ነዋ፡፡
 • ራስዎን እንደ ሕዝብ ነው እንዴ የሚቆጥሩት?
 • አልገባኝም?
 • ዕድሜዎን ሙሉ ራስዎን ሲያገለግሉ ነበራ፡፡
 • አሁንማ የማንም መጫወቻ መሆኔን አውቃለሁ፡፡
 • ምን ያደርጉታል?
 • ለማንኛውም ሊስት ውስጥ አለሁበት?
 • የምን ሊስት?
 • ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እጓዛለሁ ወይ ብዬ ነው፡፡
 • ለምንድነው የሚጓዙት?
 • መደመሬን ለማሳየት ነዋ፡፡
 • ለማን ነው የሚያሳዩት?
 • ለዓለም ሕዝብ ነዋ፡፡
 • ሞራልዎ እኮ ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • የዓለም ሕዝብ ያውቀኛል ብለው ነው የሚያስቡት?
 • በሚገባ እንጂ፡፡
 • ኧረ እንደዚህ መወጣጠር አያስፈልግም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ማለት ነው?
 • እንኳን በዓለም እዚህም በቅጡ የሚያውቅዎ የለም፡፡
 • ምን ነካህ ታዋቂማ ነኝ፡፡
 • ከታወቁም የሚታወቁት በአንድ ነገር ነው፡፡
 • በምን?
 • በሌብነት፡፡
 • እንከባበራ?
 • ለመከበር መጀመርያ የሚያስከብር ሥራ መሥራት አለብዎ፡፡
 • ከዚህ በላይ ምን ልሥራ?
 • የሠሩት ለራስዎ እንጂ ለአገር አይደለም፡፡
 • ተረቱም እኮ ከራስ በላይ ንፋስ ነው የሚለው፡፡
 • ስለዚህ እርስዎ ተደምረዋል ለማለት ይከብዳል፡፡
 • እኔ ሙሉ ለሙሉ ነው የተደመርኩት፡፡
 • እንዳይነቀሱ ይፍሩ፡፡
 • ለማንኛውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መሄድ እፈልጋለሁ፡፡
 • እ. . .
 • በርካታ ማግኘት የምፈልጋቸው ባለሀብቶች እዚያ አሉ፡፡
 • የት?
 • ዳቮስ፡፡
 • እና ዳቮስ ነው መሄድ የፈለጉት?
 • አዎን፡፡
 • እርስዎ መሄድ ያለብዎ ዳቮስ ሳይሆን ሌላ ቦታ  ነው፡፡
 • የት?
 • እንጦሮጦስ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ደውሎላቸው እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሪቷን እየለመድካት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ኧረ በፍፁም ልለምዳት አልቻልኩም፡፡
 • እናንተ ዳያስፖራዎች ደግሞ ማካበድ ታውቁበታላችሁ፡፡
 • እያካበድኩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?
 • ታዲያ ምን እያደረግህ ነው?
 • አገሪቱ እኮ በየጊዜው ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደች ነው፡፡
 • ምን ጠብቀህ ነበር?
 • እኔማ ለውጡን ተማምኜ ነበር አገር ቤት የገባሁት?
 • ወይ ለውጥ?
 • ለነገሩ እርስዎ የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በቃ ብዙ ነገር ቀርቶብዎታል፡፡
 • ምን ቀረብኝ?
 • አሁን ፈላጭ ቆራጭ አይደሉማ፡፡
 • ውጤቱን እኮ እያየነው ነው፡፡
 • የምን ውጤት?
 • ይኸው አገሪቱ ያለችበትን ችግር አታየውም እንዴ?
 • እሱ እንኳን አሳሳቢ ነው፡፡
 • አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አሥጊ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በየቀኑ የምሰማው ወሬ እያሳመመኝ ነው፡፡
 • ለምን?
 • አገሪቱ እኮ ልትፈራርስ ነው የምትመስለው?
 • መፍረስ እንኳን አትፈርስም፣ ግን ያው ቤት ሲታደስ የሚፈርስ ነገር አለው፡፡
 • ለማንኛውም ከሰሞኑ ስብሰባችሁ እኮ ብዙ ነበር የሚጠበቀው፡፡
 • የትኛውም ስብሰባ?
 • የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ነዋ፡፡
 • ምን ጠብቀህ ነበር?
 • ማለቴ አገሪቱ እንዲህ በምጥ ላይ እያለች ሕዝቡ ወሳኝ መግለጫ ነበር የሚጠብቀው፡፡
 • መግለጫው ምን ሆነ?
 • የተለመደና በቃላት የተደረተ ብቻ ነው፡፡
 • አየህ እሱ የኢሕአዴግ ባህል ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ውስጥ እርስ በርሳችን እንፋለማለን፣ ስንወጣ ግን ሁሉንም ነገር ሰላም እንደሆነ እናስመስለዋለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሚሻለው ግን ፊት ለፊት ሁሉን ነገር በግልጽ ማውጣት ነው፡፡
 • እሱማ የኒዮሊበራሎች አካሄድ ነው፡፡
 • አሁንም ኒዮሊበራሎችን ይቃወማሉ እንዴ?
 • ሁሌም ጠላቶቼ ናቸው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት እየሄደበት ያለው አቅጣጫ እኮ በእሱ መስሎኝ?
 • ቢሆንም እኔ በእሱ አልስማማም፡፡
 • ውስጣችሁማ ክፍፍል እንዳለ ያስታውቃል፡፡
 • የምን ክፍፍል?
 • የብዙ ነገር ክፍፍል፡፡
 • ይኼ የጠላት ወሬ ነው፡፡
 • እኔ እንዲያውም የሥራ አስፈጻሚው አባላት ሁሉም ሥራ አስፈጻሚ አይመስሉኝም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አንዳንዶቹ የሚያስፈጽሙት ሥራ አይደለም፡፡
 • ምንድነው የሚያስፈጽሙት?
 • ሕገወጥነት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ]

 • አንተ ሰውዬ ምን ሆነሃል?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በተከታታይ ስልክ ስደውልልህ ለምንድነው የማታነሳው?
 • ስልኩ ጥሩ አይደለም ብዬ እኮ ብዙ ጊዜ ቢሮ ብመጣ አጣሁዎት፡፡
 • ምን ሆነህ ነው የጠፋኸው?
 • ክቡር ሚኒስትር ድምፄን ላጥፋ ብዬ እኮ ነው፡፡
 • ለምን?
 • ከነገ ዛሬ ቢያስገቡኝስ?
 • ስማ እስከ መጨረሻው ጠብታ ነው መታገል ያለብህ፡፡
 • ምን ተገኘ ታዲያ?
 • ቢዝነሱን ተውከው እንዴ?
 • ምን ያው ሁሉ ነገር ስለተቀያየረ አስቸጋሪ ሆኗል እኮ?
 • አንተ ደግሞ ለዚህ መቼ ትታማለህ? ለ20 ዓመታት ጥርስህን የነቀልክበት አይደል እንዴ?
 • እንዲያው እንዲህ ሞራል የሚሰጠኝ ካገኘሁማ አሁኑኑ ነው የምጀምረው፡፡
 • ለመሆኑ ሰሞኑን ሚዲያ እየተከታተልክ ነው?
 • ምን አዲስ ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር?
 • በየቦታው እኮ ባንኮች እየተዘረፉ ነው፡፡
 • እሱን ሰምቻለሁ፡፡
 • ታዲያ ቶሎ ብለህ ሥራውን አትጀምርም እንዴ?
 • የቱን?
 • የእጥበቱን ነዋ፡፡
 • እ. . .
 • በአዲስ መልክ ጀምረናል ብለህ ማስታወቂያ ማስነገር እኮ ነው፡፡
 • በሚዲያ?
 • ኧረ በኔትወርክህ፡፡
 • የምን እጥበት ነው ግን?
 • የገንዘብ!