Skip to main content
x
‹‹መንግሥት የስቶክ ገበያ ከመመሥረቱ በፊት መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን ሊያጤን ይገባል›› አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል፣ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያና የአክሲዮን ገበያ ኤክስፐርት

‹‹መንግሥት የስቶክ ገበያ ከመመሥረቱ በፊት መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን ሊያጤን ይገባል›› አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል፣ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያና የአክሲዮን ገበያ ኤክስፐርት

አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል ‹‹ኮርነርስቶን አድቫይሰሪ ሰርቪስስ›› የተሰኘው የግል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የኢስት አፍሪካ ታይገር ብራንድስ የቀድሞ ቦርድ ሰብሳቢም ነበሩ፡፡ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያ (ሲፒኤ) ሲሆኑ፣ በአሜሪካ የተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ከቦርድ ሰብሳቢነት ጀምሮ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት፣ በዋና የገንዘብ ኃላፊነት፣ በግምጃ ቤት ኃላፊነትና በኮርፖሬት ጸሐፊነት ለአሠርት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ቮሉሽን የተሰውን በካሊፎርኒያ ሳን ዲዬጎ የፋይበር ኦፕቲክና የኤሌክትሪኮ ኦፕቲክ አምራች ኩባንያን በጋራ መመሥረት የቻሉ፣ እ.ኤ.አ. በ2007 እና በ2008 የሳን ዲዬጎ ቢዝነስ ጆርናል የዓመቱ ‹‹ቺፍ ፋይናንሺያል ኦፊሰር›› ዕጩ ለመሆን የበቁና ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ በማካበት ኩባንያዎችን ወደ ሕዝባዊ ተቋምነት ወይም በስቶክ ገበያ እንዲመዘገቡ በማስቻል፣ እንዲዋሀዱ በማገዝና አንዱ ሌላውን እንዲጠቀልለው በማመቻቸት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በሽርክና የሠሩ ኩባንያዎችን በማደራጀት፣ ፈንድ በማሰባሰብ፣ እንዲሁም በአሜሪካ የሴኪዩሪቲ ኤንድ ስቶክ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን የኩባያዎችን የገንዘብ ሪፖርት ዓለም አቀፍ ኦፕሬሽኖችም በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ በአሜሪካ በስቶክ ገበያ ያስመገቧቸው ኩባንያዎች ቀድሞ ከነበራቸው ከ20 በመቶ በላይ ዋጋ ሲያስገኙ፣ በዚሁ ሒደት ወደ ሕዝባዊ ኩባንያነት መለወጥ የሚችሉ ኩባንያዎችን በመለየት ባለአክሲዮኖች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በአካውንቲንግ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አሜሪካ ሠርተዋል፡፡ በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የተመረቁት አቶ ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን ስለሚታሰበው የአክሲዮን ገበያ፣ መሟላት ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ ወደ ግል እንዲዛወሩ የታሰቡት የልማት ድርጅቶች በአክሲዮን ገበያ መሸጣቸው ስለሚኖረው ፋይዳና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከአሥራት ስዩም ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በፖሊቲካና በኢኮኖሚያዊ ለውጦች ውስጥ ትገኛለች፡፡ በመንግሥት ሥር የነበሩ የኢኮኖሚ አውታሮች ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት የሚደረጉበት እንቅስቃሴ መጀመሩ ከበርካታ ለውጦች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ይዞታ የሚዛወሩት የልማት ድርጅቶች፣ እንዲሁም የግሉና የመንግሥት የአጋርነት ማዕቀፍ መፈጠራቸው የአገሪቱን የተለምዶ አካሄድ እንደሚቀይሩት ይጠበቃል፡፡ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መስፋት እንዳለበት የሚያምኑ በርካቶች ቢኖሩም እንደ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ ኃይልና በመሳሰሉ መንግሥት በሚያስተዳድራቸው ተቋማት ውስጥ የግል ካፒታል መግባቱ የዋጋ ውድነትን ያስከትላል፣ ሸማቾች ተጠቃሚ አያደርግም፣ ሌሎችም በእነዚህ ተቋማት አገልግሎት ላይ የተመሠረቱ የኢኮኖሚው ክፍሎችም ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ሥጋቶች እየተደመጡ ነው፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? የጉዳት ማቃለያ ዕርምጃዎችስ ምንድን ናቸው? 

አቶ ተስፋዬ፡- የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወሩ በጎ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተገቢው መሠረተ ልማት ባልተዘረጋበት፣ የሙያ ታማኝነትና ልምዱ ያላቸው የቆረጡ ባለሙያዎች ባልተዘጋጁበት ወቅት የተሳካ ፕራይቬታይዜሽን ሊኖር አይችልም፡፡ የትኛውም ፕሮጀክት ከመተግበሩም ሆነ ተቋም ከመመሥረቱ በፊት ሰፊ ጊዜ ወስዶ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል ማዛወር ከሚኖረው ተወዳዳሪነት ጭምር ለሸማቹ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡ አገልግሎት አቅራቢዎች ተገቢውን አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ እንዲያቀርቡ ያስገድዳቸዋል፡፡ የገበያው ተለዋዋጭነት ሸማቹ የተሻለ አማራጭ እንዲያገኝ ያግዘዋል፡፡ ዓላማው የመንግሥትን ዘርፍ ለግሉ ክፍት በማድረግ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ነው፡፡ ቁልፉ ጉዳይ ክፍትና ፍትኃዊ የመጫወቻ ሜዳ እንዲኖር በመፍቀድ ተጨማሪ ውድድር እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሒደት በግልጽነት አንዱን ሌላውን የመቆጣጠርና የመከታተል አስተዳደር ሥርዓትን በማስፈን ሊታገዝ ይገባዋል፡፡ ይህ ሒደት በአግባቡ ካልተመራ ግን ጥቂቶች ተሰባስበው ገበያውን የሚቆጣጠሩበትና ዋጋ የሚወስኑበትን ሥርዓት በመፍጠር፣ ሸማቹን የሚጎዳ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል፡፡ በርካታ አገሮች እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለው አገልግሎት ታሪፍ ላይ የግል ኩባንያዎች ዋጋ እንዳሻቸው እንዳይጨምሩ የሚከለክሉ ሕጎች አሏቸው፡፡ አንዳንዴም መንግሥታት ድጎማ በማድረግ የሕዝብ አገልግሎት በተሻለ ዋጋ እንዲቀርብ ያደርጋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የፓልም ዘይት ላይ የሚደረገው ድጎማ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎም እንደጠቀሱት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲህ ባሉት መስኮች ውስጥ በመግባታቸው  ለራሳቸው ጥቅም በሚሮጡ ጥቂቶች ቡድኖች እጅ ሥርዓቱ እንዲወድቅ ያደርገዋል ብለው የሚሠጉ ሲኖሩ፣ ሌሎች ደግሞ የውጭ ካፒታሊስቶች በመግባታቸው የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ይጋፋሉ የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ እርስዎ በእነዚህ ሥጋቶች ይስማማሉ? እንዴትስ ነው ይህንን ሥርዓት በመልካም መንገድ ማስኬድ የሚቻለው?

አቶ ተስፋዬ፡- ፕራይቬታይዜሽኑ መምጣት ሲጀምር ሒደቱንና የግሉን ዘርፍ በሚገባ ለመምራት የሚያስችል ተገቢውን የአመራር ሥርዓት መዘርጋት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ፕራይቬታይዜሽን በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ፈተናው ግን አቅሙና ብቃቱ ያላቸውን፣ ለአገሪቱና ለባለአክሲዮኖች ጥቅም ለመሥራት ተነሳሽነቱ ያላቸውን ትክክለኛ ባለሙያዎች ማግኘቱና ሒደቱን እንዲመሩት ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ሰብዕናቸው፣ የሞራል ልዕልናቸው፣ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በአግባቡ መገዘንዘባቸው የግልና የመንግሥት ኩባንያዎችን ለመምራት የመሠረት ድንጋዮች ናቸው፡፡ ከላይ ያለው አመራር ቁርጠኝነት ከታየበት፣ መልካም በመሥራት ክብር የሚሰማው ከሆነ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱንና ቤተሰባዊ እሴቶቹን የሚያከብር አመራር ከሆነ፣ ፕራይቬታይዜሽኑንም ሆነ ሌሎቹንም የአገሪቱን ዓላማዎች ለማሳካት ዋስትና ይኖራል፡፡ ሉዓላዊነት የአመራሩ ጫንቃ ላይ ያረፈ ኃላፊነት ነው፡፡ የመንግሥት ድርጅቶች ለአገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ አካል በሚሸጡበት ወቅት በተገቢው ሁኔታ የሕዝብን ፍላጎት የሚያስጠብቅና ለሁሉም በእኩል የሚዳኝ አሠራር ካልተዘረጋ፣ ያኔ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነቱን የሚያጣው፡፡ የሕግ ማዕቀፍ፣ ጠንካራ ተቋማትና ትምህርት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዓይነተኛ ዋስትናዎች ናቸው፡፡ የአገርን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ጥሩ አማራጭ ሊባል የሚችለው፣ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማጣጣም መተግበር ሲቻል ነው፡፡ በዓለም ላይ ጥሩ ውጤት ያስገኙ ነገሮችን ሁልጊዜም በዝግ ነው ልንተገብራቸው ስንሞክር የምንታየው፡፡ ወይም በአግባቡ ሳንረዳና ተገቢው መሣሪያ ሳይኖረን እነዚህን መልካም ተሞክሮዎች ለመቅዳት እንሞክራለን፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች ምን እንደሚያስፈልጋቸው የሚገነዘብና ከኢትዮጵያ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ አኳያ እንዴት ሊስማሙ እንደሚችሉ የሚያውቅ ትክክለኛ የአመራር ስብስብ ማግኘቱ ላይ ነው፡፡ አንድን ነገር ከውጭ ስንዋስ ለራሳችን ከፍተኛውን ደረጃ በማስቀመጥ በዚያ መሠረት እንዲፈጸም ማድረግ አለብን፡፡ ይህንን ማስለመድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- መዋቅራዊ የካፒታል ገበያ በመመሥረት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ቢዛወሩ ይሻላል የሚሉም አሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል መንግሥት የተቻኮለ ዕቅድ በማውጣት እ.ኤ.አ. በ2020 የካፒታል ገበያ ለመመሥረት ያሰበው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ይህ ዕቅድ ተገቢነት አለው ብለው ያስባሉ? ከዚህ ባሻገር ግን የስቶክ ገበያ መፈጠሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ዓይነተኛው መንገድ ነው ሊባል ይችላል?

አቶ ተስፋዬ፡- የስቶክ ገበያ አቅሙ ላላቸውና ሥጋትን መቋቋም ለሚችሉ አማራጭ የኢንቨስትመንት መሣሪያ ነው፡፡ በተፈጥሮው የስቶክ ገበያ ለመቶዎቹ ዓመታት ሲነግዱበት በቆዩት ያደጉ አገሮች ውስጥም ቢሆን ለሥጋት የተጋለጠ መስክ ነው፡፡ የስቶክ ገበያ ጉዳይ ትንሽ ወሰብሰብ ይላል፡፡ ይኸውም ገበያው ከመፈጠሩ በፊት ጠንካራ ተቋማትን የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ እንደ የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲ ኮሚሽን ያሉ ተቋማት ያስፈልጉናል፡፡ ሕግ ለማርቀቅና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሴኪዩሪቲ ማስፈጸሚያ ዲቪዥንም መፈጠር አለበት፡፡ ኦዲተሮችንና የሒሳብ ባለሙያዎችን፣ እንደ ስቶክ ብሮከሮች ማኅበር ያሉትን የሙያ ማኅበራትና አባላቱን የሚቆጣጠር፣ ጠበቆችን፣ ኦዲተሮችን፣ የሒሳብ ባለሙያዎችን፣ ዋና የገንዘብ ኃላፊዎችን የሚያሠለጥን ወዘተ. የሚያከናውን ነው፡፡ ወደ ስቶክ ገበያ ከመግባታቸው በፊት እነዚህ ባለሙያዎች የግድ መሠልጠንና ሕጉን አስቀድመው መረዳትና ማወቅ አለባቸው፡፡ በአጭሩ እ.ኤ.አ. በ2020 እንዲተገበር የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አያስኬድም፡፡ እንደ ስቶክ ገበያው ሁሉ ፕራይቬታይዜሽኑንም በሚገባ አቅዶ ለመተግበር ሰፊ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ሁሉም አስፈላጊ ጉዳዮች ተሟልተው የስቶክ ገበያውን የምንጀምረው ከሆነ፣ ለሕዝብ የሚቀርቡት የመጀመሪያዎቹ ሽያጮች ላይ በጣም ከትንሹ መነሳት ቢቻል፣ ምናልባትም ከአምስት እስከ 15 የሚደርሱ ኩባንያዎች ብቻ እንዲሳተፉ በመፍቀድ፣ የገበያውን ባህሪ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት እየተከታተሉ መቆየቱ ይበጃል የሚል ምክረ ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ ይህ ሒደት መንግሥት ሒደቱን እንዲገነዘበውና አስተዳደሩን ወይም ሕጋዊ መዋቅሩን እንዲያሻሽል ሊረዳው ይችላል፡፡ ለሁሉም ነፃ ተደርጎ መቀመጥም የለበትም፡፡ ይህ ከሆነ ግን ገበያው እንደሚገባው የማይሠራ ይሆንና ማንም እምነት የማይጥልበት ደረጃ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በጠቅላላው ግን የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ ትልቅ ዋጋ ያላቸውና ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኙ በመሆናቸው፣ መንግሥትና የአገሩ ዜጎች እንዲሳተፉበት ማድረጉ መልካም ነገር ነው፡፡ ይሁንና የስቶክ ገበያ በመፍጠር እንዲህ ያሉ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ድርጅቶች ወዲያውኑ ማገበያየቱ ከፍተኛ ሥጋት እንዳለው ነው የማስበው፡፡ በሰፊው ካየነው አንደኛው መንገድ ሕዝቡ ውሱን ድርሻዎችን ከእነዚህ ድርጅቶች እንዲገዛ በመፍቀድ፣ በሁለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ እነዚህኑ ድርሻዎች ለመሸጥና ለመግዛት እንዲችል ማድረጉ ሲሆን፣ አስፈላጊው የቁጥጥር ወይም የአስተዳደር ሥርዓት ከተዘረጋ በኋላ ግን በስቶክ ገበያው እንዲገበያዩ መፍቀድ ሥርዓቱ በአግባቡ እንዲሠራ ለማድረግ ያግዛል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ጉዳይ ግን አሁን ኢትዮጵያ ለስቶክ ገበያ ዝግጁ ነች ወይ? ወይስ ከ20 ዓመታት በፊት ነበር ዝግጁ የነበረችው? የሚለውን ጥያቄ እንድንቃኝ ያደርጋል፡፡ በወቅቱ የቀረበው ጥናት አገሪቱ ዝግጁ እንዳልሆነች አመላክቷል በማለት መንግሥት አቋሙን አስታውቆ ነበር፡፡ ኢኮኖሚው በአግባቡ ለተደራጀ የአክሲዮን ገበያ ዝግጁ ነው ሊያሰኝ የሚችል ምን ምልክት አለ?

አቶ ተስፋዬ፡- እርግጥ በኢትዮጵያ የስቶክ ገበያ እንዲጀመር የአገር ውስጥም የውጭም ፍላጎት አለ፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ለዚህ ዝግጁ ነች ማለት አይደለም፡፡ በተወሰነና በተገደበ ደረጃ ግን መጀመር አይቻልም ማለትም አይደለም፡፡ ቁልፉ ጉዳይ የኮርፖሬት አስተዳደርና ይህንኑ በተዓማኒነትና እምነት በሚጣልበት አግባብ ግዴታውን ሊወጣ የሚችል አካል መኖሩ ነው፡፡ በስቶክ ገበያም ሆነ በሰፊው በተያዘ የአክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ገንዘብህን በአደራ ስትሰጥ፣ ገንዘቡ እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውል ማረጋገጫ የሚሰጥ መተማመን መኖር አለበት፡፡ በአገር በቀል የግል ኩባንያዎች በኩል ለጊዜው በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ችግሮች እያየን ነው፡፡ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በሰፊው የሚታወቀውን አንዱን ብናይ የአክሰስ ሪል ስቴት ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሪል ስቴት መስክ ተገቢው ቁጥጥር ባለመኖሩ ዘርፉ ለሁሉም ክፍት ተደረገና በርካታ ሰዎች ተበልተው ቀሩ፡፡ የአክሲዮን ገበያ መጀመራችንን እደግፋለሁ፡፡ ነገር ግን ዝግ ባለና በተወሰነ ደረጃ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት ለአክሲዮን ገበያ ዝግጁ የነበረች አይመስለኝም፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት ለአክሲዮን ገበያ ተብሎ ለምን ጥናት ማካሄድ እንዳስፈለገም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንኳንና ያን ጊዜ አሁንም ዝግጁ አይደለችም፡፡ ይኸውም ለስቶክ ገበያ የሚያስፈልጉ ተቋማትና መሣሪያዎች ስለሌሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተደራጀ የስቶክ ገበያ ከመጀመሩ በፊት መንግሥት ‹ሰከንደሪ ማርኬት› የሚባለውንና የመንግሥት የዋስትና ሰነዶች የሚገበያዩበትን ሥርዓት ለማስጀመር ሲሞክር ነበር፡፡ ይሁንና በመዋቅር ደረጃ የስቶክ ገበያም ሆነ ሰከንደሪ ማርኬት የሚባለው ልዩነት የላቸውም፡፡ ካላቸውም ለግብይት የሚውሉት ጉዳዮች ላይ ያለው የምርጫ ልዩነት ካልሆነ በቀር የሚሉ ስላሉ፣ እርስዎ በዚህ ይማማሉ? የትኛው ነው ቅድሚያ የሚሰጠው?

አቶ ተስፋዬ፡- የመንግሥት ቦንድም ሆነ ስቶክ ወይም የዋስትና ሰነዶች ለኢንቨስትመንት መሣሪዎች ናቸው፡፡ ባደጉት አገሮች ውስጥም እኮ ኮርፖሬት ቦንድ የሚባሉት ላይ ግብይት ይፈጸማል፡፡ ለሁሉም የግብይት ሰነዶችም ሆነ ስቶክ ላይ ያለው ሥጋትን የመቀበል ደረጃ ይለያያል፡፡ ይሁንና የመንግሥት ቦንድ ከኮርፖሬት ቦንድ ወይም ከስቶክ አኳያ አነስተኛ ሥጋት ያለበት ነው፡፡ እኔ ብሆን ስቶክ ገበያን ከብድር ሰነድ ግብይት እንዲጀምር አደርግ ነበር፡፡ ይህም ካለው ደኅንነትና ከወለድ ሥሪቱ አኳያ ዋስትና ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ለኢንቨስተሮች ያለው ሥጋት ዝቅተኛ በመሆኑና ግዴታ ያለባቸው ወይም ገንዘብ የሚያስተዳሩ አካላትንም ለኢንቨሰተሮች የሚገቧቸውን ግዴታዎች የሚቀንስ በመሆኑ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም የስቶክ ገበያው ምን ያህል ከዋጋ በላይ እንደወጣና እንደወረደ ለመረዳት ከመቸገር ይልቅ፣ እንደ ወለድ ዓይነት ክፍያ ማግኘት የሚችሉበት አሠራር በመሆኑ የዋስትና ሰነድ ሽያጩ ቢቀድም ይሻላል እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የስቶክ ግብይትና የቦንድ ወይም የዋስትና ሰነዶች የሚሸጡባቸው መድረኮች የሚከተሏቸው ሕጎችና መመርያዎች ተመሳሳይ ናቸው? እስከማውቀው የስቶክ ግብይቶች የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ የድርሻ ወይም የስቶክ ግብይት መፈጸሚያዎች ናቸው፡፡ ለቦንድ ሽያጭስ እንዴት ነው ግብይቱ የሚካሄደው? አንድ ሉዓላዊ አገርስ የዕዳ ሰነዶቹን በስቶክ ገበያ ለመጀመርያ ጊዜ ለሽያጭ ማቅረብ ይችላል ማለት ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- የቦንድም ሆነ የስቶክ ግብይት የሚፈጸምባቸው ሕጎች በጠቅላላው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አንድ ሉዓላዊ አካል ሁሉንም ሕግጋት እስካሟላ ድረስ ሰነዶቹን በስቶክ ገበያ ማገበያየት ይችላል፡፡ ከድንጋጌዎቹ በተጓዳኝ፣ ሕጎቹንና ግዴታዎቻቸውን መሠረት በማድረግ የተፈለገው ቦንድ ወይም ስቶክ በግብይቱ እንዲካተት ወይም ሊስት እንዲደረግ የሚያደርጉ ዋስትና ሰጪዎችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች የብድር ሰነዶችስ እንዴት ይታያሉ? ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ. በ2008 ለተፈጠረው የፋይናንስ ቀውስ ሰበብ የነበሩት እንደ ‹ሰብፕራይም ሀውሲንግ ሞርጌጅ› ያሉት የድብር ሰነዶች በካፒታል ገበያው ተመዝገው በሰፊው ሲሸጡ ነበር፡፡ ስለዚህ የትኛውም የብድር ሰነድ ለስቶክ ገበያው በሚስማማ መንገድ ተዘጋጅቶ ግብይት ላይ ሊውል ይችላል ማለት ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- የባንክ ብድሮች ለንግድ ወይም ለግል ጉዳይ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ባንኮች ብድር ለማፅደቅ የሚከተሏቸው የራሳቸው አሠራሮች አሏቸው፡፡ በአብዛኛው ግን በንብረት ዋስትና ላይ የተመሠረተ ብድር አሰጣጥ ነው የሚከተሉት፡፡ የዕዳ ሰነዶች በስቶክ ገበያው ሊገበያዩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲተገበር አልመክርም፡፡ ከትንሹና ከቀላሉ ነው መጀመር ያለብን፡፡ እኛ ካለን የተበዳሪና የአበዳሪ ሁኔታ አኳያ ስናየው፣ ውስብስብ  የግብይት ሥልቶችን ማምጣቱ ብዙም ትርጉም አይሰጥም፡፡ ቦንዶችን ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ (አሞርታይዝ) የሚያስችሉ ቀላል ሥልቶችን በመከተል መጀመር ይሻለናል፡፡ በእኛ ሁኔታ እንደ ሰብፕራይም ያሉ የግብይት ሥልቶች አያስፈልጉንም፡፡ የሰብፕራይም ሞርጌጅ ቀውስን በተመለከተ ለቤት ብድር ይጠየቅ የነበረው የተለመደ አሠራር ሆን ተብሎ በጣልቃ ገብ ዘዴ ስለተነካ ነው፡፡ በተለምዶ በአሜሪካም ሆነ በዩናይትድ ኪንግደም የቤት መሥሪያ ወይም መግዣ ብድር ለማግኘት፣ በመጀመርያ ተበዳሪው የማይቋረጥ ገቢ የሚያስገኝለት ሥራ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚያም ቤት ሲያገኝ ወይም ስታገኝ በአብዛኛው በደላሎች በኩል የሚሆን ቢሆንም፣ ወደ ባንክ በመሄድ ብድር ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ባንኮቹ ቤት ለሚገዛው ሰው ከሚያገኘው ገቢ አኳያ ለክፍያ የሚያመቸውን ብድር ከእነ ወለዱ ያቀርቡለታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ባንኮቹ ስለተበዳሪው የቅጥር ሁኔታ፣ የአገልግሎት ዘመን፣ የገቢ ምንጮች፣ ሌላ ተጨማሪ ገቢ እንዳለውና የቤተሰቡን ብዛት ብሎም የሚያስተዳድራቸው ሰዎች ብዛት፣ ወዘተ. ያጣራሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚፈልጉት ተበዳሪው ዕዳውን በየወሩ መክፈል ይችላል ወይ የሚለውን ለማወቅ ነው፡፡ ወርኃዊ ክፍያው ከተበዳሪው ጠቅላላ ደመወዝ ከ30 በመቶ መብለጥ የለበትም፡፡

ይሁንና እ.ኤ.አ. ከ2008 ቀውስ በፊት ግን ለሞርጌጅ ብድር የተለመደው አሠራር ሰብፕራይም ሞርጌጅ በተሰኘ በሌላ የብድር ሥርዓት ተቀየረ፡፡ ያደረጉት ነገር ቀድሞ የነበረውን ጠንካራ የብድር ሥርዓት መጠይቆችን በማለፍ፣ አቅሙ ላላቸው ኢንቨስተሮች መሸጥ የሚችሉ ሌሎች የሞርጌጅ ዓይነቶችን በማምጣትና እነሱ እንደሚጠሯቸው ተለዋዋጭ የወለድ ምጣኔ ያላቸውን አሠራሮች በመከተል ነባሮቹን አሠራሮች ገሸሽ አደረጉ፡፡ አዲሱ የተለዋዋጭ ወለድ ምጣኔ በተበዳሪዎች ላይ ሥጋት የሚደቅንና በወርኃዊ የሞርጌጅ ክፍያቸውም ላይ ዋጋ የሚጨምርባቸው አሠራር ነበር፡፡ በዝቅተኛ ወለድ ምጣኔ ቤት ገዥዎች መግዛት የሚችሏቸው ቤቶች የወለድ ዋጋው ሲጨምር ግን ዕዳቸውን መክፈል እስኪያቅታቸው ድረስ ችግር ውስት ከተታቸው፡፡ ችግሩን ያባባሰው ደግሞ አበዳሪዎቹ ባንኮች የሞርጌጅ ብድሩን ለሦስተኛ ወገን የመሸጥ ዕድል መያዛቸው ነው፡፡ ባንኮቹም የወለድ ምጣኔው ተለዋዋጭ እንደመሆኑ እያደገ ይሄዳል በሚል ሐሳብ የሞርጌጅ ብድሮችን መሸጥ ጀመሩ፡፡ የወለድ ምጣኔው እያደገ እንደሚሄድ በመታሰቡ የሞርጌጅ ብድሮቹን ለገዙት ኢንቨስተሮች አጓጊ ነበር፡፡ ነገር ግን የወለድ ምጣኔው በየጊዜው ማደጉ ለቤት ገዥዎች ዕዳ መክፈል አዳጋች አድርጎባቸው ስለነበር በርካቶቹ መክፈል አቅቷቸዋል፡፡ አብዛኞቹ የሞርጌጅ ብድሮችም ዋስትና የተገባላቸው በመሆናቸው የአደጋው ሰደድ ወደ ሌሎችም ተዳርሷል፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህም ለብድር የሚቀርቡት መሥፈርቶች በጣም ጥብቅና ምንም ዓይነት ተለዋዋጭ ወለድ የማይጣልባቸው ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ስንነሳ፣ እንዲህ ካለው ውስብስብ የግብይት ስልት መጀመሩ ምንም ትርጉም የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በአሜሪካ ለበርካታ ኩባንያዎች ዋና የገንዘብ ኃላፊ በመሆን በሠሩባቸው ወቅት ወደ አክሲዮን ድርሻ ሽያጭ ያቀኑ ‹‹ጎይንግ ፐብሊክ›› ኩባንያዎችን ፕሮጀክቶች  መርተዋል፡፡ ለመሆኑ ይህ ምን ማለት ነው? ለመነሻ የሚቀርበው ወይም ‹‹ኢኒሺያል ፐብሊክ ኦፈሪንግ›› የሚባለውስ ምንድነው? አንድ ኩባንያ በሕዝብ ዘንድ አክሲዮኖቹ ግብይት ለመፈጸም የሚያስፈልጉ ወሳኝ የሽግግር ሒደቶችስ ምንድን ናቸው? ምናልባት ከባዱ ሒደት ሊባል የሚችለው የትኛው ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- የሴኪዩሪቲና የኤክስቼንጅ ኮሚሽን የተሰኘውን ተቋም ሕጎችና ግዴታዎች የሚያሟሉ ኩባንያዎች፣ የመነሻ የሽያጭ ድርሻቸውን ያካተተ ሰነድ ለተቋሙ ሲያቀርቡ ወደ ስቶክ ግብይቱ ይገባሉ፡፡ ይህም ማለት በየዕለቱ በሕዝብ ዘንድ ግብይት የሚፈጸምባቸውና የተመዘገቡ ኩባንያዎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ እኔ የተሳተፍኩባቸውና በአሜሪካ ለሕዝብ ክፍት የተደረጉ ኩባንያዎችን ስቶክ ለግብይት ማቅረቡ ከባድ ሥራ ነበር፡፡ ኩባንያዎች ኮሚሽኑ ያወጣቸውን በርካታ ሕግጋት ማክበርና መሥፈርቶቹንም የማሟላት ግዴታ አለባቻው፡፡ የሒሳብ ቁጥጥር ቦርድ (አካውንቲንግ ኦቨርሳይት ቦርድ)፣ የስቶክ ኤክስቼንጅ ቦርድ፣ እንዲሁም ለስቶክ ኢንቨስትመንት ዋስትና ሰጪዎችና አበዳሪ ባንኮችም የራሳቸውን ግምገማ በማካሄድ የኩባንያውን የገንዘብ መረጃዎች የሚያሳውቁበት አሠራር ሁሉ አለ፡፡ መሥፈርቱ ተገቢውን ሥራ አስፈጻሚ እስከ መምረጥ ያለውን ሒደት ሁሉ ይመለከታል፡፡ ኮሚሽኑ በሕዝብ ዘንድ ግብይት ለሚፈጸምባቸው ኩባንያዎች ያስቀመጣቸው ዋና የገንዘብ ኃላፊዎች አመዳደብ መሥፈርቶችም አሉ፡፡ የኃላፊዎቹ የሙያዊ ብቃትና ደረጃ፣ ያላቸው ሞራላዊና ሙያዊ ሰብዕና ኩባንያውን ለመመራት ያበቃቸዋል ወይ ተብለው ይፈተሻሉ፣ ይጠናሉ፡፡ በተመሳሳይ የኩባንያው ቦርድ አመራሮችም ይፈተሻሉ፡፡ ኩባንያው ብቃት ባላቸው ቦርድ አባላት የሚመራና ኃላፊዎቹም ተዛነፍ የሌለበት የሙያና የግል ሕይወት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገር የፋይናንስ መጠይቆችም ይቀርባሉ፡፡ በመጀመርያ ኩባንያው ቢያንስ ሦስት ዓመታት ያስቆጠረ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የሦስት ዓመታት የገንዘብ ኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ያለቀለት የኦዲት መዝገብ ማቅረብ አለበት፡፡ የኦዲት ሥራውም በተመሰከረለትና ብቃት ባለው የኦዲት ኩባንያ የተከናወነ መሆን አለበት፡፡ ለስቶክ ገበያ የታጨው ኩባንያ በሚገባ የተደረጃ የውስጥ የገንዘብ ሪፖርት ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡ ተፈትሾ የተረጋገጠ የኮርፖሬት አስተዳደር ፖሊሲም ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላም ብቃት ያላቸው ጠበቆች የተካተቱበት የአማካሪ ቡድን በማዋቀር ለሴኪዩሪቲ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽኑ ለሚያቀርባቸው የዋስትና ሰነዶችና ሌሎችም ዶሴዎች ምክር ማግኘት አለበት፡፡

በመሆኑም አንድ ኩባንያ ለሕዝብ አክሲዮን ለመሸጥ ሲወስን ለከባድ ምርጫ  እንደተዘጋጀ ማሰብ አለበት፡፡ ቤቱን በአግባቡ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ሁሉንም በአግባቡ ካዘጋጀ በኋላ ተስማሚ ዋስትና ሰጪ አካል መምረጥም ይጠበቅበታል፡፡ ሆኖም ዋስትና ሰጪዎቹ ራሳቸውም ኩባንያውን መምረጥ መቻል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛውን ደንበኛ ስለማግኘታቸው ማረጋገጥ ይፈልጋሉና፡፡ ይህንን ሁሉ ሒደት ካጠናቀቅ በኋላ ሰነዶችህን ለኮሚሽኑ ታስገባለህ፡፡ ሰነዱ የቢዝነስ ፕላን፣ የሠራተኞች ሁኔታንና ኦዲት የተደረገ የገንዘብ መግለጫም ያካትታል፡፡ በመሠረቱ ሰነዱ የኩባንያውን ኃላፊዎች ግለ ታሪክ፣ ስምምነቶች፣ የምርት መግለጫዎች፣ የባለቤትነት መብት፣ የስምምነት ውልና መሰል ጉዳዮች የሚካተቱበት ግዙፍ መዝገብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሰነዱ ለኮሚሽኑ በሚቀርብበት ጊዜም ለሚቀርቡ ጥያቄዎችም ምላሽ መስጠት ግዴታ ነው፡፡ ይህ ሒደት እስኪጠናቀቅ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ሰነዱ ወደ ሌሎች ግዛቶችም ሊላክ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ከኮሚሽኑ በመጠኑ ልዩነት ያለበት አሠራር ስላላቸው ነው፡፡ በአንዳንዶቹ ግዛቶች ያልተለመደ አሠራርም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በአብዛኛው ግን የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ በአብዛኞቹ ግዛቶች ዘንድ ተቀባይነት ስላለው (በእነሱ አጠራር ‹ብሉ ስካይ ሎው› ይሉታል) ሒደቱ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ስለዚህ ለሕዝብ የሚቀርብ ኩባንያ ትክክለኛና ለሥራው ብቁ ባለሙያዎች እንዳሉት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ነገሮችን በአግባቡ ሳያስተካክሉና ሳያዘጋጁ የኩባንያን አክሰዮኖችን ለሕዝብ ለመሸጥ መቻኮሉ አይመከርም፡፡ ወደ ሕዝብ ንብረትነት የሚመጣ ኩባንያ ዝግጅቱን በሙሉ ሚስጥራዊ ማድረግ መቻል አለበት፡፡ ይህም ወደ ሕዝብ ሳይመጣ ገና በስቶክ ገበያው ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ግምት እንዳይፈጠር ለማስቀረት ይረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓመታት የስቶክ ገበያን ለመምራት የሚያስችል አቀም የለም የሚለው ነበር ትልቁ መከራከሪያ ጉዳይ፡፡ የስቶክ ገበያን ለመምራት ከባዱ ጉዳይ ምንድነው ይላሉ? ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ገበያ ለመምራት የሚያበቃ የሰው ሀብት አላት?

አቶ ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ በዓለም ዳርቻ ተበትነው የሚገኙ ብቁና ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች አሏት፡፡ የሚያስፈልጉን በስቶክ ገበያ ላይ ተሞክሮው ያላቸው፣ የሰዎችን ገንዘብና ሀብት በአግባቡና በተጠያቂነት ስሜት ለማስተዳደር አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሲሟሉ ተገቢውን የአስተዳደር መዋቅር መፍጠር ይቻላል፡፡ የስቶክ ገበያ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት ካልተዘረጋለት፣ ለማስተዳደርና ሕግ ለማስፈጸም የሠለጠኑ ባለሙያዎች ከሌሉት በጣም አደገኛ ሥጋት ያለበት ሥርዓት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ መንግሥት የስቶክ ገበያ ከመመሥረቱ በፊት መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን ሊያጤን ይገባል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ መንግሥት ጊዜያዊ ኮሚሽን በማቋቋም አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ማሟላት፣ ፓርላማውን በማገዝም ሕጎች እንዲዘጋጁና የስቶክ ገበያው መተግበሪያዎች እንዲሟሉ ማድረግ መቻል አለበት፡፡ በዳያስፖራው ዘንድ ያለውን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ሒደቱንም ማፋጠን ይቻላል፡፡ የጊዜያዊ ኮሚሽኑ አባላት በመንግሥት የአክሲዮን ሽያጭ ወቅት ልምድ ያካበቱ የተመሰከረላቸው የመንግሥት ሒሳብ ባለሙያዎችን፣ በዋስትና ሰነዶችና ተዛማጅ መስክ ልምድ ያላቸው የሴኪዩሪቲ የሕግ ጠበቆችን፣ የስቶክ ገበያ ክህሎት ያላቸውን፣ የስቶክ ብሮከሮችን፣ በውጭ ባንኮች ውስጥ የሠሩ ዋስትና ሰጪዎችን (አንደርራይተርስ)፣ ያካተተ ቢሆን ይመረጣል፡፡ የጊዜያዊ ኮሚሽኑ አባላት ብዛት ከሰባት እስከ ዘጠኝ ቢሆንና አባላቱም የስቶክ ገበያውን ለመመሥረት የሚያስችል ተገቢነት ያለው የጊዜ ሰሌዳ ቢቀመጥላቸው ይበጃል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የስቶክ ወኪሎች ወይም ስቶክ ብሮከርስ የሚባሉትም ኢንቨስተሮችን በማማከርና በመወከል በስቶክ ገበያው ይሳተፋሉ፡፡ ባደጉት አገሮች ውስጥ እንደምንሰማው ‹‹ሔጅ ፈንድ፣ ካፒታል ወይም ኢኩዩቲ ፈንድ›› እንደሚባሉት ዓይነት ያሉ ኩባንያዎችም በተቋም ደረጃ በስቶክ ገበያው እንደሚሳተፉ ይገለጻል፡፡ የእነዚህ ተቋማት ሚና ምንድነው? የኢንቨስትመንት ባንኮች ተሳትፎስ ምን ይመስላል?

አቶ ተስፋዬ፡- ደላሎች ወይም ብሮከሮች ገዥና ሻጭ እንዲገበያዩ ያግዛሉ፡፡ በስቶክ ገበያው ውስጥ እነዚህ ሰዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ የኢኪዩቲ ፈንድ ማኔጀሮች ግን ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የበርካታ ተቋማትን ወይም ግለሰቦችን ገንዘብ በማሰባሰብ ድርሻቸውን ይበልጥ ለማደራጀት እንዲችሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የፈንድ ማኔጀሮች በተቋማቱ ፈንታ ሆነው ገንዘቡን ያስተዳድራሉ፡፡ ከተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ውስጥ የትኛውን መምረጥ እንዳለባቸው ለመወሰን በርካቶች ጊዜውም ግንዛቤም ስለማይኖራቸው፣ እነዚህ ተቋማት በጣም አስፈላጊዎች ይመስሉኛል፡፡ እነዚህ በአብዛኛው የረዥም ጊዜ ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ ተቋማቱ ፈንዱን ኢንቨስት የሚያደርጉት ከኢንቨስተሮች ጋር በሚገቡት ስምምነት መሠረት ነው፡፡ የገንዘብ አስተዳዳሪዎቹ በሚያድጉና ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኙ ኩባንያዎች ውስጥ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ፈንዱ የሚቀይበት ጊዜ እንደ ሁኔታው ይለያያል፡፡ ‹‹ሔጅ ፈንድ›› የሚባሉት አማራጭ የኢንቨስትመንት መሣሪያዎች ሲሆኑ፣ ከየአቅጣጫው ያሰባሰቡትን ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ ለኢንቨስተሮቻቸው ከፍተኛ ትርፍ እንደሚያስገኙ ስለሚታሰብ አማራጭ የኢንቨስትመንት ዘዴዎች ናቸው፡፡ ሔጅ ፈንድ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት የሚጠይቅና ኢንቨስተሮቹም ዕውቅና የተሰጣቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎቹ ይልቅ የሴኪዩሪቲ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽንን ድንጋጌዎች ብዙም ማሟላት አይጠበቅባቸውም፡፡ ዕውቅና የተሰጣቸው ኢንቨስተሮች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ግለሰቦችና ውስብስብ ኢንቨስተሮች በመሆናቸው ከፍተኛ ሥጋት የመቋቋም አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ለኢንቨስተሮች እንዲገቡ የማይፈቀድበት የተወሰነ ጊዜም በሥርዓቱ ተካቷል፡፡ ሔጅ ፈንድ ከሌሎች የኢንቨስትመንት የፈንድ ዓይቶች ይልቅ ሰፊ አማራጭ የሚሰጥ ነው፡፡ የግል ድርሻውን ይዞ ኢንቨስት ማድረግ በማይቻልባቸው ቦታዎች ሁሉ ሔጅ ፈንድ መግባት ይችላል፡፡ ከፍተኛ ተጋፋጭ ወይም ሥጋት ተቀባይ ፈንድ አስተዳዳሪዎችን ይጠቀማል፡፡ አንዳንዴ ከባንክ በመበደር ይዞታቸውን ሊያጠናክሩም ይችላሉ፡፡ የስቶክ ዋጋ ይቀንሳል ብለው ባሰቡ ጊዜም አነስተኛ ይዞታ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ፈንድ የሚያስተዳድሩት ኃላፊዎች ከየትኛውም ጥቅም እስከ 20 በመቶ ሊካፈሉ፣ እስከ ሁለት በመቶም ከወጪ ምጣኔና ከክፍያ ሥሪት አኳያ ተካፋይ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ያሉቱ የሔጅ ፈንድ ዓይነቶች ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተግባራ እንዲሆኑ መፍቀድ አይመከርም፡፡