Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ የታሰሩ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ለመጠየቅ እስር ቤት ሄዱ

ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ የታሰሩ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ለመጠየቅ እስር ቤት ሄዱ

[ክቡር ሚኒስትሩ የአንድ ሀብታም አቀንቃኝ ግለሰብ ይደውልላቸዋል]   

 • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • ያው የእኛ ደስታ የእናንተም ደስታ ነው ብዬ ነው፡፡
 • ምንድነው ያስደሰታችሁ?
 • የደስታችን ምክንያትማ እናንተም ናችሁ፡፡
 • እኛማ ሁሌም ሕዝቡን ለማስደሰት እንተጋለን፡፡
 • ያለእናንተ ትግል እኮ የሚቻል አልነበረም፡፡
 • ምኑ?
 • የስንቶች አባት የሆኑት እንዲፈቱ እኮ ያደረጋችሁት ጥረት ቀላል አይደለም፡፡
 • የዜጎቻችን መጎዳት እኮ ሁሌም ይቆረቁረናል፡፡
 • በተለይ ደግሞ እንደ እሳቸው ዓይነት አባት የሆነ ሰው ሲታሰር ያማል፡፡
 • አንተ ግን የምር ለእሳቸው አዝነህ ነው ወይስ ጥቅምህ ቀርቶ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ማለቴ በእሳቸው መታሰር ምክንያት ብዙ ጥቅማ ጥቅሞች ስለቀረብህ ነው እንጂ በእርግጥ ስለ እሳቸው ያሳስብሃል?
 • ምንም ቢሆን ስንት ነገር አሳልፈናል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም እንኳን ደስ አለህ፡፡
 • እኛማ ደስታውን ምክንያት አድርገን አንድ ኮሚቴ አቋቁመናል፡፡
 • የምን ኮሚቴ?
 • ለአባታችን ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ነዋ፡፡
 • ከመቼው?
 • የሚገርምዎት እኔ የኮሚቴው ሰብሳቢ ነኝ፡፡
 • ምን ልታደርጉ ነው ታዲያ?
 • በመጀመርያ ያሰብነው ከውጭ ታዋቂ ባንድ ለማስመጣት ነበር፡፡
 • የምን ባንድ?
 • ለግብዣው የሚሆን የሙዚቃ ባንድ ነዋ፡፡
 • ተሳካላችሁ ታዲያ?
 • ጊዜ ስለሌለን አገር ውስጥ ያለ ታዋቂ ባንድ እንዲሆን ወስነናል፡፡
 • ሌላስ?
 • ፕሮግራሙ ላይ ውስኪ በቧንቧ እንዲቀዳ ነው ያሰብነው፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • በቃ ተጋባዦቹ እጃቸውን በውስኪ እንዲታጠቡ ነው የምናደርገው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ለድግሱ የሚሆን ሼፍ ከፈረንሣይ ነው የምናስመጣው፡፡
 • ይገርማል፡፡
 • በአገር ውስጥ ደግሞ አሉ ከሚባሉ ሥጋ ቤቶች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡
 • ትልቅ ድግስ ነዋ የምታዘጋጁት?
 • ክቡር ሚኒስትር በዝግጁቱ ላይ ለየት ያለ ፕሮግራምም አዘጋጅተናል፡፡
 • ምን ዓይነት ፕሮግራም?
 • አባታችን በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያ ሲታገሉና ለእሳቸው ሲደግፉ ለነበሩ ሰዎች ሽልማት አዘጋጅተናል፡፡
 • የገንዘብ ሽልማት ነው?
 • ኧረ የዕውቅና ሠርቲፊኬት በቂ ነው፡፡
 • እንዴ እሳቸው እኮ ገንዘብ በመሸለም ነበር የሚታወቁት?
 • ያው አሁን ሀብታቸው በጣም ስለቀነሰ ሽልማት የለም፡፡
 • ታዲያ በዚህ ዓይነት እንደዚህ ትልቅ ድግስ ከየት አምጥታችሁ ነው የምታደርጉት?
 • እሳቸው ሁሌም ለበርካቶች እጃቸው ስለሚዘረጋ፣ የድግሱን ወጪ ለመሸፈን ከዚያ በፊት አንድ ፕሮግራም እናዘጋጃለን፡፡
 • የምን ፕሮግራም?
 • የገቢ ማሰባሰቢያ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ የታሰሩ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ለመጠየቅ እስር ቤት ሄዱ]

 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • በጣም ነው የገረመኝ፡፡
 • ምኑ ነው የገረመህ?
 • መጥተው ስለጠየቁኝ ነዋ፡፡
 • ምንም ችግር የለውም፡፡
 • ከሰው ጋር ግን ተዛዘብኩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ከቤተሰቤ ውጪ እኮ እርስዎ ነዎት ሁለተኛ የጠየቁኝ ሰው፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ያ ሁሉ ባለሥልጣንና ባለሀብት ያሸረግድልኝ ነበር እኮ?
 • የሚያሸረግድልህ ወዶህ መስሎህ ነው ታዲያ?
 • ክቡር ሚኒስትር ጫማህን ካልጠረግንልህ ነበር እኮ የሚሉኝ?
 • ፈርተውህ ነዋ፡፡
 • አሁን ደስ ብሏቸዋል በሉኛ?
 • ሕዝቡ እየፈነደቀ ነው፡፡
 • ችግር የለውም ጊዜ ጥሎኝ ነው፡፡
 • ታዲያ ጥሩ ሰው ነኝ ልትል ነው?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሪቱን ለዚህ ያበቃሃት እኮ አንተ ነህ፡፡
 • ምን አድርጌ?
 • ምን ያላደረከው ነገር አለ?
 • እርስዎም በመታሰሬ ተደስተዋል?
 • መቼም በሰው ችግር መደሰት ባህላችንም አይደለም፡፡
 • እንጂ ይገባሃል እያሉኝ ነው?
 • ምኑ?
 • እስሩ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከሠራኸው አንፃርማ ሲያንስህ ነው፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ሊጠይቁኝ የመጡ መስሎኝ?
 • እሱማ ልጠይቅህ ነው የመጣሁት፡፡
 • የመጡት ሊጠይቁኝ ሳይሆን ሊያሳቅቁኝ ነው፡፡
 • እሱም ሲያንስህ ነው፡፡
 • ኧረ ይተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን አጠፋሁ?
 • እኔ እኮ ባለውለታዎት ነኝ፡፡
 • የምን ውለታ?
 • እዚህ እንዲደርሱ ብዙ ነገር አድርጌልዎታለሁ እኮ?
 • ጥረቴ ነው እዚህ ያደረሰኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንዲያው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ይዤዎታለሁ አንድ ነገር ይርዱኝ፡፡
 • ምን?
 • ስልክ እንዲገባልኝ ያስደርጉ፡፡
 • ምን?
 • ስልክ እፈልጋለሁ፡፡
 • እስር ቤት ውስጥ?
 • እዚህ ብዙ ስልክ ያላቸው እስረኞች አሉ፣ ስለዚህ ችግር የለውም፡፡
 • በቃ ሕገወጥነት ተጠናውቶሃል አይደል?
 • የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም አርፈህ ተቀመጥ፡፡
 • ለምን?
 • ባለብህ ክስ ላይ ሌላ እንዳይጨምሩብህ፡፡
 • ሌላ ምን?
 • ኮንትሮባንዲስትነት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው]

 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ዱባይ ለልጄ ሠርግ ሾፕ ለማድረግ ልሄድ ብዬ ከኤርፖርት መለሱኝ፡፡
 • ለምን?
 • ምን አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • መመለስ ነዋ ምን ይደረጋል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነፃ ነህ ተብዬ በቅርቡ አይደል እንዴ አገር የገባሁት?
 • ሲጣራ ችግር ከተገኘብህማ ድጋሚ ትጠየቃለሃ?
 • ይኼ ነው ሪፎርሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት?
 • ሰላም ነው ብለን አገር ስንገባ አባብላችሁ ልትከቱን?
 • የት ነው የምትገባው?
 • እስር ቤት ልትከቱን ነዋ?
 • ምን ያለበት ምን አይችልም አሉ፡፡
 • እኔ እኮ ለአገሬ ስንትና ስንት ውለታ የዋልኩ ሰው ነኝ፡፡
 • የምን ውለታ?
 • ክቡር ሚኒስትር ለስንቶች የሥራ ዕድል መፍጠሬን ረሱት?
 • እንዴት አድርገህ?
 • ይኸው በጣም በርካታ ግዙፍ ድርጅቶችን አቋቁሜ የስንቶችን ጉሮሮ እየደፈንኩ ነው፡፡
 • ለምን እንወሻሻለን?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እዚህ እንዴት እንደደረስክ እኮ ይታወቃል፡፡
 • በሥራዬ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡
 • ስማ እዚህ የደረስከው ከቱባ ባለሥልጣናት ጋር ባለህ ግንኙነት እንጂ በሥራህ አይደለም፡፡
 • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ የምልህ የሕዝቡን ጤና የሚጎዳ ዘይት በግፍ ቸብችበህ አይደል እንዴ እዚህ የደረስከው?
 • እ…
 • ስንትና ስንት ለጤና ፀር የሆኑ ጁሶችን አምጥተህ ከብረህ ስታበቃ፣ በሥራዬ ነው የከበርኩት ስትል አታፍርም?
 • ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር እኔ የሥራ ሰው ነኝ፡፡
 • እኮ ሥራህ ሌብነት ነዋ፡፡
 • ይተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እውነቴን ነው፡፡
 • እኔም እናንተን አምኜ መምጣቴ ነው ጥፋቴ፡፡
 • ለማንኛውም የአገሪቱ ባለሀብት ሁሉም ይመረመራል፡፡
 • ምኑ ነው የሚመረመረው?
 • የሀብቱ አመጣጥ ነዋ፡፡
 • አልገባኝም?
 • የሀብታችሁ ትክክለኛ ምንጭና በአግባቡ መገኘቱ ይመረመራል፡፡
 • እኔ እኮ በሥራ ነው ያመጣሁት አልኩዎት?
 • እሱን ተወው ለባለሥልጣን በማጨብጨብ ነው ያመጣኸው፡፡
 • ወይኔ?
 • ስለዚህ መንግሥት የሀብታችሁን ምንጭ ያጣራና ይወስናል፡፡
 • ምንድነው የሚወስነው?
 • ሲጣራ ሀብታችሁ በትክክለኛ መንገድ ካልተገኘ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡
 • እ…
 • ሀብቱ በትክክል ያልተገኘ ከሆነ ምን እንደሚደረግ ታውቃለህ?
 • ምን ይደረጋል?
 • ይወረሳል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ ባለሀብት ጋር ተገናኙ]

 • እንኳን ለአገርህ አበቃህ?
 • እንኳን በሰላም ቆዩኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እኮ ተመልሰህ አገርህ ትገባለህ ብዬ አላሰብኩም?
 • ብዙዎች እንደዚያ ነበር የሚያስቡት፡፡
 • ጤንነትህም ጥሩ አይደለም እያሉ ነበር የሚያወሩት፡፡
 • እነሱ እንኳን ሀብቴን ለመውረስ ብለው ነው የሚያስወሩት፡፡
 • ዋናው እንኳን በደህና ተመለስክ፡፡
 • እኔ እኮ ገና እንደገባሁ ብዙ ለውጥ አለ ስለተባልኩ ቀጥታ ከኤርፖርት ወደ እርስዎ ነው የመጣሁት፡፡
 • አገሪቱማ በከፍተኛ ሪፎርም ውስጥ ናት፡፡
 • ምንድነው ሁሉም ሪፎርም ሪፎርም እያለ ነው የሚያወራው? ህዳሴው ቀረ እንዴ?
 • ህዳሴው በሪፎርም ተቀይሯል፡፡
 • ለመሆኑ አለቃችሁ ደህና ነው?
 • የትኛው አለቃ?
 • የምናቀው የድሮ አለቃችሁ ነዋ?
 • አሁን ሌላ ቆፍጣና አለቃ መጥቶልናል፡፡
 • ለነገሩ ያኔ እኔም የቀድሞው አለቃችሁ ብዙም እንደማይዘልቁ ተናግሬ ነበር፡፡
 • ለማን ነው የተናገርኸው?
 • ለእኔ ቅርብ ጓደኛና ወዳጅ ባለሥልጣኑ ነዋ፡፡
 • ውይ እሳቸው እኮ እስር ቤት ገቡ፡፡
 • ምን?
 • በቅርቡ ነው እንዲያውም የገቡት?
 • እንዴ የደኅንነት ኃላፊው ወዳጃችን ይኼን ያውቃሉ?
 • ለእሳቸው የእስር ቤት ማዘዣ ተቆርጦላቸዋል፡፡
 • እንዴ ምን እየተካሄደ ነው?
 • ሪፎርም፡፡
 • በቃ በዚህ ዓይነት እኔንም ሳታስገቡኝ ልመለስ፡፡
 • እሱማ አይቻልም፡፡
 • እኔ እኮ ነፃ ሰው ነኝ ክቡር ሚኒስትር፣ በቅርቡ ነው ከእስር የተለቀቅኩት፡፡
 • ከእስር አልተለቀክም፡፡
 • እንዴት?
 • ቀይረህ ነው፡፡
 • ምን?
 • እስር ቤት!