Skip to main content
x
በአዲስ አበባ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ የጤና ከተማ ሊገነባ ነው
የጤና ከተማ ፕሮጀክት ገጽታዎች

በአዲስ አበባ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ የጤና ከተማ ሊገነባ ነው

ቪዥን አፍሪካ ሆስፒታል የተባለው የግል ኩባንያ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ የጤና ከተማ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው፡፡

በሚቀጥለው ዓመት (ጥር 2012 ዓ.ም.) ይጀመራል የተባለው ይኸው የግንባታ ፕሮጀክት፣ በቦሌ ለሚ አይሲቲ ፓርክ በአንድ ሚሊዮን ስኩዌር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ለግንባታ የሚውለው ገንዘብ ከዓለም አቀፉ አበዳሪዎችም የሚገኝ መሆኑን የቪዥን አፍሪካ ሆስፒታል ኩባንያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2028 ይጠናቀቃል የተባለው ይኸው ፕሮጀክት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ቅድመ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና በዚህ ጊዜም በጣሊያን ዲዛይን ኩባንያ የተሠራው የሆስፒታሉ ሥነ ሕንፃ ዲዛይን መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡

የጤና ከተማ ሆስፒታሉ አምስት ሺሕ አልጋዎች ያሉትና በቀን እስከ ሰባት ሺሕ ተኝተውና በተመላላሽ ለማከም የሚያስችል ሆስፒታል፣ ሦስት ሺሕ ተማሪዎችን በአዳሪነት መያዝ የሚችል የሕክምና ትምህርት ቤት፣ የአፍሪካ የባህል ማዕከልና ሙዚየም፣ ለኤምባሲዎችና ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚያገለግሉ ቢሮዎች፣ ምግብ ማደራጃዎች፣ የገንዘብ ተቋማት፣ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ የስፖርትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዕከል፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የገበያ ማዕከል፣ ተጨማሪ የጤና ማዕከላትና ማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ይኖሩታል፡፡

የኢትዮጵያን የወደፊት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ቴክኖሎጂያዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከትም ያቀደው ቪዥን አፍሪካ ሆስፒታል ኩባንያ፣ በግማሽ ቢሊዮን ብር በኢትዮጵያ መመሥረቱና ከመንግሥት ጋር በአጋርነት የሚሠራ መሆኑም ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው እ.ኤ.አ. በ2022፣ ሁለተኛው በ2025 እንዲሁም ሦስተኛው በ2028 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለ40 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራልም ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ይሠራሉ ተብለው የነበሩ ሜዲካል ሲቲና ሌሎችም ግንባታዎች በወሬ ብቻ መቅረታቸውን በማውሳት ይኼኛው ምን ያህል ተዓማኒ ነው በሚል ለአቶ ቴዎድሮስ ላነሳነው ጥያቄ፣ ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በተግባራዊነቱ ላይ ሲሠራ መቆየቱን፣ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት የሚሠራና ወደ ሚዲያው የወጣውም የፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ስለታመነበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡